Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከጦርነቱ ወደ ኢኮኖሚ ልማቱ ማለፊያ በሮችን የማስከፈት ትንቅንቅ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረውን የሥልጣን ሽኩቻ ድል አድርገው የፓርቲውን ሊቀመንበርነትና የአገሪቱ ጠቅላይ የሚኒስትርነት መንበር በ2010 ዓ.ም. ሲረከቡ በፈተና የተሞላውን የሥልጣን ጉዞ ያጠናቀቁ ቢመስልም ዕውነታው ግን ሌላውን ውስብስብ የፈተና ጎዳና አንድ ብለው መጀመራቸው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወቅቱን ገዢ ፓርቲ የመምራትና አገር የማስተዳደር ሥልጣን ቢረከቡም፣ ከሥልጣን ባሻገር በውስብስብ ግጭቶች የሚተራመስ የፖለቲካ ዓውድንና በከፍተኛ የውጭ የዕዳ ክምችት የታሰረ ኢኮኖሚን ከኢሕአዴግ መውረሳቸው እሙን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡ ማግሥት የወሰዷቸውን ዓበይት ዕርምጃዎች በአንክሮ ያስተዋለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢሕአዴግ የወረሱት የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ፈተና እንደሚሆንባቸው አስቀድመው መረዳታቸውን መገንዘብ ይችላል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን በመጡ የመጀመሪያ ሳምንት ከተገበሯቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የመዘወር አቅም አላቸው የሚባሉትን ግዙፍ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታነት እንዲዘዋወሩ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ማስወሰን ነበር። በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ ኢትዮ ቴሌኮምን፣ ግዙፎቹን ስኳር ፋብሪካዎችን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ የባቡር መሠረተ ልማቶችንና የኃይል ማመንጫዎችንና ሌሎችን በከፊልና ሙሉ በሙሉ በመሸጥ ወደ ግል ይዞታነት እንዲዘዋወሩ በገዢው ፓርቲ አስወስነዋል። ይህም በከፍተኛ ደረጃ የተቆለለውን የአገሪቱን የውጭ ብድር በማቅለል ተጨማሪ የውጭ ፋይናንስ ለማግኘትና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እንዲሁም ለውጭ ምንዛሪ ቀውሱም መጠነኛ እፎይታ ለመስጠት ያለመ ነበር። ውጥኑ ይህ ስለመሆኑም ዘግየት ብሎ የወጣው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የተሰኘው የሦስት ዓመት የኢኮኖሚ ልማት መርሐ ግብር ግልጽ አድርጎታል። 

አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በተባለው የሦስት ዓመት የኢኮኖሚ መርሐ ግብር ውስጥ ከተካተቱት የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አንኳር ጉዳዮች መካከል በከፊል የተተገበረው በመንግሥት ሞኖፖሊ ሥር የነበረውን የቴሌኮም አገልግሎት ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት የማድረግ ግብ ነው። በዚህም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ለመሆን ከተወዳደሩት መካከል የኬንያው ሳፊሪኮም ጨረታውን በማሸነፍ ፈቃድ አግኝቶ ከጥቂት ወራትች በፊት አገልግሎቱን ጀምሯል። ለዚህ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ የኢትዮጵያ መንግጨት የተቀበለው 850 ሚሊዮን ዶላር የፈቃድ ክፍያ ያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም በግልጽ አይታወቅም።

በርካታ የኢትዮጵያ ልሒቃን አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የተባለውን የሦስት ዓመት የኢኮኖሚ ልማት መርሐ ግብር በጥርጣሬ ቢያዩትም እንደ አይኤምኤፍ ያሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች ግን በደስታ ተቀብለው ለተግባራዊነቱም በርከት ያሉ ቢሊዮን ዶላሮችን በድጋፍ መልክ ለማቅረብ ፊርማቸውን አኑረዋል። 

ይሁን እንጂ የዚህ የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ በተጀመረ አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላው ከኢሕአዴግ ውስጥ ተቆርሶ በወጣው ሕወሓትና በገዢው ብልጽግና ፓርቲ መካከል የተፋፋመው የፖለቲካ ጥል ተካሮ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን በመውለዱ የታሰበው የኢኮኖሚ ሪፎርም ከባድ እክል ውስጥ ገብቷል። የታሰበውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ለመደገፍ ገንዘባቸውን ያሰናዱት የውጭ የፋይናይስ ተቋማትና የልማት አጋሮች አገሪቱ ጦርነት ውስጥ መግባቷን በመቃወም የድጋፍ እጆቻቸውን ሰብስበዋል። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ሰሞኑን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በመቀስቀሱ ምክንያት አይኤምኤፍም ሆነ የዓለም ባንክ ቃል የገቧቸውን የኢኮኖሚ ድጋፎች ማጠፋቸውን ያረጋግጣሉ።

‹‹አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማስቀጠል፣ ልማትን ለማፋጠንና አገር በቀል ኢኮኖሚ ፕሮግራሙን እንዲደግፉ ለቀረበላቸው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡ ለምሳሌ አይኤምኤፍ (IMF) 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ ለመስጠት ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም ከዚህ ውስጥ 300 ሚሊዮን ዶላሩን ብቻ ሰጥቶ ቀሪውን 2.6 ቢሊዮን ዶላር በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ሳይለቀቅ ቀርቷል፤›› ብለዋል፡፡ 

የዓለም ባንክም ሦስት ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም ቃል የተገባውን ማግኘት እንዳልተቻለ አቶ ተክለወልድ ገልጸዋል።

‹‹ስለዚህ ከእነዚህ ተቋማት ብቻ ይገኛል ተብሎ የታሰበው በድምሩ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የፋይናንስ ድጋፍ አልተገኘም፤›› ብለዋል።

በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከተጣሉ ግቦች መካከል ሌላኛው ኢትዮጵያ ያለባትን ግዙፍ የውጭ ዕዳ መክፈያ ጊዜ አበዳሪ አገሮቹ እንዲያራዝሙ ወይም እንዲያሸጋሽጉ ማድረግ ነበር። ለዚህም ሲባል ለግል ባለሀብቶች ከሽያጭ ከሚተላለፉ የመንግሥት ተቋማት የሚገኘውን ገቢ በተወሰነ ደረጃ ለዕዳ ክፍያ በማዋል አገሪቱ የተወሰነ እፎይታ ቢሰጣት ኢኮኖሚዋ መልሶ መክፈል ይችላል የሚል ማስተማመኛ በመስጠት የብድር ክፍያ ማራዘሚያ ማግኘት የውጥኑ ማስፈጸሚያ ሥልት ነበር። 

‹‹የቡድን 20 አገሮች ባስቀመጡት የዕዳ ማራዘመያ ማዕቀፍ (G20 Framework) መሠረት መንግሥት የዕዳ መክፈያ ጊዜን ለማራዘም ከፓሪስ ክለብ አበዳሪ አገሮች ጋር የጀመረው ድርድርም የተቋረጠው በጦርነቱ ምክንያት ነው፤›› ሲሉ አቶ ተክለወልድ ገልጸዋል።

አገሪቱ ያለባት የውጭ ዕዳ መጠን በዓለም አቀፍ መመዘኛ መሠረት የመጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ሲሆን፣ ይህ ውዝፍ ዕዳ ሳይቃለል ሌላ ተጨማሪ የውጭ ብድር መውሰድ አገሪቱን የውጭ ዕዳ መክፈል የማትችል ምድብ ውስጥ እንደሚከታት ይነገራል። ከአገር ውስጥ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ዓመታዊ ገቢ፣ ማለትም ከአገር ውስጥ ግብርና ታክስ የሚገኘው የገቢ መጠን ከአፍሪካ ዝቅተኛው የሚባል ሲሆን፣ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት ፍላጎት ለመሸፈን ጨርሶ የሚችል እንዳልሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በመሆኑም መንግሥት የአገሪቱን የውጭ ዕዳ መጠን አቃሎ ወይም በድርድር ማራዘሚያ አግኝቶ ተጨማሪ የውጭ ብድር ካላገኘ የኢኮኖሚ ልማቶችን ለማከናወን ፈጽሞ እንደማይችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አገሪቱ በጦርነት ውስጥም ሆና ያለባትን የውጭ ብድር መጠን ለመቀነስ በዓመት እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እያወጣች መሆኑን ከብሔራዊ ባንክ መረጃ ለመረዳት ተችሏል። ይህም ሆኖ የአገሪቱ አጠቃላይ የውጭ ብድር መጠን በአሁኑ ወቅት 29 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከአጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ (ጂዲፒ) ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳለው የገንዘብ ሚኒስቴር በየሩብ ዓመቱ የሚያወጣው የውጭ ዕዳ መረጃ ያመለክታል።

በመሆኑም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት መንግሥት ያቀደው የኢኮኖሚ ሪፎርም መርሐ ግብር አልተሳካም ማለት ይቻላል። ከዚህም ባለፈ ጦርነቱ ከመቶ ቢሊዮኖች ብር በላይ አዲስ ወጪን በመጠየቁ መንግሥት ለካፒታል ፕሮጀክቶች ይዞት የነበረውን በጀት በማጠፍ ለጦርነቱ ለማዋል ተገዷል። በዓለም አቀፍ መመዘኛ መሠረት የፌዴራል መንግሥት የበጀት ጉድለትን ለመሙላት ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደው ቀጥታ ብድር ከጂዲፒው ሦስት በመቶ መብለጥ የሌለበት ቢሆንም በ2014 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት የወሰደው ቀጥታ ብደር ግን ከዚህ ጣራ አልፎ አራት በመቶ እንደነበር የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። 

በዚህ ሳምንት የዘንድሮውን የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ከወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎች ጋር በተገናኘ ጥብቅ የገንዘብና የበጀት ፖሊሲ ለመከተል እንዳልተቻለ ግልጽ አድርገዋል። 

የሰሜኑ ጦርነት የማኅበረሰቦች መስተጋብርን ከማሳሳት ባለፈ በመሠረተ ልማቶች ላይ ያስከተለው ውድመት እጅግ ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ ወደነበረበት ለመመለስ 20 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚያስፈልግ መንግሥት በይፋ አስታውቋል። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን ጦርነቱን ለማቆምና ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማበጀት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የውጭ ዲፕሎማቶች ከአንድ ወር በፊት በሰጡት ማብራርያ፣ ጦርነቱ ያደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በጥናት መለየቱን ገልጸው ድጋፋቸውን መጠያቃቸው ይታወሳል።

ከጦርነቱ ወደ ኢኮኖሚ ልማቱ ለማቅናት

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለማቆምና ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የሰላም ስምምነትን ተከትሎ ቀደም ሲል በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተይዘው ሳይፈጸሙ የቀሩ ወይም የዘገዩ ተግባራትን መልሶ ማንቀሳቀስ ጀምሯል። 

ከነዚህም መካከል በዋነኝነት መቀነስ የሚችለው የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ እንደ አዲስ የፍላጎት መግለጫ ጥሪ መውጣቱ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት የተዘጉበትን የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በሮች ለማስከፈት ጥረት ማድረግ ጀምሯል። በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የሚመራ ልዑካን ቡድን ከአንድ ወር በፊት በአሜሪካን አገር በተካሄደው የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ ዓመታዊ የጋራ ጉባዔ ላይ በመሳተፍ የጎንዮሽ ድርድሮችን ማድረጉ የተጀመረው ጥረት አካል ነው። በወቅቱም በአሜሪካን አገር የሚገኙ ተቃዋሚ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማቱ ያጠፉትን ገንዘብ እንዳይለቁ የመወትወትና ጫና የመፍጠር ጥረት ሲያደርጉና በጉባዔው ለመታደም የተገኙ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካንን ሲያወግዙ እንደነበር ይታወሳል።

በዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑክ ውስጥ የተካተቱት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪና የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ገዥ የነበሩት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ የቡድኑ ተልዕኮ ከፋይናንስ ተቋማቱ ጋር ውይይቶችን ለመጀመር እንጂ፣ ‹‹ገንዘብ ለመውሰድ መጥተው አስከለከልን›› እንደሚባለው አለመሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

በቅርቡ ወደ እነዚህ ተቋማት በመሄድ የተደረገው ውይይት ከዚህ ቀደም የነበረው ፕሮግራምን ለማስቀጠል እንዳልነበረ የገለጹት አቶ ተክለወልድ፣ ‹‹የሰላም ስምምነቱን ለመተግበር ያለንን ቁርጠኝነት ለማሳወቅና፣ በእኛ በኩል ጥሩ እያደረግን መሆኑን በማስረዳት የቆሙ ፕሮግራሞች እንዲጀምሩ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ለመምከር እንጂ ገንዘቡን ለማስለቀቅ አልነበረም፤›› ብለዋል።

አክለውም የልዑክ ቡድኑ ጉዞው ዓላማ ገንዘብ ለማስለቀቅ ሳይሆን ሁኔታቸውን ለማመቻችና አዲስ ፕሮግራም ተቀርፆ ወደ ሥራ መግባት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር እንደነበር ገልጸዋል።

‹‹ባለፈው ሰጥተኸኝ ነበርና ያንን ገንዘብ ስጠኝ የሚባል ነገር ስለሌለ የድጋፍ ጥያቄው በአዲስ መልክ ይቀርባል፤›› በማለት ሒደቱን አስረድተዋል፡፡  

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ነገሮች ጥሩ እየሆኑ በመምጣታቸው የድጋፍ ጥያቄ መቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን የገለጹት አቶ ተክለወልድ፣ ቀድሞ የነበረው ፕሮግራም ሁለት ዓመታት ከቆየ በኋላ ዋጋ ስለሌለው፣ በአዲስ መልክ ፕሮግራም ተቀርፆ ለፋይናንስ ተቋማቱ የድጋፍ ጥያቄ እንደሚቀርብ አመልክተዋል፡፡  

አዲሱ የድጋፍ ጥያቄም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የአገሪቱን ኢኮኖሚ በየዘርፉ በመተንተን አዲስ ፕሮግራም በመቅረፅ ለዚህ የኢኮኖሚ ልማት ፕሮግራም የሚሆነውን የገንዘብ መጠን በመለየት ጥያቄው እንደሚቀርብም ከአቶ ተክለወልድ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

አሁንም ለዚህ ፕሮግራም የሚቀርበው የገንዘብ ድጋፍ በምን መልኩ ይሁን የሚለውም የሚታየው አገር በቀል የኢኮኖሚ ፕሮግራሙ ከደረሰበት ደረጃ በመነሳት በሚዘጋጅ አዲስ የኢኮኖሚ ልማት መርሐ ግብር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ 

‹‹አገር በቀል ኢኮኖሚ ፕሮግራሙም ቢሆን ሦስት ዓመት ሆኖታል፡፡ ይህንን ሪፎርም ለመተግበር ብዙ ሠርተናል፣ የሚቀሩት አሉ፤›› ያሉት አቶ ተክለወልድ፣ ከዚህ በኋላ የሚቀርብ የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄም ይህንን ፕሮግራም በማሻሻል የሚጠየቅ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ 

‹‹ስለዚህ ነገሮች የሚስተካከሉ ከሆነ ልክ ላለፈው የኢኮኖሚ ፕሮግራም እንዳደረግነው ሁሉ አሁንም ኢኮኖሚው እንዲያገግም ምን ማድረግ ያስፈልጋል የሚለውን ቁጭ ብለን በመገምገም የሦስትና የአራት ዓመት ፕሮግራም ቀርፀን ከዚያ በኋላም በእኛ በኩል መውሰድ ያለብንን ዕርምጃዎች ላይ ተወያይተንና ተደራድረን ከተስማማን በኋላ ለአይኤምኤፍ ቦርድ ቀርቦ የሚወሰን ይሆናል፤›› ብለዋል።

የዕዳ መክፈያ ጊዜን ለማራዘም ከፓሪስ ክለብ አበዳሪ አገሮች ጋር የተጀመረው ድርድርም የተቋረጠው በጦርነቱ ምክንያት ሲሆን፣ ይህንን ድርድር ለማስቀጠልና አወንታዊ ምላሽ ለማግኘት ጥረቶች መጀመራቸውንም አቶ ተክለወልድ አስረድተዋል፡፡ የዕዳ ክፍያውን ለማራዘምና ለማሸጋሸግ እየተሠራ ያለው ዝርዝር ዕቅድ በአይኤምኤፍ የሚደገፍ ሲሆን የዕቅድ ዝግጅቱ አገሪቱ ያለባትን የውጭ ዕዳ ክምችት ከኢኮኖሚ ልማት ፕሮግራሞች ጋር በማስተሳሰር እንደሚነደፍ ጠቁመዋል። 

በዚህም መሠረት የሚዘጋጀው ሰነድ፣ አገሪቱ የተወሰነ የዕዳ ቅነሳና የዕዳ መክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ ቢፈቀድላት ተጨማሪ አዲስ የውጭ ብድር መበደርም ሆነ ነባሩን ዕዳ ለመክፈል እንደምትችል በሚያመላክት መልኩ እንደሆነ ገልጸዋል። 

ስለሆነም የሚዘጋጀው ዝርዝር ዕቅድ የዕዳ ሽግሽግና የመክፈያ ጊዜ እፎይታ ወይም ማራዘሚያን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ቀጣይ የኢኮኖሚ ልማት ዕቅዶችንና ለዚህ የሚያስፈልገውን የውጭ ብድርንም ከሚጠቁም የልማት ፕሮግራም ጋር የሚሰናሰል እንደሚሆን አስረድተዋል። 

በዚህ መልኩ የሚዘጋጀው ዕቅድ ለአይኤምኤፍ ቦርድ ቀርቦ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ የአገሪቱን የውጭ ዕዳ መክፈያ ጊዜ ለማራዘም መንግሥት ለፓሪስ ክለብ አበዳሪ አገሮች ያቀረበው ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ እንዲያገኝ የሚያስችል ሲሆን፣ ሌሎች የተቆለፉ የውጭ አበዳሪዎች በሮችንም እንደሚከፍት ጠቁመዋል። 

በመሆኑም የሰላም ስምምነቱ መፈጸም የአገሪቱን የውጭ ዕዳ መክፈያ ጊዜ ለማራዘምና አዲስ ብድር ለማግኘት የሚያስችሉ ድርድሮችን ለማስቀጠል ዕድል የሚሰጥ ሲሆን፣ ድርድሮቹ የሚያስገኙት ውጤት ድግሞ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ የሆነ አወንታዊ ተፅዕኖ ያበረክታል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ተክለወልድ ገልጸዋል። የእነዚህ ድርድሮች መጀመርና መሳካት በተለይ ኢኮኖሚው ውስጥ ዋነኛ የሚባሉ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳልም ብለዋል፡፡ 

አሁን ላለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች ዋነኛው የውጭ ምንዛሪ እጥረት መሆኑን በመጥቀስ፣ ለእነዚህ የገንዘብ ተቋማት በሚቀርቡ ፕሮግራሞች የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በእጅጉ እንደሚደግፍ እምነታቸውን ገልጸዋል። 

‹‹የውጭ ምንዛሪ አገኘህ ማለት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ይቻላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ካለህ ዕቃ አምጥቶ ገበያን ማረጋጋት ይቻላል፡፡ ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን ለማምጣትና ለሁሉም የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ያስቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ኢኮኖሚውን ያጠነክራል፤›› ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ሪዘርቭን (ክምችትን) ለማጠናከርም ጭምር ስለሚያግዝ ድጋፍ ሰጪ ተቋማቱ የሚሰጡት መልስ ኢኮኖሚውን እንዲያንሰራራ ለማድረግ ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ያምናሉ፡፡ ከእነዚህ ተቋማት ጋር የሚደረገው ድርድር የመንግሥት የፋይናንስ ጉድለትን ለመሸፈን የሚሰጠው ዕድል ሌላው ጥቅም እንደሆነም ተናግረዋል።

ይህ የሰላም ስምምነት በሚፈለገው መንገድ ከተተገበረ፣ የመልሶ ማቋቋሙና የመሳሰሉት ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ኢኮኖሚውን ለማስቀጠልና ብዙ የውጭ ገንዘቦችን ለማምጣት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FID) ለመሳብ እንዲሁም ኢኮኖሚውን በአጭር ጊዜ እንዲያገግም ለማድረግ የሚያስችለውን በር የመክፈት ያህል እንደሆነ አመልክተዋል፡፡  

‹‹ይህንን በተግባር ለመቀየር እንዲሁም ወደ ቀድሞው ጥሩ ነገር ለመሄድ አሁን ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የታሰቡትን ነገሮች በአንድ ዓመት ውስጥ ማስፈጸም ይቻላል ማለት አይደለም። ሥራችንን እየሠራን በሁለትና በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ኢኮኖሚው እንዲያገግም የሚደረግበት ሁኔታ ይኖራል፤›› ብለዋል፡፡ 

  ዳዊት ታዬ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች