Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ሊጀመር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ከገነባቸው 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግዙፉ የሆነው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ፣ በተያዘው ዓመት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በ300 ሔክታር ላይ ለመገንባት ከታቀደው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመጀመርያው ምዕራፍ የለማው 140 ሔክታር መሆኑን ለሪፖርተር የተናገሩት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ማቲዎስ አሸናፊ፣ ቀሪውን 160 ሔክታር መሬት ለማልማት ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡

‹‹እስካሁን ድረስ ያለማበት ምክንያት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ያላለቁ ጉዳዮች ስለነበሩ ነው፡፡ ይህም ማስፋፊያ የሚደረግበት ቦታ ከሦስተኛ ወገን ነፃ ማድረግን የሚመለከት ነው፤›› ያሉት አቶ ማቴዎስ፣ ፓርኩ ቦታውን በአጥር ለመከለል ጨረታ አውጥቶ እንደነበረና ነገር ግን መሬቱ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሲደረግ ግንባታው ቢከናወን ይሻላል የሚል ውሳኔ ላይ መደረሱን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ባለመካለሉ በታሰበው መሬት ላይ የሚገኙ የመንግሥትም ሆነ የግለሰብ ይዞታዎች ሳይለቀቁ መቆየታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ እነዚህን አካላት የፓርኩ አካል አድርጎ መሄድ ይሻላል ወይስ ሌላ አማራጭ አለ? የሚለውን የሚመለከት ከከተማ አስተዳደሩና ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተውጣጣ ኮሚቴ መዋቀሩን አቶ ማቴዎስ አስረድተዋል፡፡

ፓርኩ እንደከዚህ ቀደሙ በሁለተኛው  ምዕራፍ ግንባታ ላይ ለባለሀብቶች ሼዶችን እንደማይገነባ፣ ይልቁንም የለማውን መሬት አስተላልፎላቸው በሚቀመጥላቸው ስታንዳርድ መሠረት ሼዶችን እንደሚገነቡ ታውቋል፡፡ 

‹‹ባለሀብቶች ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው ለማልማት ጥያቄ ቢያቀርቡ በአሁኑ ወቅት ያለው ቦታ በቂ ስላልሆነ፣ ፈጥነን ቦታ ማዘጋጀት ይኖርብናል፤›› በማለት ለሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ጥያቄ መቅረቡን የተናገሩት አቶ ማቴዎስ፣ በከተማ አስተዳደሩ በኩል መሬቱን ነፃ የማድረግ ሥራ እንደተጠናቀቀ የአጥር ግንባታውን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ባለሀብቶችን ወደ ፓርኩ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡

በመጀመርያው ምዕራፍ በ140 ሔክታር መሬት ላይ በለማው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 52 ሼዶች ተገንብተው 23 ድርጅቶች እያመረቱ መሆናቸውን፣ ተጨማሪ አንድ ድርጅት በፓርኩ ውስጥ ለመግባት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በተያያዘም በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን በአብዛኛው ወደ አውሮፓ አገሮች በመላክ፣ በተያዘው ዓመት አምስት ወራት 32 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳስገቡ ታውቋል። ምንም እንኳ የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ከአጎዋ የቀረጥ ነፃ ገበያ ዕድል ተጠቃሚነት ያገደ ቢሆንም፣ ኩባንያዎቹ በአውሮፓ አገሮች አዳዲስ ገበያዎችን በማፈላለግ ምርቶቻቸውን በብዛት በመላክ ላይ እንደሆኑ አቶ ማቴዎስ ተናግረዋል። በተጨማሪም ኩባያዎቹ ወደ አፍሪካ አገሮች ምርቶች በመላክ ላይ ናቸው ብለዋል።

አንዳንድ ኩባንያዎች ቀረጡን ችለው ወደ አሜሪካ ገበያ ምርቶቻቸውን በመላክ ላይ እንደሆኑ፣ ከአጎዋ ክልከላ በፊት 23 የነበሩት ኩባንያዎች በአሁኑ ወቅት አንድ ተጨምሮ 24 መሆናቸውንና ያሉትም ኩባንያዎች ማስፋፊያ እየጠየቁ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት በማገዱ ምክንያት፣ ምርታቸውን ወደ አሜሪካ ሲልኩ የነበሩ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ አምራቾች በገበያ ዕጦት ያሰናበቱዋቸው ሠራተኞች ቁጥር ከአምስት ሺሕ በላይ ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዳስታወቁት፣ ከአጎዋ ዕገዳ በተገናኘ በፓርኩ የደረሰው ተፅዕኖ እንደሚባለው የተጋነነ አይደለም፡፡ በፓርኩ ከሚመረቱ ምርቶች ከ85 በመቶ በላይ ይቀርቡ የነበረው ለአሜሪካ ገበያ እንደነበር፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ኩባንያዎች ወደ አውሮፓና አፍሪካ ገበያዎች በመግባት ኤክስፖርት እያደረጉ መሆናቸውን አቶ ማቴዎስ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች