Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

እኔም ሆንኩ በአካባቢዬ ያሉ የቅርብ ሰዎቼ (ወንድም እህቶቼ፣ ዘመዶቼ፣ ጓደኞቼና የሥራ ባልደረቦቼ) እዚህች አገር ውስጥ እየተከናወኑ ባሉ በርካታ ጉዳዮች እየተገረምን፣ እየተናደድን፣ እየተቆጨን አገራችን ናትና ተስፋ ሳንቆርጥ ነገን እያሰብን ብዙ ነገሮችን እንነጋገራለን፡፡ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው እንደ ጠላት በማንነታቸው ምክንያት ሲጨፈጨፉ፣ ለዓመታት ከኖሩበት ቀዬአቸው ንብረታቸው ተዘርፎ ሲፈናቀሉና እንደ ቆሻሻ ሜዳ ላይ ሲጣሉ በተደጋጋሚ አንብተናል፡፡

አገራቸውን በዓለም አደባባይ አንገቷን ቀና የሚያደርጉ ብርቅዬ አትሌቶቻችን ሰንደቋን ከፍ ሲያደርጉ በደስታ ጨፍረናል፡፡ ወገኖቻችን በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ለችግር ሲጋለጡ ያለንን ለማካፈል ጥረት አድርገናል፡፡ በብዙ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚበጁ ምክረ ሐሳቦችን በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ለማድረስ ሞክረናል፡፡ ጠቃሚ የመሰሉንን የሌሎች ሐሳቦችም በማጋራት ተባብረናል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ለአገራችን ይህንን አደረግን ብለን እንኳንስ ለማስተጋባት ለማሰብም አልደፈርንም፡፡

‹‹አገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ከማለት ይልቅ እኔ ምን አደረግኩላት›› የሚለው አባባል በጣም አስደሳችና ተደጋግሞ መባል ያለበት ቢሆንም፣ በአሁኑ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግን ማስተካከያ የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ አገራቸውን በመምህርነት፣ በጤና ባለሙያነት፣ በውትድርና፣ በምህንድስና፣ በታሪክ ተመራማሪነትና በሌሎች በርካታ መስኮች ያገለገሉ ወገኖች እንደ አልባሌ ዕቃ ተጥለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንኳንስ ውለታ ለመክፈል ለምክር የሚፈልጋቸው ባለመኖሩ ብዙዎቹ በከፋ ድህነት ውስጥ ሆነው ተስፋ ቆርጠው መጨረሻቸውን ይጠባበቃሉ፡፡ የረባ ጡረታ ሳያገኙና የተደላደለ መኖሪያ ሳይኖራቸው ለሌሎች ጥገኝነት የተዳረጉም ብዙ ናቸው፡፡ የባሰባቸው ደግሞ ጎዳና ላይ ወድቀው በዚያው ሲቀሩ፣ ዕድሜ ለመቄዶንያ ጊዜያዊ ዕፎይታ ያገኙም መኖራቸው አይዘነጋም፡፡

የዘመኑ ሹማምንት ነገ ወደ ጡረታ የሚሸኙ ስለማይመስላቸው ነው መሰል ስለጡረተኞች ማሰብ አይፈልጉም፡፡ የጡረታ ፈንድ አትራፊ ኢንቨስትመንቶች ላይ ውሎ ለተጧሪዎች የበለጠ ገቢ እንዲጨምር ማድረግ ሲገባ፣ ስለዚህ ጉዳይ ማንሳት የሚፈልግ ማንም የለም፡፡

አንዲት ወይዘሮ በቅርቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲያጫውቱኝ፣ “ከድሮ ጀምሮ ጡረተኛ አገሩን እንዳገለገለ ሰው ሳይሆን የሚቆጠረው እንደ ሸክም ነው…” ብለውኝ ነበር፡፡ አገሩን አገልግሎ በክብር ወደ ጡረታ መሸኘት ያለበት ዜጋ፣ ወደ መቃብሩ የሚሸኝ ይመስል ከንፈራቸውን እየመጠጡ የሚሰናበቱ ሰዎች ራሳቸው ለራሳቸው የሚያስቡ አይመስልም፡፡ አጠቃላይ ሁኔታችን ሲታይ አስመሳይነት ተፀናውቶናል፡፡

ባለፈው ሳምንት ያ በሠራቸው ደስ የሚሉ የተለያዩ ፊልሞቹ ገፀ ባህርያት ከመጠን በላይ የምንወደው ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ)፣ ድንገተኛ ሕልፈቱ ከተሰማ በኋላ የፈጠረብን ድንጋጤ ሳያልፍልን፣ እንደ ሥራውና ስሙ ያልሆነው አሟሟቱ ያስከተለብን የልብ ስብራት መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም፡፡ ‹‹ተቀጣሪ የባጃጅ ሹፌር በቀን 500 ብር ዕቁብ የሚጥልበት አገር ላይ 46 ፊልም ላይ የተሳተፈ፣ የሚያምር፣ ደስ የሚል ታዋቂ ፊልም አክተር እንዴት ብሎ ነው ተቸግሮ፣ እናቱ ቤት ገብቶ፣ የመታከሚያ አጥቶ፣ በሰው ተረድቶ የሚሞተው?›› በማለት አንድ ልባም ሰው በፌስቡክ ገጹ ላይ ያሠፈረውን ካየሁ በኋላ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡

ስንቶች ሳይሠሩ በዝርፊያ በሚከብሩባት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን ኢፍትሐዊነት ሳይ ተስፋ እቆርጣለሁ፡፡ በብሔርና በጥቅም እየተቧደኑ በሚዘርፉት ሀብት በምስኪኖች ላይ የኑሮ ውድነት እሳት በሚያነዱባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ታሪኩ ባባ ተቸግሮ አለፈ ሲባል ልብ ይሰብራል፡፡

ሌላው የሚያናድደኝ ደግሞ ባለሀብትና ባለሥልጣን ጉያ ውስጥ ሆነው እንዳሻቸው የሚፈነጩ ወንበዴዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ‹‹የሹም ዶሮዎች›› ተቆጪና ገላማጭ ስለሌለባቸው ማንንም ሲዘልፉና ሲያዋርዱ ጠያቂ የላቸውም፡፡ ጊዜው ተመቸን ብለው ያገኙት ላይ አፋቸውን ከሚከፍቱት መሀል ተምረን አስተምረናል የሚሉ ጭምር ስላሉበት፣ ይህች ምስኪን አገር ስንቱን ተሸክማዋለች ያስብላል፡፡

ከጫትና ከአረቄ ግሳታቸው ጋር አደባባይ እየወጡ ሰውን ማዋረድ ለጊዜው በቀጣሪዎቻቸው ምክንያት ባያስጠይቃቸውም፣ ይዋል ይደር እንጂ ነገ ተነገ ወዲያ ተጠያቂነት እንዳለባቸው ቢገነዘቡት መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ያሉበት የጥጋብ ደረጃና የተለከፉበት ሱስ ይህንን አያሳስባቸውም፡፡ ለዚህም ነበር አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነባር መምህር፣ ‹‹ጉድጓድ ውስጥ ያለች እንቁራሪት ከጉድጓዱ ውጪ ሌላ ዓለም ያለ ስለማይመስላት የሚመጣውን አደጋ ማየት አትችልም…›› ይሉን የነበሩት፡፡ አፈሩን ገለባ ያድረግላቸውና፡፡

ለአገር ማሰብ በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡ ለአገር የሚያስቡ እያነሱ አጥፊዎች ሲበዙ ደግሞ የዋህነት አያስፈልግም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ አገሬ ሞኘ ነሽ ተላላ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ›› የሚለውን የዮፍታሔ ንጉሤ የቁጭት ግጥም እያስታወሱ መብሰልሰል ተገቢ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሰው በለፋበት መጠን መብቱን ማስከበር አለበት፡፡

ጡረተኛው ባለመብት እንጂ ሸክም አይደለም፡፡ ለፍቶ ታክሞ መዳን ሲገባው የሰው ጥገኛ ሆኖ ማንም እንደ ቀልድ መሞት የለበትም፡፡ ሒዩማን ሔር በመቶ ሺሕ ብር እየተገዛ ስጦታ የሚሰጥበት አገር ውስጥ፣ የመቶ ብር መድኃኒት አጥቶ መሰቃየት ልክ አይደለም፡፡ አገሩን በክብር የሚያገለግል በማንም ባለጌ ሲሰደብ ዝም ማለት መቆም አለበት፡፡ ባለጌ ከእነ ነውሩ ልኩን የሚያውቅበት ሕግ ሊኖር የግድ ነው፡፡ አገር የሁሉም ዜጎቿ የጋራ ቤት መሆን የምትችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

(ዘውዱ ተጫኔ፣ ከባልደራስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...