Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ሰላም አደፍራሾች ከአስከፊው ድርጊታቸው ይታቀቡ!

ለሐሳብ ነፃነት ክብር ቢሰጥ ኖሮ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ግጭት ውስጥ አትዘፈቅም ነበር፡፡ ልዩነትን በሐሳብ ሙግት የማስተናገድ ባህል ባለመኖሩ ግን ከሰላማዊ ክርክር ይልቅ ዱላ ይበረታል፡፡ ለሐሳብ ነፃነት የሚሰጠው ክብርና ፍላጎት ዝቅተኛ በመሆኑ፣ በየዘመኑ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚውረገረጉ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ቅርበታቸው ለፍጥጫ ነው፡፡ በሐሳብ ልዩነት ላይ በሰከነ መንገድ ከመነጋገር ይልቅ በሐሳብ የሚለዩትን ስም ማጥፋት፣ ማሳደድ፣ ማሰርና መግደል ነው የለመዱት፡፡ ይህ ችግር የመንግሥት ሥልጣን በሚቆናጠጡት ላይ ቢበረታም፣ ሥልጣን ለመያዝ በሚራኮቱ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ዘንድም በስፋት ይንፀባረቃል፡፡ በዚህም የተነሳ የፖለቲካ ምኅዳሩ የሰላም አደፍራሾች መናኸሪያ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ጥቅም እስከተገኘበት ድረስ ለታሪካዊ ጠላቶች በመገዛት አገርን ማተራመስ የተለመደ ተግባር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም እከሌ ከእከሌ ሳይባል በዚህ ሳቢያ የመከራ ገፈት ቀማሽ ሆኗል፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝም ሆነ ጥቅም ለማጋበስ ሲባል ሰላማዊ የሐሳብ ክርክር ሳይሆን ማስፈራራትና ዕርምጃ መውሰድ ልማድ በመደረጉ፣ ኢትዮጵያ የሰላም አደፍራሾች መፈንጫ ሆናለች፡፡ ሰላም አደፍራሾች ጭር ሲል ስለማይወዱ ምክንያት እየፈለጉ አገርና ሕዝብ እያመሱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ በመመሥረት ሰላም አደፍራሾች ለምን ከየአቅጣጫው መንቀሳቀስ ጀመሩ ሲባል፣ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳትገነባ በታሪካዊ ጠላቶችም ሆነ በሌሎች ሴራ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ሊኖራት የሚገባትን የክብር ሥፍራ መያዝ እንደሚገባት በአገር ወዳዶች ጥረት ሲደረግ፣ በአካባቢው ጥቅማቸው ሊነካ ከሚችል ኃያላን ጀምሮ እስከ ግብፅና መሰሎቿ ድረስ በርካታ ሴራዎችን ያዳውራሉ፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉና ከመዋቅሩ ውጪ ሆነው የአገርን ጥቅምና ብሔራዊ ደኅንነት የሚያናጉ፣ የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈለጉ በኢትዮጵያውያን መካከል ጥላቻ የሚዘሩ የሴራው ተባባሪ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከሰሜኑ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አማካይነት ጊዜያዊ ዕፎይታ ያገኘች በመሰለችበት ወቅት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ እስከ ኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች ድረስ የሚስተዋለው ሰላም አደፍራሽነት አገርን ከማናጋት ተለይቶ የሚታይ ሴራ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የትብብር ማዕከል እንዳትሆን፣ የተፈጥሮ ፀጋዎቿን አልምታ እንዳታድግ፣ በዓባይ ውኃ ላይ ያላትን ተጠቃሚነት ለማደናቀፍና ለመሳሰሉት እኩይ ሴራ ማሳኪያ አንዱ ዘዴ ሰላም መንሳት ነው፡፡

ኢትዮጵያን ከአንዱ ችግር ወደ ሌላው በማንከባለል ሰላም አልባ ለማድረግ በሚደረገው የታሪካዊ ጠላቶች ሴራ ተባባሪ የሚሆኑት ደግሞ፣ ከተፀነሱበት ጊዜ ጀምሮ በአገር ጥላቻና ቂም ተኮትኩተው ያደጉ የጥፋት ትርክት ሰለባዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አገር ሰላም ስትሆን በመንግሥትና በፓርቲ መዋቅር ውስጥ ሰርገው በመግባት መጠነ ሰፊ ዝርፊያ መፈጸምና ማስፈጸም፣ መሬት ማስወረር፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት በመፍጠር ተገልጋዮችን ማስመረር፣ ፍትሕን እንደ ሸቀጥ መቸብቸብ፣ በሕዝብ መካከል ሊኖር የሚገባውን መተማመን ማጥፋት፣ ንፁኃንን ማሰቃየት፣ የመንግሥትና የፓርቲን ሥራ በማደባላለቅ ግራ ማጋባት፣ እጃቸው የገባ የአገር ሚስጥር ማባከንና በመሳሰሉት የክፋት ድርጊቶች ለሰላም መደፍረስ የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ፡፡ ተጠያቂነት እንዳይኖርባቸውም ኔትወርካቸውን አጠናክረው ስለሚንቀሳቀሱ፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ተከፋይ ቀስቃሾቸቸውን በማሰማራት ጭምር የተፅዕኖ አድማሳቸውን ያሰፋሉ፡፡ በማኅበረሰቦች ውስጥም የብሔርና የእምነት ተራ ልዩነቶችን በመለጠጥ ከፋፋይ አጀንዳዎችን ይነዛሉ፡፡ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ሆነው አመፃ ከሚያራምዱ ኃይሎች ጋር በመተባበር የጭካኔ ድርጊቶችን ያስፈጽማሉ፡፡

ቁጥራቸው ከ120 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆኑ ከሚታሰቡ ኢትዮጵያውያን መካከል አብዛኞቹ ምግብ ለማግኘት ከባድ ፈተና በሚያዩባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ አንዱን ምስኪን ኢትዮጵያዊ የሌላው ምስኪን ጠላት አድርጎ በመፈረጅ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጭፍጨፋዎችን ያበረታታሉ፡፡ ከጭፍጨፋ የተረፉ በርካታ ሚሊዮኖች ከቀዬአቸው ተፈናቅለውና ሜዳ ላይ ወድቀው ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ጠባቂነት ተዳርገው፣ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጋራ መሠረተ ልማቶችና የግለሰብ ንብረቶች ወድመው፣ ወገኖቻቸውን በጦርነቱና በተለያዩ ሥፍራዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ያጡ በጣም በርካቶች ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተዳርገውና ለመግለጽ የሚያስቸግሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ብዙዎችን ተስፋ ቢስ አድርገው አገር የሰላም ያለህ ብትልም ለማዳመጥ አይፈልጉም፡፡ ነገር ግን ድብቅ ፍላጎታቸውን በተገኘው አጋጣሚ ለማሳካት ስለሚፈልጉ ደግሞ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› በሚባለው የክፉዎች መርህ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዳይፈጠር ምክንያት እየፈለጉ ግጭት ለመቀስቀስ ማናቸውንም ድርጊቶች ከመፈጸም አይመለሱም፡፡ በዚህም ኢትዮጵያን ለማዳከም ከሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እየተባበሩ ሰላም ያደፈርሳሉ፡፡

እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ትናንት ጠላት ሆነው ትርምስ ሲፈጥሩ የነበሩ ዛሬ ወዳጅ ሆነው ሲቀርቡ መታየታቸው ነው፡፡ እነሱ ለረዥም ጊዜ የተካኑበት ‹‹ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ጠላትና ወዳጅ የሚባል የለም›› የሚሉት መርህ፣ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች መቃብር ላይ ከትናንት ባላንጣዎቻቸው ጋራ ‹‹ለጤናችን›› እያሉ መለኪያ እንዲያጋጩ አይከለክላቸውም፡፡ የትናንት ባላጋራ እስከገበረና ፍላጎታቸውን ለማሟላት ቃል እስከገባ ድረስ፣ የትናንት ወዳጃቸውን ገለል ለማድረግ ዓይናቸውን አያሹም፡፡ እነሱ ዘንድ ዋናው ቁምነገር ‹‹እኛ እስከመሰለን ድረስ በጨረታው አንገደድም›› የሚለው ነው፡፡ አሜሪካም ሆነች አውሮፓ በዚህ የተካኑ በመሆናቸው፣ ወዳጅነታቸውም ሆነ ጠላትነታቸው በብልኃት ነው መያዝ ያለበት፡፡ በማንም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለ መግባት ዓለም አቀፋዊው መርህ እነሱ በሚፈልጉት ጊዜ ሊጣስ እንደሚችል ዋናው ማሳያ፣ ‹‹የሰብዓዊ መብት አከባበር›› ጥያቄ ማንሳት መሆኑን ማንም አይስተውም፡፡ የሚደግፉት መንግሥት ዜጎቹን መፈጠራቸውን እስኪጠሉ ድረስ ቀጥቅጦ ሲገዛ ገላማጭ የለውም፡፡ የሚጠሉት ሲሆን ደግሞ ጭው ካለ በረሃ ውስጥ ንፁህ አውጥቶ ዜጎቹን ቢያጠጣ እንኳን እንደ ሰይጣን ይፈረጃል፡፡ በውስጥ የተደራጁ ጠላቶቹ ዕገዛ ተደርጎላቸው የመጨረሻው ስንብትም ይደረግለታል፡፡

የሙአመር ጋዳፊን የምድር ገነት ሊቢያና የአሁኗን የምድር ሲኦል ሊቢያ፣ እንዲሁም የሳዳም ሁሴንን የተረጋጋችና የታፈረች ኢራቅንና የአሁኗን ምስቅልቅል ኢራቅ፣ እንዲሁም ሌሎች በአካባቢው የወደሙ አገሮችን የሚያስታውስ ማንም ሰው የሰላም መደፍረስ በምን ምክንያት እንደሚከሰት አይስተውም፡፡ እዚህ ላይ እየተነጋገርን ያለነው አምባገነኖችን በመሸከም አገርን ወደ ቀጣዩ ትውልድ ስለማስተላለፍ አይደለም፡፡ ነገር ግን አገርን በሥርዓት እየገነቡ ልማትን በማስፋፋት አንገትን ቀና ለማድረግ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከሌሎች ወድቀት መማር እንዳለባቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁሉንም ዜጎች ያለ አድልኦ በእኩልነት የሚያስተናግድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ይቻላል፡፡ ኅብረ ብሔራዊቷ ኢትዮጵያ ከብሔርና መሰል ጭቅጭቆች ተላቃ ፍትሕ፣ እኩልነትና ነፃነት የሚያስገኝ ፌዴራላዊ ሥርዓት መገንባት ትችላለች፡፡ ለዚህ ግንባታ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉ በተለያዩ መስኮች አንቱ የተባሉ የተማሩና የተመራመሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥም በውጭም አሉ፡፡ ሰላማዊትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በሁሉም ዜጎቿ ትብብር እንድትገነባ የሚያግዙ ዕውቀት ያላቸው፣ ልምድ ያካበቱና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው በርካታ ልጆቿ እያሉ፣ ለአገር ክብርና ፍቅር የሌላቸው የጠላት ተላላኪዎች በተደጋጋሚ ሰላም እንዲያደፈርሱ መፈቀድ የለበትም፡፡ ሰላም አደፍራሾች ከአስከፊው ድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...