Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ሙስና ከብሔር ፖለቲካ ጋር ተጋምዶ ውስብስብ ችግር ፈጥሯል›› አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል፣ የሕግ ባለሙያ

በ1983 ዓ.ም. በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ሥር በሲዳማ አስተዳደርና በደቡብ ሸዋ አስተዳደር በዓቃቤ ሕግነት ሠርተዋል፡፡ ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ በልዩ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት በልዩ ዓቃቤ ሕግነት አገልግለዋል፡፡ በ1993 ዓ.ም. ደግሞ እንደ አዲስ በተቋቋመው የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለስድስት ወራት የፀረ ሙስና ዓቃቤያነ ሕግ አስተባባሪ ነበሩ፡፡ ከ1994 ዓ.ም. አጋማሽ እስከ 1998 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ መምርያና ጉምሩክ ዓቃቤያነ ሕግ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የግልግል ተቋም ዳይሬክተር ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ አንጋፋው የሕግ ባለሙያ አቶ ዮሐንስ ወልደገብርኤል በኢትዮጵያ ሙስናን ለመዋጋት በተቋቋሙ ተቋማት እንደ መሥራታቸው የፀረ ሙስና ትግል የሚጠይቀውን ጥረት ከአካዴሚ፣ ከሥራ ልምድና ካለፉበት ሕይወት በመነሳት የግል ሐሳባቸውን በሰፊው አጋርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አገር አቀፍ ትኩረት እያገኘ ስለመጣው የፀረ ሙስና ትግልና ከዚህ ቀደም አገሪቱ ስለነበሯት ልምዶች ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ያለውን የሙስና ተጋላጭነት እንዴት ያዩታል፡፡ ከቀደሙ ጊዜያት ጋር በማነፃፀር ሙስና አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው ይላሉ?

አቶ ዮሐንስ፡- በአፄ ኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ ዘመን የሙስና ተጋላጭነት የከፋ ደረጃ የደረሰ ነበር ማለት በግሌ ይከብደኛል፡፡ ይህን ስል ግን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎች አልተፈጸሙም ለማለት አይደለም፡፡ ከሙስና ጋር በተያያዘ ወይም ኢኮኖሚያዊ ወንጀሎች የምንላቸው ዘረፋ፣ ጉቦ፣ በሥልጣን ያላግባብ መገልገልና የመሳሰሉት አስቸጋሪ ደረጃ የደረሱ አልነበሩም፡፡ በሁለቱ መንግሥታት ወቅት የነበሩ ተቋማት፣ አሠራሮች፣ ኅጎችና መዋቅሮች ሙስናና ሌብነት እንዳይስፋፋ የራሳቸው አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ሙስናን በሚመለከት ትልቅ ፍርኃትና ግንዛቤን የፈጠሩ መዋቅሮች ነበሩ፡፡ ሙስናን መዋጋት አንዱ መሠረታዊ የመንግሥት ሥራ መሆኑን እነዚህ ተቋማት ግንዛቤ አዳብረው ቆይተዋል፡፡ ከድኅረ ደርግ በኋላ በደርግ ዘመን የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የሙስና ወንጀሎችን ለመመርመር የተቋቋመው የልዩ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት፣ በደርግ ባለሥልጣናት ላይ አንዳችም ተጨባጭ የሆነ የሙስና ወንጀል ክስ አልመሠረተም፡፡

ከመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ጀምሮ እስከ ታች ባለው ተዋረድ የደርግ ባለሥልጣናት ላይ የቀረበ የሙስና ወንጀል ክስ የለም፡፡ የተሰጠ ፍርድም የለም፡፡ በደርግ ጊዜ ሙስና ጨርሶ ሳይኖር ቀርቶ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህን ለማጣራት በተቋቋመ ተቋም የቀረበ የወንጀል ክስ አልነበረም፡፡ ይህን የሚደግፉ ሌሎች ጥናቶችም አሉ፡፡ በደርግ ጊዜ ሙስና ፈታኝ ችግር አለመሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ለማቋቋም የተደረገ ጥናት የደርግ ዘመን ሙስና ያልተንሰራፋበት መሆኑን አቅርቦ ነበር፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ጊዜ ምንም እንኳን የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችና ሌሎች ጥፋቶች ሊፈጸሙ ቢችሉም ነገር ግን ሙስናን በተመለከተ የጨዋነት ምሳሌ የነበሩ ተቋማትና ባለሥልጣናት እንደነበሩ መመስከር ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞ ባለሥልጣናትና የሁለቱን መንግሥታት ታሪክ ያጠኑ ሰዎች ጭምር ሙስናና ምዝበራው እንደነበረ ብዙ ጽፈዋል እኮ?

አቶ ዮሐንስ፡– ካነበብኩትና ካለኝ መረጃ ተነስቼ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የሙስና ወንጀል የተስፋፋበት ነበር ብሎ ለመናገር በጣም ከባድ ይሆንብኛል፡፡ የመንግሥት የንብረት፣ የበጀትም ሆነ የሀብት አያያዝ ሥርዓት ታማኝነት ያልጎደለው መሆኑን ማንም የሚክደው አይደለም፡፡ በደርግ ዘመንም ቢሆን መንግሥት የንጉሡ ሥርዓት በፈጠረው የሕግ፣ የአስተዳደር፣ የፍትሕ ሕጎችና ማዕቀፎች ነበር ሲመራ የነበረው፡፡ እነዚያ ሕጎችና አሠራሮች ለሌብነት ብዙ የሚያፈናፍኑ አይደሉም፡፡ ሙሉ መረጃ፣ ማስረጃም ሆነ ሌላ እንደ ልብ ማግኘትና ማውጣት የመቻል ሙሉ አቅምና ችሎታ ኖሮት የተመሠረተው የደርግ መርማሪ ኮሚሲዮንም፣ በኃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የረባ የሙስና ክስ ማቅረብ አለመቻሉ የንጉሡን ዘመን በሙስና ንቅዘት ለመበየን አያስችልም፡፡

በደርግ ዘመን በዘውዳዊው ሥርዓት ብዙ ሙስና ስለመፈጸሙ ይነገር ነበር፡፡ የቀደመውን ሥርዓት ጉድለት እንደሚያስተካክልም ደርግ ይናገር ነበር፡፡ ሆኖም በወሰዳቸው ሥር ነቀል ለውጦች የተነሳ ከሕግ ውጪ የሆኑ ጥፋቶችን መፈጸሙ ሊካድ አይቻልም፡፡ የንጉሡን ባለሥልጣናት ያለ ምንም የሕግ ይሁንታ ከመግደሉ ባለፈ፣ የብዙ ግለሰቦችን ንብረቶች በኮሙዩኒስታዊ ዕርምጃዎች በመውረስ የመንግሥት እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ብዙ የአክሲዮን ማኅበራት የንጉሠ ነገሥቱ ናቸው በማለት እንዲወረሱ አድርጓል፡፡ ተቋማቱ በሕግና በሥርዓት ሥራቸውን የሚሠሩ የንግድ ተቋማት ነበሩ፡፡ በውጭ ኦዲተር ጭምር በየዓመቱ እየተመረመሩ ወጪና ገቢያቸው የሚታወቅ ነበሩ፡፡ ተቋማቱ በሕገወጥና በኢፍትሐዊ መንገድ ስለመቋቋማቸው አልተረጋገጠም፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ እስካሁንም ነጋዴ እንደ ሰው አይቆጠርም፡፡ የንግድ ሥራ ክቡርነት አይታይም፡፡ ንጉሡ እንደ ተራ ነጋዴ ወርደው ንግድ ሥራ ውስጥ ገቡ ለማለት፣ አንዳንድ የአክሲዮን መረጃዎችን እያወጡ ለውንጀላ ተጠቅመውበታል፡፡ ይሁን እንጂ ንጉሡና ባለሥልጣኖቻቸው የዘረፋ ተግባር ውስጥ መግባታቸውን የሚያረጋግጥ አልነበረም፡፡ ተገኘ ተብሎ በብጥስጣሽ መረጃ ሲቀርብ የነበረውን የፕሮናፓጋንዳ ውንጀላ የሙስና ውጤት መሆኑን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ በንጉሡ መንግሥት ላይ የቀረቡ መሰል ውንጀላዎች በውሸት ላይ የተመሠረቱ ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ዘውዳዊው ሥርዓት የፈጠረው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ለውድቀቱ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሥርዓቱ በብልሹ አሠራርና ሙስና የተዘፈቀ መሆኑ ለውድቀት ዳርጎታል ቢባል አሳማኝ አይሆንም?

አቶ ዮሐንስ፡- ከየካቲት 1966 እስከ መስከረም 1967 ዓ.ም. የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ እጅግ ነፃ የሆነበት ወቅት ነበረ፡፡ በ1967 ዓ.ም. ለጥቂት ወራት ቢዘልቅም ነገር ግን ይህ ወቅት ቆይታው አጭር የሚባል ነበር፡፡ በእነዚህ ወራት ይጻፉ የነበሩ የፕሬስ ውጤቶች እጅግ ነፃ የነበሩ ሲሆን፣ ብዙዎቹ ደግሞ ባልተጨበጡ መረጃዎች የተደገፉ ዘገባዎች ነበሩ፡፡ ወቅቱ በርካታ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ዜጎች ያነሱበት ሲሆን፣ የንጉሡ መንግሥት መጨረሻም ነበር፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ጥያቄዎች ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መነሻ እንደነበራቸው አይካድም፡፡ ይሁን እንጂ የንጉሡ መንግሥት በሙስና የተጨማለቀ፣ የመንግሥቱ ተቋማት ሙስና ማስፈጸሚያ እንደሆኑ፣ እንዲሁም የመንግሥቱ ባለሥልጣናትም ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ ናቸው የሚል ከፍተኛ ውንጀላ ይቀርብ ነበር፡፡ የፕሬስ ነፃነቱ የፈጠረውን ዕድል በመጠቀም በጣም በርካታ አሉባልታዎችና ውሸቶች ጭምር በመንግሥት ጋዜጦች ሳይቀር ሲወጡ እንደነበር አንብቤያለሁ፡፡

እንግሊዞች ጣሊያንን ለመውጋት ብለው መጥተው ከነፃነት በኋላ ዘርፈውት የሄዱት ንብረት ሁሉ፣ ልክ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት የዘረፉት ተደርጎ ሲጻፍ በ1966 ዓ.ም. ዓይቼያለሁ፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፣ የጣሊያን ወራሪዎች ለራሳቸው ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብለው አፄ ኃይለ ሥላሴ የአገሩን ሀብት፣ ወርቅና ገንዘብ ዘርፈዋል፣ የቪዲዮ ማስረጃው አለ ብለው የፈጠሩትን የውሸት ውንጀላ ሁሉ በ1966 ዓ.ም. የነበረው ትውልድ ተቀብሎ ሲጽፈው ነበር፡፡ ንጉሡ የሀገር ሀብት ዘርፈዋል፣ በስዊዘርላንድ ባንኮች ደብቀዋል እየተባለ በየጋዜጣው፣ በየመጽሔቱና በሚበተኑ የተለያዩ ወረቀቶች መጻፍ የተለመደ ሆኖ ነበር፡፡

የወቅቱ ፖለቲከኞች፣ ተማሪዎች፣ ማኅበራዊ አንቂዎችና የዋና ኦዲተር ጽሕፈት ቤት ኃላፊውም ጭምር በተለያየ ስም ይህን መሰል ጽሑፎች ሲያወጡ ዓይተናል፡፡ እነዚህ ጽሑፎች የፈጠሩት ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም፡፡ ብዙ የስም ማጥፋት ዘመቻ፣ ጥቂት እውነትና ብዙ ውሸት የነበረበት፣ እንዲሁም አብዮታዊ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ወቅት ነበር፡፡ በጊዜው በሚሠራው ፕሮፓጋንዳ ግፊት ይመስላል መርማሪ ኮሚሲዮን የሚባል አንድ ተቋም መጋቢት/ሚያዝያ 1966 ዓ.ም. አካባቢ በፓርላማው እንዲቋቋም ረቂቅ ሕግ ቀረበ፡፡ ተቋሙ ተጠሪነቱ ለፓርላማው መሆኑ ተደነገገ፡፡ በዚህ ረቂቅ ሕግ መሠረትም ኮሚሲዮኑ የመመርመርና የመረመረውን ለዓቃቤ ሕግ እንዲያስተላልፍ ሥልጣን ተሰጠው፡፡  

መርማሪ ኮሚሲዮኑ የሁለት ዓመት ዕድሜ ነበረው፡፡ ትልልቅ ለሚዲያ ፍጆታ የሚሆኑ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ የተለያዩ ኃላፊዎችን እያስቀረበ ይመረምርም ነበር፡፡ ነገር ግን የመጨረሻ ትልቁ ግኝቱ ከወሎ ረሃብ ጋር በተገናኘ ትንሽ ሰዎችን የሚያስወነጅል ሪፖርት ነበር ያቀረበው፡፡ ሕዝብን ማስራብ የሚል በወንጀለኛ መቅጫው ሕግ ዝቅተኛው ሦስት፣ ከፍተኛው አሥር ዓመት የሚያስፈርድ አንድ የምርመራ ውጤት አጠናቆ ወደ ልዩ የጦር ፍርድ ቤት መላኩ ነው የሚታወቀው፡፡ ልዩ የጦር ፍርድ ቤትም ይህንኑ ክስ ለመመሥረት በዝግጅት ላይ ነበር፡፡ ሆኖም የደርግ ባለሥልጣናት ይህን የምርመራ መዝገብ ከልዩ የጦር ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ ወስደው፣ በእስር ላይ የነበሩ 60 የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለሥልጣናትን አስረሸኑ፡፡ ከሕግና ከሥርዓት ውጪ በማስገደል የደርግ ባለሥልጣናት ሒደቱን ደመደሙት፡፡

መርማሪ ኮሚሲዮን ከዚህ በኋላ የተወሰኑ የምርመራ ሒደቶችን ቢያደርግም፣ ያን ያህል ዕርባና ያለው ሥራ ሳይሠራ በ1968 ዓ.ም. የተቋቋመበትን ሕግ የሚያፈርስ ሌላ ረቂቅ ሕግ ቀርቦ ሰዎቹም እንዲበተኑ ተደርጓል፡፡ የመርማሪ ኮሚሲዮኑ ዋና ሥራ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለሥልጣናት ፈጽመዋል የተባለውን በሥልጣን ያላግባብ መገልገል፣ ጉቦና የፍትሕ መጓደልን መመርመር ነበር፡፡ የተጨናገፈ ውክልና ተሰጥቶት ሥራው የተጨናገፈ የምርመራ ኮሚሽን ነበር ማለት እንችላለን፡፡ በኮሚሽኑ ጥሩ ልምድ የነበራቸው ትልልቅ ምሁራን ተካተው ነበር፡፡ በጊዜው ከሚነዛው ፕሮፓጋንዳ ባለፈ የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ባለሥልጣናት የፈጸሙትን የተጨበጠ ወንጀል ማቅረብ ግን አልቻለም፡፡ ለሕዝብ ትምህርትና ምሳሌ ሊሆን የሚችል በማስረጃ የተረጋገጠ ወንጀል አልቀረበም፡፡  

ሪፖርተር፡- ከዚያ ወዲህ የነበረው የፀረ ሙስና ትግል ወዴት አመራ?

አቶ ዮሐንስ፡- ደርግ በንጉሡ ባለሥልጣናት ላይ ለማስፈረድ ብሎ የጀመረውን የሙስናን ወንጀል የመዳኘት ሥራ፣ የራሱን ተቋም በማቋቋም አጠናክሮ ለመቀጠል ሙከራ አደረገ፡፡ በልዩ የጦር ፍርድ ቤት ልዩ ዓቃቤ ሕግ አቋቋመ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እጅግ ጠንካራ ቅጣት የሚጥል ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አወጣ፡፡ የልዩ ፍርድ ቤት ዳኞችንም ሾመ፡፡ ከፍተኛ ቅጣት የሚጥል ዳኝነት ይከተል የነበረው ይህ የልዩ ፍርድ ቤት ሥርዓትም፣ ለተራ ወንጀሎች እስከ ሞት የሚፈርድ በጣም ጨካኝ የፍርድ ሒደትን ያሰፈነ ነበር፡፡ ደርግ በ1967 ዓ.ም. የፀረ ሙስና ዘመቻን የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር፡፡ በ1968 ዓ.ም. ደግሞ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ለመከላከል የአብዮትና የልማት ኮሚቴ የተባለ ሌላ ኮሚቴ አቋቁሞ ነበር፡፡ በዚህም ሕገወጥነትና ሙስናን ለመከላከል ሞክሮ ነበር፡፡ በ1969 ዓ.ም. ደግሞ የአብዮት ዘመቻ አስተባባሪ ኮሚቴ የሚል አቋቁሞ ተመሳሳይ ሥራዎችን ለመሥራት ሙከራ አድርጓል፡፡

በደርግ ጊዜ በሙስናና ተዛማጅ ወንጀሎች ላይ ምርመራ የሚያደርጉና የሚከሱ በርካታ ተቋማት ለመመሥረት ተሞክሯል፡፡ የደርግ ምርመራ፣ ልዩ ምርመራና ማዕከላዊ ምርመራ የተባሉ ተቋማት ተቋቁመዋል፡፡ በ1974 ዓ.ም. ደግሞ ከዚያ ቀደም አቋቁሞት የነበረውን ልዩ የጦር ፍርድ ቤት እንደ አዲስ አሻሽሎ ልዩ ፍርድ ቤትና የልዩ ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ ብሎ አቋቁሟል፡፡ በዚሁ 1974 ዓ.ም. የሠርቶ አደር ቁጥጥር ኮሚቴ ብሎ ሌላ ተቋም አቋቁሟል፡፡ እነዚህ በሙሉ በሙስና ላይ የሚሠሩ ተቋማት ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በኋላ የመጣው ግዙፍ ሥልጣን ተሰጥቶት የተቋቋመው በ1980 ዓ.ም. የተመሠረተው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ በዚሁ ዓመት የሠርቶ አደር ቁጥጥር ኮሚቴንም አሻሽሎ ለማቋቋም ጥረት ተደርጓል፡፡

እነዚህ ተቋማት በሙሉ በደርግ ጊዜ ያከናወኑት የፀረ ሙስና ትግል ግን መታየት ይኖርበታል፡፡ በጊዜው የግሉ ዘርፍ የማይበረታታ መሆኑ ታክሎበት፣ በሕዝቡ ዘንድ ተቋማቱ ሙስናን በተመለከተ ትልቅ ግንዛቤ ፈጥረዋል ማለት ይቻላል፡፡ ተቋማቱ መብዛታቸውና ሕጉም መጠናከሩ የፈጠረው ፍርኃት ሙስና እንዳይስፋፋ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡          

ሪፖርተር፡- በዘመነ ኢሕአዴግ የሙስና ጉዳይ ጎልቶ መታየት በመጀመሩ የፀረ ሙስና ትግል የተጠናከረ ይመስል ነበር እንዴ?

አቶ ዮሐንስ፡– ሙስና እንደ ትልቅ ፈተና ታይቶ በድኅረ ደርግ አንዳንድ ተቋማት ተመሥርተዋል፡፡ በ1984 ዓ.ም. የሕግ ማዕቀፍ የሌለው ቢሆንም፣ ብሔራዊ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ የሚባል ተቋም ተቋቁሞ ነበር፡፡ በአብዛኛው ከሥልጣን ሽግሽግና ከፖለቲካ ብቀላ ጋር ለተያያዘ ዓላማ ካልሆነ በስተቀር በሙስና ላይ የሠራው ሥራ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልነበረ ይታወሳል፡፡ አጋልጥ እየተባለ በደርግ ወቅት እንዲህ አድርገሃል በሚል ከሕግና አሠራር ውጪ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎችን ለማስወገድ ነው የዋለው፡፡ በ1984 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ደግሞ የልዩ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ደግሞ ተቋቋመ፡፡ በደርግ ዘመን የተፈጸመ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለማጣራት የተቋቋመ ሲሆን፣ ለ15 ዓመታት ያህል ሥራ ላይ ውሎ ፈረሰ፡፡ በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር አንድ የሙስና አጣሪ ቡድን ተደራጅቶም ነበር፡፡ ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሠራ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተለይ እስከ 1989 ዓ.ም. የእነ ታምራት ላይኔ ጉዳዮችን ሲያጣራ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከዚያ በኋላ በሕወሓት መከፋፈል ገፊ ምክንያትነት የተነሳ በ1993 ዓ.ም. የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተብሎ መቋቋሙ የሚታወስ ነው፡፡ ይህ ኮሚሽን ከመጀመሪያውም የፖለቲካ መሣሪያ ነው የሚል ግንዛቤ በኅብረተሰቡ ዘንድ የፈጠረ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በእርግጥም ለዚያ ዓይነት ዓላማ መዋሉ በተለያዩ ማስረጃዎች አጣቅሶ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሙስናን፣ በሥልጣን ያላግባብ መገልገልን ለመከላከል ተብሎ የተመሠረተው የዕንባ ጠባቂ ኮሚሽን የሚባል ተቋም አሁንም አለ፡፡ ምን ያህል ውጤታማ ሥራ እንደሠራ ግን ጎልቶ የሚታይ ነገር ብዙም የለም፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መምጣት ጥቂት ቀደም ብሎ በ2008 ዓ.ም. የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስቀድሞ ተሰጥቶት የነበረውን የምርመራም ሆነ የመክሰስ ሥልጣን እንዲገፈፍ ተደረገ፡፡ ፓርላማው የሰጠውን ሥልጣን መልሶ ገፈፈው፡፡ የተቋሙ ሥልጣን በዝቷል፣ አምባገነን ሊያደርገው ይችላልና ወይ የመመርመር አልያም የመክሰስ ሥልጣኑ ይወሰድ የሚል ሙግት ነበር፡፡

በ1993 ዓ.ም. ተቋሙ ሲመሠረት የተሰጠው ሥልጣን በመብዛቱ፣ ራሱ ተቋሙን ለሙስና የተጋለጠ ያደርገዋል የሚል በጥናት የተደገፈ መከራከሪያ ጭምር በአማካሪ ድርጅት ሲቀርብ ነበረ፡፡ ይሁን እንጂ ፓርላማው ይህን ወደ ጎን ብሎ መመርመርም መክሰስም እንዲችል ፈቀደለት፡፡ በ1997 ዓ.ም. ተሻሽሎ በወጣው የተቋሙ ሥልጣንና ኃላፊነት ላይ ይህ ሕግ ተረጋግጦ ቀጠለ፡፡ ይህ ኮሚሽን ምን ሠራ? ምን አከናወነ? በማኅበረሰቡ ዘንድ ምን አተረፈ? ኃላፊዎቹስ ለፀረ ሙስና ትግል ተምሳሌት ሆኑ? ተቋሙ ምን ያህል የመንግሥት መገለጫ ሆነ? ተብሎ ሲጠየቅ ግን ብዙ ያጠያይቃል፡፡ መንግሥት ስለዚህ ባይገልጽልንም በ2008 ዓ.ም. የተቋሙን ሥልጣን የመግፈፍ ዕርምጃ ሲወሰድ በተዘዋዋሪ መልሱን እናገኘዋለን፡፡ በ1986 ዓ.ም. የፈረሰው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንደገና እንዲያንሰራራ ተደረገ፡፡ ይህ ሲደረግ ደግሞ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ለማድረግ፣ ወዘተ የሚሉ ምክንያቶች ነበሩ በአዋጁ መቅድም ላይ የተቀመጡት፡፡ በዚህ ዕርምጃ ተበታትኖ የነበረቅ የዓቃቤ ሕግና የምርመራ ሥራ ተሰብስቦ ወደ ትክክለኛው አንድ ቦታ እንዲገባ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ፓርላማው የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ሥልጣን መልሶ የገፈፈው፣ ተቋሙ ዓላማውን ለማሳካት አለመቻሉን በመገንዘብ ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡ በምርመራም ሆነ በመክሰስ ሥልጣኑ ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዳልነበር ፓርላማው ተገንዝቦ ነው ዕርምጃውን የወሰደ የሚመስለኝ፡፡ ኮሚሽኑ አሁንም ቢሆን አለ፣ ነገር ግን ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎችን ነው የሚያከናውነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የፀረ ሙስና ዘመቻ እንደ አዲስ ተጀምሯል፡፡ የዘመቻ ግብረ ኃይልም በፌደራልና በክልሎች እየተቋቋመ ነው፡፡ ይህ ጥረትስ ይሰምራል?

አቶ ዮሐንስ፡- የሙስና ግብረ ኃይል መቋቋሙንና ሰባት ሰዎች መሾማቸውን ሰምተናል፡፡ ይህ ዕርምጃ ሙስናና ከሙስና ጋር ተዛማጅ የሆኑ ወንጀሎችን ለአንድ ወይም ለተወሰኑ አካላት ጠቅልሎ ለመስጠት እንዳልተፈለገ፣ ከግብረ ኃይሉ ስብጥር መረዳት ይቻላል፡፡ ግብረ ኃይሉ ከምርመራውም ሆነ ከውሳኔውም ጋር የተያያዙ ሰዎችን ያካተተ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የደኅንነቱ፣ የፍትሕ ሚኒስቴርና የሌሎችም የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተካተውበታል፡፡ የግብረ ኃይሉ ሥልጣንና ኃላፊነትን በተመለከተ ከየት እስከየት እንደሆነ ወሰኑን የሚያሳይ ሕጋዊ ማዕቀፍ (ሰነድ) ባላይም እንኳን፣ ግብረ ኃይሉን የማዋቀሩ ዘዴ ግን ከዚህ ቀደም ያልተሞከረና ያልታየ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

አሁን በአገራችን የሙስና ጉዳይ ተራ የኢኮኖሚ ወንጀል ከመሆን አልፏል፡፡ ሙስና ለአገራችን ህልውና ፈታኝ የሆነበት ደረጃ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ሙስና የአገራችን ሉዓላዊነት፣ ህልውናና ቀጣይነት የሚገዳደር አደጋ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ በተጨባጭ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የተመለከትነው ለአገር የነበረን ታማኝነትና ቀናዒነት ትቶ፣ ሁሉንም የአገር ሀብትና ሥልጣን ካልጠቀለልኩ በሚል መንፈስ አገርን ለአደጋ የሚጥል ድርጊት የሚያራምዱ ኃይሎች የፈጠሩትን ቀውስ ነው፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እየተዘረፈና ከአገር እየወጣ የአገር ሉዓላዊነትን ለማፍረስ ለማዋል ጥረት ሲደረግ ይታያል፡፡ በሙስና የተመሠረቱና ወደ መንግሥት ሀብትነት መቀየር የነበረባቸው ሀብቶች አገር ለማፍረስ ሴራ ለማዋል ሲሞከር ዓይተናል፡፡ በዚህ የተነሳ ሙስና ዛሬ በአገራችን በዓይነትም፣ በይዘትም ሆነ በጥልቀት እጅግ አስፈሪ ደረጃ ላይ የደረሰበት ሁኔታ ይታያል፡፡

ሪፖርተር፡– ደርግ ሲመጣ የራሱን የፀረ ሙስና ተቋማት አዋቀረ፣ ኢሕአዴግም በጊዜው የራሱን መዋቅር መሠረተ፡፡ በኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ትግልና መታገያ ተቋማት ለፖለቲካ ዓላማ ይውላሉ ይባላል፡፡ ይህ ምን ያህል አሳማኝ ነው?

አቶ ዮሐንስ፡- የፀረ ሙስና ትግል ብዙ ጊዜ እግረ መንገዱን ለፖለቲካ ሥራ መዋሉ የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲቋቋም በአንድ የውጭ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ግምገማ፣ የደርግ ዘመን የፀረ ሙስና ተቋማት ታማኝነት ኖሯቸው ሊቀጥሉ ያልቻሉበትን ምክንያት አጥንቶ አቅርቦ ነበር፡፡ የጥናቱ መደምደሚያ ላይ ተቋማቱ የፖለቲካ መሣሪያ በመሆን፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ፀጥ ለማሰኘት በመዋላቸው ነው ሲል አንደኛውን ምክንያት ያስቀምጣል፡፡ በሁለተኝነት ደግሞ ተቋማቱ ሥልጣንን ለተወሰኑ ግለሰቦችና ቡድን መገልገያ በማዋላቸው ይላል፡፡ ሙስናን ለማጣራትና በወንጀል ለመክሰስ ሕጎቹ በሁሉም ዜጎች ላይ በአንድ ዓይነት መንገድ ተፈጻሚ የማይሆኑ በመሆናቸው፣ ይልቁንም አንዳንድ ሰዎች ከሕግ በላይ በመሆናቸው ሦስተኛው ችግር ነው ይላል፡፡ አራተኛው ደግሞ የተቋማቱ አንዳንድ አባላት ጭምር በሙስና የተዘፈቁ መሆናቸው ሲሆን፣ አምስተኛው ምክንያት ተቋማቱ ሥራቸውን የሚያከናውኑት በብቀላና በኢመደበኛ መንገድ መሆኑን ያወሳል፡፡ ተቋማቱ ከፓርቲ አደረጃጀት ጋር በመቆላለፍ ከፖለቲካው ጋር መተሳሰራቸው በስድስተኛነት ይነሳል፡፡

ፍርድ ቤቶችም በፖለቲካ ተፅዕኖ ሥር የወደቁ ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ ነፃነታቸውን የተሸረሸረ ማድረጉ ሰባተኛ ተብሏል፡፡ ስምንተኛው ደግሞ በመንግሥት ዘንድ ሁሉን አቀፍ የተጣጣመና ግልጽ የፖሊሲ ማዕቀፍ አለመኖሩ፣ እንዲሁም የተገነጠለና አንዱን ገጽታ ብቻ የሚያይ መሆኑ ተብሎ ተቀምጧል፡፡ በዘጠነኛ ላይ መላ ሕዝቡን በጅምላ በመቀስቀስና ዕርምጃ እንዲወስድ በማነሳሳት ዕርምጃ ለመውሰድ እንጂ፣ ሊተኮርበት የሚገባን የሕዝብ አስተዳደር ችግር አለመለየት የሚል ምክንያት ይገኛል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በምርመራ፣ በክስና በፍርድ ሒደቶች ከፍተኛ ቅጣት የሚጥሉ ሕጎችን ማውጣት ላይ እንጂ፣ የሙስናን ክፉነት በማስተማር ሕዝባዊ ድጋፍ እንዲገኝ ተገቢው ትኩረት አለመሰጠቱ አሥረኛው ምክንያት ተብሎ ቀርቧል፡፡ ጥረቱ ወጥነትና እርስ በእርሱ የተሳሰረ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ያደረገ በመሆኑ አሥራ አንደኛ ላይ ተመልክቷል፡፡ በአሥራ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የመንግሥት ጥረቶች ሕዝባዊ ድጋፍ ቢኖራቸውም፣ ድጋፉ ግን ዘለቄታዊ ሆኖ እንዲቆይ በቂ ጥረት አለመደረጉ ሌላው ችግር ነው ተብሏል፡፡

ይህን በዚያ ወቅት የቀረበ የጥናት መደምደሚያ ስመለከት በግሌ አንዳንድ ችግሮች መቀረፋቸውን ባምንም፣ ነገር ግን ከሞላ ጎደል ችግሮቹ ዛሬም ድረስ መኖራቸውን እረዳለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ የፀረ ሙስና ትግሎች በአገራችን እነዚህን በመሰሉ ችግሮች የተተበተቡ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው አሁን የተጀመረውን የፀረ ሙስና ዘመቻ ትግል በተመለከተ ገና ጅማሮ ላይ ነን፣ ውጤቱን አላየንም፡፡ ይህ የጥናት ምክረ ሐሳብ በደርግ ዘመን የነበሩ የፀረ ሙስና መታገያ ተቋማትን የተመለከተ ቢሆንም፣ ነገር ግን በኢሕአዴግም ሆነ አሁን ድረስ በእኩል ደረጃ መቀመጥ የሚችል ጠቃሚ ግምገማ ነው፡፡

የፀረ ሙስና ተቋም በሕግ የተደገፈ ይሁንታ ተሰጥቶትና ከፖለቲካ ነፃ ሆኖ መመሥረት አለበት፡፡ ለፓርላማው ሪፖርት እንዲያደርግ ማድረግ የበለጠ ነፃነቱን ያረጋግጣል፡፡ እነዚህ ሳንካዎች ተወግደው ከፖለቲካ ሥርዓቱ በፀዳ መንገድ ከተመሠረተ ውጤታማ ይሆናል፡፡ አሁን የተመሠረተው ግብረ ኃይል በመንግሥት ምን ያህል ይሁንታና ነፃነት እንደተሰጠው ገና አላወቅንም፡፡ የመንግሥትን ይሁንታ በነፃነት ያገኘ መሆኑን ገና የምናየው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደምናየው ከሆነ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ድጋፍና ፈቃድ ሳይኖር ታች ያሉ ባለሥልጣናት በሙስና ወደ መዘፈቅ አይገቡም፡፡ አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ ደግሞ ሙስና ከብሔር ፖለቲካ ጋር ተጋምዶ ውስብስብ ችግር ፈጥሯል፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ተቋማዊ በሆነበት አገር የሙስና ችግር የሚነሳው ከዚህ ነው፡፡ ብቃትና ችሎታን የዘር ፖለቲካ አያይም፡፡ በዚህ የተነሳ የጎሳ ፖለቲካ በአድልኦ ላይ የተመሠረተ ነው የሚሆነው፡፡ ዕውቀትና ችሎታን ሳይሆን የጎሳ ስብጥርን ያማከለ ፖለቲካ ሁሌም ለአድልዎ የተጋለጠ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– በኢትዮጵያ ምን ዓይነት ዘርፎች ናቸው በሙስናና በምዝበራ በእጅጉ የነቀዙት?

አቶ ዮሐንስ፡– በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ መተኮር አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የምንዛሪ መውጣትና መግባት ጉዳይ ትልቁ ለሙስና የተጋለጠ ዘርፍ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በገቢ ዕቃዎችና በወጪ ዕቃዎች የሚንቀሳቀሰው የውጭ ምንዛሪ ትልቁ ለሙስና የተጋለጠ ነው፡፡ በጥቃቅን ችግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ቢተኮር እላለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ለመቆጣጠር ደግሞ ቀላል መንገዶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖች አሉ፡፡ አባል የሆነችባቸው ትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት የመረጃ ልውውጥ የሚያደርጉባቸው ሥርዓቶች አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በግሌ አሁን በተቋቋመው ግብረ ኃይል ውስጥ አግባብነት ያላቸው ሰዎች ተወክለዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ዝም ብሎ በየአቅጣጫው ከሚወጣው ሀብት ይልቅ፣ በመደበኛ ሁኔታ በመደበኛ የንግድ ልውውጥ ስም በባንኮች በኩል የሚወጣው ምንዛሪ ብዙ ነው፡፡ የደኅንነቱም ሆነ የፋይናንስ ተቋማት በግብረ ኃይሉ መካተታቸው አግባብ ነው፡፡

ሌላው ሊተኮርበት የሚገባ ደግሞ መንግሥት እጅግ ትልቅ ሀብት የሚያፈስበት የዕቃና የአገልግሎት ግዥ ዘርፍ ነው፡፡ ትልቅ የሀገር ሀብት የሚፈስበት የዕቃ ግዥ ዘርፍ ሊተኮርበት ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ትልቅ የሀብት ምንጭ የሆነው መሬት፣ ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ አሰጣጡም ሆነ አጠቃቀሙ የተምታታ ነገር ያለው መሆኑ ለሙስናና ለዘረፋ የተጋለጠ ዘርፍ አድርጎታል፡፡ መሬት ትልቁ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጭቆና፣ የሙስናና የሌላም መሣሪያ እየሆነ ነው ያለው፡፡ በዚህ ጉዳይ ውሳኔ የሚሰጥበት አግባብም ሆነ አሠራር ከፍተኛ ትኩረት ያሻዋል፡፡ ከዕርዳታ አቅርቦት ሥራ ጋር በተያያዘ፣ እንዲሁም ከመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተገናኘም ትኩረት ያስፈልጋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የፀረ ሙስና ተቋማትም ሆነ ሥራዎች ለምን አልሰመሩም? አገሪቱ አሁን የምትገኝበት የሙስና ቀውስ ውስጥ ልትሸጋገር የቻለችው ለምንድን ነው?

አቶ ዮሐንስ፡- የፀረ ሙስና ሥራ በአንድ ተቋም ላይ የሚጣል አይደለም፡፡ እዚህ ደረጃ የደረስነው ደግሞ ለዓመታት የተፈጸሙ ነውሮች ተደማምረው ነው፡፡ መንግሥታዊ አሠራሮች በተለይም የሀብት አስተዳደር ሥርዓቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየላሉ ሄደዋል፡፡ በየጊዜው ተቋማቶቻችንን አፍርሰናል፡፡ ያሉት ተቋማትም ቢሆን ብቃትም፣ ዝግጁነትም ሆነ ቆራጥነት በሌላቸው ኃላፊዎች እየተሞሉ ለዓመታት እንዲሽመደመዱ ተደርገዋል፡፡ የነበሩ ጥብቅ አሠራሮች እንዲላሉና ለሙስና ተጋላጭ በሆኑ አሠራሮች እንዲተኩ ተደርገዋል፡፡ አንዱ ይህን የማድረጉ ምክንያት ዴሞክራሲን ማስፈን (ዴሞክራታይዜሽን) የሚል ፈሊጥ ነበር፡፡ ያልተማከለ ፌደራላዊ ሥርዓት ለመፍጠር ነው የሚል ሌላ አመክንዮም ይሰጣል፡፡ ለተባለው ምክንያት ቢደረግ እንኳን በመንግሥት ግዥዎችና የሀብት አስተዳደር ሥራዎች ላይ ብቁ ሰዎችን በመመደብ የተጠናከረ አሠራር ለመከተል የተደረገ ጥረት የለም፡፡

የቁጥጥርና የሕግ ማስከበር ተቋማት እንዲዳከሙና ሙያተኛውም እንዲወጣ ሲደረግ ነው የኖረው፡፡ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውና ተዓማኒ የሆኑ ሰዎች እንዲመጡ አይደረግም ነበር፡፡ ያለ አንዳች ዲሲፕሊን፣ ያለ አንዳች የዕውቀት ዝግጅት፣ ከእነ ጭራሹ የተጭበረበሩ የትምህርት ማስረጃዎችን ይዘው የሚመጡ ሰዎች በክልልም በፌደራልም የመንግሥት ተቋማት ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ሕግና ሥርዓት ለማስከበርም ሆነ ተገቢ አገልግሎት ለሕዝቡ ለማቅረብ የማይቻል ሆነ፡፡ በአጠቃላይ የመንግሥት ተዓማኒነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጓል፡፡ ይህ ሁሉ ነው አሁን ላለንበት የሙስና ዝቅጠት ያበቃን፡፡

ሌላው ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሲተካ ለሙስና ክፍተት የማይሰጡ አሠራሮችን፣ የድንቁርናና ኋላቀርነት ሥራ አድርጎ መቁጠር ተጀመረ፡፡ የነበሩ አሠራሮችን ማጥላላት፣ የነበሩ ኃላፊዎችን መተቸት፣ እንዲሁም አሠራሮቹን የመለወጥ ዝንባሌ ለሙስናና ምዝባራ በር የከፈተ ችግር ሆኗል፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታና ቅቡልነት ለማግኘት ሲባል የአሠራር ማሻሻያ እየተባለ፣ የአሠራር ጥፋትን ለመፍጠር የተሄደበት መንገድ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ችሎታና ብቃት፣ እንዲሁም ልምድ ያላቸው ሙያተኞችን በአሠራር ማሻሻያ ስም በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ምንም ዝግጅትና ልምድ በሌላቸው ሰዎች የመተካት ዘመቻ በይፋ ሲካሄድ መቆየቱ የሙስና ተጋላጭነትን ጨምሯል፡፡ የፀረ ሙስና ተቋምም ቢሆን በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ያለፈ ነው፡፡ ለዚህ ነው ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል መፍትሔ ሳይፈጥር የቆየው፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ይህን ሁኔታ በቅጡ የተረዳ ይመስላል፡፡ በፖሊሲና በአሠራር ተደግፈው አገር ለማፍረስ ሲውሉ የነበሩ ችግሮች ደግሞ በአንድ ጊዜ በቃ ተብለው ሊቆሙ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ከችግር ለመውጣት አገሪቱ ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃት ነው በግሌ የማስበው፡፡

ሪፖርተር፡- ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለምን ተሽመደመደ?

አቶ ዮሐንስ፡- ሲጀመር ተቋሙ በአገሪቱ ያሉ የሙስና ችግሮችን እንዲፈታ የተመሠረተ አልነበረም፡፡ ከዚህ በመለስ ተብሎ አቅጣጫ ተሰጥቶ የተነደፈልህን እንድትሠራ ተብሎ ነው ተቋሙ ሥራ የጀመረው፡፡ ተቋሙ በዚህ መንገድ ሲሠራ እንደነበር በዚያ ተቋም በመሥራት ብቻ ሳይሆን፣ የተቋሙ ሰለባ ሆኜም ይህን ዓይቼዋለሁ፡፡ ፈጽሞ የሕዝብ አለኝታ ሆኖ የሙስናን ወንጀል ለመከላከል ያለ ተቋም ነው ብዬ አላምንም፡፡ ይህንን ስል ግን ጥቂት ነገሮች አልሠራም አልልም፡፡ ያስፈረዱትን ጉዳይና ያሳሰሩትን ሰው ሪፖርት ሲያቀርቡ ይታያል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች የአገሪቱን ሙስና በመሠረታዊነት ለመፍታት የሚረዱ አልነበሩም፡፡ ሕጉን ለተመለከተ ሙሉ ሥልጣን የተሰጠው ቢመስልም፣ ነገር ግን በተመረጠ ሁኔታና ቦታ ካልሆነ በተጨባጭ ሥራውን መሥራት የሚችል አልነበረም፡፡ ሥልጣኑ በሚገፈፍበት ጊዜ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትን ለማቋቋም ያስፈለገው፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚል በአዋጁ መቅድም ላይ ተቀምጧል፡፡ ፀረ ሙስና የተባለውን ነገር ይሠራ ነበር ማለት ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ለረዥም ዓመታት የኖረውን የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም ኢሕአዴግ በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር ወስዶ ደብዛው እንዲጠፋ አደረገው፡፡ በ2008 ዓ.ም. ደግሞ መልሶ እንዲቋቋም አደረገው፡፡ የተመረመረ ወንጀልን ይከሳል የሚባልና ትልቁ የወንጀል ፍትሕ ተቋም ነው የሚባል መዋቅርን አስወግደህ፣ እሱን የሚተኩ አራትም አምስትም ተቋማት አቋቁመህና ሥልጣኑንም በትነህ ለ22 ዓመታት ካቆየህ በኋላ ዳግም መሰብሰብ አለበት ብለህ ታቋቁማለህ፡፡ ተቋሙ ዳግም ሲመሠረትም በመቅድሙ ላይ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ብልሹ አሠራርን ለመቅረፍ የሚል ነገር ተቀመጠ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በእነዚያ 22 ዓመታት እነዚህ ነገሮች በአገሪቱ አፈር ድሜ ግጠዋል ማለት ነው፡፡ ይህ በተዘዋዋሪ ፀረ ሙስና ተቋም የሚጠበቅበትን ያልሠራ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተለያዩ ጥናቶች ተደርገው የሙስናና የሀብት ብክነት ግኝቶችን በመሰብሰብ ለመንግሥት የቀረቡበት ጊዜያት ቢኖሩም፣ ዕርምጃ ያልተወሰደባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ለመንግሥት ቢቀርቡም ዕርምጃ አለመወሰዱ ይነገራል፡፡ ይህን መሰል ፈተናዎች ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲገጥመው ነበር ይባላል?

አቶ ዮሐንስ፡– ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይሁንታን ባገኘባቸው ጉዳዮች ብቻ ነው ሥራውን የሚሠራው፡፡ ከአናቱ ፈቃድ ሰጪ አካል አለው፡፡ በራሱ የመወሰን ሥልጣን ያለው አካል ሆኖ አይታየኝም፡፡ ከዚህ በመለስ እከሌና እነ እከሌ እየተባለ የሚሠራ ተቋም መሆኑን ነው የማውቀው፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ ሰሞን ዘመቻ ሙስናን መከላከል ይቻላል? አሁን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድገቱ የፈጠረው ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል ዕድል አለ? የገንዘብ ዝውውርን ከካሽ ነፃ በማድረግና ቴክኖሎጂያዊ ቁጥጥር በማካሄድ ሙስናን መቆጣጠር ለምንድነው የማይቻለው? ሰሞኑን እንደሚሰማው ሙስና … ሙስና … ከማለት በቋሚነት መሥራት አይቻልም?

አቶ ዮሐንስ፡- ቴክኖሎጂ ሙስናን ለመከላከል ትልልቅ ዕድሎችን አምጥቷል፡፡ ስለዚህ አሁን ባለንበት ጊዜ ሙስናን ለመከላከል ትልቅ ዕድል አለ፡፡ አብዛኛውን መሠረተ ልማት ደግሞ በመንግሥት እጅ ያለ ነው፡፡ የመንግሥት ይሁንታ ካለ ይህን ማድረግ ይቻላል፡፡ አሁን በተቋቋመው ግብረ ኃይልም ይህን ለማድረግ ጥሩ ቅንጅት ለመፍጠር ታስቦ የተዋቀረ ይመስላል፡፡ አሁን ያላወቅነው እነዚህ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የሌላ አካልን ይሁንታ ሳይጠይቁ፣ በራሳቸው የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት የሚችሉ ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውን ነው፡፡ የሙስና ወንጀል ተከታታይነትና ቋሚነት ባለው ሁኔታ የሚሠራ እንጂ፣ እያረፉ የሚካሄድ የአንድ ሰሞን ሥራ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ለውጥ መጥቷል፡፡ ከተሸኘው የፖለቲካ ሥርዓት ጋር መሸኘት ያለባቸው አሠራሮች ደግሞ አሉ፡፡ ሙስናን በአንድ በተጠናከረና መቼም ጊዜ ሊለወጥ በማይችል ወጥ በሆነ አንድ አካል ልምድ ባላቸው ሙያተኞች መዋጋት አዋጪ ነው፡፡ በየጊዜው ለሁሉ ነገር አዲስ የማይሆን ራሱን እያሻሻለና እያበቃ በሚሄድ የሙያ ሥራ በሚያከናውን ተቋም ሙስናን መዋጋት አስፈላጊ ነው፡፡ ሙስናን በመከላከል ላይም እንዲሁ አተኩሮ መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡ ከትምህርት ሥርዓቱ ጀምሮ ስለሙስና ጎጂነትና ጠንቅነት ግንዛቤ መፍጠርና ኅብረተሰቡን ለዘመቻው ማሠለፍ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...