Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉመሬትን የግል?

መሬትን የግል?

ቀን:

በአንዳርጋቸው አሰግድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም. በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የከተማ መሬትን ወደ ግል ይዞታ ስለማዞር አስፈላጊነት ጣል አደረጉ። መግለጫቸው አንደተጠበቀው መሬት የግል ይዞታ መሆን እንዳለበት ሲሞግቱ በኖሩት ወገኖች ዘንድ፣ ‹‹የመሬት ሥሪቱን ለመቀየር እንደ አንድ አመቺ አጋጣሚ ተቆጠረ። የመሬት ፖሊሲው የዜጎችን የመሬት ባለቤትነት የነፈገ ብቻ ሳይሆን፣ መሬት የሀብት ምንጭ እንዳይሆን አግቶ የያዘ ነው የሚለውን ትችት መንግሥትም እየተጋራው ያለ ይመስላል፤›› እያሉ ጭምር ወደ መጻጻፍ ተሻገሩ (ሪፖርተር ኅዳር 18 ቀን 2015 ዓ.ም.) መጣጥፎች ይቀጥላሉ። የውይይት መድረኮች ይከታተላሉ። በምርጫው ዘመን መሬትን የግል ይዞታ የማድረግ ዕቅዳቸውን ሲያሳውቁ የነበሩ አንዳንድ ፓርቲዎችና ግለሰቦችም ይነቃቃሉ። ‹‹መሬትን የግል›› ሰሞነኛ ሆኖ ይዘመራል። የድኅረ 2010 ዓ.ም. መስተዳድር የሚያዘወትረው የማስታወቂያ አካሄድ/ሒደት ነው ቢባልም ያስኬዳል።

አንድ የሆነ ቀን ያንና ይህንን የመንግሥት ይዞታ (ብሔራዊ ሀብት) ለመሸጥ እንደተወሰነ፣ ወይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አለዚያም በአንዱ ባለሥልጣን በድንገት ይገለጻል። ያንና ይህንን የኢኮኖሚ መስክ ለውጭ ባለሀብቶች ለመክፈት እንደተወሰነ፣ እንደዚሁ በአንድ የሆነ ቀን በድንገት ይነገራል፡፡ ስለኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደተሰማውም፣ አንድ የሆነ ቀን የመሸጡ ውሳኔ እንደተሰረዘ ይነገራል። ተላልፎ የነበረው የኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭም እንደገና እንደተቀሰቀሰ ይገለጻል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ወዲያውኑ ለማለት ይቻላል ባለሥልጣናትና ዕውቅ ተወያዮች በየወግ መድረኩ ይታደማሉ። የቴሌቪዥን መድረኮችን ይጨብጣሉ። የውሳኔውን አግባብነትና አገራዊ ጥቅም ያብራራሉ። አድማጩ እንኳን ለውሳኔ ያስደረሱትን ጭብጥ ምክንያቶች ቀርቶ ውሳኔዎቹ በድንገት የተነገሩበትን ምክንያት ባለማወቁ ግር ይሰኛል። አንዳንዱም አነሰ ቢባል ከየመስኩ ባለሙያዎችና ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ ድርጅቶች ጋር የቅድሚያ ምክክር የማይደረግበት ምክንያት ምንድነው? እያሉ ይጠይቃል። ሌላውም የአገር ሀብትን ሽያጭና የአገርን ኢኮኖሚ ለውጭ ባለሀብቶች የመክፈትን በሚያህል ጉዳይ ላይ የተወካዮች ምክር ቤት የማይመክርበትን ምክንያት ይጠይቃል። ደግሞም ሌላው ስለአገራዊ ምክክር ስንት በሚነገርባት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔራዊ ሀብቶችን ሽያጭ የሚያህል ብሔራዊ ጉዳይ የአገራዊ ምክክሩ ርዕስ የማይሆንበትን ምክንያት ያጠያይቃል።

በተዘወተረው አካሄድ በመቀጠል ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኅዳር 6 ለምክር ቤቱ በሰጡት መግለጫ፣ የጫካ ቤት የተባለ መንደር እየተገነባ እንደሆነ አሳወቁ፡፡ ዋጋው እንደሚወራው 49 ቢሊዮን ብር ሳይሆን 500 ቢሊዮን ብር (9.4 ቢሊዮን ዶላር) እንደሚደርስ ገለጹ። ገንዘቡ ከየትና ከየትኛው ምንጭና በምን ሁኔታ እንደተገኝ አልተገለጸም። የተወካዮች ምክር ቤትም ‹‹ያላፀደቅከው ገንዘብ አይመለከትህም›› ስለተባለ ይሆናል አልጠየቀም። ቀደም ሲል በጥቅምት 2011 ዓ.ም. አንድ ኤግል ሒልስ የተባለ የዱባይ ኩባንያ በአዲስ አበባ ውስጥ የ50 ቢሊዮን ብር (935 ሚሊዮን ዶላር) ግንባታ እንደሚያካሄድ ተገልጾ ነበር፡፡ 27 በመቶውም (13 ቢሊዮን አምስት መቶ ሺሕ ብር/254 ሚሊዮን ዶላር) በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚሸፈን ተነግሮ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በኅዳር 6 የከተማ መሬትን ወደ ግል ንብረት ማዞር ያስፈልግ እንደሆን ለምክር ቤቱ ሲያመለክቱ፣ ‹‹መሬት የደላላና የሌቦች ሆኖ እንዳበቃም›› በምሬት ገልጸው ነበር። ገለጻቸው ነባራዊውን ሀቅ ያመለከተ ቢሆንም ቅሉ ግን ‹‹ደላሎችና ሌቦች ቀይ ምንጣፋቸውን ዘርግተው›› በሚወሩት መሬትና መሬትን ወደ ግል ይዞታ በማዞር መካከል ያለውን አመክንዮ ለመረዳት አስቸጋሪ ሆነ። ለአሁኑ ለማለት የሚቻለው ‹‹ደላሎቹና ሌቦቹ›› በየከተማው አስፋፍተው የሚዘረጉትን ‹‹የሙስና ቀይ ምንጣፍ›› በኅዳር 8 የተቋቋመው ‹‹የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ›› ያጥፈው እንደሆነ ወደፊት ይታያል ብቻ ነው፡፡ ኮሚቴው የፀረ ሙስና ኮሚሽን ያልነበረውን የመክሰሰ መብት እንደሚኖረው ተሰምቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹አንድ ቁጥር ሙሰኛ›› ያሉት የኢትዮጵያ ፍትሕ ሥርዓት ኃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣ እንደሆን ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

እዚሁ ላይ በተጨማሪ ለማስታወስ ያህል ግን የከተማ መሬት ወደ ግል ይዞታ በመዞሩ ምክንያት፣ ከቀድሞ ባለንብረቶች እስከ ሊዝ ባለቤቶችና ወራሪ ‹‹ባለቤቶች›› ድረስ ሊከተል የሚችለው የይገባኛል ትርምስ በዝርዝር ታስቦበት እንደሆነ አልተገለጸም። እንዲሁም በከተሞች ውስጥ ከመኖሪያ ቤቶች እስከ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ከመንገዶች እስከ አደባባዮች፣ ከፓርኮች እስከ ስፖርት ሜዳዎች፣ ከመጻሕፍት አዳራሽ እስከ ሙዚየሞች፣ ከትምህርት ቤቶች እስከ የጤና ጣቢያዎች፣ ከእሑድ ገበያ እስከ የማዕድ ማጋሪያ አዳራሾች ወዘተ ድረስ በመንግሥትና በማዘጋጃ ቤቶች ይገነባሉ። የከተማ መሬት የግል ይዞታ ሲሆን፣ ገንቢዎቹ መሬትንም ለመግዛት መገደዳቸው የማይቀር ይሆናል። የግንባታ ወጪ በስንት እጥፍ እንደሚያደግ ተሰልቶ እንደሆነ አልተገለጸም።

ለማንኛውም ለጥያቄዎቹ ጭብጥ መልስ እስኪሰጥ ድረስ መጠበቁ የተሻለ ነው፡፡ የኢትዮጵያን አርሶና አርብቶ አደሮች የመሬት ይዞታ በሚመለከተው ግን፣ ከሁሉም ነገር በፊት አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን ወደ አዕምሮ መጥራት ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። በቅድሚያ ስለውስጣዊውና ውጫዊው ሁኔታ።

ውስጣዊው ሁኔታ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የባንኩን መስክ ለውጭ ባለሀብቶች ለመክፈት እንደወሰነ በድንገት ተነገረ። እንዲሁም ከሳፋሪኮም በተጨማሪ ሌሎች ሁለት የቴሌ አገልግሎት አቅራቢዎች ኢትዮ ቴሌኮምን ለመወዳዳር እንደሚገቡ ተገለጸ። ደግሞም 40 በመቶ የሚያክለውን የኢትዮ ቴሌኮም ንብረት ለውጭ ባለሀብት ለመሸጥ እንደተወሰነ ተሰማ፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የግል ባንኮች ሥራ አስኪያጆችና በርካታ የመስኩ ባለሙያዎች፣ በውሳኔው ምንነትና አዋጭነት ላይ በርካታ ውይይቶችን አካሄዱ። ‹‹ውሳኔው የተደረገው ኢትዮጵያ ባልተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ ባለችበት፣ የዋጋ ንረት ገዝፎ በሚታይበትና በጦርነት ውስጥ በምትገኝበት ወቅት በመሆኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ጎረቤታችን ኬንያ ቀደም ሲል ባልተረጋጋ ኢኮኖሚ ውስጥ ሆና የውጭ ባንኮችን በማስገባቷ ከ30 ያላነሱ የግል ባንኮቿ ከገበያ ውጪ ሆነውባታል፤›› እያሉ ውሳኔው ወቅታዊ አለመሆኑን አጠንክርው አመለከቱ፣ አሳሰቡ፡፡ አድማጭ ስለማግኘታቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

በእኔ ዕይታ አንደኛ የአኮኖሚ ባለሙያዎቹ በገለጹት የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ብቻ እንኳን፣ መሬትን ወደ ግል የማዞር ጉዳይ ለመስተዳደራዊ ውሳኔ የሚቀርብበት ወቅት አይደለም፡፡ ሁለተኛ የሰሜኑ ሁኔታ ወደ በጎ ያቀና ቢመስልም ገና ረዥም መንገድ እንዳለ ከአሁኑ በግልጽ እየተሰማ ነው፡፡ የሕወሓት ጦር አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ለምሳሌ፣ ‹‹ትጥቅ የመፍታቱ ጉዳይ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ሊወስድ እንደሚችል›› አመልክተዋል።

የጄኔራሉን መግለጫ ምንነት ለመረዳት ከሩቅ መፈለግ አያስፈልግም፡፡ የሕወሓት አመራር ‹‹የኤርትራ ሠራዊትና የአማራ ሚሊሺያ ከክልሌ ይውጡ›› እያለ በተደጋጋሚ እየጠየቀ ነው። የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ስለመገኘቱ ተቃራኒ ዜናዎች ስለሚሰሙ አስተያየት ከመስጠት እቆጠባለሁ። ‹‹የአማራ ሚሊሺያ ከክልሌ ይውጣ›› የሚለው ጥያቄ፣ ‹ከወልቃይትና ከራያ ክልሌ ይውጣ› ማለት እንደሆነ ግን ግልጽ ይመስለኛል። ጥያቄው ውሎ አድሮ፣ ‹የአማራ ሚሊሺያ ከክልሌ እስካልወጣ ድረስ ትጥቅ አልፈታም› ወደ የሚል ቅድመ ሁኔታ ይለወጥ/አይለወጥ እንደሆን በቅርብ ይታያል።

ይህ በዚህ ቢሆን ሦስተኛ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠር አርሶና አርብቶ አደር ሕዝቧ በአንድ ወገን፣ በክልሎች መካከል በሚነሱ የወሰን ግጭቶችና በሌላውም ወገን በተፈጥሮ ማምረር ምክንያት ከየቄየው ተፈናቅሎና ተሰዶ የሚገኝባት አገር ነች።  መሬት በዚህ ሁኔታ ወደ ግል ይዞታ እንዲዛወር መሞገት፣ የተፈናቀለው ሕዝብ በየቀዬው የሌለበትን ሁኔታ ተጠቅሞ መሬትን ወደ ግል ይዞታ ለማዞር የመነሳሳት ያህል አይሆንም ወይ? አራተኛ በዓብይ (ዶ/ር) ገለጻ መሠረት የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በመሬት ደላሎችና ሌቦች የተወረረች አገር ሆናለች። የየክልሉ የብሔር ድርጅቶች ካድሬዎች በመሬት ሽያጭ ተሰማርተው የሚከብሩባት አገር ሆናለች። እንዲሁም ራሳቸውን ‹‹ነፃ አውጭ›› ብለው የሰየሙ ቡድኖች በክልል መስተዳድር ተቀጣሪዎች እየታገዙ ጭምር ከወለጋ እስከ ሐረር፣ ከሸዋ እስከ ባሌ ገበሬዎችን በግፍና በገፍ የሚያፈናቅሉበት አገር ሆናለች። የጅምላ ግድያ፣ የንብረት ውድመትና ዕገታ ዕለታዊ ወደ መሆን ያቀኑባት አገር ሆናለች። ስለአንዳንድ ክልሎች እንደሚሰማው ደግሞ የአስተዳደር ባለሥልጣናት፣ ተቀጣሪዎች፣ የክልል ልዩ ፖሊሶችና ሚሊሺያዎች ከታጠቁ ቡድኖች ጋር እያበሩ ጭምር ናቸው።

መሬት በዚህ ሁኔታ ወደ ግል ይዞታ እንዲዛወር መሞገት፣ በአገሪቱ የተዘረጋው የደላሎችና የሌቦች ነገረ ሥራ ተስፋፍቶ እንዲደራ የማመቻቸት ያህል አይሆንም ወይ? በማንነት ላይ ጭምር የሚፈጸመውን ግፍ መስፋፋት መጋበዝ አይሆንም ወይ? በ1983 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት የለውጥ መሐንዲስ የነበረው ሔርማን ኮኸን ዛሬ ዛሬ ደግሞ የኦሮሞ/አማራን መጋጨት ወደ መቆስቆስ ተሻግሮ እየተደመጠ ነው። ሔርማን ኮኸን በጳጉሜን 2 ቀን 2014 ዓ.ም. (07/09/2022) በሰደደው ትዊት ለምሳሌ፣ ‹‹የኦሮሞ ብሔር ለብዙ ትውልድ ከፖለቲካ ሥልጣን ተገልሎ ነበር፡፡ አሁን በከፍተኛ ደረጃ የታጠቀው የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር የአሮሞን ድምፅ መሰማት ያረጋግጣል፤›› እስከማለት ድረስ ሄዶ ተነቧል። በሔርማን ኮኸን ቢበረታቱ ይሆናል አንዳንድ የኦሮሞ መገናኛ ዘዴዎችና የአንዳንድ የኦሮሞ ድርጅት ተዋናዮችም ስለማይቀረው የኦሮሞ/አማራ መተላለቅ እያራገቡ ናቸው። አንዳንዶቹም ለዳግማዊ ፕሪቶሪያ በመዳዳት ዓይነት፣ ‹‹በመንግሥትና ኦነግ ሸኔ በሚባለው መካከል ድርድር እንዲደረግ እየጠሩ ናቸው፡፡ የሕወሓት አመራርን አካሄድ በመከተልም ይመስላል፣ ‹‹የአማራ ሚሊሺያ ከኦሮሚያ ይውጣ›› እያሉም ናቸው።

አቶ ጌታቸው ረዳ ኅዳር 28 ቀን በሰደደው ትዊት፣ ‹‹በምዕራብ ወለጋ ዛሬ የሚካሄደው በትግራይ ሲፈጸም የነበረው ድጋሚ ነው፤›› እስከ ማለት ሄዶ አተተ። የአንዳንድ የኦሮሞ ተዋናዮችን ጥሪ እንደ ማስተጋባት ብሎም፣ ‹‹በመንግሥትና በኦነግ መካከል ውይይት እንዲደረግ›› ጠራ። በዚሁ ሰሞን በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁከቶች ተቀሰቀሱ። የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ትምህርት ቤቶችን የሁከት ማዕከል ለማድረግ የሚንቀሳቀስ የተደራጀ ቡድን እንዳለ›› ገለጸ። ‹‹የተደራጀው (ጁት) ቡድን (ኖች)›› ምንነትና ምንነት ግን አልተገለጸም። ጄኔራል ታደሰ ወረደ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በፊት፣ ‹‹የኦነግ ሠራዊት ትልልቅ ከተሞችን ለመቆጣጠር ከሚያስችለው ደረጃ ላይ ደርሷል፤›› ብሎ እንደነበር ሲታወስ፣ ነገሮች ወዴት እያመሩ እንደሆነ ለማስተዋል የሚከብድ ሊሆን አይችልም።

ይህ ሁኔታ አንዳች መሠረታዊና የማያዳግም መፍትሔ እስካላገኘ ድረስ፣ መሬትን ወደ ግል ይዞታ ስለማዞር መሞገት ጋሪውን ከፈረሱ ማስቀደም አይሆንም ወይ? ወቅታዊው ውስጣዊ ሁኔታ በአጭሩ እንደተመለከተው ሲሆን፣ የወቅቱ ውጫዊ ሁኔታ አጠቃላይ ዳሰሳም፣ መሬት የግል ይዞታ ካልሆነ የሚያሰኝ ወቅት ሆኖ አይገኝም፡፡

ውጫዊው ሁኔታ

ወቅታዊው ውጫዊ ሁኔታ በአንድ ወገን የአሜሪካ አስተዳደርና የምዕራቡ ዓለም አጋሮቹ፣ ከሕወሓት አመራር ጋር በአንድ ቃል እየተናገሩ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ስለኤርትራ ሠራዊትና ስለአማራ ሚሊሺያ ከትግራይ መውጣት እየጎተጎቱ ናቸው። ሱዳን ከኢትዮጵያ ግዛት ትውጣ ብለው ግን አያውቁም። በሌላው ወገን የአስተዳደሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከንና አንዳንድ የኮንግረስ አባላቱ፣ ‹የፕሪቶሪያው ስምምነት በኢትዮጵያ መስተዳድር ካልተፈጸመ›› የዕቀባ በትራቸውን እንደሚጥሉ እያስታወቁ ናቸው፡፡ በሕወሓት ካልተፈጸመ የሚል ቃል ግን ወጥቷቸው አያውቅም፡፡ ይህ የአሜሪካ አስተዳደር አካሄድ፣ የአሜሪካ አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ያንንና ይህንን ያህል የሚጨክንበት ምክንያት ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ መጫሩ የግድ ነው። 

የአሜሪካ አስተዳደር የአፍሪካ ቀንድ ፖሊሲ ከሁሉም በፊት የሚገዛው ለጂኦ ፖለቲካ የበላይነት ባለው ግቡ ነው፡፡ በዛሬው ጊዜ በተለይም ቻይናንና ሩሲያን፣ ህንድንና ቱርክን ከአፍሪካ ቀንድ ማፈናቀል ለሚለው አቃፊ ግቡ የሚገዛ ነው፡፡ ለአስተዳደሩና ግብፅን ለመሳሰሉት አጋሮቹ ለዚህ ግብ የምትመቸው የተከፋፈለችና የተዳከመች ኢትዮጵያ ናት፡፡ የተከፋፈለና የተዳከመ የአፍሪካ ቀንድ ነው፡፡ ከግባቸው ለመድረስ በተግባር የሚያውሉትን ስትራቴጂ ለማንበብ ብዙ መድከም አያስፈልግም፡፡

አንደኛው ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ብሔሮች አብሮነት የሚፃረርን ማንኛውንም የውስጥና የውጭ ኃይል በተለያዩ መንገዶች በማገዝና በማበረታት ኢትዮጵያን ማዳከም ነው፡፡ የእስካሁኑ እስከ ፕሪቶሪያው ስምምነት ድረስ የዘለቀው ነበር፡፡ የአሁኑ በሔርማን ኮኸን በግልጽ እንደተነገረው ማብቂያው የማይታወቀውን የኦሮሞ/አማራ ጦርነት፣ ዕልቂትና ውድመት መቆስቆስ ነው፡፡ ሥሌቱ ግልጽ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሰባ ከመቶ የሚሆኑት ኦሮሞና አማራ ናቸው፡፡ እነሱ በአንድ ከቆሙ ኢትዮጵያን የመከፋፈልና የማዳከም ስትራቴጂ አይሠራም፡፡ ስለዚህም እነሱን ማቆራቆዝ ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱ የተጠፋፉትንና የተዳከሙትን ያህል ኢትዮጵያ ትዳከማለች፡፡ በተዳከመች ኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ የአፍሪካ ቀንድን በቁጥጥር ሥር የማዋል ጂኦ ፖለቲካ ግብ ይሳካል።

ሁለተኛው ስትራቴጂ ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ጥያቄ ከግብፅ ጋር አንዳች ዓይነት አሳሪ ስምምነት ውስጥ እንድትገባ የማድረግ ነው፡፡ ይህ ስትራቴጂ የተሳካውን ያህል ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚኖራት የበላይነት ይፀናል። ሦስተኛው ስትራቴጂ በኢትዮጵያና በኤርትራ መስተዳድሮች መካከል የተጀመረውን ግንኙነት ለመበጠስ ማንኛውንም ጫና ማሳረፍ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አራተኛው ስትራቴጂ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ለጋራ ህልውናቸው የሚያደርጉትን ስትራቴጂካዊ ትብብር ጥረት ማፋለስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ በምትገኝበት በዚህ ውስብስብ ውጫዊ ሁኔታ ላይ መሬት የግል ይዞታ እንዲሆን መሞገት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍን የመጥራት ያህል አይሆንም ወይ?

ማጠቃለያ

ስለመሬት ይዞታ በርካታ ጥናቶችን በማድረግ የሚታወቁት  ደሳለኝ ራህማቶ (ዶ/ር)፣ ‹‹የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬታቸውን ለመሸጥ ዕድሉ ቢሰጣቸው እንኳን የመሸጥ ፍላጎት እንደሌላቸው›› በአንድ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማኅበር ጥናት እንደተረጋገጠ ጠቅሰዋል (Searching Tenure Insecurity the Land System and New Policy Initiatives in Ethiopia; FSS Discussion Paper 2000)። ይሁን እንጂ ዛሬ ዛሬ ደግሞ እንደ አበባው አያሌው (ዶ/ር) አንዳንዶች ‹‹ዜጎች›› የሚሏቸውን ባያብራሩም፣ የ1967 ዓ.ም. የገጠር መሬት አዋጅ ‹‹የዜጎችን የመሬት ባለቤትነት የነፈገ›› እስከማለት ድረስ ሄደው፣ መሬት የግል ይዞት መሆን እንዳለበት እየሞገቱ ናቸው (የተጠቀሰው ሪፖርተር)፡፡  በተለይም የምርጫን ሰሞን እየጠበቁ የሚንቀሳቀሱት የአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፅ መሰማቱም የማይቀር ይሆናል። 

ሞጋቾቹ ይሁንና የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደር ‹‹ዜጎች›› መሬታችን የሚሸጥ የሚለውጥ ሸቀጥ ይደረግልን እያሉ መችና የት እንደጠየቁ አያሳውቁም። መችና የት ነው መሬታችን ካልተሸጠ/ካልተለወጠ እያሉ ለአቤቱታ የወጡት? የታገሉት? መቼና የት በተደረገ ጥናት ነው አዎንታዊ መልሳቸው የተረጋገጠው?

የነጋ፣ የአድነውና የገብረ ሥላሴ የ2021 (2013) ሰፊ ጥናት እንዳመለከተው፣ ‹‹Farmers preferred alternative choice of land tenure system has revealed that the issue of tenure security is a more important consideration than the particular form of ownership. The results clearly show that farmers seem to have a more pragmatic approach than those involved in the debate. Most farmers are not keen on unrestricted freehold, as indicated by the large support for state ownership with secured rights as their first choice. Neither do they seem to be willing to sacrifice security of tenure when they feel that state ownership fails to do so. Instead, the data seem to suggest that a more flexible landholding system centered around providing security of tenure and that takes into account local sensibilities including a mixture of private, state and communal holding would be a favorable option among the farming population rather than one fixated by the public/private dichotomy that characterizes the current debate in the country.

“Further analysis…. Shows that government action to increase tenure security and transferability of land rights can significantly enhance rural investment and productivity (B. Nega, B. Adenew and S. Gebre Sellasie, Ethiopian Economic Policy Research Institute, Addis Ababa, Ethiopia, 2021).

በሌላ በኩል ዛሬ በግልጽ የሚታወቁት የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደር ጭብጥ ጥያቄዎች ሀ) ሰላም እና ፀጥታ ነው። ለ) ‹‹መሬትን የደላላና የሌቦች አድርጎ ካበቃው›› የመሬት ወራሪ ሥርዓት መላቀቅን ነው። ሐ) የመሬት ወረራን ከሚያስተናግዱ ባለሥልጣናትና የፓርቲ ካድሬዎች መገላገል ነው። መ) በክልሎች መካከል በሚነሱ የወሰን ጥያቄዎችና ግጭቶች ምክንያት የሚፈጽምባቸው ግድያና መፈነቃቀል እንዲያበቃ ነው። ሰ) ከገዳይ፣ አፈናቃይ፣ አጋችና ዘራፊ ‹‹ነፃ አውጭዎች›› ነፃ መውጣት ነው። ረ) ማዳበሪያና የተባይ መከላከያ በወቅቱና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብላቸው ነው። ሠ) ትምህርት ቤት፣ የጤና ጣቢያ፣ የመብራት ኃይልና የስልክ ግንኙነት እንዲዳረስላቸው ነው። ሸ) ደላሎች ከምርት ሽያጭ ሰንሰለት ውስጥ እንዲወጡላቸው ነው። ቀ) መንገዶች እንዲገነቡና የገበያ ትስስራቸው በተሻለ እንዲሳለጥ ነው።

የዛሬው ተቀዳሚ ጉድይ ይልቁኑም ለተመለከቱትና ለተመሳሳይ የገበሬዎች ጥያቄዎች ቴክኒካዊ አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን ማቅረብና ለሐሳቦቹ መታገል አይሆንም ወይ? በእርግጥም ደግሞ ግን የመሬት ድልድል ባስከተለው የመሬት መሸንሸን ምክንያት የአርሶ አደሩ የእርሻ መሬት ይዞታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነና የነፍስ ወከፍ ምርታማነት እየቀነሰ ሄዷል። የኢትዮጵያ የግብርናና የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚመክሩት፣ ዛሬ ባለው ሁኔታ ለኢትዮጵያ የሚበጀው የተጀመረውን ኩታ ገጠም ግብርናና የበጋ እርሻ ለማት ማጠናከርና ማስፋፋት ነው። ሌላውም የኢንዱስትሪ፣ የአገልግሎት፣ የቱሪዝምና የማዕድን ዘርፎችን በማሳደግ፣ የከተማውንና ከገጠር የሚፈልሰውን ሥራ አጥ ለማሰማራት መጣር ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች እንደሚሠራበትም የግብርና መሣሪያዎች ጣቢያዎች (ፑል) እያደራጁና ሥራ አጡን ወጣት በቡድን በቡድን እያደረጉ በግብርና ሥራዎች ላይ ማሰማራት ነው፡፡ በትንንሽና በመካከለኛ አግሮ ኢንዱስትሪ መስኮች ማስገባት ነው።

ኢትዮጵያ የበርካታ አገር ወዳድ የግብርናና የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች አገር ናት። የዓብይ (ዶ/ር) መስተዳድር ለኢትዮጵያ አገር ወዳድ ባለሙያዎቹ ምክረ ሐሳቦች ጆሮ መስጠትን በተለያዩ መንገዶች ማስቻልና ማጠናከር ይገባዋል። በሌላም በኩል ብልፅግና ፓርቲውን ከሙሰኞችና በሁለት ቢላ ከሚበሉ ባለሥልጣናቱና ከካድሬዎቹ ከእጅግም በላይ እጅግ ማፅዳት ይኖርበታል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...