- አዲስ አበባ ከሁሉም አካባቢዎች በተለየ መልኩ ሰላሟ ተጠብቆ መቆየቱ ያንገበገባቸው ኃይሎች በመንግሥትና በሕዝብ ትምህርት ቤቶች ከሰሞኑ ረብሻ ለመቀስቀስ ሙከራ አድርገዋል።
- እንደምታውቁት እነዚህ ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችን በመቀስቀስ መንግሥት ለመጣል ያደረጉት ሙከራ አልሳካ ሲላቸው አሁን ደግሞ ትኩረታቸውን በመዲናችን በማድረግ አዲስ አበባን የረብሻ ማዕከል ለማድረግ እያሴሩ ነው።
- ክቡር ሚኒስትር… በዚህ ላይ የምጨምረው አለኝ?
- ጥሩ… ይቀጥሉ አባታችን?
- ክቡር ሚኒስትር ቀደም ብለው የገለጹት እንዳለ ሆኖ እነዚህ ኃይሎች ሌላም ድብቅ ዓላማም አላቸው።
- ልክ ነው… ይቀጥሉ፡፡
- መንግሥት በውስጡ የተሰገሰጉ ሌቦችን ለመመንጠር ሰሞኑን የጀመረውን እንቅስቃሴ ማጨናገፍ ሌላው የእነዚህ ኃይሎች ድብቅ ዓላማ ይመስለኛል።
- ይህ ብቻ አይደለም ክቡር ሚኒስትር?
- እባካችሁ አንድ ጊዜ… እየተደማመጥን እንጂ? እሺ ይህ ብቻ አይደለም ያሉት… እዚያ… አዎ… እርሶ… ይቀጥሉ።
- ክቡር ሚኒስትር ዜጎች ሀብት እንዳያፈሩ ማድረግም ሌላው ዓላማቸው ነው።
- እንዴት?
- አሁን እኔ ባለችኝ መሬት ላይ ሱቆች ለማከራየት ብዬ ግንባታ ጀምሬ ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው…
- ምን ገጠመዎት?
- እነዚህ ኃይሎች የሲሚንቶ ገበያውን ተቆጣጠሩት፣ ምርቱም ከገበያ ጠፉ።
- ክቡር ሚኒስትር ይህ ነገር አልገባኝም?
- ይቀጥሉ እስኪ ምኑ ነው ያልገባዎት?
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎም ታዳሚውም እነዚህ ኃይሎች… እነዚህ ኃይሎች ትላላችሁ…
- አዎ።
- እነዚህ ኃይሎች እነማን ናቸው? መንግሥትን ለመጣል ትምህርት ቤት ምን ያደርጋሉ?
- እንዴት ያለ ጥያቄ ነው? ከተማሪ ቤት ሊጀምሩ ነዋ?
- እስኪ ቆይ… ክቡር ሚኒስትሩ እራሳቸው ቢመልሱ አይሻልም?
- ክቡር ሚኒስትር የአካሄድ ጥያቄ አለኝ?
- እሺ የአካሄድ ጥያቄ ያነሳኸው… ቀጥል?
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። ውይይታችን በዚህ መንግድ ከቀጠለ መግባባት የምንችል አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር።
- ሥጋትህ ትክክል ነው። ታዲያ እንዴት ብናደርግ የተሻለ ነው ትላለህ?
- ጥሩ። ክቡር ሚኒስትር በእኔ እምነት ከችግሩ ጀርባ እነማን እንዳሉ መወያየት ለእኛ ጠቃሚ አይደለም።
- ለምን?
- ክቡር ሚኒስትር ይህንን የመለየትና ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት የመንግሥት ነው። የእኛ ውይይት የችግሩ መፍትሔ ላይ ቢያተኩር የሚሻል ይመስለኛል።
- ትክክል ነው፡፡ አይ የተማረ ሰው… ትክክል ነው።
- አንዴ ፀጥታ እባካችሁ ስለዚህ የጀመርከውን ቀጥል…
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። በእኔ እምነት ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው የሚደገፍ እንጂ የግጭት መንስዔ መሆን የለበትም ግን…
- እባካችሁ ፀጥታ ቀጥል…
- ቀደም ብዬ እንዳልኩት ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው ተገቢ ነው። ነገር ግን በአፍ መፍቻ ቋንቋ ከመማር መብት ጋር መያያዝ የሌለባቸው ፖለቲካዊ ጉዳዮች አብረው እንዲሄዱ መደረጉ ለረብሻው መቀስቀስ መንስዔ የሆነ ይመስለኛል።
- እስኪ አብራራው?
- ክቡር ሚኒስትር ለምሳሌ መዝሙር ፖለቲካዊ ጉዳይ እንጂ ከቋንቋ መብት ጋር የሚያገናኝ ነገር አይደለም። ፖለቲካዊ በመሆኑ ደግሞ ከሌሎች ፍላጎት ጋር ይጋጫል።
- ስለዚህ?
- ስለዚህ መዝሙሩን ለጊዜው ማስቀረት አንድ መፍትሔ የሚሆን ይመስለኛል…
- አካሄድ ክቡር ሚኒስትር… ማሳሰቢያ አለን፡፡
- እሺ… ማሳሰቢያ ያልከው፣ ማቅረብ ትችላለህ።
- ክቡር ሚኒስትር እየተወያየን ያለነው በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ በመሆኑ አንድ አንድ ነገሮችን እያስተዋልን ለማለት ነው።
- ምንድነው?
- ክቡር ሚኒስትር ለምሳሌ ቀደም ሲል ከተሰጠው አስተያየት እነዚህ ኃይሎች እዚህ አይኖሩም ማለት አይቻልም።
- የት?
- በመካከላችን!