Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሞተር ኢንሹራንስ መክሰራቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2015 የመጀመርያ ሩብ ዓመት ለተሽከርካሪዎች የሰጡት የመድን ሽፋን ኪሳራ ውስጥ የከተታቸው ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት አጠቃላይ የትርፍ ምጣኔያቸው እንደቀነሰ ታወቀ፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የ2015 የሩብ ዓመት አፈጻጸም በጥቅል የዓረቦን አሰባሰብ ረገድ ገቢያቸው ቢጨምርም፣ የሞተር ኢንሹራንስ ያስከተለው ኪሣራ እስካሁን በኢንዱስትሪው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የትርፍ ምጣኔያቸውን እንዲወርድ አድርጎታል፡፡

ከኢትዮጵያ የመድን ሰጪዎች ማኅበር የተገኘው መረጃም እንደሚያመለክተው፣ በሒሳብ ዓመቱ በሩብ ዓመት ኩባንያዎች 5.85 ቢሊዮን ብር ዓረቦን በመሰብሰብ፣ ከቀዳሚው ዓመት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ገቢ ቢገኝም፣ በሞተር ኢንሹራንስ ያስከተለው ኪሣራ የኢንዱስትሪውን ትርፍ አውርዶታል፡፡ በሩብ ዓመቱ ከሞተር ኢንሹራንስ የተሰበሰበው ዓረቦንም ቢሆን ከቀዳሚው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ ያለው ገቢ የተገኘበት ነው፡፡ ነገር ግን ለተሰጠው ሽፋን የተከፈለው የጉዳት ካሳ መጠን በእጅጉ ጭማሪ ማሳየቱ፣ ኩባንያዎቹ ኪሣራ እንዲያጽፉ ምክንያት መሆኑንም ከማኅበሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በሞተር ኢንሹራንስ የገጠመውን ኪሣራ የተመለከተው የማኅበሩ አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየውም፣ በሩብ ዓመቱ ኢንዱስትሪው በሞተር የመድን ሽፋን 70.12 ሚሊዮን ብር ኪሣራ ገጥሞታል፡፡ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ግን 176 ሚሊዮን ብር ትርፍ ተመዝግቦበት ነበር፡፡

ኩባንያዎቹ በሒሳብ ዓመቱ ከሞተር ኢንሹራንስ ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን 2.76 ቢሊዮን ብር መሆኑን የሚጠቁመው መረጃ፣ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከዘርፉ የተሰበሰበው ዓረቦን 2.11 ቢሊዮን ብር ገቢ የተገኘበት መሆኑን ያሳያል፡፡

ይህም በሩብ ዓመት ከሞተር ኢንሹራንስ የተገኘው የዓረቦን ገቢ ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ መጨመሩን የትርፍ ምጣኔያቸውን ያሳድጋል ተብሎ ቢታሰብም፣ የጉዳት ካሳው በእጅጉ መጨመር ጥቅል ትርፋቸውን ዝቅ ሊያደርገው መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህ ክስተት ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ያሬድ ሞላ እንደገለጹት፣ ከሞተር ኢንሹራንስ የተገኘው የረቦን ገቢ ቢያድግም በኪሣራ እንዲመዘገቡ ያደረገው አሁን ያለው የመለዋወጫ ዋጋ ጭማሪ የጋራጅ ዋጋ በእጅጉ ጭማሪ ማሳየቱ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም 40 ሺሕ ዋጋ ያለው ፍሬንች 150 ሺሕ ብር መግባቱ የጋራጅ ዋጋ አራትና አምስት እጥፍ መጨመሩ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሩብ ዓመቱ ከሞተር ኢንሹራንስ ኪሣራ እንዲያጽፉ አስገድዷቸዋል፡፡

እንዲህ ያለው ኪሣራ በኢንዲስትሪው ተመዝግቦ እንደሚያውቅ የገለጹት አቶ ያሬድ በሌላው የመድን ሽፋን የተገኘው ትርፍ ማካካስ ባይቻል ኖሮ፣ ትልቅ ኪሣራ ያስከትል እንደነበር ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በሞተር ኢንሹራንስ የገጠመው ኪሣራም ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ በ2014 ሩብ ዓመት ካገኙት ያነሰ ትርፍ እንዲያስመዘግቡ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የተሽከርካሪዎች አደጋ መብዛትም ለተመዘገበው ኪሣራ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡

ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳውም በ2014 የሒሳብ ዓመት የአገሪቱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከታክስ በፊት ማስመዝገብ ችለው የነበሩት 347.5 ሚሊዮን ብር ዘንድሮ በሩብ ዓመቱ ማትረፍ የቻሉት ግን በ219 ሚሊዮን ብር ዝቅ ሊል ችሏል፡፡ ይህም በሩብ ዓመቱ ከ126.5 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፋቸው እንዲቀንስ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሩብ ዓመቱ የገጠማቸውን የትርፍ ምጣኔ መቀነስና የሞተር ኢንሹራንስ ያስከተለውን ኪሣራ በተመለተ ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ኪሣራ በኢንዱስትሪው መታየቱ ትልቅ ችግር ያለመሆኑን ያሳያል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አደጋዎችን መሸፈን የሚችል የዓረቦን ዋጋ ሊኖራቸው እንደሚገባ ያመለክታል ብለዋል፡፡

ዋጋ አስተካክለው የማይቀጥሉ ከሆነ ግን ለኢንዱስትሪው አደጋ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ከማኅበሩ የተገኘው መረጃ ግን ይህንን ችግር ለመቅረፍ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የዓረቦን ማስተካከያ እያደረጉ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 16.7 ቢሊዮን ብር መሰብሰባቸው መገለጹ አይዘነጋም፡፡ ይህም የዓረቦን አሰባሰቡ 18.7 በመቶ መጨመሩን አመልክቶም ነበር፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያዎች ከከፈሉት 4.7 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ውስጥ ወደ 70 በመቶ የሚሆነው ከተሽከርካሪ አደጋ ጋር በተያያዙ ላደረሱ ጉዳቶች የተከፈለ ነው፡፡

በ2014 የሒሳብ ዓመት ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሕይወት ነክ ላልሆነው የመድን ዘርፍ የከፈሉት የካሣ መጠን በ16 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 4.7 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ለሕይወት የመድን ዘርፍ ደግሞ 466.8 ሚሊዮን ብር ካሣ ተከፍሏል፡፡ ጥቅል ትርፋቸው ደግሞ 2.8 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች