Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየዓለም እግር ኳስ ኮኮቡን ከተስፈኛው ኮኮብ ተጫዋች ያፋጠጠው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ

የዓለም እግር ኳስ ኮኮቡን ከተስፈኛው ኮኮብ ተጫዋች ያፋጠጠው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ

ቀን:

በዓረቡ አገር ለመጀመርያ ጊዜ የተሰናዳው የኳታር ዓለም ዋንጫ በርትቶበት በነበረው የምዕራቡ ዓለም ጫና መዝለቁ አጠራጣሪ ሆኖ ነበር፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎች በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ትችት አዘል መረጃዎች ሲናፈሱበት የከረመው የኳታር ዓለም ዋንጫ የአንድ ወር ውድድር ሳምንት ይመስል፣ ደምቆና በማይገመቱ ውጤቶች ታጅቦ ፍጻሜው ላይ ደርሷል፡፡ ለዋንጫ ሲታጩ የከረሙ ብሔራዊ ቡድኖች ከምድባቸው ማለፍ ተስኗቸው ወደየቤታቸው ሲመለሱ፣ ግምት ያልተሰጣቸው ቡድኖች ግማሽ ፍጻሜ ደርሰው በርካቶችን ያስደመሙበት የዓለም ዋንጫ ፍጻሜው ላይ ደርሷል፡፡

ከአምስት ቢሊዮን ተመልካች በላይ በቴሌቪዥን መስኮት እንደተመለከተው የተነገረለት የ2022 የዓለም ዋንጫ፣ በሕፃናትና አዋቂ ሳይቀር ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ ዓለም ዋንጫው መሽቶ ሲነጋ በሁሉም ዘንድ መነጋገሪያ ርዕስ ከመሆንም አልፎ የማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት መወያያና የጨዋታ ድምቀት ሆኖ የከረመበት ነበር፡፡

በተለያዩ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ እግር ኳስ ግንዛቤው የሌላቸው ሁሉ ምሽት በተመለከቱት የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ሲከራከሩና የአድናቆት ቃላት ሲለወው መመልከት የተለመደ ነበር፡፡ ሠራተኞች በምሳ ሰዓት ላይ በሚያስቆጭ ትዕይንት ላይ ሲወያዩ መመልከት የዚህ ወር አባዜ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተለይ በአብዛኛው ሰው አፍ ላይ ሞሮኮና ሜሲ የሚሉ ስሞች አይታጡም ነበር፡፡ ምክንያቱም የዚህ ዓለም ዋንጫ ክስተቶች ሜሲና የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን መሆናቸው ነበር፡፡ የእነዚህ በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ የመቅረት ምስጢር የአርጀንቲናዊው ምትሃተኛ የ35 ዓመት ተጫዋች ድንቅ ብቃትና የሞሮኮ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ግማሽ ፍጻሜ መግባት ነበር።

የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ቁጥር ሁለት ደረጃ ላይ የተቀመጠችውን ቤልጂየም ከረታ በኋላ ካናዳን፣ ስፔንንና ፖርቱጋልን ከውድድር ውጪ በማድረግና የግማሽ ፍጻሜ በመግባት ለአፍሪካ ኩራት ከመሆኑ ባሻገር የዓለም ሕዝብን ጉድ ያሰኘ ክስተት መሆን ችሏል፡፡ ሆኖም የአትላስ አንበሶቹ ፍጻሜ ለመድረስ ከፈረንሣይ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ከጉዟቸው ተገተዋል፡፡

በዚህም የ2018 ሩሲያ ዓለም ዋንጫ አሸናፊ ፈረንሣይ ከአርጄንቲና ጋር ለፍጻሜ ተፋጣለች፡፡ የውድድሩ ሌላኛው ድምቀት የሆነው የአርጄንቲናው ሊዮኔሜሲ፣ አዲስ ተስፋ ከተጣለበት የፈረንሣዩ ኪሊያን ማፔ ጋር ተፋጠዋል፡፡ የፍጻሜ ጨዋታው ለሜሲ የመጨረሻ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ሲሆን፣ ለፈረንሣዩ ታዳጊ አዲስ የእግር ኳስ የስኬት መንገድ የሚከፍትለት አድርጎታል፡፡ በዚህም በርካታ ተመልካቾች የፈረንሣይ ብሔራዊ ቡድንን ቢደግፉም፣ ከሁለት አሠርታት በላይ የእግር ኳስ ድምቀት ለነበረው ሜሲ የመሰናበቻ ድል እንዲሆን ምኞታቸው እንደሚሆን ሲገልጹ እየተስተዋለ ነው፡፡

ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች አሰባስቦ  በዚህ ዓለም ዋንጫ የቀረበው የፈረንሣይ ብሔራዊ ቡድን የማሸነፍ ከፍተኛ ግምት ቢሰጠውም፣ በአንፃሩ የሜሲ ድንቅ ብቃት ሰማያዊዎቹን ሳያሳስባቸው እንዳልቀረ እየተነገረ ይገኛል፡፡ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በምድቡ የመጀመርያ ጨዋታ በሳዑዲ ዓረቢያ አስደንጋጭ ሽንፈት ከገጠመው በኋላ፣ በውድድሩ መዝለቁ አጠራጣሪ ሆኖ ቢቆይም፣  ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ መጥቶ፣ ለፍጻሜ መድረስ ችሏል፡፡

የዓለም ዋንጫው የመጨረሻ የብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ እንደሆነ የገለጸው የሰባት ጊዜ የባልንዶር ሽልማት አሸናፊው ሜሲ፣ የፍጻሜ ጨዋታው የመሰናበቻ ድል እንዲሆንና ለአገሩም የዓለም ዋንጫን ማሳካት እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1930 ጀምሮ በዓለም ዋንጫው መሳተፍ የጀመረው የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን 18 ጊዜ ተካፍሎ፣ በ1978 እና በ1986 የዓለም ዋንጫን ማሳካት ችሏል፡፡ በእግር ኳስ ወዳጅነታቸው በቀዳሚነት ስማቸው የሚነሳውና በስታዲየሞች የማይታጡት የአርጀንቲና ደጋፊዎች፣ የቀድሞ እግር ኳስ ንጉሣቸውን የዲያጎ አርማንዶ ማራዶና የ1986 የሜክሲኮ ዓለም ዋንጫ ስኬት ሜሲም በኳታር እንዲደግም የሜሲን ስም እያነሱ ሲያወድሱት ነበር፡፡

ሜሲ በኳታር ዓለም ዋንጫ ለአገሩ እያደረገ የሚገኘውን ተጋድሎ የተመለከቱ በርካታ እግር ኳስ አፍቃሪያን ‹‹ማራዶና በሕይወት ኖሮ ይህቺን ቀን ተመልክቶ ቢሞትም አይቆጨውም፤›› በማለት ያወደሱም አልታጡም፡፡

አስተያየቱን ከተመልካች የሰሙ ጋዜጠኞችም ጥያቄውን ለሜሲ ያነሱለት ሲሆን ‹‹ማራዶን ሁሉንም ከላይ እንደሚመለከተው እምነት አለኝ›› ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ለአርጀንቲና ዋናው ብሔራዊ ቡድን ከ2004 ጀምሮ መካፈል የጀመረው ሜሲ በ171 ጨዋታዎች ላይ ተሠልፎ 96 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል፡፡ የ2021 የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ማንሳት የቻለው ሜሲ፣ የዓለም ዋንጫን ስኬት ለማረጋገጥና አዲስ ታሪክ ለመጻፍ 90 ደቂቃዎች ብቻ ይቀሩታል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1930 ጀምሮ መሳተፍ የጀመረው የፈረንሣይ ብሔራዊ ቡድን በ1998 እና 2018 የዓለም ዋንጫን ማንሳት ችለዋል፡፡ ከ2017 ጀምሮ ለብሔራዊ ቡድን መሠለፍ የቻለው የ23 ዓመቱ ኪሊያን ማፔ 63 ጨዋታዎችን አድርጎ፣ 33 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡ የወደፊቱ የዘመኑ ምርጥ ተጨዋች እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት ማፔ፣ በ2018 ዓለም ዋንጫ ማንሳት የቻለ ወጣት ተጫዋች ነው፡፡

ዛሬ እሑድ ታኅሣሥ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በኳታር ፍጻሜውን የሚያገኘው የዘንድሮ ዓለም ዋንጫ፣ ለመጨረሻ ጊዜ ለሚሰናበተው ሜሲ ወይስ  ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ለማንሳት ከጫፍ ለደረሰው ማፔ ለማን ይሳካል? የሚለው ጥያቄ በቢሊዮኖች ይጠበቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...