Tuesday, February 27, 2024

የፀረ ሙስና ዘመቻ ተስፋና ተግዳሮት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እ.ኤ.አ. በ2018 ኮኔን ራህማን ያዘጋጀችው ‹Overview of Corruption and Anti-Corruption in Ethiopia› የተባለ የኢትዮጵያን የሙስናና የፀረ ሙስና ዘመቻ ሁኔታ የዳሰሰ የጥናት ውጤት ብዙ መረጃዎችን ይዟል፡፡ ‹‹የፀረ ሙስና ሕጎች በኢትዮጵያ በመርህ ደረጃ ጠንካራ የሚባሉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በቅጡ በተግባር ሲተረጎሙ አይታዩም፤›› በማለት ጥናቱ ከሕግ አኳያ የገመገመውን ያስቀምጣል፡፡ ‹‹የሥራ አስፈጻሚው አካል ሕግ አውጭውንም ሆነ የፍትሕ ተቋማቱን ይቆጣጠራል፤›› የሚለው ይህ ጥናት፣ የፀረ ሙስና ሕጎችም ሆኑ ተቋማት በኢትዮጵያ ጥርስ የሌላቸው አንበሳ መሆናቸውን ነው የሚያትተው፡፡

ጥናቱ ሙስናና ንቅዘት በኢትዮጵያ ያለበትን አስከፊ ገጽታ ካቀረበ በኋላ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር [ዓብይ አህመድ] ይህን ችግር ቅድሚያ በመስጠት ለመፍታት ቃል መግባታቸው ትልቅ ዕድል መሆኑን ነበር በወቅቱ ያስረዳው፡፡

ጥናቱ እንደጠቀሰው ብቻም ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡባቸው የመጀመርያዎቹ ወቅቶች እንደታየው፣ የፀረ ሙስና ጉዳይ ልዩ ትኩረት አግኝቶ አስገራሚ ሥራዎች ሲከናወኑ ለመታዘብ ተችሎ ነበር፡፡

በወቅቱ ባለሥልጣናት ከአባካኝ የውጭ ጉዞዎችና አሠራሮች እንዲታቀቡ ልዩ ትዕዛዝ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ የውጭ ምንዛሪ በእጁ ያለ ማንኛውም ግለሰብ ወደ ባንክ በመሄድ እንዲመነዘር የተደረገውን ጥሪ ተከትሎ፣ እጁ ላይ ያከማቸውን ዶላርና ዩሮ በባንክ ለመመንዘር ሲሽቀዳደም ታየ፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቪ8 መኪና መንፈላሰሳቸው ቆመ ተባለ፡፡ የሥራ ሰዓት ስርቆትና ማባከንን ከማስቀረት ጀምሮ የካቢኔ ስብሰባ ቅዳሜ መሆኑ ተነገረ፡፡ በዕረፍት ቀናት ጭምር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነን የሚሉ በዙ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሙስናን ያለማሽሞንሞን ነበር ‹ሌብነት› ሲሉ በስሙ ሲጠሩ ነበር፡፡ በቀድሞ አስተዳደር ወቅት የተፈጸመው የሌብነትና የምዝበራ ወንጀሎች ተጣርተው ዕርምጃ እንደሚወሰድ ቃል ከመግባት በተጨማሪ የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት በተጨባጭ የሚታይ ዕርምጃ ወደ መውሰድ ገባ፡፡ በተለይ ሜቴክ ከሚባለው ተቋም ክስረትና የሀብት ብክነት ጋር በተያያዘ ዕርምጃ ተወሰደባቸው የተባሉ ሰዎች በርካታ ነበሩ፡፡ ያን ሰሞን በቀደመው አስተዳደር የምዝበራ ወንጀሎች ላይ ይሠሩ የነበሩ ዶክመንተሪዎችም በርካታ ነበሩ፡፡

አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት ሥልጣን በያዘ የመጀመርያዎቹ ሰሞን፣ በሙስና ላይ እጅግ የሚያመር ይመስል ነበር፡፡ እንደ አጀማመሩ በሙስናና በብልሹ አሠራር ላይ የተጠናከረ ዕርምጃ ይወስዳል ተብሎ ሲጠበቅ ግን በሒደት የሙስና ጉዳይን የዘነጋ መንግሥት ወደ መምሰል ተሸጋገረ የሚሉ ታዛቢዎች ድምፃቸው መሰማት ጀመረ፡፡

የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሙስና ተጋላጭነት የ2021 ሪፖርት እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ከ180 የዓለም አሮች 87ኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከመጡ ወዲህ ብዙ ተሻሻለች ቢባልም፣ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ግን መሻሻሉ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2012 ወዲህ ስድስት ያህል ደረጃዎችን እንዳሻሻለች ብቻ ነው ትራንስፓረንሲ የሚናገረው፡፡

የዓለም ባንክ መረጃ በበኩሉ ኢትዮጵያን እ.ኤ.አ. የ2021 የሙስና ተጋላጭነት ሪፖርት ላይ ከ113 አገሮች በ61 ነጥብ እጅግ ከፍተኛ ሙስና ካለባቸው አገሮች ተርታ ያስቀምጣታል፡፡ በኢትዮጵያ የመንግሥታዊ ዘርፎች ሙስናው እጅግ ሥር የሰደደ መሆኑን የሚናገረው የዓለም ባንክ፣ ይህ ደግሞ በፖለቲካ ችግርና በባህል ተፅዕኖ የመጣ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም፣ የኑሮ ወጪ ግን ውድ የሆነባት አገር ናት የሚላት ኢትዮጵያ በሙስና መከላከል ላይ ጠንክራ ሥራ ካልሠራች አደጋው የከፋ መሆኑን ነው የዓለም ባንክ የሚያሳስበው፡፡

በኢትዮጵያ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በ1993 ዓ.ም. ሲቋቋም በዓቃቤ ሕግነት ያገለገሉት ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል፣ ‹‹ሙስና የአገርን ህልውና፣ እንዲሁም የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እየጣለ የሚገኝበት ደረጃ ላይ ነን፤›› ይላሉ፡፡

የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት ከሆነ መንግሥት ሙስናን መዋጋት የህልውና ጉዳይ ሆኖበታል፡፡ ጥብቅ የፀረ ሙስና ዘመቻዎች ማካሄድ እጅግ አስገዳጅ የሆነበት ወቅት መሆኑንም ያክላሉ፡፡ መንግሥት እንደ ከዚህ ቀደሙ ‹‹ሙስናን ዓይቶ እንዳላየ ለማለፍ የሚችልበት ጊዜ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው በቅርቡ ጠንከር ያለ የፀረ ሙስና ዘመቻ ለማካሄድ ግብረ ኃይል ያቋቋመው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

መንግሥት በኅዳር ወር መግቢያ ላይ ነበር ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ማዋቀሩን ይፋ ያደረገው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በፓርላማ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ሙስና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በመጥቀስ ብሔራዊ ኮሚቴ እንደሚቋቋም ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡ ይህን ባሉ በሁለት ቀናት ልዩነትም ሰባት አባላት ያሉት ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ መዋቀሩን ይፋ አደረጉ፡፡ ኮሚቴውን ይፋ ያደረገው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫም ሙስና ብሔራዊ ሥጋት ሲል ነበር የበየነው፡፡

‹‹የገጠመንን አገራዊ ፈተናና ችግር እንደ ዕድል የወሰዱ ሰዎች ቀይ መስመር ያልነውን ሌብነት ቀይ ምንጣፍ አድርገውታል፡፡ እንደ ማኅበረሰብ በየሁሉም ተቋማት ውስጥ ሌብነት እየተለማመድን ነው፡፡ በሌብነት ቤት እንጂ አገር አይገነባም፡፡ አገር አልባ ቤት እንጂ ዘላቂ አይሆንም፤›› በማለት ነበር ዓብይ (ዶ/ር) በሙስና ላይ ያላቸውን ምሬት የገለጹት፡፡

ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ የማዋቀር ዕርምጃ ተከትሎ፣ በየክልሉ ተመሳሳይ መዋቅሮች በመመሥረት ላይ ናቸው፡፡ ትናንት ሰባት አባላት ያሉት የፀረ ሙስና ኮሚቴ መመሥረቱን ይፋ እስካደረገው ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ድረስ በየክልሉ የኮሚቴ ምሥረታ ተጧጡፎ ነው የሰነበተው፡፡

ይህ ብቻም አይደለም ከሰሞኑ መንግሥት የተጠናከረ የፀረ ሙስና ዕርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን እያስታወቀ ነው፡፡ በየመገናኛ ብዙኃኑ ከፀረ ሙስና ትግል ጋር በተገናኘ እጅግ በርካታ ዜና በመዘገብ ላይም ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የመንግሥት የፀረ ሙስና ዕርምጃ ዘላቂነት አለው ወይ? የሚል ጥያቄ እየተነሳ ይገኛል፡፡ ሙስናን መከላከል የሚቻለው ወጥና ቋሚ የሆነ የፀረ ሙስና ተቋምና መዋቅር በመገንባት እንጂ፣ በአንድ ሰሞን ዘመቻና የኮሚቴ ምሥረታ አይደለም የሚል ሙግትም ከዚህ ጋር ተያይዞ እየተነሳም ይገኛል፡፡

በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተስፋዬ ሻሜቦ፣ ‹‹የሰሞኑ እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡን በከፍተኛ ደረጃ ለፀረ ሙስና ትግል አነሳስቷል፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ኮሚሽናቸው 200 ሠራተኞች ብቻ እንዳሉት የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፣ ተቋሙ ለብቻው ይህን ሥራ ይሥራ ቢባል ከባድ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

‹‹የፀረ ሙስና ኮሚሽንም የኮሚቴው አባል ነው፡፡ ዘመቻው መጀመሩ በዘርፉ ለሚሠሩ ሥራዎች ትልቅ ጉልበት ይሆናል፡፡ መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንደሰጠ ያሳያል፡፡ ብዙ ጥቆማዎች ከኅብረተሰቡ እየመጡ ነው፡፡ ዘመቻው ለፀረ ሙስና ትግሉ ትልቅ ዕገዛ ያደርጋል፡፡ ተቋማቱም ቢሆኑ ይህን መነሻ በማድረግ ለፀረ ሙስና ትግሉ ዘላቂ ስትራቴጂ ለመቀየስ ያግዛቸዋል፤›› በማለት ነው የተናገሩት፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ደግሞ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ዓለማትም የተለመደ ነው በማለትም አክለዋል፡፡

ዘመቻው አንዳችም የፖለቲካ ዓላማ እንደሌለው የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹ሌባ ሌባ ነው፣ ብሔር የለውም፡፡ በየክልሉ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ አሁን  ከኅብረተሰቡ ብዙ ጥቆማ እየመጣ ነው፡፡ የሙስናው ችግር ሥር የሰደደ መሆኑንም ሆነ ዘመቻው መቀጠሉ አስፈላጊ እንደሆነ ነው የምንረዳው፣ የኅብረተሰቡ ጥቆማ እየቀጠለ ሲሄድ ነው፤›› በማለትም ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ግን የፀረ ሙስና ጉዳይ በዘመቻ ወይም በአንድ ሰሞን ዕርምጃ ሳይሆን ወጥ በሆነ ተቋማዊ አሠራር የሚከናወን ውጊያ ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ እስከ ኢሕአዴግ መንግሥት በተለያዩ ወቅቶች የፀረ ሙስና ተቋማትና መዋቅር ለመፍጠር መሞከሩን ያወሱት አቶ ዮሐንስ፣ ብዙዎቹ ዘላቂ ሥራ እንዲሠሩ ታስቦ ባለመመሥረታቸው ዘመቻዎቹ በአጭሩ እንዲቀሩና ችግሩም ሳይፈታ እንዲቀጥል ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

‹‹ያም ቢሆን ግን በአሁኑ የፀረ ሙስና ግብረ ኃይል እንቅስቃሴ ተስፋ አለኝ፡፡ ተቋማዊ ወሰኑም ሆነ በሕግ የተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት እስከምን ድረስ እንደሆነ ለማወቅ ባይቻልም፣ መንግሥት ተነሳሽነት ወስዶ ይህን እንቅስቃሴ መጀመሩ በራሱ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አሁን ያለውን የሙስና ጉዳት የሚያከፋው ችግሩ በተለይ ከጎሳ ፖለቲካ ጋር መወሳሰቡ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ በዘር ፖለቲካ ተደራጅቶ መዝረፍና መመዝበር የአገሪቱን ህልውና ለአደጋ የጣለ ችግር እንደሆነ መንግሥት እየተገነዘበው መምጣቱን በበጎ እንደሚመለከቱት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -