Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሼክ ዓሊ አልአሙዲ የተከሰሱት አቶ አብነት ገብረ መስቀል ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተወሰነ

በሼክ ዓሊ አልአሙዲ የተከሰሱት አቶ አብነት ገብረ መስቀል ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተወሰነ

ቀን:

  • ይመሩት የነበረው ማኅበር ለሃያ ዓመታት ስብሰባ አላካሄደም
  • የማኅበሩን ሒሳብ የሚመረምር ባለሙያ እንዲሾም ትዕዛዝ ተሰጠ

ከሼክ መሐመድ ዓሊ አልአሙዲ ጋር ከ21 ዓመታት በፊት በ1994 ዓ.ም. በሽርክና ላቋቋሙት ‹‹ቦሌ ታወርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› ሥራ አስኪያጅ ሆነው የቆዩት አቶ አብነት ገብረ መስቀል፣ ለሃያ ዓመታት የማኅበሩን አባላት ስብሰባ ጠርተውም ሆነ ቃለ ጉባዔ ይዘው እንደማያውቁ እንዲሁም ማኅበሩ የየዓመቱ የሀብትና ዕዳ መግለጫ ወይም የሒሳብ ሚዛን እንደሌለው በፍርድ ቤት በመረጋገጡ ከሥራ አስኪያጅነት ኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተወሰነ፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት በሳዑዲ ዓረቢያው አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጥሪ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ከሄዱ በኋላ ታስረው የከረሙትና በኋላም በነፃ መላቀቃቸው ቢነገርም እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ያልቻሉት ሼክ መሐመድ ዓሊ አልአሙዲ በቀጠሯቸው ሦስት ጠበቆች ከሁለት ዓመት በፊት በ2013 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ንግድና ኢንቨስትመንት ምድብ አምስተኛ ችሎት በአቶ አብነት ላይ ክስ መሥርተው ነበር፡፡

የክሱ መነሻ ወይም ምክንያት ሼክ መሐመድ 60 በመቶና አቶ አብነት 40 በመቶ ባለድርሻ የሆኑበት ‹‹ቦሌ ታወርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› መሆኑን ክሱ ያብራራል፡፡ ማኅበሩን በሥራ አስኪያጅነት እንዲመሩ አቶ አብነት መሾማቸውንና በንግድ ሕጉ አንቀጽ 516 እና በማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው በክሱ ተጠቅሷል፡፡ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2208 እና 2209 ድንጋጌ መሠረት እንዲወጡ የሕግ ግዴታ የተጣለባቸው ቢሆንም ግዴታቸውን እንዳልተወጡ በክሱ ተዘርዝሮ ቀርቧል፡፡ አቶ አብነት ለማኅበሩ ይዞታ የሆነውንና ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን 3,383 ካሬ ሜትርና 1,971 ካሬ ሜትር ቦታዎች ወደ እራሳቸው ማዛወራቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ በተጠቀሰው ልክ በከሳሽ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንም አክሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከሳሽ የማኅበሩን ንብረት ሁኔታ የማወቅ፣ ዝርዝር  የሒሳብ ሚዛን የማወቅ፣ የኦዲት ሪፖርት፣ የስብሰባ ቃለ ጉባዔና ሌሎች ሰነዶችን የማግኘትና የመጠየቅ መብት ቢኖራቸውም፣ ማኅበሩ ከተቋቋመት ጊዜ ጀምሮ ሊሰጧቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸውንም ክሱ ያስረዳል፡፡ ከሳሽ ሌላው ያቀረበው ክስ፣ አቶ አብነት ከሕግ አግባብ ውጭ በማኅበሩ ስም 425 ሚሊዮን ብር ተበድረው ለግል ጥቅም መዋላቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ከሳሽ በጠበቆቻቸው አማካይነት በጠቀሷቸው የክስ ጉዳዮች ላይ ማለትም አቶ አብነት ከማኅበሩ ሥራ አስኪያጅነት እንዲነሱ፣ የማኅበሩን ንብረትና ሰነድ እንዲያስረክቡ፣ የማኅበሩ ሒሳብ እንዲመረመርና ሌሎችም በክሱ ላይ የተጠቀሱ ጉዳቶች ላይ እንዲወሰንላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

አቶ አብነት በቀጠሯቸው አምስት ጠበቆች አማካይነት ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የክስ መልስ፣ ከሳሽ ያቀረቡት ክስ ከፍርድ ቤቱ የሥልጣን ወሰን በላይ በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ከሳሽ 120 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትን ይዞታ ተከሳሽ ለግል ጥቅም አውለዋል መባሉና በማኅበሩ ስም 425 ሚሊዮን ብር በመበደር ለግል ጥቅም አውለዋል መባላቸው፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 248 ድንጋጌ መሠረት መጣራት እንዳለበትም በምላሹ ጠቁመዋል፡፡ አቶ አብነት ከሳሽ ላቀረቡት ዘርዘር ያለ ክስ እሳቸውም ዘርዘር ያለ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ከማኅበሩ ሥራ አስኪያጅነት እንዲነሱ የተጠየቀውን ዳኝነት በሚመለከት በሰጡት ምላሽ ከሳሽ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዘጠኝ የክስ መዝገቦችንና በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንድ የክስ መዝገብ ከፍተው እየተከራከሩ መሆኑን ጠቁመው፣ የተጀመረው ክስ መታየት የሚችለው እሳቸው ጉዳት ማድረሳቸው ተረጋግጦ በተጀመሩት ክሶች ፍርድ ሲሰጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቦሌ ታወርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በክሱ እንደተጠቀሰው በ1994 ዓ.ም. በጋራ መቋቋሙን ያረጋገጡት አቶ አብነት፣ የማኅብሩ ሕንፃ የተገነባበት ቦታ (2,000 ካሬ ሜትር) በራሳቸው ስም የነበረ መሆኑንና (ካርታ ቁጥር ጠቅሰዋል) በማኅበሩ ስም እንዲዛወር በማድረግ መብታቸውንና ግዴታቸውን ለማኅበሩ ለማስተላለፍ ተስማምተው ማስተላለፋቸውን ጠቁመዋል፡፡ ይኽም የሆነው ከከሳሽ በኩል ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይፈጸምላቸው በዓይነት ለማኅበሩ ገቢ ያደረጉ መሆኑን ገልጸው፣ ከላይ በከሳሽ የተጠቀሱት ይዞታዎችን ሲያስተላልፉ የሰነድ ላይ ስምምነት ሳያደርጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ አብነት ዘርዘር ያለ ምላሽ ሰጥተው፣ የቀረበባቸው ክስ በማስረጃ የተደገፈ ባመሆኑ ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ 425 ሚሊዮን ብር ለግል ጥቅማቸው አለማዋላቸውንና ለከሳሽ ቅርብ ቤተሰቦች በተለያዩ ጊዜያት ማስተላለፋቸውን አክለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ክሱንና ምስክሮችን ከሰማ በኋላ አቶ አብነት ከማኅበሩ ሥራ አስኪያጅነታቸው ሊነሱ ይገባል ወይስ አይገባም? በቂ ምክንያት አለ ወይስ  የለም? እና ክሱ በመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ ሊደረግ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚሉ ጭብጦችን ብቻ ይዞ መዝገቡን መመርመሩን ባለፈው ሳምንት የሰጠው ፍርድ ያብራራል፡፡

መዝገቡን ለመመርመርም ፍርድ ቤቱ አቶ አብነትን ከማኅበሩ ሥራ አስኪያጅነት ለማንሳት ሥልጣን የለውም መባሉን በሚመለከት ለተነሳው ጥያቄ ከሳሽ በክሱ ውስጥ የጠቀሷቸው የገንዘብ መጠንና በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 ድንጋጌ መሠረት ሥልጣኑ አሥር ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ጉዳዮች ማየት መሆኑ እንደሚታወቅ ጠቁሞ፣ ነገር ግን የተጠቀሰው ገንዘብ አቶ አብነት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የሠሯቸውን ጥፋቶች የሚያሳይና ከሥራ አስኪያጅነት እንዲነሱ በመሆኑና ኃላፊነታቸው በገንዘብ የማይተመን በመሆኑ፣ ጉዳዩን (ክሱ)ን የማየት ሥልጣን እንዳለው ገልጾ የአቶ አብነትን መከራከሪያ ሐሳብ ውድቅ አድርጎታል፡፡

አቶ አብነት ማኅበሩን ሲመሩ ለሃያ ዓመታት ስብሰባ ጠርተውና ቃለ ጉባዔ ይዘው አያውቁም መባሉን በሚመለከት እራሳቸው ምስክርነት ተቆጥረው (በከሳሽ) በሰጡት ምስክርነት፣ ከሳሽ (ሼክ መሐመድ) ጊዜ ስላልነበራቸው ሁሉም ነገር በቃል ይሠራ እንደነበር ራሳቸው ማረጋገጣቸውን ፍርዱ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም ከሥራ አስኪያጅነት ሥልጣን ለመሻር በቂ ምክንያት መሆኑን ፍርዱ ይገልጻል፡፡ ፍርድ ቤቱ በ40 ገጽ የፍርድ ትንታኔው አቶ አብነት የማኅበሩን ሀብት በትክክል አለመመዝገባቸውና ሪፖርት አለማድረጋቸው፣ የሒሳብ መዝገቦች አለመኖር፣ ባለድርሻ ሆነው ሥራ አስኪያጅ መሆናቸው የጥቅም ግጭት መፍጠሩ፣ ከከሳሽ ጋር አለመግባባት መፈጠሩን፣ የማኅበሩን ሰነዶች በአግባቡ አለመያዛቸው፣ በሕጉ መሠረት ማኅበሩን በተገቢው ሁኔታ አለመምራታቸው፣ በገለልተኛ ኦዲተር ጥፋተኛ መሆናቸው መረጋገጡና ውክልናቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸውን በበቂ ሁኔታ ማረጋገጡን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ሰፋ ያለ ትንታኔ አብራርቶ አቶ አብነት ከሥራ አስኪያጅነታቸው እንዲነሱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ የማኅበሩ ዝርዝር የሒሳብ ሚዛን፣ የኦዲት ሪፖርትና ቃለ ጉባዔ ለከሳሽ እንዲሰጥ፣ የማኅበሩን ሒሳብ የሚመረምር ባለሙያ በሁለቱም አቅራቢነት እንዲሾም ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ አቶ አብነት የተጣለባቸውን 2,000 ብር ቅጣት እንዲከፍሉም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...