Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ የተከፈለ ካፒታሉን ካላሟላ ከሌላ ባንክ ጋር እንደሚዋሀድ አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከታክስ በኋላ 344.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉ ተገልጿል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት የተከፈለ ካፒታሉን በተሰጠው የጊዜ ገደብ አምስት ቢሊዮን ብር ማድረስ ካልቻለ፣ ከሌላ ባንክ ጋር ለመዋሀድ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ እንደሚጀምር አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ አስታወቀ፡፡

ባንኩ ቅዳሜ ታኅሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ በዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው፣ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የባንኩን ካፒታል አምስት ቢሊዮን ብር ማድረስ የማይቻል ከሆነ፣ ከሌላ ባንክ ጋር መዋሀድን እንደ አማራጭ ይወስዳል፡፡

‹‹ባንኩ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ የሚጠበቅበትን ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታል አምስት ቢሊዮን ብር ለማሟላትና ካፒታሉን ለማሳደግ የሚረዱ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ወደ ተግባር ገብቷል፤›› የሚለው የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት፣ አፈጻጸሙንም በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡

ሆኖም የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ በሚቻልበት አማራጮች ላይ ለመወያየት ከመካከለኛና ከከፍተኛ ባለአክሲዮኖች ጋር ሦስት ዙር ስብሰባ ቢያካሄድም፣ የተገኘው ውጤት የተጠበቀውን ያህል አለመሆኑን በመጥቀስ ውህደትን አማራጭ አድርጎ ለመንቀሳቀስ መነሳቱን ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡   

የአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ካሳሁን በቀለ በዚሁ ጉዳይ ላይ በግልጽ ሲናገሩ፣ ‹‹ሁሉም ባለአክሲዮኖች በባለቤትነት ስሜት በመነሳት የሚችሉትን ያህል አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የሚጠበቀውን የካፒታል መጠን ለማሟላት የማይቻል መሆኑ ከታወቀ፣ ከሌላ ባንክ ጋር ለመዋሀድ የሚያስችለንን ጥናት ባንኩ ቀደም ብሎ የሚጀምር መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ፤›› ብለዋል፡፡

አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉን 1.4 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ በሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ተጨማሪ 3.6 ቢሊዮን ብር ካፒታል በማሰባሰብ አምስት ቢሊዮን ብር ማድረስ ይጠበቅበታል፡፡  

ከአራት ዓመት ባነሰ ጊዜ ካፒታሉን አምስት ቢሊዮን ብር ለማድረስ የባለአክሲዮኖች ድጋፍ የግድ ስለመሆኑ በጠቅላላ ጉባዔ ላይም ተመክሮበታል፡፡ አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ወደ ውህደት ለማቅናት በይፋ ያስታውቅ እንጂ፣ ሌሎች የግል ባንኮችም በውህደት ጉዳይ ላይ ውስጥ ውስጡን እየመከሩበት መሆኑን በተለያዩ መንገዶች እያስታወቁ ነው፡፡ ከሰሞኑ እየተካሄዱ ባሉ የባንኮች ጠቅላላ ጉባዔዎች ላይም ይኼው ጉዳይ ተነስቶ ውይይት ሲደረግበት መታዘብ የተቻለ ሲሆን፣ በተለይ የተከፈለ ካፒታላቸው ከአምስት ቢሊዮን ብር በታች የሆኑ ባንኮች ውህደትን በአማራጭነት ሊመለከቱ እንደሚችሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የተከፈለ ካፒታል መጠናቸው ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ በተሻገረ አንዳንድ ባንኮችም ይህ ጉዳይ በቦርድ ደረጃ እየታየ ስለመሆኑ የሚናገሩ አሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ የ2014 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም እንደሚያመለክተው፣ ባንኩ አሁንም አትራፊ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ካቀረቡት ዝርዝር ሪፖርት ለመረዳት እንደሚቻለው፣ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከዚህ ቀደም ከነበረው አፈጻጸም የተሻለ ውጤት የተገኘበት ዓመት ነው፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ካስመዘገባቸው ወጤቶች መካከል ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ኤልሲ ማርጅንን ጨምሮ በ23 በመቶ በማደግ 7.9 ቢሊዮን ብር ማድረሱ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡

የባንኩ የአስቀማጮች ቁጥርም በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 366,299 የደረሰ መሆኑን፣ በዚህም የባንኩን የአስቀማጮች ቁጥር በ31 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ያሳያል ተብሏል፡፡

ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የተሰጠ የብድር ክምችት 6.1 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተጠቁሟል፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ የሰጠው አዲስ ብድር 1.6 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ከቀዳሚው ዓመት የ35 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተመልክቷል፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ በደንበኞች እጅ ከሚገኘው ብድር ውስጥ 96.8 በመቶ ጤናማ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ቦርድ ሊቀመንበር፣ የተበላሸ ብድር መጠኑም 3.2 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው አምስት በመቶ መሥፈርት በታች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡   

በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ በዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት አበረታች ውጤት ያስመዘገበ መሆኑን የጠቀሱት ቦርድ ሰብሳቢው፣ ከዘርፉ በጠቅላላው 539.4 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት መቻሉንና ከቀዳሚው ዓመት ከተገኘው ገቢ በ155.9 ሚሊዮን ብር ማደጉን ያሳያል ብለዋል፡፡ እንዲሁም በሒሳብ ዓመቱ የተሰበሰበው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 146.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ፣ ካለፈው ሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ27.6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አክለዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ያስመዘገበውን ትርፍ በተመለከተ ከታክስ በፊት 472.8 ሚሊዮን ብር፣ ከታክስ በኋላ ደግሞ 344.9 ሚሊዮን ብር ሆኖ ማትረፉ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ሕጋዊ መጠባበቂያና የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የሥራ ዋጋ ክፍያ ከተቀነሰ በኋላ፣ ባንኩ ባለአክሲዮኖች ባላቸው የተከፈለ አክሲዮን መጠን መሠረት እንዲከፈል የዳይሬክተሮች ቦርድ ለጠቅላላ ጉባዔ ሐሳብ አቅርቦ ፀድቋል፡፡ ሆኖም የባንኩን ካፒታል የበለጠ ለማሳደግ ባለአክሲዮኖች ያገኛኙት ትርፍ በፈቃደኝነት ለተጨማሪ አክሲዮኖች መግዣ እንዲውል እንዲወስኑም ለባለአክሲዮኖች ጥሪ ተላልፏል፡፡   

በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 10.8 ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ1.9 ቢሊዮን ብር መጨመሩ ተገልጿል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉ 1.4 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ30.3 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የባንኩ ባለአክሲዮኖች ቁጥር የ7.8 በመቶ ዕድገት በማሳየት 14,077 መድረሱ ተጠቁሟል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች