Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየቂም በቀልና የጥላቻ ቁስል እንዲሽር ምን ይደረግ?

የቂም በቀልና የጥላቻ ቁስል እንዲሽር ምን ይደረግ?

ቀን:

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

 ‘‘አናጨብሱ’’ – ስበረኝ… አንተ ወደ ቤቴ መጥተኻልና በትህትና ልሸነፍልህ!! (የጂማ ኦሮሞዎች)፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት ‘የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ’ እና ‘ጀስቲስ ፎር ኦል’ የተባለ አገር በቀል ድርጅት፣ ‘‘አገር በቀል የሆኑ ዕሴቶቻችን ለሰላም ግንባታ’’ በሚል መሪ ቃል፣ በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት ባዘጋጁት የምክክር መድረክ ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡

- Advertisement -

የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ እናቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የሰላም አምባሳደሮችና የግጭት አፈታት ምሁራን የተገኙበት በዚህ መድረክ ላይ፣ የጀስቲስ ፎሮ ኦል ዳይሬክተር ፓስተር ዳንኤል ገብረ ሥላሴ፣ ‘‘በእንኳን ደህና መጣችሁ!’’ ንግግራቸው፣ ተወልደው ባደጉበት በጅማ ኦሮሞዎች ዘንድ ለእንግዳ ያለን ክብርንና ትህትናን የሚገልጽ አንድ አስደናቂ የሆነ የሕዝባቸውን ባህል አጫውተውን ነበር፡፡

ፓስተር ዳንኤል እንደነገሩን በቀደመው ዘመን በጅማ ኦሮሞዎች ባህል አንድ እንግዳ ወደ ቤታቸው ሲመጣ፣ የቤታቸውንና የልባቸውን በር ከፍተውና ከመቀመጫቸው ተነስተው በሞቀ ፈገግታ እንግዳውን ወደ ቤቱ እንዲገባ በክብር ይጋብዙታል፣ በትህትና ዝቅ ብለውም ‘‘አናጨብሱ’’ ይሉታል፡፡ ‘‘አናጨብሱ’’ ማለት በአፋን ኦሮሞ ትርጉሙ ‘‘ስበረኝ’’ እንደማለት ሲሆን፣ የቤቱ ባለቤት ወደ ቤቱ አክብሮት የመጣው እንግዳ ሰው ከእሱ የሚበልጥ መሆኑንና በፍቅርና በትሁት መንፈስ ለእንግዳው ተሸናፊና ታዛዥ መሆኑን የሚያሳይበት የእንግዳ አቀባበል ሥነ ሥርዓት ነው፣ አ-ና-ጨ-ብ-ሱ!!

አናጨብሱ!! ይህ በጅማ ኦሮሞዎች ዘንድ ለእንግዳ የሚሰጥ ፍቅርን የተላበሰ ትህትና፣ አሁንም ድረስ በሌሎች የአገራችን ክፍሎችም ቢደበዝዝ እንጂ ጨርሶ አልጠፋም ማለት ይቻላል፡፡ ዛሬም በአገራችን ባህል እንግዳ ክቡር ነው፡፡ እስከ ተረቱም፣ ‹‹ቤት ለእንግዳ፣ የእግዜር እንግዳ ከሜዳ አያድርም፤›› የሚል ዘመን ጠገብ ብሂል አለን፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህ ለእንግዳ ያለንን ክብር፣ ፍቅርንና ትህትናን አስመልክቶ በውጭ አገሮች ተጓዦችና አሳሾች፣ ጸሐፍትና የታሪክ ሊቃውንት ዘንድም በብዙ የተመሰከረለት ነው፡፡

ፓስተር ዳንኤል ባደጉበት በጅማ ኦሮሞ ባህል ባህል የታዘቡትን በሰላም፣ በፍቅር፣ በትህትና የመሸነፍ ‘የአናጨብሱ’ ባህል ከተረኩልን በኋላ፣ በዚህ መድረክ የክብር እንግዳና ተናጋሪ የነበሩት፣ የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ ሰብሳቢና አሁን ደግሞ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር የሆኑት መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) ቁጭትና ሐዘን ባረበበበት መንፈስ እንዲህ አሉን፣ ‹‹… ይህ አኩሪና ዓለም የተደነቀበትና ሰላም የሰፈነበት መከባበራችን፣ ለሌላው በትህትና ዝቅ ማለትና በፍቅር የመሸነፍ ባህል፣ ‘‘አናጨብሱ!’’ በፖለቲካችን መድረክ፣ በሐሳብ ተዋስዖችን፣ በፖለቲካ መሪዎቻችን፣ በመንግሥት ባለሥልጣናቶቻችን ዘንድ፣ በዕለት ተዕለት ማኅበራዊ መስተጋብራችን… ወዘተ. ለምን ጎልቶ አይታይም?!’ ለምንድነው ‘የአንተ ይብስ፣ የአንቺ ይብስ’ በሚል በትህትና ሌላው ዝቅ ማለት፣ በፍቅር መሸነፍ ባህላችንን ምን ዋጠው?!…››፡፡

በእውነቱ የ‘አናጨብሱ’ ባህል በፖለቲካችን መድረክ ሥፍራው የት ነው?! ይህ በአክብሮትና በመከባበር ትሁት መንፈስ መቀባበላችን በአብሮነታችን፣ በማኅበራዊ መስተጋብራችን ዘንድ ሥፍራው ወዴት ነው?! ብለን እንጠይቅ እስቲ!?

ለጽሑፌ ፈር ማስያዣ ይሆነኝ ዘንድ ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን ጥቂት ገጾችን ልምዘዝ እስቲ፡፡

የፖለቲካና የመንግሥታት መለዋወጥ ታሪካችንን ወደኋላ ተጉዘን ስንፈትሸው፣ ከ‘አናጨብሱ’ ባህል ይልቅ የእኔነት መንፈስ የተጫነውና የእኔ ብቻ ካልሆነ የሚል ግትርነት የተጣባው ነው፡፡ ከቅርብ የታሪካችን ዘመን ለመጀመር እንኳን የአገራችን ዘመናዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴ መንገዱ የተመረቀው በደም ነው፡፡ ‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!›› ተብሎ የተጀመረ ነውጥ ለውጥን ሳይሆን፣ በሒደት ‹‹አብዮት ልጆቿን ሳይቀር እንኳን ትበላለች!›› በሚል በአንድ ጀምበር ወደ አስፈሪና ዘግናኝ ፃዕረ ሞትነት ነው የተቀየረው፡፡ ከዚህም የተነሳ ከአንድ ማህፀን የወጡ ወንድማማቾች እንደ ክፉ ባላጋራ ሁሉ ሳንጃ ተማዘዋል፡፡

የትናንትናው ኢትዮጵያ ባለ ታላቅ ታሪክ ባለቤት የሆነው ያ ትውልድ የሐሳብ ልዩነቱን ለማስታረቅም፣ የጠመንጃ አፈሙዝን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ እንዲወስድ ነበር የተገደደው፡፡ በዚህም ምክንያት አንዱ በለስ ቀንቶት አንዱን ቢጥል እንደ ጀግና ይወደስም ነበር፡፡ አባት ልጁን መምራትና መቆጣጠር ተስኖት ነበር፡፡ ይባስ ብሎም አባትና ልጅ ተመሳሳይ የፖለቲካ አመለካከት ከሌላቸው እርስ በርስ በዓይነ ቁራኛ መጠባበቅ ነበረባቸው፣ ለምን ቢባል ‘አጥፊና ጠፊ’ ናቸውና፡፡

የታሪክ ምሁሩ ኢመሬትስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፣ ‹‹ያለ መቻቻል ፖለቲካ ሰማዕታት- መቼም እንዳይደገም›› በሚል የጥናት መጽሐፍ ላይ ባቀረቡት፣ ‹‹ቀይ ሽብር በኢትዮጵያ ታሪካዊ ይዘትና አንድምታ›› በሚለው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንደጠቀሱት፣ ‹‹የኢትዮጵያ አብዮት ተፃራሪ ገጽታዎችን ያሳየ ክስተት ነበር፡፡ እንደ ታላቆቹ የፈረንሣይና የሩሲያ አብዮቶች በደስታና በተስፋ ተጀምሮ በሰቆቃና በፀፀት የተደመደመ ነው፤›› በማለት ያን አገሪቱን የወላድ መካን፣ የደም ምድር/አኬልዳማ ያደረጋትንና የብዙ ወገኖቻቸውን ሕይወት ጭዳ ያደረገውንና ገና በፅንሱ የጨነገፈውን አብዮት፣ ‹‹በደም፣ በሰቆቃና በፀፀት የተደመደመ ነበር፤›› በማለት ነው በቁጭት የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ያሻግራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ተማሪ፣ ገበሬ፣ ወታደር፣ ምሁሩ በነቂስ ሆ! ብሎ የተሳተፈበት የለውጥ ዕርምጃና አብዮት በአገራችን ላይ ጥሎት ያለፈው ጠባሳ እጅግ ከባድና መራር ነው፡፡ እስካሁንም ድረስ በዚያን ዘመን ትውልድ አባላት ለውጥን ናፋቂና አራማጅ ቅሬታዎች ላይ የፈጠረው የልዩነት ገደል፣ ጥላቻና መራርነት ሳይናድ እዚህ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡

ከ60ዎቹ በኋላም በአገራችን ለውጥ በጠረጴዛ ዙሪያ ሰጥቶ በመቀበል ሳይሆን በኃይል፣ በብረት ነው፡፡ ደርግን ለመፋለም በረሃ የገቡ ወጣቶች ከ17 ዓመታት ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ መንግሥት የሆነው ኢሕአዴግ በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ዕውን ለማድረግ ሙከራዎች ቢያደርግም የታሰበውንና የተመኘነውን ያህል ሙከራው እምብዛም የተሳካ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ለአብነትም፣ ለአገራችን ትልቅ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማበብ ጥሩ መደላደል ይሆናል ተብሎ የታሰበው ምርጫ 97 ፍፃሜው ደም ያፋሰሰና አንገታችንን የደፋንበት አሳፋሪና አሳዛኝ ክስተት ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡

እንደ መውጫ

አገራችን ያለችበት ሁኔታ አስቸጋሪና እጅግ አሳሳቢ መሆኑ የሁላችንንም ግንዛቤ የሚሻ ጉዳይ ቢሆንም፣ ይህ ግን በራሳችንና በአገራችን ዕጣ ፈንታ ላይ ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም፡፡ ጉዳዩ የእያንዳንዳችን ጉዳይ እንደሆነ ተገንዝበን፣ እጅጉን ተጨንቀን ተጠበን ከመከርንበት መፍትሔ ሊገኝለት የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ ታሪካችንን ስንመረምርም፣ አገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ የደረሰችው በረጅም ችግርና ፈተና አልፋ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡ በእርስ በርስ ጦርነቶችን አልፈናል፡፡ በበርካታ የውጭ ወረራዎች ተፈትነናል፡፡ አሰቃቂ በሆኑ የድርቅና ረሃብ ወቅቶችም አልፈናል፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ እንደ አገርና እንደ ሕዝብ አለን፡፡ እነዚህን አልፈን እዚህ ድረስ ለመዝለቅ ያስቻሉን እንደ ‘‘አናጨብሱ’’ ያሉ አገራዊ በጎ እሴቶቻችን ፈጽመው እንዳልጠፉና ከውስጣችን እንዳሉ አምነን፣ እንዲህ ባለው ፈታኝ ወቅት እነሱን ማፈላለግና አጥብቆ መያዝ ይገባናል፡፡

ስለሆነም ዛሬም በጥላቻ፣ በቂም በቀለኝነትና በጽንፈኝነት እግረ ሙቅ ውስጥ ለወደቀው የአገራችን ፖለቲካ መፍትሔው፣ በ‘አናጨብሱ’ ባህልና ትውፊት የተቃኘ በመደማመጥ፣ በመከባበር፣ በመጋገር የሰላምንና የዕርቅን ባንዲራ ከፍ አድርጎ ማንሳት ነው፡፡ የኢትዮጵያችንን የዘመናት ፖለቲካዊ ስብራቷና እያመረቀዘ ያስቸገራትን የቂም በቀልና የጥላቻ ቁስሏ ይሽር ዘንድ ብሔራዊ ዕርቅና ምክክር ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልገናል፡፡

በጥላቻ፣ በቂም በቀለኝነትና በጽንፈኝነት እግረ ሙቅ ውስጥ ለወደቀው የአገራችን ፖለቲካና አብሮነታችን መፍትሔው ከልብ የሆነ ብሔራዊ ዕርቅ፣ መግባባት፣ በሰላማዊ መንገድ በግልጽ መነጋገር/መወያየት እንደሆነ በግሌ በእጅጉ አምናለሁ፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የጥናትና ምርምር ባለሙያ፣ በዓለም ዕርቅና ሰላም ግብር ሰናይ ድርጅት የቦርድ አባልና በዩኒቨርሳል ፒስ ፋውንዴሽን (UPF) የሰላም አምባሳደር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...