Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየክላስተር እርሻን ‹‹ይቃወማል›› ትርክት! (ክፍል ሁለት)

የክላስተር እርሻን ‹‹ይቃወማል›› ትርክት! (ክፍል ሁለት)

ቀን:

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)   

የኩታ ገጠም/ክላስተር እርሻ የአጭርና የረዥም ጊዜ ውጤታማነት

ቀደም ባሉት የዚህ ጽሑፍ ክፍሎች በኩታ ገጠም (Land Consolidation)፣ ችብቻቦ (Cluster) ዙሪያ ከማቀርባቸው ትችቶችና አስተያየቶች መሀል አንዱ፣ በዚህ አሠራር የሚደራጁ እርሻዎች ለዘላቂና በማሳ ስፋት መዋቅራዊ ለውጥ ለታገዘ ዘመናዊና ንግድ ተኮር ግብርና መሠረት ይሆኑ ዘንድ አደረጃጀታቸው ፍላጎት መር (Demand Driven) እንጂ አቅርቦት መር (Supply Driven) መሆን እንደሌለበት ነው፡፡ በእርግጥ ከመንግሥት የምግብ ዋስትና ማረጋጋጥ ስትራቴጂካዊ ግብ አንፃር ለአጭር ጊዜ የአቅርቦት መሩ አካሄድ የአምራቹን ይሁንታ እስካገኘና የመንግሥት አካላትም ገበሬውን እንደ ፖለቲካ ጉዳይ ማስፈጸሚያ መሣሪያነት የማይመለከቱት እስከሆነ ድረስ፣ ቅቡልነት ሊኖረው የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በተከታይ እነዚህን የአጭርና ረዥም ጊዜ ዕሳቤዎች በአጭሩ አብራራለሁ፡፡ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለሚሹ አንባብያን ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2017 ከጻፍኩት መጽሐፍ በንዑስ ክፍል 8.3.5 ‹‹ACC Institutionalization›› ብዬ የፃፍኩትን፣ እንዲሁም በዚሁ መጽሐፍ በንዑስ ክፍል 9.5 ‹‹Private Smallholder Farmers: Natural, Nominal, Real›› ብዬ የጻፍኩትን፣ በ2012 ዓ.ም. ኢኮኖሚው ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ በሚለው መጽሐፌ በንዑስ ክፍል 8.3.3 ‹‹የችብቻቦ ግብርና (Agricultural Clusters)›› ብዬ የጻፍኩትን፣ በ2013 ዓ.ም. ‹‹ኮረፖራቶክራሲ››… በሚለው መጽሐፍ ንዑስ ክፍል 5.4.2 ‹‹በመዋቅራዊ ለውጥ ውስጥ የነፃ አነስተኛ ገበሬ ሚና›› በሚል ርዕስ የጻፍኩትን እንዲያነቡ እጠቁማለሁ፡፡ እንደዚህ በዝርዝር መጻሕፍቶቹን ለማጣቀስ የገፋፋኝ በቅርቡ በአንድ የስብሰባ መድረክ በክላስተር እርሻ ዙሪያ ወይይትና ክርክር አድርገን ለዕረፍት ስንወጣ፣ አንዱ ተሳታፊ ለምን የምታነሳቸውን ዕሳቤዎችና ይስተካካል የምትለውን በጽሑፍ አዘጋጅተህ አታቀርበውም ብሎ ስለጠየቀኝ ነው፡፡ የሚገርመው ግን ይኸው የዶክትሬት ድግሪ ያለው ጠያቂዬ መጻሕፍቶቼን የገዛ እንደነበር ሳስታውስ፣ ቤቱ ወስዶ ግን ያላነበበው እንደሆነና በየመድረኩ እኔን ‹‹በተቃዋሚነት ለመፈረጅ›› የሚፈጥን መሆኑን መመልከቴ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ስለኩታ ገጠም/ክላስተር እርሻ የአጭርና ረዥም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታና ውጤታማነት ሳብራራ፣ በክፍል አንድ በስተመጨረሻ ላይ በአቀረብኳቸው ሦስት መላምታዊ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያም በማቅረብ ነው፡፡ ጉዳዮቹ ያጠነጠኑት የትኛውም አገር ሊያድግ፣ ሊለማና ሊበለፅግ የሚችለው ሦስቱ የሀብት ምንጮች ማለትም የሰው ኃይል/ጉልበት፣ መሬትና ካፒታል/ፋይናንስ በነፃነት፣ ከፍተኛ የምርታማነት ውጤት ሊያስገኙ በሚችሉ የአገር ግንባታና የልማት ሥራ ላይ እየተዘዋወሩ በዜጎች ለዜጎች ጥቀም ላይ ሲውሉ መሆን አለበት የሚሉ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለንተናዊ አውንታዊ ለውጥ ለማምጣት በቅድሚያ የኢትዮጵያ አነስተኛ ባለይዞታ አርሶና አርብቶ አደሮች ነፃና ዕውን (Real) የግል ክፍለ ኢኮኖሚ ተዋንያን መሆናቸው መታወቅና በፖስፕኢ መታገዝ አለበት፡፡ በተለይም ይኸው ማንነታቸው በሕግ ላይ በተመሠረተ የአሠራር ሥርዓት መጠበቅ አለበት፡፡ ይህን አቋሜን በውይይትና መከራከሪያ መድረኮች ላይ መግለጽና ማብራራት ከጀመርኩ በርካታ አሠርት ዓመታት ያስቆጠር ቢሆንም፣ በተለይ በኢሕአዴግ ዘመን በግልጽ በ1997 ዓ.ም. በተዘጋጀ አንድ ከፍተኛ የውይይት መድረክ ላይ ሳነሳ ከነበሩት ታዳሚዎች መሀል አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበር፡፡ አብረውትም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ነበሩ፡፡ በዚሁ መድረክ ጥሪ የተደረገላቸው የሙያ ማኅበራት መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ተቃዋሚ ናቸው ተብለው የሚገመቱ የፖለቲካ ሰዎች፣ የውጭ አገር የብዝኃና ሁለትዮሽ የልማት አጋር ድርጅቶች መሪዎችና አምባሳደሮች፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክና የአፍሪካ ልማት ባንክ ኃላፊዎችና ኤክስፐርቶችም ነበሩ፡፡ ስብሰባውን የመራው አቶ ነዋየ ክርስቶስ ገብረ አብ (ነፍሰሔር) ነው፡፡

በዚህ መድረክ በግብርናና ገጠር ልማት ረገድ በተለያዩ የፖስፕኢ ጉዳዮች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከእነዚህም መሀል በወቅቱ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማኅበር አመራር ላይ የነበረው ብርሃኑ ነጋ ዶ/ር (ዛሬ ፕሮፌሰር)፣ በተባባሩት መንግሥታት የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (ኤፍኤኦ)  ውስጥ ካሉ ኤክስፐርቶች ጋር በመቀናጀት የሙያ ማኅበሩ በመሬት ፖሊሲ ዙሪያ ያደረገውን ጥናት ሪፖረት አቅርበው ነበር፡፡ ከግኝቶቹ መሀል አንደኛው በሙያተኞች ዙሪያ በተደረገ መጠይቅና በተገኘ አኃዛዊ መረጃ 96 በመቶ ያህሉ መላሾች፣ መሬት በኢትዮጵያ ውስጥ በግል ባለቤትነት ጭምር መያዝ አለበት የሚለውን እንደሚደግፉ ተገለጸ፣ ውይይትም ተደረገበት፡፡

በውይይቱ ወቅት ከነበረው ክርክር አንፃር የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ስሜት ግለት የጨመረ አገላለጽ ስለነበር፣ በዚያው መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ ‹‹በኢሕአዴግ  መቃብር ላይ ነው የመሬት ፖሊሲው የሚቀየረው›› የሚል ቁጣ የተላበሰ አስተያየትና ማብራሪያ ሰጠ፡፡ ቀደም ሲል በውይይቱ ወቅት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) እና የጥናቱ ባልደረቦች ያቀረቡት መወያያ ነጥብና የመከራከሪያ ሐሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጋለ አስተያየት አስተዋጽኦ ቢያደርጉም፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በኋላ አስተያየት ለመስጠት ዕድሉን ካገኙት መሀል አንዱ እኔ ስሆን ሌላኛው ደግሞ ጋሽ እየሱስ ወርቅ ነበር፡፡  እኛም የሰጠነው አስተያየት ቁጣውን የአበረደው አልነበረም፡፡ በዚህም ሳቢያ ከሦስት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በኢቲቪ በጉዳዩ ዙሪያ ዶክመንተሪ መሰል ዘገባ ተሠርቶ የብርሃኑ፣ የጋሽ እየሱስና የእኔ ሐሳቦችና አስተያየቶች ተቀናብረው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጽና አቋም ማለትም፣ ‹‹በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ነው የመሬት ፖሊሲው የሚቀየረው›› ላለው  እንዲያግዝ ተደርጎ ለሕዝብ ተላላፈ፡፡ በእርግጥ የዚህን ድራማ ሙሉ ገጽታና ይዘት እዚህ ለማቅረብ ቦታና የጊዜ ሀብት ስለማይበቃ እዚሁ ላይ ገታ አድርጌ፣ እኔ በዚያን ወቅት ያነሳሁትና ለዚህኛው ጽሑፌ መነሻ ዕሳቤዎችና እስከ ዛሬም የማምንበትን፣ ከመሬት ፖሊሲ መሻሻል፣ በተለይ የግል ባለቤትነት፣ ከሌሎች የባለቤትነት ዓይነቶች ጋር ተጎዳኝቶ መታየት እንዳለበትና የገበሬን ነፃ የኢኮኖሚ ተዋናይነት ማክበር  እንደሚገባና ገበሬን የፖለቲካ መሣሪያ አድርጎ ፖስፕኢ መቅረፅና መተግበር ተገቢ አይደለም የሚል አቋሜን በወፍ በረር አቀርባለሁ፡፡

ከላይ በተጠቀሰው መድረክ ላይ አስተያየት ስሰጥ፣ በወቅቱ የመለስንና የሌሎችን ፊት ወደ እኔ እንዲመልሱ ያደረግኩት፣ በቅድሚያ በኢትዮጵያ ውስጥ የቀደሙት ሆነ የዛሬዎቹ መንግሥታት (ያኔ ኢሕአዴግ) ገበሬውን፣ በተለይም አነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሮችን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ ማየታቸው እንደሆነና መሆን የሚገባው፣ መታየትና መጠበቅ ያለበት ግን የኢኮኖሚ ተዋንያን መሆናቸው ነው የሚለው ማብራሪያዬ  ነበር፡፡  ገበሬን እንደ ፖለቲካ መሣሪያነት ማየታችን ካላቆመና መሬትም ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው አንፃር ከፍተኛ ውጤት በሚያመጡ እጆች ውስጥ እስካልተንሸራሸረ ጊዜ ድረስ፣ በግብርናው ዘርፍ ሆነ በሌላው ኢኮኖሚ ዘርፍ ዘለቄታ ያለው ዕድገትና ልማት ሊመጣ አይችልም ብዬም ተናገርኩ፡፡ በሌላ አገላለጽ ዋነኛ የሆኑት ሁለቱ ቁልፍ ግብዓቶች (የሰው ኃይልና መሬት) በመንግሥት ቁጥጥርና ጥፍነጋ ውስጥ ከወደቁና የፖስፕኢ ቀረፃውና ትግበራው ከዚያ ጋር ከተያያዘ፣ አገራዊ ዕድገትና ልማቱ አዎንታዊ ቢመስልም ዘላቂ፣ ብቁና ውጤታማ (Sustainable, Efficient and Effective) አይሆንም የሚል ነበር፡፡ ከዚህ ጋርም አያይዤ ያነሳኋቸው ሌሎች አካዴሚያዊ የሆኑ ጉዳዮችም ነበሩ፡፡

ዛሬም ማለትም በዘመነ ብልፅግና፣ በግብርናው ዘርፍ ከኩታ ገጠም/ክላስተር እርሻው ጋር ተያይዘው አሉ የምላቸው ችግሮች መሀል ዋነኛው ገበሬን እንደ ፖለቲካ መሣሪያነት መቁጠር፣ ለመንግሥት የፖለቲካ ግብዓት በሚያመች ሁኔታ በመሬት ላይ ተንተርሶ፣ ብሎም በቴክኖሎጂ ሞኖፖሊያዊ አቅራቢነት በተንሰላሰለ ሥርዓት የእሱን ነፃነት ገፎ የእርሻውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለመምራት የመፈለጉ አባዜ ነው፡፡

ገበሬው ያለ ፍላጎቱ በክላስተር እርሻ እንዲደራጅ መደረጉ አነስተኛ ግን ውጤታማ የሆኑና ሚሊዮን መቁጠር የጀመሩ ገበሬዎችን ወደ ማቀጨጭ፣ በአገራቸው ውስጥ ጥረው ግረው ከትንሽ ጀምረው ወደ ከፍተኛ የግብርና ኢንተርፕራይዞች ባለቤትነት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚሹ ገበሬዎችን ራዕይም ሆነ ዕውናዊ እንቀስቃሴ የሚያኮላሽ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በቅርብ ከቢሾፍቱ አካባቢ ጀምሮ እስከ አርባ ምንጭ ዙሪያ በአትክልትና ፍራፍሬ ጥሩ ውጤት ያመጡ ገበሬዎች ጭምር፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች በግድ ስንዴ ካላመረታቸሁ በሚል ተፅዕኖ ምክንያት በቅሬታና በሐዘን ውስጥ ተዘፍቀው እንደሚገኙ ከሚዲያ ዘገባና ከሌሎች መረጃ ምንጮች መረዳት ተችሏል፡፡

ለዚህም ነው ከ2013 ዓ.ም. ምርጫ ጥቂት ወራት በፊት፣ ‹‹የምርጫ ሰሞን ፈተና›› ብዬ በጻፍኩትና በኤሌክትሮኒክስ ኅትመት ማሠራጫ ለሕዝብ ተደራሽ እዲሆን በአደረኩት ጽሑፍ ውስጥ የሚከተለውን ጥያቄ ያነሳሁት፣ ዛሬም ድረስ የማነሳውም፡፡ ጥያቄውም፣ ‹‹ፖለቲከኞቻችን (በገዥውም ሆነ በተቃዋሚ ጎራ ያላችሁ) በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አነስተኛ የእርሻ መሬት ይዞታ ያለው ገበሬ ጥሬ፣ ግሬ፣ ላቤን አንጠፍጥፌ ካመረትኩት፣ ሸጬ ከማገኘው ገቢ ቆጥቤ፣ ጥሪት ከያዝኩና ራሴን ለማሻሻል በሚያስችሉኝ ግብዓቶች ላይ ኢንቨስት ካደረግኩ፣ ቀስ በቀስ በግብርናው ውስጥ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ብሎም ትላልቅ/ሰፋፊ የእርሻም ሆነ ከእርሻ ውጪ ያሉ የግብርና ኢንተርፕራይዞች ባለቤት መሆን እችላለሁ ብሎ ራዕይ ሊኖረው ይችላል ብላችሁ ትገምታላችሁ? መልሳችሁ አዎ ከሆነ፣ እንዴት፣ በምን ዓይነት ፖስፕኢ ቀረፃና ትግበራ፣ መቼ ወዘተ…?›› የሚል ነው፡፡

ከላይ ባቀረብኩት ጥያቄና ተዛማጅነት ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ፣ በተለያዩ ጊዜያት በጻፍኳቸው መጻሕፍቴ ውስጥ ተጨማሪ መግለጫዎችንና ማብራሪያዎችን አቅርቤያለሁ፡፡ ከእነዚህም መሀል በ2009 ዓ.ም. በጻፍኩት መጽሐፍ ውስጥ፣ ‹‹ለመሆኑ ኢሕአዴግ በየዓመቱ ሚሊየነር ሆኑ፣ ምርጥ፣ ሞዴል ገበሬዎች ናቸው እያለ በከፍተኛ ድግስና በቴሊቪዥን አስቀርፆ በሚተላለፍ ክብረ በዓል ላይ ሽልማትና ዕውቅና የሰጣቸው አነስተኛ ሀብታም የሆኑ ገበሬዎች የት ገቡ?›› ብዬ ጠይቄ፣ አንዳንዶች በአካባቢያቸው ወፍጮ ቤት በመክፈት፣ በአቅራቢያ ባሉ ከተሞች ቤት ሠርተው በማከራየት፣ አይሱዙ መኪና ገዝተው በሾፌር በማስነገድ፣ ሆቴል ቤቶችና ዲሰኮ ቤቶች በመክፈት፣ ባጃጅ በመግዛት፣ ወዘተ ያገኙትን ተጨማሪ ሀብት ሲያንቀሳቅሱ መመልከቴንም አሳውቄያለሁ፡፡ ለምን እዚያው በእርሻው ሥራ (ሰብልም ሆነ እንስሳት ልማት) ላይ ኢንቨስት አላደረጉም? ለምንስ በተገቢው ቴክኖሎጂ ታግዘው ባለቻቸው አነስተኛ ማሳ ዘመናዊና ንግድ ተኮር እርሻ ወይም ሌሎች በእሴት ጭመራ የታገዙ የግብርና ሥራዎች ላይ አልተሰማሩም? ብዬ ጠይቄ ሙያዊ ተገማች መልስና ምክረ ሐሳብም አቅርቤያለሁ፡፡ የሚገርመኝ ይህ የመሸለም፣ ፖለቲካዊ ትርክት የበዛባት ኢንቨስተር/ሚሊየነር አነስተኛ ገበሬዎችን ማፍራት ዲስኩር በዛሬውም መንግሥት በተለያዩ ክልሎች ተደግሶ እየተሞካሸ በቴሌቪዥን መስኮትም መታያቱ ቀጥሏል፡፡ 

የቅርብ  ጊዜው የክላስተር እርሻ አሠራር  ዕሳቤ ችግር፣ ትብታቦና የእኔ ምልከታዎች

ከላይ ያነሳኋቸው ጥያቄዎችና ተያያዥ ጉዳዩች በአብዛኛው ከመሬት ፖሊሲያችን ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል አነስተኛ ገበሬዎች ምንም ያህል ይጣሩ፣ ይልፉ፣ መንግሥታት (ፖለቲከኞች) የሚያዩዋቸውና የሚቀርፁዋቸው ፖስፕኢዎች ገበሬዎቹን እንደ ፖለቲካ መሣሪያ በመቁጠር የሚጀምሩ፣ ነፃ የግል ኢኮኖሚ ዘርፍ ኢኮኖሚ ተዋንያን እንዳልሆኑ የሚገምቱ ናቸው፡፡ የቅርብ ጊዜው የኩታ ገጠም/ክላስተር እርሻ አሠራር ዕሳቤና አፈጻጸምም ከዚህ ችግርና ትብታቦሽ የተላቀቀ አይደለም፡፡ ቀደም ብዬ በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት፣ እኔ የኩታ ገጠም/ክላስተር እርሻ አደረጃጃት በአጭር ሆነ በረዥም ጊዜ ልማት ዕቅድ ውስጥ ስትራቴጂካዊ ተመራጭነት ሲሰጠው በቅድሚያ የገበሬውን ነፃነትና የግል ኢኮኖሚ ተዋንያንነት ባስጠበቀ የአፈጻጸም መርህና ሥርዓት ላይ ተመሥርቶ መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ፍላጎት መር (Demand Driven) ሆኖ መተግበር አለበት እላለሁ፡፡ በዚህም አቋሜም በግብርና ሚኒስትርና በክልል ግብርና ቢሮዎች በኩል ዕዝ ሥር ውሎ በአቅርቦት መር (Supply Driven) ከሚተገበረው የክላስተር እርሻ አደረጃጃትና አፈጻጸም ጋር ተቃርኖ አለኝ፡፡

የመሬት ፖሊሲው ተከልሶና ተሻሻሎ የግል ባለቤትነትን ወደ የሚያስተናግድ የኢኮኖሚ ሥርዓት እስከሚቀየር ድረስ አሁን ባለው የገበሬዎች አነስተኛ የማሳ ስፋት፣ አነስተኛ ገበሬዎች ሚሊየነር እየሆኑ ሲመጡ ሰፋፊ መሬትን በሚሹ የሰብልም ሆነ የእንስሳት ምርቶች ልማት ላይ በዕውን ዘመናዊና ንግድ ተኮር ሥራዎችን እንዲሠሩና ለውጥ ለማምጣት እንዲችሉ፣ ያላቸውን የማደግና የመበልፀግ ራዕይና ተነሳሽነት እዲያጎለብቱ፣ እያፈሩ  የመጡትን ጥሪት መልሰው በግብርናው፣ በተለይም በእርሻው ንዑስ ዘርፍ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ይችሉ ዘንድ የማሳ ሽግሽግ፣ የእርሻዎች ልውውጥ፣ ኩታ ገጠም (Land Consolidation) ፖስፕኢ ተቀርፆ መተግበር ያለበት የገበሬውን ነፃ የግል ተዋንያንነት ባገናዘበና በተቀበለ ይዘት መሆን አለበትም እላለሁ፡፡ ያለው የመሬት ፖሊሲ እስኪከለስ ጊዜ ድረስ ግን ለማሳ ማሰባሰቡ እንደ ሥልት ስድስት አማራጮችን አመላክቼ በ2012 ዓ.ም. ባሳተምኩት መጽሐፍ በምዕራፍ 6 ንዑስ ክፍል 6.4 ‹‹የመሬት ፖሊሲ፣ ሜካናይዤሽንና የማሳ ሽግሽግ›› በሚል ርዕስ አቅርቤዋለሁ፡፡ በተጨማሪም የኩታ ገጠም (Land Consolidation) ማብራሪያንና ቴክኒካዊ ጭብጦቹን በምዕራፍ 8 ንዑስ ክፍል 8.3 ‹‹የምርምር፣ ኤክስቴንሽንና የችብቻቦ ግብርና አደረጃጃቶችና ሥርዓቶች›› አብራርቼ፣ በፍላጎት መርና በአቅርቦት መር መሀል ያለውን ልዩነትም በንዑስ ክፍል 8.3.3 አመላክቼያለሁ፡፡ ታዲያ ይህን ሳያነቡ ወይም አንብበው ከድብቅ ወይም ፖለቲካዊ ጨዋታቸው ጋር በማዛመድ ውዥንብር ፈጥረው፣ ‹‹ደምስ የክላስተር እርሻን ይቃወማል›› የሚል ትርክት በመተረክ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ብቅ ብቅ ብለዋል፡፡

እዚህ ላይ ጠቆም አድርጌ ለማለፍ የምፈልገው በ2012 እና በ2013 ዓ.ም. በጻፍኳቸው መጻሕፍት ውስጥ የእርሻ ማሳ ስፋትን ከማሰባሰብ ስትራቴጂ (Land Consolidation) እና ከተሻሻለ ቴክኖሎጂ አጠቀቀም ጋር በማቀናጀት፣ እንዴት በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊና ንግድ ተኮር እርሻ ሊስፋፋ እንደሚችል አመላክቼያለሁ፡፡ በተለይም የዚህ መቀናጆ ዕሳቤ ማጠንጠኛ እርሻን በማናቸውም ማሳ ስፋት፣ የሚፈለገውን ምርት ዓይነት ከተገቢ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በማቆራኘት፣ ዘመናዊና ንግድ ተኮር አድርጎ መከወን እንደሚቻል ነው፡፡ በአደጉት አገሮች በኮቪድ ወቅት በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ታግዞ፣ በቤት ውስጥ በተለይ ጤናማ የሆነና ወዲያው ተቆርጦ መመገብ የሚቻል የአትክልት ምርት የማምረት ልህቀት ደረጃ ላይ እንደተደረሰ የኛም አገር ሚዲያዎች የዘገቡት ሀቅ ነው፡፡

የእኔ መጻሐፍት ለሽያጭ ከቀረቡ በኋላ ብልፅግና ፓርቲ መር የአሥር ዓመት የልማት ዕቀድ፣ ፍኖተ ብልፅግና 2013 እስከ 2022 ዓ.ም. ተዘጋጅቶ ሲወጣ ኩታ ገጠም ማለት የእንግሊዝኛውን (Land Consolidation) የሚገልጽ ሆኖ በግብርናው ልማት ንዑስ ክፍል 3.1 እንደሚከተለው ተጽፎ ወጣ፡፡ …በአገራችን የአርሶ አደሮች የመሬት ይዞታዎች እጅግ አነስተኛ፣ የተበጣጠሱ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው የሚገኙ በመሆናቸው… ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና ዘርፉን ለማዘመን አርሶ አደሮች በመሬታቸው የመጠቀም መብትን፣ እንዲሁም መሬት ነክ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በማይነካ ሁኔታና አሠራሩ አዋጭ በሆነባቸው አካባቢዎች ኩታ ገጠም መሬቶችን አንድ ላይ በማሰባሰብ (Land Consolidation) የኩታ ገጠም ይዞታ አሠራር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም በረቂቅ የመሬት አጠቃቀም አዋጁ ላይ የተጠቀሱትን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀምና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የገጠር መሬት የኩታ ገጠም ይዞታ አሠራርን የማሻሻልና የኮንትራት እርሻ አሠራር በልማት ዕቅዱ ዘመን በስፋት ይሠራል፡፡  

በግብርናው ልማት ዕቅድ ክፍል ውስጥ ‹‹ክላስተር›› እርሻ የሚል የእርሻ ልማት ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ አያገኝበትም፡፡ ‹‹የክላስተር አደረጃጀትን ማጠናከር›› እንደ ስትራቴጂካዊ የልማት አቅጣጫ ተጠቅሶና ተብራርቶ የሚገኘው በንዑስ ክፈል 3.2 በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱሰትሪ ልማት ዕቀድ የትኩረት አቅጣጫዎች ማብራሪያ ውስጥ ነው፡፡ ከላይ ከተገለጸው በአጠራርና በጽንሰ ሐሳብ ይዘት ላይ ካለው ክፍተት በተጨማሪ፣ በመንግሥት ተቋማት መሀል ከፍላጎት መርና ከአቅርቦት መር አደረጃጀት ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ልዩነቶች አሉ፡፡ በሲነርጎዝ ተጀምሮ የነበረውና በኤትኤ እ.ኤ.አ. ከ2014 (2006 ዓ.ም.) ጀምሮ የሚተገበረው የግብርና ንግድ ተኮር ክላስተር (ኤሰሲ) አደረጃጃት ዓላማው በክላስተር አደረጃጀት አነስተኛ ገበሬዎች እንዲደራጁ ግንዛቤ መፍጠርና ማስፋፈት ሆኖ፣ በዚህ አደረጃጃት ለመታቀፍ ለሚፈልጉ አነስተኛ ገበሬዎች ከሥልጠናና የማማከር አገለግሎት ጀምሮ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ፣ ግብዓት ማቅረብና ከገበያ ጋር ማቆራኘት የሚል መረጃ ይገኝበታል፡፡ ከገበያ ጋር የማቆራኘቱን ሥራ በኮንትራት እርሻ አሠራር ገዥዎችና አምራቾች ከሰብል አጨዳ በፊት በሚያደርጉት ስምምነት እንዲፈጸም የሚያደርግ ዕሳቤ አለው፡፡ ይህ የክላስተር እርሻ አተገባበር ገዥዎች ለአምራቾች የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ታሳቢ የሚያደርግ ሆኖ ከድጋፎችም መሀል ገዥው ለገበሬዎቸ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ አግሮ ኬሚካሎችና የሜካናይዤሽን አገልግሎት ማቅረብን እንደሚያካትት ያትታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ገበሬው ያመረተውን ምርት ገዥው በጥሩ ዋጋ መግዛትና ምርቱን ገበሬው ደጃፍ ድረስ ሄዶ መሰብሰብ፣ ገበሬው ምንም የምርት ማጓጓዝ የትራንስፖርት ወጪ እንደማያደርግ የሚያመለክት አሠራርን ያካትታል፡፡ በእኔ ግምት ይህ ምናባዊ የሚመስል በወረቀት ላይ የቀረ ዕሳቤ ነው፡፡

ከላይ የተገለጸው የኤትኤ ዓይነት የክላስተር እርሻ አደረጃጀትና አፈጻጸም ሊተገበር የታሰበው በተመረጡ የምርት ዓይነቶችና በተመረጡ ወረዳዎች በአራት ክልሎች ነው፡፡ ይህ ብዙም ሳይተገበር፣ በግብርና ሚኒስትርና በክልል ግብርና ቢሮዎች በሁሉም ክልሎች የሚተገበር አቅርቦት መር የሆነ የኩታ ገጠም/ክላስተር እርሻ አሠራር ተጀመረ፡፡ ዓላማውና ግቡ ምርታማነትንና ምርትን በብቃትና በውጤታማነት ለማስፈን፣ ምርጥ ዘርንና ማዳበሪያን በመደበኛው የኤክስቴንሽን ፕሮግራምና ኢንስቲትዩሽን በኩል ማድረስ ነው፡፡ በዚህ ዕሳቤ ላይ የተመሠረተው የክላስተር እርሻ አደረጃጃት በገበሬውና በገዥዎች (ፋብሪካዎች ወይም ኤክስፖርተሮች) መሀል መፈጸም የሚገባው የኮንትራት ስምምነት ሥልትን አያካትትም፡፡ በዲስኩር ደረጃ የመንግሥት ተቋማት ገበያ የማፈላለጉን ሥረ ይሠራሉ የሚል አባባል አለ፡፡ በአብዛኛው ግን በክላስተር የተደራጁ ገበሬዎች ምርታቸውን ለመሸጥ እንደሚቸገሩ የመንግሥት ሚዲያዎች ጭምር እየዘገቡት ነው፡፡

በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. በግብርና ባለሙያዎች ማኅበር ዓመታዊ ኮንፍረስ ላይ ያቀረብኩትን ጽሑፍ በማዘጋጅበት ወቅት ባደረግኩት መጠያይቅ፣ በኤትአይ ሆነ በግብርና ሚኒስትርና በክልል ግብርና ቢሮዎች በኩል ለሚሠሩ የኩታ ገጠም/ክላስተር አደረጃጃቶች ገበሬው ደጃፍ ያለው የልማት ሠራተኛ የሚጠቀምበት በጽሑፍ ተሰንዶ የሚገኝ የክለስተር ማደራጃና መተግበሪያ መመርያ ወይም ማኑዋል እንደሌለ አውቄያለሁ፡፡ ይህ ጉዳዩ ዘመቻዊና ግብታዊ እንደሆነ ያመላክታል፡፡ በየት አካባቢ፣ በምን ዓይነት ምርቶች ላይ፣ በገበሬዎች ፈቃደኝነት ዙሪያ፣ ፈቃደኛ ለማይሆኑ ገበሬዎች ደግሞ ስለሚኖር ሕጋዊ ከለላና ተገቢ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ማግኘት፣ ወዘተ ያለው የመብትና ግዴታ ማሳወቂያ ዝርዝር መመርያ ወይም ማኑዋል ያስፈለገው ነበር፡፡ በክላስተር አደረጃጃት ለታቀፉ አምራቾች ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርትና ድኅረ ምርት ስብስቦሽ ድረስ የሚዘልቅ ዝርዝር እንቅስቃሴዎችን በጊዜ ለይቶ፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ያቀፈ የማደራጃና የማስፈጸሚያ መመርያ መኖር ነበረበት፡፡  በጥቅሉ ዛሬም ላይ በሁሉም ክልሎች ያለው ከሰባት ዓመት በፊት እንደተጀመረው በዕዝ የሚመራ፣ በዘመቻ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረና ከዘላቂ ልማት ማሳለጫ ስትራቴጂካዊ መሣሪያነት ይልቅ ለአጭር ጊዜ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ አለፍ ብሎም ለፖለቲካ ትርክት ማሟሟቂያነት የሚተገበር የክላስተር እንቀስቃሴ ይመስላል፡፡

የአሁነኛው ክላስተር እርሻ ፖለቲካ ይዘቱ ደርግ ከጀመረው የአምራቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንቅስቃሴ ጋር እምብዛም ልዩነት የለውም የሚል ድምዳሜ ላይም እንድደርስም ገፋፍቶኛል፡፡ ለአንባቢያን ግንዛቤ ይረዳም ዘንድ ለገፊ ሁኔታው አመላካች ይሆን ዘንድ የሚከተለውን ከደርግ፣ ‹‹የብሔራዊ አብዮታዊ የምርትና የባህል ዕድገት ዘመቻ›› የሁለተኛው ዓመት (1972 ዓ.ም.) ያገኘሁትን ማስረጃ በአመላካችነት አቅርቤዋለሁ፡፡

‹‹… በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በግልና በተበታታነ መንገድ የሚካሄደው የግብርና ሥራ ለካፒታሊስት ሥርዓት ማቆጥቆጥ ምክንያት እንዳይሆንና አርሶ አደሩ መሬቱን፣ የማምረቻ መሣሪያውንና ጉልበቱን የወል በማድረግ የሶሻሊስትን የልማት አቅጣጫ ፈር ለማስያዝ እንዲቻል ገበሬው በአምራቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዲደራጅ ግልጽና የማያሻማ መመሪያ ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ መዋል ጀምሯል፡፡ …በተለይም የአምራቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ማደራጀት ለማፋጠን የሚከተሉት ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ የአምራቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከኋላቀር ልማዳዊ አሠራር እንዲላቀቁና ምርታማነታቸው ከፍተኛ እንዲሆን የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ፀረ ተባይ፣ ምርጥ የርቢ እንስሳት፣ የእንስሳት መኖ፣ መድኃኒትና የእርሻ መሣሪያ በቅድሚያ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ የመስኖ እርሻ ማቋቋም ገበሬው በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ምርት እንዲያገኝ፣ በዝብናም እጥረት ምክንያት የሚጠፋውን ምርት ለማዳንና የምርቱ መጠን ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆን በአምራቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለተደራጁ ገበሬዎች የመስኖ እርሻ እንዲያቋቁሙ የቴክኒክ ድጋፍ ይሰጣቸዋል፤››፡፡

ሌላው ከደርግ ጋር የበለጠ የሚያቀራርብ የክላስተር መሰል ዕሳቤ ወይም አተገባበር ሒደት ደግሞ በቅርቡ ኤትአይ  ከውጭ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በተቀረፀ፣ የክላስተር እርሻ አሠራርን ዘመናዊና ንግድ ተኮር ግብርናን አስፋፋበታለሁ ብሎ የጀመረው ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት የገበሬ ምርት ክላስተር (Farmer Production Clusters (FPC-ኤፍፒሲ) ተብሎ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ አተገባበሩም በአንድ አካባቢ ያሉ ከ30 እስከ 200 ያህል ገበሬዎች የማሳ ግጥምጥሞሽ ፈጥረው (Adjacent Land to Farm) እዲያርሱ የሚያስችል ቡድን በማቋቋም ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እነዚህ ገበሬዎች በኤክስቴንሽን ሥርዓቱ የሚመከሩትን ወቅታዊ የሆነ የተሟላ የቴክኖሎጂ ፓኬጅን መጠቀም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፓኬጁ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪና ሌሎች ምርጥ አግሮኖሚና የእርሻ አሠራርንና ማኔጅመንት ያካትታል፡፡ የኤፍፒሲ ፕሮጀክት በሒደት ቡድኖቹ ወደ ንግድ ካምፓኒነት ይለወጣሉ የሚል ዕሳቤ ይዟል፡፡ ታዲያ ይህ ደርግ መሬት የመንግሥት ነው ከሚል ድንጋጌ ተነስቶ ከአቋቋማቸውና እስከ 200 ገበሬዎችን በሚያቅፍ በ800 ሔክታር መሬት ላይ በሚቋቋሙ የገበሬ ማኅበራት ውስጥ፣ የአምራቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በማቋቋም እንዲሠሩ ከላይ ከ1972 ዓ.ም. ዕቅዱ ጋር በማጣቀስ ያቀረብኩትን የቴክኖሎጂና የመስኖ ግብርና አገልግሎት ከሚያስገኝ አደረጃጃት ጋር በምን ሊለይ እንደሚችል፣ ምናልባት ፖለቲከኞቹ እንደሚሉት በርዕዮተ ዓለም ካልሆነ በስተቀር ለመለየት ቀላል አይሆንም፡፡ የርዕዮተ ዓለሙን ጉዳይ ወደኋላ እመለስበታለሁ፡፡

በእኔ ግምት የኤትኤይ የንግድ ካምፓኒ ቅርፅ ያላቸውን የገበሬ አደረጃጀት የመፍጠር ዕሳቤ በከፊል መነሻው እ.ኤ.አ. በ2007 (1999/2000ዓ.ም.) ከተደረገ ጥናት ላይ ነው፡፡ በዚህ ጥናት የመሬት ፖሊሲው የማይቀየር ከሆነ አነስተኛ ገበሬዎች በኢንቨስተርነት ተሰባስበው ወደ ኮርፖሬት ዘመናዊና ንግድ ተኮር እርሻ፣ እንዲሁም የግብርና ኢንተርፕራይዞች ባለቤትነት እንዴት ሊሰማሩ እንደሚችሉ የተሰጠውን ምክረ ሐሳብ ሳያላምጡ በመዋጥ የተከሰተ ብዥታ ነው ብዬ እጠረጥራለሁ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2007 የገጠር መሬት ግመታና ካሳ ክፍያ ጥናት በሚል በዩኤስኤድ ፈንድ፣ በአሜሪካ አገር ባለና በአገር ውሰጥ በተጎዳኘው አጥኚ ድርጅት ጥምረት በእኔ ቡድን መሪነት በተደረገው ጥናትና ከቀረበው ምክረ ሐሳብ ላይ ተንተርሼ እ.ኤ.አ. በ2015 (2007/2008 ዓ.ም.) በእንግሊዝኛ በአሳተምኩት መጽሐፍ በገጽ 223 ‹‹Smallholder Investors (ኢንቨስተር አነስተኛ ገበሬዎች)›› በሚል ርዕስ ገበሬዎቻችንን ከአነስተኛ ከእጅ ወደ አፍ ካለ የግብርና አሠራር ወደ አነስተኛ ንግድ ተኮር አምራችነትና ኢንቨስተርነት፣ የኪራይ መሬት ፖሊሲውንና የገጠር መሬትን ለልማት ማውረስ የሚለውን የሕግ ማዕቅፍ በመሻሻል እንዴት እንደሚቻል የቀረበውን ማብራሪያ  አንባቢያን እንዲያነቡት እመክራለሁ፡፡ የኤፍፒሲ አዘጋጆች ይህን የመጽሐፉን ክፍል ዓይተውታል ብዬ ገምቻለሁ፡፡ ግን ምክረ ሐሳቡን ሲረዱ በዕሳቤም ሆነ በይዘት አዛብተውታል የሚል ድምደሜ ላይ ደርሻለሁ፡፡ በተለይ የመሬት ፖሊሲው የግል ባለቤትነትን በሚያካትት ይዘት ሳይሻሻል፣ በአንድ አካባቢ ያሉ አነስተኛ ገበሬዎችን በኮርፖሬሽን አደረጃጃት ማሰባሰብ ማለት፣ እያንዳንዱ ገበሬ በግል ጥረቱ ጥሮ ግሮ ያፈራውን የእርሻ መሣሪያና ሀብት እንደ ደርግ በአምራቾች ኅብረት ሥራ አደረጃጃት ማሰባሰብ፣ ታታሪና ሰነፍ ገበሬን አብሮ ማጎዳኘት፣ በግሉ የአነስተኛ፣ መካከለኛና ብሎም ሰፋፊ ዘመናዊና ንግድ ተኮር የግብርና ኢኮኖሚው ተዋናይ ለመሆን የሚጥር ገበሬን ራዕይ መግደል፣ ተነሳሽነቱን ማቀጨጭ፣ በጥቅሉ ገበሬውን ደሃ ሆኖ የመንግሥት ፖለቲካ ካድሬዎች (በልማት ሠራተኛነት ስም) የፖለቲካ ጉዳይ ማስፈጸሚያ መሣሪያ አድርጎ መግዛት ነው፡፡  በዚህ ዓይነት አካሄድ መንግሥታት ቢቀያየሩም ለገበሬው ገቢና ኑሮ መሻሻል ጉልህ ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም፡፡

በውጭ ኃይሎች በምዕራቡ በፕሮጀክት ይዘት የተጀመረው ኤፍፒሲ (FPC) አካሄድ፣ በንጉሡ ዘመን ገበሬው (ጉልተኛው፣ ገባሩ፣ ሲሶ አራሹ፣ ወዘተ) እስከ አርባ ሔክታር (አንድ ጋሻ) መሬት ድረስ እንዲሰጠው በ1940ዎቹ ባሳወጁት የመሬት ለአራሹ አዋጅ ለዚህ ማስፈጸሚያ ምዕራባውያን እንቢ ሲሉዋቸው፣ ከሩሲያ መንግሥት ብድር አግኝተው ሥራውን በጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ መሪነት ለማስጀመር ሲንቀሳቀሱ፣ የምዕራባውያን አገሮች በአምባሳደሮቻቸው በኩል በሸረቡት ሴራ የ1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት መሞከራቸውን እንዳስታውስ አድርጎኛል፡፡ ምዕራባውያን በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የኢትዮጵያን መሬት በሚፈልጉት መጠንና ሥፍራ ይዘው አስከሚጠቀሙ ድረስ ኢትዮጵያዊ ገበሬዎችን በተበጣጠሰ መሬት፣ ተረጂና ደሃ ገበሬ አድርገው ማስቀረት ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ተግባራቸው ነው ብዬ መላምታዊ ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡ ይህን ያልኩት እስከ ዛሬ ካነበብኳቸው፣ በሌሎች አገሮች በተለይም በበርካታ አፍሪካ አገሮች ካደረጓቸው፣ ዛሬም ድረስ እንደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባሉ አገሮች ውስጥ በሚያደርጓቸው ድርጊቶች ላይ ተመርኩዤ ነው፡፡ የኤፍፒሲ ፕሮጀክትም የዚህ ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ አንደኛው ሴራ ነው ብዬ መላምታዊ ሐሳቤን አቀርባለሁ፡፡

ወደ ርዕዮተ ዓለሙ ጉዳይ ልመለስ፡፡ ምናልባት የደርግን አካሄድ ከዛሬው አካሄድ የሚለየው ከፖለቲካ ትርክት አንፃር፣ ደርግ ሶሻሊዝምን ሲሰብክ የአሁነኛው ደግሞ በገበያ መር ኢኮኖሚ ውሉ በቅጡ ባለየለት፣ በደፈናው ከኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተለየ ነው በሚባል፣ በተለይም በርዕዮተ ዓለም አልተጠመድኩም፣ ሊበራልም፣ ሶሻል ዴሞክራትም ሳልሆን በመደመር ዕሳቤ፣ በሚመዘን ፕራግማቲክ ፍልስፍና የምመራ ነኝ ነው የሚለው አቀራረብ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ዙሪያ ያለ ትርምስን በተለይ ደግሞ በቅርቡ ልክ እንደ ኢሕአዴግ፣ የግሉ ዘርፍ አስከሚጠናከር ድረስ በሌሎችም ኢኮኖሚ ዘርፎች መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶችንም አቋቁመን ልማቱን እንመራዋለን ከሚሉት ክልሎች አካሄድ ተነስቼ፣ በእርግጥ ከርዕዮተ ዓለም መጠሪያ ባሻገር በሆነ ነገር ውስጥ  እየተንገዋለለ ያለ ሚስጥር አለ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይህ ጉዳይ ግን የዚህ ጽሑፌ ዓላማ ክፍል ስላልሆነ በሌላ ጊዜ እንደምመለስበት እገልጻለሁ፡፡ እሰከዚያው ግን በዚህ በመጠሪያና በርዕዮተ ዓለም ትርክት ዙሪያ በ2012 ዓ.ም. መጽሐፌ በምዕራፍ 11 ንዑስ ክፍል 11.1፣ ‹‹የኢሕአዴግ መንግሥት ፖስፕኢ መሠረትና ድርጅታዊ ርዕዮተ ዓለም›› በሚል ርዕስ ውስጥ የጻፍኩትን የሚከተለውን ጠቅሼ ወደ ማሰባሰብና መደምደሚያ አልፋለሁ፡፡

‹‹…ዛሬም ድረስ ያልገባኝን ነገር ለአንባብያን ማጋራት ነው፡፡ ምናልባትም የኢሕአዴግ መሪዎች በተለይም የቀድሞዎቹ ከዚህ በኋላ ሊያብራሩት ይችሉ ይሆናል፡፡ ይኸውም ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የሚለውን ሐረግ ለምን በ1992 ዓ.ም. ካወጡት መጽሐፍ ጀምሮ ስያሜ እንዳደረጉት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ስያሜ በዚያን ጊዜ የወጣውን ሰነድ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ፖስፕኢ ይዘት በሚገባ የማይገልጸውና ዛሬም ድረስ ከይዘቱ ይልቅ፣ ሐረጉን የፖለቲካ ትርክት ነጋሪ ብቻ አድርገው በማቅረብ የሚተቹት ብዙዎች ናቸውና ነው፡፡ ሰነዱ የኢትዮጵያ አገራዊ (Indigeneous) የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት የፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ኢንስቲትዩሽኖች መሠረት ተብሎ ቢሆን ኖሮ ከበፊት ጀምሮ ለሚሰነዘርበት ጅምላ ትችት በቀላሉ ተጋላጭ ካለመሆኑም በተጨማሪ የአገሪቱንና…››፡፡

ስብሳቦሽ፣ መደምደሚያና ጥቂት ምክሮች

ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ በተደጋጋሚ የምሰማው ‹‹ደምስ የክላስተር እርሻን ይቃወማል›› የሚለው አገላላጽ ወይም አባባል ነው፡፡ ይህ መታረምና የማቀርባቸው ሐሳቦች ሙያዊ ከሆኑ፣ በትምህርታዊ መሠረት፣ ዕውቀትና ተሞክሮ ላይ በተመሠረቱ ጭብጦች ላይ የተመረኮዙ፣ ከጊዜ አንፃር የለውጥ መንግሥት የሚባለው ከመፀነሱ በፊትም የነበሩ እንደሆኑ ለማሳወቅም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አንባቢያን እንዲያተኩሩ የምሻው በቃላት ማለትም በኩታ ገጠም፣ ክላስተር፣ ችብቻቦ፣ ማሳ ሽግሽግ፣ ማሳ ልውውጥ በሚሉት አጠቃቀም ላይ ባለው መምታታት ሳይሆን በዋነኛነት የብልፅግናው መንግሥት በግብርናው ልማት ዕቅድ ንዑስ ክፍል 1.3 ውስጥ ያስቀመጠውን፣ ‹‹በከፍተኛ ምርታማነታቸው የሚታወቁ አነስተኛ ገበሬዎችን የተሻለ የመሬት ይዞታ እንዲኖራቸው ማገዝ፣ ቀስ በቀስ ወደ ኢንቨስተርነት ማሳደግ›› የሚለውን ስትራቴጂ የመሬት ፖሊሲው ሳይከለስ እንዴት መሬት ላይ እናውለው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ላይ ነው፡፡ ለእኔ ይህ ሊሆን የሚችለው አነስተኛ ግን ሚሊየነር የሆኑ ወይም ወደ መሆን በማምራት ላይ የሚያመሩ ገበሬዎቻችንን በማስገደድ (ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ) መሆን የለበትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በግብርና ሚኒስቴርና በክልል ግብርና ቢሮዎች ያለው አቅርቦት መር ክላስተር አደረጃጃት ከዚህ አንፃር በሚገባ መፈተሽ አለበት፡፡  በማናቸውም ጊዜ የገበሬዎች ነፃ የኢኮኖሚ ተዋንያንነት፣ አንድ ነፃ የሌላ ክፍለ ኢኮኖሚ ተዋናይ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ባለኝ ምን ላምርት? ለማን ላምርት? ከየት ግብዓት ልግዛ? ለማን ልሽጥ? ወዘተ በመሳሳሉት የመወሰን መብታቸው ከመጠበቅ ጋር የተያያዘም መሆን አለበት፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኤትአይ የምከተለው ፍላጎት መር ነው ስለሚል፣ በአፈጻጸሙም ከግብርና ሚኒስቴርና ከክልል ግብርና ቢሮዎች ኤክስቴንሽን እንቅስቃሴ አንፃር ልዩነት ስላለው ይህ ጉዳይ ይጣራ፡፡ ሁለቱም አካላት አካሄዳቸውን በመሬት ላይ ወጥ በሆነ አፈጻጸም ለመተግበር እንዲቻል፣ በጽሑፍ ተዘጋጅቶ ለልማት ሠራተኞች የሚሠራጭ መመርያ ወይም ማንዋል ይዘጋጅ፡፡ ኤትአይ በቅርቡ ከውጭ ባገኘሁት ዕገዛ በሚል ኤፍፒሲን አደራጅቼ የገበሬዎች ኢንቨስትመንትን በኮርፖሬሽን አደረጃጀት እመራዋለሁ የሚለው አካሄድ በሚገባ ይጠና፡፡ መሬት የግል ባልሆነበትና ከላይ የገለጽኩትን የገበሬዎችን ነፃ የኢኮኖሚ ተዋንያንነት መብት ባልጠበቀ ይዘቱ ይህ ቅዠትና ትርምስ ፈጣሪ፣ በእርሻ መዋቅራዊ ለውጥ ላይ የተመሠረተ ዘላቂነት ያለው ዜጎች በራሳቸው ጥረት የሰፋፊ እርሻዎች ባለቤት እንዳይሆኑ ከውጭ ኃይሎች ጋር የተወሳሳበ ሴራዊ አካሄድ ያለው ይመስላልና፡፡ በሒደት በኢንቨስተርነት ስም ትልልቅ እርሻዎች የውጭዎቹ እንጂ ኢትዮጵውያን እዳይኖራቸው የሚያደርግ አካሄድ ያለው ይመስላልና መቆም አለበት እላለሁ፡፡ በመጨረሻም ምንም እንኳ የይቃወማል ተናጋሪዎችን የመናገር ነፃነት ማክበር ቢገባም፣ ከፖለቲካ ሥራቸው አንፃርም ትክክል ነው ተብሎ ሊገመት ቢችልም፣ ሙያዊ ከሆነ ምልከታ አንፃር ግን ተገቢነት የሌለው መሆኑን ማስገንዘብ እሻለሁ፡፡ 

‹‹መቃወም›› የሚለው የፖለቲከኞች መጫወቻ ቃል ነው፡፡ እኔም ሆንኩ ሌሎች በተቧደነ ፖለቲካ ትብታቦሽ ውስጥ ያልወደቅን፣ በአንድ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ስናነሳም ሆነ በይዘቱም ሆነ በአካሄድ ላይ መሻሻል፣ መስተካካልና መታረም ያለባቸው ነገሮች ካሉ ስንጠቁም ወይም ምክረ ሐሳብ ስናቀርብ እንደ ‹‹ተቃውሞ›› መቆጠሩ ለአገር ዕድገትና ልማት ከመመካካርና አብሮ ከመሥራት አንፃር ቅቡልነት ማግኘት የለበትም፡፡ ይህ  እንኳ ለእኔ ዓይነቱ ከፖለቲካ ቡድን ስብስብ ውሰጥ ለሌለበት ቀርቶ፣ በፖለቲካው ቡድን ውስጥ ያለ ሙያተኛም በሚያቀርበው ትችትና ምክር እንደ ተቃዋሚ ተድርጎ ሊፈረጅ አይገባም፡፡ ፍረጃው ለአገር ዕድገትና ልማት ደንቃራ ወይም አሰናካይ ድርጊት ነው፡፡ እኔ በክላስተር እርሻ አሠራር ላይ ያነሳኋቸው ጥያቄዎችና በዚህ መንገድ በረዥምና በአጭር ጊዜ ከስትራቴጂካዊ ጠቀሜታቸው አንፃር የሰጠሁት አስተያየትና ምክረ ሐሳብ፣ ቀደም ባሉት ክፍሎች እንዳብራራሁት የመቃወም ሳይሆን ለበለጠ ውጤታማነት፣ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ በዜጎች የሚመራ መዋቅራዊ ለውጥ፣ ዘለቄታዊ ዕድገትና ብልፅግና ለማምጣት እንዴት እየተመካከርን መሥራት እንዳለብን ለማሳወቅ ነው፡፡ 

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እኔ ያቀረብኳቸውና ዛሬም ድረስ ከኩታ ገጠም፣ ክላስተር፣ ችብቻቦ፣ የማሳ ስብሳቦሽ፣ ወዘተ አሠራሮች አንፃር የማነሳቸው ሐሳቦችና ማብራሪያዎች በኢኮኖሚክስ ሳይንስ ፖስፕኢ አስተምህሮትና የሥራ ልምዴ ላይ ተመሥርቼ ሲሆን፣ በግብርናው ሳይንስ ውስጥ በሰብሉም ሆነ በእንስሳቱ ልማት ወይም በተፈጥሮ ሀብት፣ አፈርን ጨምሮ፣ በእርሻ ምህንድስና፣ ወዘተ ምርምርና ሥርጭት ውስጥ ባሉ ሙያተኞችም ዛሬ እየተካሄደ ባለው ኩታ ገጠም/ክላስተር እርሻ አሠራር ዙሪያ የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎችና ማሳሰቢያዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም እንደ እኔው አንዳንዶችን በተቃዋሚነት ለመፈረጅ ሙከራ ሲደረግም አስተውያለሁ፡፡ ይህም መቆም አለበት፡፡ በተለይም ሳይንሳዊ በሆነ አመክንዮ ከሥነ ምኅዳር ጥበቃና እንክብካቤ፣ በተናጠልና በተሰባጠር ሰብል እርሻ ክዋኔ አንፃር ከሚቀርቡ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች፣ የጥቅምና ጉዳት መረጃዎች፣ ትንተናዎች፣ ከሥነ ሕይወት ተፈጥሯዊ ውህደትና እሽክርክሮሽ፣ ከሰብልም ሆነ ከእንስሳት በሽታ፣ ተባይ፣ አረም፣ ወዘተ ተፈጥሯዊ መጠባበቅና መከላከል፣ ከተሻሻሉ የእርሻ መሣሪያዎች ቀልጣፋና ውጤታማ አጠቃቀም፣ ከአፈር ጥበቃ፣ እንክብካቤ፣ አሲዳማነት፣ ጨዋማነትና የዘላቂ መሬት አጠቃቃም ሥርዓት፣ በመስኖ ልማቱ አንፃር የሚቀርቡ ትችቶች፣ አስተያየቶችና ምክረ ሐሳቦች መደመጥ አለባቸው፡፡ በዚህ መሰል ርዕሶች የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች አሉና ፖለቲከኞቻችን አደብ ገዝተው፣ ሙያተኞችን ማዳመጥና ለመመከር ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ከእዚህ ጋር አያይዤ  እኔ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሬ፣ በተለይ ደግሞ አጽንኦት ሰጥቼ በ2012 ዓ.ም. ‹‹ኢኮኖሚው ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ›› በሚል ርዕስ በጻፍኩት መጽሐፍ በገጽ 377 ላይ ያቀረብኩትን ‹‹…የመንግሥት ባለሥልጣናትም ዕውቀት ከሥልጣን ወንበር ሥር የሚመነጭ እየመሰላቸው፣ ኢትዮጵውያን ሙያተኞችን ያለማዳመጥ አባዜ ይዟቸው ቆይቷል…፤›› ብያለሁ፡፡

መስፍን (ፕሮፌሰር)፣ በ1986 ‹‹ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ በገጽ 40፣ ‹‹…በእኛ ዓለም ግን ኃይል ዕውቀት ነው፡፡ በሥልጣን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከሥልጣኑ ጋር ሙሉ ዕውቀት ከእግዜአብሔር የተሰጠው ወይም ከጠመንጃው ኃይል የሚፈልቅ ይመስለዋል፤›› ብሎ የጻፈውን፣ በቅርቡ ሪፖርተር ጋዜጣ በእሑድ ኅዳር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትም፣ ‹‹መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!›› በሚል ርዕስ ባወጣው ርዕሰ አንቀጽ ውስጥ ከተካተተው የሚከተለውን ጠቅሼ ይህን ጽሑፌን ደመደምኩ፡፡

‹‹…መንግሥት ሊያዳምጠን ይገባል የሚሉ ዕውቀትና ክህሎት የሰነቁ ወገኖችን ችላ ብሎ፣ በተለመደው ጎዳና መንጎድ ለአገር ፋይዳ የለውም፡፡ የአገር ጉዳይ ሁሌም ምክክርና ትብብር ነው የሚያስፈልገው፡፡ …መንግሥት ጠቃሚ ምክረ ሐሳቦችን ቢያዳምጥ ሕዝብና አገር ይጠቀማሉ!››፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የግብርና ኢኮኖሚስትና ከ40 ዓመት በላይ በማስተማር፣ በምርምርና በማማከር ልምድና ተሞክሮ ያካበቱና የተለያዩ አካዴሚያዊ ጽሑፎችንና መጻሕፍትን የጻፉ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...