Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትሞሮኮ ሌላ ታሪክ የምትጽፈበት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ

ሞሮኮ ሌላ ታሪክ የምትጽፈበት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ

ቀን:

ሳዑዲ ዓረቢያ አርጀንቲናን በመርታት የጀመረው በዓረቡ አገር ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የኳታር ዓለም ዋንጫ ሊጠናቀቅ ከአንድ ሳምንት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል፡፡ የዓለም ዋንጫው ባልተጠበቁ ውጤቶች ታጅቦ የዘለቀ ሲሆን፣ 28 ቡድኖችን አሰናብቶ፣ አራት ብሔራዊ ቡድኖች ለዋንጫው አፋጧል፡፡ አርጀንቲና፣ ፈረንሣይ፣ ሞሮኮና ክሮሽያ ለግማሽ ፍፃሜው ደርሰዋል፡፡

የውድድሩ ክስተት የሆነችው ሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሮኮ፣ ከፈረንሣይ ጋር የምታደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡ የአትላስ አንበሶቹ ካናዳን፣ ቤልጂየምን፣ ፖርቱጋልንና ስፔንን አሸንፈው ከክሮሺያ ጋር አቻ በመውጣት የአፍሪካ ኩራት መሆን የቻሉበት ውድድር ሆኗል፡፡

ሞሮኮ በጥሎ ማለፉ ፖርቱጋልን 1 ለ0 በመርታት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ፍፃሜ መግባት የቻለች አፍሪካዊት አገር ሆናለች፡፡ በርካታ የዓለም ሚዲያዎች፣ የተለያዩ ተቋማት፣ ፖለቲከኞች፣ የቀድሞ ተጫዋቾች ሳይቀሩ ስለሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ስሜቱን ያልገለጸ አልነበረም፡፡

የሞሮኮ ዋና ከተማ ራባትን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ሳር ቅጠሉ ሳይቀር በደስታ ስክሮ ነበር፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያንም በማኅበራዊ ሚዲያው ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ ሞሮኮ ራሷን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ወክላ በዓለም ዋንጫ መገኘቷ ደስታውን የጋራ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

የሞሮኮን ድል ተከትሎ፣ የአፍሪካ አገሮች ከሕፃናት እስከ አዋቂ ድረስ በደስታ ጮቤ ሲርግጡ ነበር፡፡ ሞሮኮ፣ በፊፋ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ ሁለተኛ ላይ መቀመጥ የቻለችውንና ለዋንጫው ቅድመ ግምት አግኝታ የነበረውን የቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን 2 ለ0 ከረታች በኋላ ነው የዓለም እግር ኳስ ተመልካችን ቀልብ መግዛት የቻለችው፡፡

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ተጫዋቾች ወደ አውሮፓ ተሻግረው የሚኖሩና ሁለት ዜግነት ያላቸው ናቸው፡፡ አንዳንዱ ለትውልድ አገሩ ተሠልፎ ሲጫወት፣ ገሚሱ ደግሞ ሁለተኛ ዜግነት ለሰጠው አገር ተሠልፎ መጫወት የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም በርካታ ተጫዋቾች በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ያላት አፍሪካ በዓለም ዋንጫው ከጥሎ ማለፍ የሚያስችል ታሪክ የላትም፡፡ ከ26 የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ውስጥ 12 ብቻ በሞሮኮ የተወለዱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ የሞሮኮ የዘር ሐረግ ኖሯቸው፣ በስፔን፣ በካናዳ፣ በፈረንሣይ፣ በኔዘርላንድና በቤልጂየም የተወለዱ ናቸው፡፡ በዋሊድ ጌግራጉይ እየተመራች ግማሽ ፍፃሜ የደረሰው የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ከፈረንሣይ ጋር ለፍፃሜ ለመድረስ በሚደረገው ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

የ2018 ዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ፈረንሣይ ሌላው የዘንድሮ ዓለም ዋንጫ ክስተት ስትሆን፣ እምብዛም ግምት ሳታገኝ ግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀል የቻለች ብሔራዊ ቡድን ናት፡፡ በዚህም ሞሮኮ እስካሁን ከገጠመቻቸው ብሔራዊ ቡድኖች አንፃር በፈረንሣይ ልትፈተን እንደምትችል ይገመታል፡፡ በተለይ የፈረንሣይ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ፍጥነት ለሞሮኮ ተከላካዮች ፈተና ሊሆንባቸው እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል፡፡

በአንፃሩ በርካታ ግምት የተሰጣቸውን የአውሮፓ አገሮች ብሔራዊ ቡድኖች ከውድድር ውጪ ማድረግ የቻሉት የአትላስ አናብስት ቀላል ግምት አላገኙም፡፡ የሞሮኮ ያለጥረት ግማሽ ፍፃሜ እንዳልደረሰች የሚናገረው የፈረንሣዩ ተከላካይ ራፋሄል ቫራን፣ ትንሽ ግምት መስጠት እንደማያስፈልግና ሞሮኮን በጥንቃቄ ማስተናገድ እንደሚገባ አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡

ለፍፃሜ መድረስ ቀላል እንዳልሆነ የሚያስረዳው ቫራን፣ ማሸነፍ ብቸኛው አማራጭ ብቻ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የሞሮኮ ተጫዋቾች እርስ በርስ የተቀራረቡና የተጠባበቁ በመሆናቸው ለተቃራኒ ፈታኝ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በዓለም ዋንጫው ለስድስተኛ ጊዜ መሳተፍ የቻለችው ሞሮኮ፣ ከምንጊዜም በላይ በዘንድሮ ዓለም ዋንጫ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈች ትገኛለች፡፡ ሞሮኮ እ.ኤ.አ በ1970 በሜክሲኮ ዓለም ዋንጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፍ የቻለች ሲሆን፣ በ1986፣ 1994፣ 1998፣ 2018 እንዲሁም 2022 መካፈል ችላለች፡፡

ሞሮኮ ፈረንሣይን ረትታ ለፍፃሜ መድረስ ከቻለች፣ አፍሪካ በዓለም ዋንጫው ወርቃማ ታሪክ የምትጽፍበት ይሆናል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...