Friday, April 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከኢትዮጵያ በላይ መሆን አይቻልም!

ኢትዮጵያ ከሰሜኑ አውዳሚ ጦርነት ጊዜያዊ ዕፎይታ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት ያገኘች ብትመስልም፣ መሰንበቻውን በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ከተፈጸመው የንፁኃን ጭፍጨፋ ጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ የሚስተዋለው አለመረጋጋት ለብዙዎች ሥጋት ፈጥሯል፡፡ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰከነ መንገድ የመፍታት ፍላጎት ባለመኖሩ ምክንያት፣ የዘፈቀደ ዕርምጃዎች አንፃራዊውን ሰላም እያደፈረሱ ለሌላ ዙር ጥፋት እያንደረደሩ ነው፡፡ በእልህ፣ በግትርነትና በግብዝነት የተወረረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ መንደር ከዕብሪትና ከመደናቆር ጋር እየተሸራረበ የአገር ሰላም መንሳቱን ቀጥሏል፡፡ አሁንም ከትናንት ስህተቶች ለመማር ባለመፈለግ የተለመደው ጥፋት እየተፋፋመ በመቀጠል ላይ ነው፡፡ በመንግሥት በኩል እያንዳንዱ ውሳኔ የተጠናና በሕዝብ ፍላጎት ላይ መመሥረት ሲገባው፣ በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ስለማይከናወን ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ የሚያደርጉ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ቅራኔው ይሰፋል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግልጽና ጥርት ያለ አቋማቸው አይታወቅም፡፡ በዚህ መሀል አገርን የምታህል ትልቅ ነገር እየተረሳች ሁሉም በየፊናው ይነጉዳል፡፡ ሕዝብ አዳማጭ አጥቶ ለጉዳት ይዳረጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚስተዋለው እያንዳንዱ ችግር አገርና ሕዝብን የረሳ እየሆነ ነው፡፡

አገርን መጥላትና ማስጠላት የራስ ወዳድ ፖለቲከኞች የዘወትር ሥራ በሆነባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ትውልድን የማዳን ተግባር መከናወን ያለበት ጥራት ባለው ትምህርት መሆን ነበረበት፡፡ የትውልድ ዕነፃው ሊከናወንባቸው የሚገቡ የትምህርት ማዕከላት፣ የጭፍን ጥላቻና የግጭት መቀስቀሻ እየተደረጉ አገር መገንባት ፈፅሞ አይታሰብም፡፡ አንድ ሕዝብ ወይም ማኅበረሰብ የሚጠፋው ትውልዱ የተዛባ የታሪክ ትርክት ሲጋት፣ የሞራልና የሥነ ምግባር እሴቶች ሲናዱ፣ መልካምነት በክፋት አረም ሲወረር፣ ሌብነት ሲያስከብር፣ ሐሰት በእውነት ላይ ስታናጥር፣ ሰዎች እኩል መሆናቸው ተክዶ የብሔር የበላይነትና የበታችነት ስሜት ሲበረታ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል አላስፈላጊ ልዩነት ሲፈጠር፣ ወጣቶች  የቀድሞዎቹን ትውልዶች ሲንቁና ሲጠሉ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲጠፋ፣ አገር በቀል ዕውቀቶች ወደ ጎን እየተገፉ የሌሎችን እንዳለ መገልበጥ ሲስፋፋና የመሳሰሉት ችግሮች ሲንሰራፉ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝባችን ከሚታወቅባቸው መልካም ፀጋዎች መካከል አንደኛው ሕግ አክባሪነት ነው፡፡ ‹‹በሕግ አምላክ›› ሲባል ሁሉም ሰው ንቅንቅ የማይልባት በነበረችው ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ከሕግ በላይ ሆኖ መፈንጨት በመለመዱ በርካታ ነገሮች እየተበላሹ ነው፡፡ ከአገር በላይ ማንም ስለማይበልጥ አሁንም በሕግ መባል አለበት፡፡

በተለያዩ አገሮች መራራውን ሽንፈትና ውድቀት የተከናነቡ መንግሥታት፣ ታዋቂ ሰዎችም ሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ታሪክ የሚነግረን፣ ራሳቸውን ከአገርና ከሕዝብ በላይ በመቁጠር ያሻቸውን ለማድረግ በመነሳታቸው ነው፡፡ ሥልጣንን የመጨረሻው የዕውቀት ጥግ ወይም የፍላጎት ማሳኪያ መንገድ በማድረግ ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑ በሙሉ አወዳደቃቸው ያላማረው፣ ሕዝብን ንቀው በራሳቸው ስሜት በመክነፋቸው መሆኑን ታሪካቸው ይዘረዝራል፡፡ የነገሥታቱ፣ የአምባገነኖችና ዴሞክራት መሰል ፈላጭ ቆራጮች ታሪክ የሚመሰክረው፣ ራስን ከአገርና ከሕዝብ በላይ የማድረግ ክፉ አባዜ አወዳደቃቸውን አለማሰመሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ከማዕከላዊ መንግሥት ምሥረታ ወዲህ ያለውን ታሪክ ብንመረምር፣ ራሳቸውን ከአገር በላይ አግዝፈው የኖሩ መጨረሻቸው ከሕዝብ ጋር ተቆራርጦ ለእስር፣ ለሞት ወይም ለስደት መዳረግ ነበረ፡፡ አሁንም የመንግሥት ሥልጣን የተቆናጠጣችሁም ሆናችሁ ሥልጣን ለመያዝ የምትፎካከሩ፣ ሕዝብና አገር የማያከብር እንቅስቃሴ ውጤቱ ጥፋት መሆኑን ተገንዘቡ፡፡ የፖለቲካ ዓላማን ለማስፈጸም በሚደረስባቸው ውሳኔዎች ራስንና ፓርቲን ከአገርና ከሕዝብ በላይ ማድረግ፣ ውጤቱ ከላይ የተገለጸውን ዕጣ ፈንታ መጋራት ነው የሚሆነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር ጋር የተያያዘው ውዝግብ፣ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ፈር መያዝ ሲገባው ወደ አላስፈላጊ ግጭት እያመራ ያለው አያያዙን ካለማወቅ የመነጨ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥትም ሆነ ሌላው አካል የመጀመሪያ ግዴታው ሕግ ማክበር ነው፡፡ ሕግ የሚከበረውም በጉልበት ሳይሆን ሕጉ በሚጠይቃቸው መሥፈርቶች መሆን አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን የፖለቲካ ቀውስ በመፍጠር አገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነት/ግጭት ውስጥ መክተት ይከተላል፡፡ ኢትዮጵያውያንን በብሔር በመከፋፈል ሌላ ዙር ፍጅት የሚቀሰቅስ ንትርክ ከመፍጠር ይልቅ፣ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን የሚያጠናክሩ በርካታ ተግባራት ላይ ቢተኮር ተመራጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አፋቸውን ከፈቱባቸው ቋንቋዎች በተጨማሪ ሌሎችንም ቢማሩ የሚጠቅመው ራሳቸውን መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ቋንቋ ከመግባቢያነት አልፎ ጥቅምና ዝምድና መፍጠሩ መልካም ሆኖ ሳለ፣ በግድ ለመጫን የሚደረግ ሙከራ ቅራኔ ከመፍጠር ውጪ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ አሁንም በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መከናወን የሚችል ተግባር በመተው፣ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ የሚያጋጭ ድርጊት መቆም አለበት፡፡

አዲስ አበባ ከተማ የፌዴራል መንግሥት መቀመጫ ስለሆነች ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል የሚስተናገዱባት መሆን አለባት፡፡ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ የሆነው አማርኛና ብሔራዊ መዝሙር በሁሉም ትምህርት ቤቶች ማገልገል አለበት፡፡ በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮች ቋንቋዎች ትምህርት የሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ጭምር ብሔራዊ መዝሙር ሊዘመርባቸው ይገባል፡፡ የራሳችንን ክልላዊ መዝሙር መዘመር አለብን የሚሉም ከሆነ መብታቸው ነው፡፡ ነገር ግን ቋንቋቸው በተጨማሪነት በሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሰንደቅ ዓላማ ስቀሉ፣ ክልላዊ መዝሙር ዘምሩ ብሎ ማስገደድ ተገቢ አይደለም፡፡ በመንግሥት በኩል የሰሞኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ረብሻ የፖለቲካ ዓላማ ባላቸው ኃይሎች ሳቢያ የተቀሰቀሰ ነው የሚል ሐሳብ ተነስቷል፡፡ በተጨማሪም የኦሮሚኛ ትምህርት በሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ፣ የኦሮሚያ ክልልን ሰንደቅ ዓላማ መስቀልም ሆነ መዝሙር መዘመር የተለመደ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ አሁን ለረብሻው ምክንያት ከውጭና ከውስጥ የተቀሰቀሰ አጀንዳ ነው ተብሏል፡፡ ችግሩን በዚህ ደረጃ ከመለጠጥ ይልቅ ለአገር የሚጠቅም መፍትሔ ይዞ መቅረብ ይሻላል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሰሞኑን ክስተት የሁለት የፖለቲካ ኃይሎች ፍላጎት መራኮቻ ነው አድርገው ያቀረቡት፡፡ የኦሮሚያ ቋንቋ ትምህርት ክፍል ባላቸው እንጂ፣ በሌላቸው ትምህርት ቤቶችም ሰንደቅ ዓላማ መስቀልም ሆነ መዝሙር የለም ብለዋል፡፡ ከንቲባዋ አንድነት ሊኖር የሚችለው አንዱ የሌላውን በመጨፍቅ አይደለም ሲሉም አክለዋል፡፡ እርግጥ ነው ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መገንባት የሚቻለው አንዱ የሌላውን ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህልና የኑሮ ዘይቤ አክብሮ እንደሆነ ማንም አይስተውም፡፡ ጉዳዩ ለፖለቲከኞች ብቻ እየተተወ አስቸገረ እንጂ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑት አኩሪ ማኅበራዊ እሴቶቹ እንዴት ተሳስቦ እንደሚኖር ነጋሪ የሚያስፈልገው አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ ለአማራው፣ ለትግሬው፣ ለኦሮሞው፣ ለጉራጌው፣ ለአፋሩ፣ ለወላይታው፣ ለሶማሌው፣ ለጋምቤላው፣ ወዘተ ትጠበው ይሆናል እንጂ አትሰፋበትም፡፡ ነገር ግን በፖለቲከኞች የጠበበ ዕይታ ምክንያት አዲስ አበባ እየጠበበች ነው፡፡ አሁንም ጊዜው አልረፈደምና የሕዝቡን የዘመናት አኩሪ እሴቶች በማክበር ችግሮች ፈር ይያዙ፡፡ ከኢትዮጵያ በላይ መሆን አይቻልም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...