Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተፈተነው አገራዊው ሰላም

የተፈተነው አገራዊው ሰላም

ቀን:

‹‹ሰላም ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች መካከል አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ነው። የሰው ልጅ ሕይወት ትርጉም ያለው ሰብዓዊ ሕይወት መኖር የሚችለው ሰላም ሲኖር ነው። ሰላም ከሌለ ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል። የሰላም መኖር ለሰው ልጅ መሠረታዊ መብት የሚሆነው ለዚህ ነው። ፀረ ሰላም የሆኑ ነገሮችን ማስወገድና ሰላምን ማጎልበት የሚያስችሉ ተግባሮችን መፈጸም የሰው ልጅ ግብረገባዊ ግዴታ ነው።››

ይህ የሰላም ምንነትና አንድምታ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአንድ ትምህርታዊ ኅትመቷ ላይ የገለጸችው ነው፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት  ወዲህ  በተለይም በሁለት ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ ሰላም ርቆ ጦርነት ሲካሄድ፣ በሁሉም ወገን ሕይወት ሲጠፋ፣  ሰዉ ሲፈናቀል ታይቷል፡፡ ባሁኑ ጊዜ ዕርቀ ሰላም ወርዶ የሰሜኑ ጦርነት  ቢቆምም፣ በምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል ግን ሰላሙ ርቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአገሪቱ ሰላምን ለማስፈን፣ ፍቅር አንድነትን ለማፅናት እየጣሩ ካሉት ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት ይገኙባቸዋል፡፡ በተለይ የኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክና ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን በአባልነት ያቀፈው  የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አንዱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ቅዱሳት መጻሕፍትን ከማስተርጐም፣ ከማሳተምና ከማሠራጨት ጎን ለጎን ወቅታዊና ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አብያተ ክርስቲያናትንና ባለድርሻ አካላትን በማወያየት ማኅበረሰባዊ የሆኑ ችግሮች በሚቀረፉበት መንገዶች ላይ ትኩረት እንዲደረግ ጥረት እንደሚያደርግ ይናገራል፡፡

በዚሁ መሠረት አገሪቱ አሁን ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ያለውን አብሮ የመኖር እሴትና ማኅበራዊ ትስስር በማጠናከር ረገድ መከናወን በሚገባቸው ተግባራት ላይ ያተኮረ ጉባዔ ባለፈው ሳምንት አካሂዶ ነበር፡፡

‹‹ማኅበራዊ ትስስርንና እኩልነትን በማጠናከር ረገድ የተቋማት፣ የመሪዎችና የማኅበረሰቡ ሚና›› በሚል ርዕስ በተካሄደው ጉባዔ የሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት አባቶች፣ የፓርላማ አባላትና ታዋቂ ግለሰቦች ተገኝተውበታል፡፡

በመድረኩ በአገራዊው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተመርኩዘው የድሮውን ከአሁን በማነፃፀር ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒው ዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

‹‹የቀደሙ አባቶች የሚችሉትን ያህል አድርገው አልፈዋል፡፡ በዚህም ሥራቸው አጠፉም፣ አላጠፉም ድርጊታቸውን ታሪክ ዘግቦ ዘግቶታል፡፡ አሁን ያለው ኅብረተሰብ ግን የራሱ የሆነ አዲስ ታሪክ ለመሥራት መንቀሳቀስ ይገባዋል፤›› ያሉት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ጴጥሮስ፣ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የተፈጸሙትን አሉታዊ ያሏቸውን ነገሮች በማንሳት ነው፡፡

‹‹ባለፉት አሠርታት በኢትዮጵያ የተዘራው የወደቁ ሰዎችን የማንሳት ሳይሆን፣ ጭርሱኑ የመቅበር፣ በየትምህርት ተቋማት የታሪክ ትምህርት ቀርቶ ዘውጌነትን ማስተማር፣ እንዲያውም ሳይማሩ መመረቅን ነው፡፡ ይህም ሁኔታ ያልተማሩ ኃላፊዎች በየቦታው የመቀመጥ ዕድል አመቻችሎላቸዋል፤›› ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፣ ፖለቲካውና ሁሉም አካል ጉድለት የመሙላት ሳይሆን፣ ማጥፋት ላይ ማተኮሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም የተሰጠው ትምህርትና እምነትም ጭምር አዕምሮና ልቦናን መግዛት እንዳቃተውና በዚህም መለወጥ እንዳልተቻለ፣ ተናጋሪዎች እንጂ አማኞች እንደሌሉ፣ የተዘራውም ዕውቀት ኅብረተሰቡን ለውጦ ሰው ሊያደርገው እንዳልቻለ ነው ከከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ማብራሪያ ለመረዳት የተቻለው፡፡

‹‹ዘመናዊነት መጥቶ ክህደት እስከሚያስተምረን ድረስ ወረቀት የሚባል ነገር አልነበረም፤›› ያሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ ማንኛውም ስምምነት በቃል ብቻ ይፈጸም እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ‹‹የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›› የሚል ብሒል የኢትዮጵያ መለያዋ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡

አሁን ግን ይህ ሁሉ መተማመን ቀርቶ በምትኩ መጠራጠር እንደሰፈነ፣ አለማወቅና መከፋፈል ተዘርቶ መተላለቅና መገዳደል እንደተመረተ፣ ሕገ መንግሥቱም ሰውነትን ሳይሆን ጎሰኝነትን እንዳስቀመጠ፣ ሌላው ቀርቶ በማያውቁት ነገር ሕፃናት ሲታረዱ ማየትና መስማት የተለመደ እየሆነ እንደመጣ ገልጸዋል፡፡

በመፍትሔነትም በኅብረተሰቡ መካከል ሰላምና መግባባት፣ ኅብረትና አንድነት፣ ወንድማማችነትንም በማስፈን ማኅበራዊ ትስስርና እኩልነትን ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡ አሁን ያለው ኅብረተሰብ በዚህ ረገድ የራሱ የሆነ አዲስ ታሪክ ለመሥራት መንቀሳቀስ ይገባዋል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

‹‹በታሪካችን ውስጥ ብዝኃነትን የሚል ቃል ሲወራ ነበር፤›› ያሉት ደግሞ መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው የኢንተርናሽናል ባይብል አድቮከሲ ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ ግርማ መሐመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እንደሳቸው አነጋገር፣ ኢትዮጵያ ብዝኃነት ያላት አገር ብትሆንም፣ ብዝኃነትን በትክክል ለማስተናገድ ጥረት ቢደረግም ጥረቱ ግን ሊሳካ አልቻለም፡፡

‹‹ኅብረተሰብንና አብሮ መኖርን የምንተረጉምበት ዕይታና ዓለምን የምናውቅበት መንገድ ቢኖርም በጥርጣሬ የተሞላ ሆኗል፡፡ መጠራጠርና ፍርኃት ዕውቀት ሆኖብናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጎረቤትንና የገዛ ወገንን መፍራት ዕውቀት ወደ መሆን ደረጃ ደርሶብናል፡፡ በዚህም የተነሳ እንጋጫለን፤ ግጭት ደግሞ በአንድ ጊዜ አይመጣም፡፡ መጀመርያ ከመለየት ነው፡፡ ከዚያም መጠራጠር ይከሰታል፡፡ ከጥርጥር ግጭት ይፈጠራል፡፡ ከዚያም ጥፋት ይከሰታል፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ዓይነቱም ሁኔታ የመኖርን ህልውና አደጋ ሊያስከትል፣ እንደ አገርም ከመፈረካከስና ከመበታተን ችግር አልፎ ወደ መጠፋፋት ደረጃ እየተገባ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡ ለዚህም ችግር መቃናት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የመፍትሔ አካል መሆን ሲገባው፣ አንዳንዶቹ ከውጭና እኩሌቶቹ ደግሞ ከፍተኛ ቦታ ካሉ መሪዎች መፍትሔ ሲሹ እንደሚታይ ነው የተናገሩት፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ታደሰ ቡርቃ (ዶ/ር) ማኅበራዊ ትስስርንና አንድነትን የማጠናከር ጉዳይ ላይ መወያየት ትልቅነት እንዳለው ገልጸው፣ በዓለም ላይ ወጡ የተባሉ ሕጎች ሁሉ በአንድም ሆነ በሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ ዕይታ ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ ከታደሙት አንዱ እንዳስገነዘቡት፣ ኢትዮጵያ የሰላም ባለቤት እንድትሆን ኅብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች ኃላፊነት አለባቸው። በርካታ ቁጥር የያዘው ወጣቱ በመሆኑ የአገሪቱ መፃኢ ዕድል በወጣቶች ላይ ነውና።

አገራዊው ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት መንግሥት በየመዋቅሩ በተዋረድ ሕግን የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል፡፡  ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት ከሕዝብ ተሰጥቶታልና፡፡

ጉባዔውን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ ተስፋ ጽዮን ደለለው (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ማኅበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከማስተርጐም፣ ከማሳተምና ከማሠራጨት ጎን ለጎን ወቅታዊና ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ አብያተ ክርስቲያናትንና ባለድርሻ አካላትን በማወያየት፣ ማኅበራዊ የሆኑ ችግሮች በሚቀረፉበት መንገዶች ላይ ትኩረት እንዲደረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...