Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚወጡ ምርቶች በአፍሪካ አኅጉር የተሻለ ገበያ እያገኙ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ ገበያ እንድታስገባ የተሰጣት የንግድ ተጠቃሚነት ዕድል ከተሰረዘ ወዲህ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚወጡ ምርቶች በአፍሪካ አኅጉር የተሻለ የገበያ ዕድል እያገኙ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የአሜሪካው አንድ የገበያ አማራጭ እንጂ ብቸኛ አለመሆኑን ከአፍሪካ ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒት አክት (አጎዋ) ዕገዳ በኋላ በመረዳት፣ በተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ድርጅቶች፣ ሌሎች የገበያ አማራጮች ፈልገው ምርቶቻቸውን መላክ መጀመራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ዕገዳው ተፅዕኖ የለውም ባይባልም ለመቆጣጠር ግን እንደተቻለ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት አቶ አክሊሉ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡

በአጎዋ ምክንያት በታሰበው ልክ ኢንዱስትሪዎች እንዳልተዘጉ፣ የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች በቁጥር ጥቂት መሆናቸውን፣ ግን ምርት የቀነሱ እንዳሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸው፣ ብዙ የሥራ አጥና የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ላላት አገር ይህም ቢሆን ተፅዕኖው ቀላል ባይሆንም በሚባለው ልክ የተጋነነ አለመሆኑን፣ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንቅስቃሴን ለመመልከት በተዘጋጀ ሁነት ላይ ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በሐዋሳ ኢንዱሰትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶች ከአጎዋ ዕገዳ በኋላ የአውሮፓና የአፍሪካ ገበያ ላይ ተወዳድረው በመግባት፣ ምርቶቻቸውን ማቅረብ መጀመራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ኬንያ፣ ግብፅ፣ ናይጄሪያ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ ላይ ምርቶቻቸውን በብዛት መላክ መጀመራቸው ታውቋል፡፡

ከአውሮፓ አገሮች ፈረንሳይ፣ ጀርመን እንዲሁም የእንግሊዝ ገበያዎች ላይ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚያመርቱ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን በብዛት መሸጥ መጀመራቸውን የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አሸናፊ አስረድተዋል፡፡

ድርጅቶቹ ወደተጠቀሱት አገሮች ገበያ ለመግባት ካስቻላቸው ጉዳይ ውስጥ ተወዳዳሪ ምርት ማቅረባቸው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በኢንዶኒዥያና ስሪንላካ ከሚቀርቡ ምርቶች ጋር ተወዳዳሪ ብሎም የተሻለ ምርት ከፓርኩ እየቀረበ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት መንግሥት ባደረገው የሰላም ድርድር የመጣው ሰላም የራሱ የሆነ ትርፍ ያመጣል ተብሎ እንደሚታሰብ ያስረዱት አቶ አክሊሉ፣ የአጎዋ ዕገዳን የሚቀጥልበት ምክንያት ከዚህ በኋላ እንደማይኖርና ጉዳዩ መልክ እየያዘ እንደሚሄድ ተናግረዋል፡፡ 

ለአፍሪካ-አሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ በአገረ አሜሪካ የቆዩት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተሳተፉበት ስብሰባ በራሱ ይዞ የሚመጣው ዕድል እንደሚኖር የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስታውቀዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ዓመት ታኅሳስ ወር ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት ዕድል እንድትሰረዝ የቀረበውን ስምምነት የፈረሙት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ከነበረው ጦርነት ጋር በተያያዘ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ ውሳኔ ከተላለፈባት በኋላ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ አምራች ኩባንያዎች፣ የኢትዮጵያን ገበያ ለቀው እንደሚወጡ ከማሳወቃቸው ውጪ ለቆ የወጣ እንዲሁም ሠራተኞቻቸውን የቀነሱ እንዳሉም የሚታወስ ነው፡፡

ከዩኤስ አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ካትሪን ታይን (አምባሳደር) የሁለቱን አገሮች የንግድ ግንኙነት ማስፋፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጥሩ ውይይት ማድረጋቸውን ዓብይ (ዶ/ር) ማስታወቃቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጮች በተመለከተ ደግሞ ከአሜሪካ የኢንቨስትመንት ማኅበረሰብ አባላት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች