Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለዓለም አቀፍ ውድድር የሚረዳ የቦክስ ሻምፒዮና ሊካሄድ ነው

ለዓለም አቀፍ ውድድር የሚረዳ የቦክስ ሻምፒዮና ሊካሄድ ነው

ቀን:

በኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን አንደኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ሻምፒዮናን ከታኅሣሥ 20 እስከ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡   

ሻምፒዮናውን በአራት ዙሮች ለማካሄድ እንደታቀደ፣ ፌዴሬሽኑ ከሲሳይ አድሬሴ ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ቦክሰኞችን ለመምረጥ ግቡ ያደረገ ሻምፒዮና እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ፌዴሬሽኑ በመግለጫው ላይ ውድድሮችን ለማዘጋጀት የበጀት እጥረት ፈተና እንደሆነበት የጠቆመ ሲሆን፣ ችግሩን ለመቅረፍና አገር አቀፍ ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ከሲሳይ አድማሴ ፕሮሞሽን ጋር በትብብር ለመሥራት ማቀዱን አስታውቋል፡፡

በዚህም የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዱልሰመድ መሐመድና ሲሳይ አድማሴ ፕሮሞሽን ሻምፒዮናው በድምቀት እንዲከናወንና የበለጠ እንዲተዋወቅ በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ ሦስት ውድድሮች መኖራቸውን ያስረዱት የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ፣ ሻምፒዮናው ኢትዮጵያን የሚወክሉ ቦክሰኞችን ለመምረጥ ግቡ ያደረገ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚካሄዱት የቦክስ ውድድሮች አንደኛው ግንቦት ላይ በህንድ የሚካሄደው የሴቶች የዓለም የቦክስ ሻምፒዮና ሲሆን፣ ሁለተኛው ሰኔ ላይ  ካዛኪስታን የሚደረግ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡ ሌላኛው ዓለም አቀፍ ውድድር ደግሞ በመጪው ሐምሌ  በጋና  የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚህም ኢትዮጵያን የሚወክሉ ቦክሰኞች በአገር ውስጥ ከሚካሄደው ሻምፒዮና የሚመረጡ ይሆናል፡፡

ብሔራዊ ሻምፒዮናው ሐሙስ ታኅሣሥ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በትንሿ ስታዲየም በድምቀት ተጀምሮ፣ መዝጊያውን እሑድ ታኅሣሥ 23 2015 ዓ.ም. እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የመጀመርያው ሻምፒዮና አዲስ አበባ የሚደረግ ሲሆን፣ ሁለተኛና ሦስተኛው ዙር ውድድር በጎንደርና አርባ ምንጭ ከተሞች ተካሂዶ ፍጻሜውን ተመልሶ በአዲስ አበባ እንደሚያደርግ በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቁሟል፡፡

ሻምፒዮናው በሁለቱም ፆታ የሚካሄድ ሲሆን፣ በውድድሩ ላይ ስምንት የቦክስ ክለቦች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል። በዚህ ሻምፒዮና የሚሳተፉት ክለቦች አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤት፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚ፣ ደሴና ጎንደር ናቸው፡፡

የተለያዩ የቦክስ ውድድሮች ዓመቱን ሙሉ የሚካሄዱ ቢሆንም ተመልካች እንደሌላቸው ይነገራል፡፡

የኦሊምፒክ ስፖርት የሆነው ቦክስ፣ ከአትሌቲክስ ቀጥሎ በዓለም አቀፍ መድረኮች በተሳትፎ በተለይም በኦሊምፒክ ደረጃ በቀዳሚነት ከሚቀመጡ ስፖርቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡

ለስፖርቱ መዳከም ትልቁ ምክንያት የበጀት እጥረት መሆኑን የገለጹት የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ፣ ለዚህም መንግሥትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የቦክስ ስፖርት እንደ አንድ የሥልጠና ዓይነት በጦር ኃይል ውስጥ ለወታደሮች ሲሰጥ እንደነበር ይነገራል፡፡ በተለይ በሐረር ጦር አካዴሚ ያሠለጥኑ የነበሩ እንግሊዞች ቦክስን እንደ ዋነኛ የሥልጠና ዓይነት ይሰጡ ነበር። በሠራዊቱ ውስጥ ከተቋቋሙ ክለቦች መካከልም የክብር ዘበኛ (መኩሪያ)፣ ምድር ጦር (መታል)፣ ፖሊስ (ኦሜድላ)፣ ፈጥኖ ደራሽ ይጠቀሳሉ፡፡ ብሔራዊ የቦክስ ፌዴሬሽኑ በ1954 ዓ.ም. መመሥቱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...