Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በነዳጅ ኮንትሮባንድ ውስጥ የተወሰኑ ባለሥልጣናት እጃቸው እንዳለበት የሚያሳይ ጥናት ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ነዳጅን በበርሜል ቀድተው ለጥቁር ገበያ የሚያስተላልፉ ተገኝተዋል

የክልል አንዳንድ ባለሥልጣናት ሥልጣናቸውን ተገን በማድረግ በነዳጅ ኮንትሮባንድ ውስጥ መግባታቸውን የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በጥናት አረጋግጫለሁ አለ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ውሳኔ አፈፃፀም ላይ የተገኙ ውጤቶች፣ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና መንስዔዎችን በተመለከተ ባለፉት ወራት ያካሄደውን ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡

ጥናቱ እንደሚያመላክተው፣ ከታለመለት የነዳጅ ድጎማ አሠራር ባፈነገጠ መልኩ ባለሥልጣናቱ በነዳጅ ኮንትሮባንድ ውስጥ ቤተሰቦቻቸውን በማሳተፍና ትስስር በመፍጠር፣ አሠራሩ ያላግባብ የግል መጠቀሚያ እየሆነ ስለመሆኑ የተናገሩት የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳድር በደል መከላከል ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ ናቸው፡፡

በመሆኑም በዚህ ተግባር የተሰማሩ አካላት ላይ አስተማሪ የዕርምት ዕርምጃ በመውሰድ ሌሎች ባለሥልጣናት ከእንደዚህ ዓይነት ተጓዳኝ መሰል ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ማስተማሪያ ዕርምጃ እንዲወሰድ ዕንባ ጠባቂ ጠይቋል፡፡

የታለመለት የነዳጅ ድጎማን በሚመለከት ኢትዮጵያ የተጻፈ የነዳጅ ድጎማ ፖሊሲ የሌላት በመሆኑ፣ በዓለም ገበያ ላይ የነዳጅ ዋጋ ንረት በሚከሰትበት ወቅት ኅብረተሰቡ እንዳይጎዳ፣ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በጀት ለማስፈቀድ የሚያስችለው  የፖሊሲ ሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ቢኖርም፣ በተጠናከረ መልኩ እየተሠራበት ባለመሆኑ መንግሥት በአማካይ በወር እስከ አሥር ቢሊዮን ብር ለወጪ መዳረጉ የተመለከተ ሲሆን፣ መንግሥት በጥናት ላይ ተመሥርቶ የነዳጅ ድጎማ ውሳኔው ኅብረተሰቡ ዘንድ ያመጣውን ውጤት ማረጋገጥ እንዳልቻለም ጥናቱ ያሳያል፡፡

በጥናቱ እንደተገለጸው አሽከርካሪዎች በተቀመጠው የነዳጅ ታሪፍ መሠረት አለማገልገልና ስለታሪፍ ጥያቄ የሚያነሱ ተገልጋዮች በአሽከርካሪዎች አላስፈላጊ ዛቻ፣ ስድብ፣ ማስፈራራት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

የተወሰኑ ድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ከድጎማው ዓላማ ውጪ በኮንትራት ሥራ ላይ መሰማራት፣ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽርካሪዎች ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ ትርፍ መጫን፣ ማቆራረጥና አመሻሽ ላይ የታሪፉን እጥፍ ማስከፈል የሚሉ በጥናቱ ተብራርቷል፡፡

በሌላ በኩል የተወሰኑ መለስተኛና ከፍተኛ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች፣ በመነሐሪያ ውስጥ የትክክለኛ ታሪፍ ደረሰኝ ከሰጡ በኋላ በጉዞ ወቅት የታሪፉን እጥፍ ማስከፈል፣ ለአብነት የ90 ብር ታሪፍ 200 ብር የማስከፈል፣ የ300 ብር ታሪፍ በእጥፍ 600 ብርና ለአጫጭር መንገዶች የተለየ ታሪፍ አለመኖሩ በጥናቱ ተገልጿል፡፡

መንግሥት የዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አለማጠናከሩ፣ የነዳጅ ድጎማ ፖሊሲው ወጥቶ እንዲተገበር በቁርጠኝነትና በቅንጅት አለመሥራት፣ እንዲሁም የነዳጅ ድጎማ ውሳኔውን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል በቂ የቅድመ ዝግጅትና የመናበብ ሥራ አለመከናወኑ ተብራርቷል፡፡

በመንግሥት የተደራጁ የታክሲ ተራ አስከባሪ ወጣቶች የትራንስፖርት አገልግሎት ማሳለጥና ሥነ ሥርዓት ማስከበር ሲገባቸው ትኩረታቸው ዕለታዊ ብር መሰብሰብ ላይ ብቻ እንደሆነ በጥናቱ ተገልጿል፡፡

በጥቅማ ጥቅም በመመሳጠር ነዳጅን በበርሜልና ሮቶ ቀድተው ለጥቁር ገበያ ሌሊት የሚያስተላልፉ የነዳጅ አዳዮች መገኘታቸውና ነዳጅ ከአገር በማውጣት ለጎረቤት አገሮች በመሸጥ፣ በአገር ውስጥ ሸጠው ከሚያገኙት ሁለት እጥፍ በላይ ለማግኘት ሕገወጥ የንግድ አሠራር ስለመገኘቱም ጥናቱ ያሳያል፡፡

ዕንባ ጠባቂ ተቋም በጥናቱ እንዳመላከተው በተሽከርካሪዎች ላይ አርቴፊሻል ሰልባቲዮ በመግጠም በአማራጭ መንገድ ነዳጅን የማሸሽ ዝንባሌ ስለመኖሩና የቤንዚን እጥረት እንደተፈጠረ በማስመሰል፣ በየሸቀጣሸቀጥ መደብርና በግለሰብ መኖሪያ ቤት ጭምር በችርቻሮ እየተሸጠ ነው፡፡

በተመሳሳይ ነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ የለንም ብለው በመዝጋት ሁለት ወይም አንድ ማደያ ብቻ እየሠራ እንዲውል በማድረግና መጨናነቅን በመፍጠር፣ በተወሰኑ ማዳያዎች በቴክኖሎጂ አሠራር ሥርዓት ተጠቅሞ ለመሸጥ ፍላጎት ያለመኖር ችግር እንዳለ ተጠቁሟል፡፡

የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪ ትክክለኛ መረጃን ወደ ጎን በመተው የማደያ ሠራተኞች ተሽከርካሪው አልተመዘገበም በማለት የማጉላላትና ቅድሚያ የድጎማው ተጠቃሚ ላልሆኑ ተሽከርካሪዎች ነዳጅን መሸጥ እንዳለም ተነግሯል፡፡

የድጎማ ተጠቃሚ ያልሆኑ ተሽከርካሪዎችን ቅድሚያ መስጠት፣ በቀጥታ በጥሬ ገንዘብ የመቀበል ፍላጎት ማሳየትና ለነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች እምብዛም የማስተናገድ ፍላጎት እንደሌላቸው ዕንባ ጠባቂ በጥናቴ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

የቴሌ ብር አሠራር ሥርዓት ኔት ወርክ በመቆራረጡ በነዳጅ ድጎማ ተሽከርካሪዎች፣ የድጎማ ነዳጅ ኮታውን በአፋጣኝ መቅዳት ባለመቻላቸው ምክንያት ከኪሳቸው ጥሬ ገንዘብ እየከፈሉ እንደሚቀዱና የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንዳደረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡

ከተመዘገቡ ከ157 ሺሕ በላይ የድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 62,730 (40 በመቶ) ተሽከርካሪዎች ብቻ የድጎማ ተጠቃሚዎች በመሆናቸው ወደ ድጎማ ሥርዓቱ የመግባት ፍላጎት አለመኖር እንደሚታይ ጥናቱ አሳይቷል፡፡

በድጎማ ሥርዓቱ ከታዩ ተጨማሪ ክፍተቶች ውስጥ ረዥም ርቀት የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ላይ የጂፒ ኤስ መሣሪያ ተግባራዊ ባለመሆኑ ምክንያት፣ የነዳጅ አጠቃቀማቸውን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑን ከድጎማ አሠራሩ በተገናኘ አጥፊዎች ላይ በፍርድ ቤት ክስ ቢመሠረትም በነፃ የማሰናበት ሁኔታ መከሰቱ አሠራሩን አዳጋች እንዳደረገው ተጠቁሟል፡፡

የድጎማ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ የታተሙት ፓዶች ምንም ሥራ ላይ ሳይውሉ መንግሥትን 91,176,545.70 ብር ወጪ እንደዳረገው ተገልጿል፡፡

በአጥፊዎች ላይ ቆንጣጭና አስተማሪ የፍርድ ውሳኔ መስጠት የሚያስችል ከፖሊስ፣ ከፍትሕና ከፍርድ ቤቶች ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር የላላ ስለመሆኑም በጥናቱ ተብራርቷል፡፡

በነዳጅ ድጎማ ሽያጭ ሌሎች አማራጭ የፋይናንስ ተቋማትን (ባንኮችን) ያለማሳተፍና መሰል ችግሮችን የጠቀሰው ጥናቱ፣ በማጠቃለያው የነዳጅ ድጎማ ውሳኔው በሚፈለገውና በተጠናከረ መልኩ ተተግብሯል ብሎ ለመናገር እንደማያስችል መደምደም ይቻላል ብሏል፡፡

በመሆኑም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን መነሻ በማድረግ በድርጊት ጥናቱ የተለዩ ግኝቶችንና የተቀመጠውን ምክረ ሐሳብ እንደ መነሻ በመውሰድና በጠራ መረጃ ላይ በመመሥረት ጥናቱ በተደረገባቸው ተቋማት ላይ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ለችግሩ ዕልባት የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲፈጠር ዕንባ ጠባቂ ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም ዓለም ላይ የነዳጅ ዋጋ ንረት በሚፈጠርበት ወቅት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳይጎዱ ከነዳጅ ድጎማ ጋር በተያያዘ ምክር ቤቱ ለውሳኔ ያመች ዘንድ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ የሚወጣበት አግባብ እንዲፈጠር ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች