Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሀብት ያስመዘገቡ የመንግሥት ሹማምንትና ሠራተኞች መረጃ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ ተጠየቀ

ሀብት ያስመዘገቡ የመንግሥት ሹማምንትና ሠራተኞች መረጃ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ ተጠየቀ

ቀን:

የፌዴራል ሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በተሿሚዎች፣ በተመራጮች ወይም በመንግሥት ሠራተኞች ላይ እያከናወነ ያለው የሀብት ምዝገባ መረጃ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ጠየቀ፡፡

በ2002 ዓ.ም. በወጣው የሀብት ማሳወቂያና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ድንጋጌ መሠረት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር  ዴኤታዎች፣  ምክትል  ሚኒስትሮች፣  ኮሚሽነሮች፣  ምክትል ኮሚሽነሮች፣ ዋና ዳይሬክተሮችና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች፣ እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባወጣው መግለጫ፣ ግለሰቦቹ ለኮሚሽኑ ያስመዘገቡትን ሀብት መረጃ በሚስጥር መያዝና ለሕዝብ ይፋ አለማድረግ ከአዋጁ ጋር  የሚፃረር ድርጊት እንደሆነ አስረድቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተለይም በመንግሥት ተቋማት የሚገኙ የሥነ ምግባር መከታተያ የሥራ ክፍሎች በየተቋማቸው ያለውን የሀብት ምዝገባ መረጃን ለማንኛውም መረጃ ጠያቂ እንዲሰጡ አለማድረግ፣ ወይም ምቹ ሁኔታ አለመፍጠር የሕገ መንግሥቱን የግልጽነትና ተጠያቂነት ድንጋጌንና የሀብት ማስመዝገቢያና ማሳወቂያ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ጽንሰ ሐሳብና መሠረታዊ ዓላማን ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን አስታውቋል፡፡

መረጃ ያለመስጠት ድርጊት ለተጀመረው የሙስና ትግል ምንም ዓይነት አበርክቶ የሌለው በመሆኑ የሀብት ምዝገባ መረጃ ለሕዝብ ክፍት እንዲሆን የዕርምት ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት፣ የመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት የሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ ምሰሶ በመሆኑ፣ የመንግሥት አሠራር ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ለሆነው ሕዝብ ግልጽ በሆነና በተጠያቂነት መንገድ መከናወን እንዳለበት መጠቀሱን ተቋሙ አስታውሷል፡፡ አክሎም በዚህ ድንጋጌ መሠረታዊ ዓላማ የመንግሥት አካላትና ባለሥልጣናት አሠራር ለሕዝብ ዕይታ ግልጽ እንዲሆንና እንዲያውቀው፣ እንዲወያይበትና እንዲቆጣጠረው ማስቻል መሆኑን ገልጿል፡፡

የሀብት ማስመዝገብ አዋጅ ዓላማ ሕዝብ የተመዘገበና ያልተመዘገ ሀብትን በማወቅ፣ የተደበቀና በሕጉ አግባብ ያልተመዘገበ ሀብት ካለ ጥቆማ ለመንግሥት እንዲሰጥ ማድረግ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል፡፡

ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ግዴታ የተጣለባቸው አካላት በግለሰብና በቡድን ጥቅም ላይ አሉታዊ ሚና ያለው ውሳኔ የሚያስተላልፉ ስለሆኑ፣ በዚያው ልክ ላልተገባ ጥቅምና ለሕገወጥ ሀብት ስብስበ በቀላሉ የተጋለጡ እንደሚሆኑ፣ የእነዚህን ግለሰቦች አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ፣ አሠራርና የግል ሀብትና ንብረት ከሕዝብ ዓይንና ጆሮ ሊደበቅ እንደማይገባ ዕንባ ጠባቂ አክሎ ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ የሀብት ማስመዝገብና ማሳወቅ ሥርዓቱ የተከናወነው በኮሚሽኑ በተፈጠረ ሚስጥራዊ የኮምፒዩተር ኮድ በመሆኑ፣ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች የሀብት ምዝገባ መረጃ ሲጠየቁ ማን ምን እንዳስመዘገበ እንደማያውቁና ሚስጥር በመሆኑ መረጃ ለመስጠት መቸገራቸውን በመግለጫው አስረድቷል፡፡

በተመሳሳይ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም የሀብት ምዝገባ መረጃን ለጠያቂ እንሰጣለን ከማለት ውጪ፣ የተመዘገበው መረጃ ለሕዝብ ክፍት አለመደረጉን ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ማብራሪያ የጠየቃቸው የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሻሜቦ፣ ስለተባለው ሁኔታ ከሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ጥያቄ አልቀረበም ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ በፌዴራል ደረጃ ወደ 900 ሺሕ የሚደርሱ የመንግሥት ሹሞችና ሠራተኞች ሀብት ማስመዝገባቸውን ገልጸው፣ ሰነዱ ካለው ብዛት አንፃር ይህን ሁሉ መረጃ በአንዴ ገልብጦ ለሕዝብ ማሳየት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

በሌሎች አገሮች መሰል ሰነዶች ለሕዝብ ይፋ የሚደረጉት ዲጂታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም እንደሆነ፣ በኢትዮጵያ አሁን ያለው አሠራር በዚያ ልክ ባለመድረሱ ዶክሜንት እየገለበጡ ለሕዝብ ለማሳወቅ ከባድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በሀብት ማስመዘገብ አዋጁ መሠረት ማንም አካል ተቋሙን መረጃ ሲጠየቅ ይሰጣል እንጂ፣ ይፋ ያደርጋል ተብሎ አለመደንገጉን አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...