Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየፖለቲካ ሰላማችንን የሚጠናወተው ማነው?

የፖለቲካ ሰላማችንን የሚጠናወተው ማነው?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

መጋቢት 2010 ዓ.ም. ይዞ ኢትዮጵያ ውስጥ የፈነጠቀው ለውጥ ያነገበው ዋናው ተልዕኮና አደራ በአገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት፣ በ1966 ዓ.ም.፣ በ1983 ዓ.ም. የጨነገፈውን የፖለቲካ ጥያቄ፣ ማለትም ከፈላጭ ቆራጭነት ወደ ዴሞክራሲ የማለፍ ወይም የመሸጋገር ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ማድረግ ነበር፡፡ የመንግሥት አውታራትን ገለልተኛ አድርጎ የመቅረፅ፣ ለረዥም ጊዜ የአገር ችግር ሆኖ የኖረ ውዝፍ ዕዳ ግን በተለይም በዚህ ጊዜ፣ ሥልጣን ላይ በነበሩና የፖለቲካ ሜዳውን ባጣበቡ ብሔርተኛ ፓርቲዎች ፍጥርጥርና የአደረጃጀት ባህርይ ምክንያት ተዳፍኖ፣ ተጭበርብሮ ቀረ፡፡ ይልቁንም የመንግሥት አውታራትን ገለልተኛ የማድረግ፣ የቡድን/የፖለቲካ መስመር ጥገኛ ሆኖ መቀጠል አይቻልም ማለት፣ ገለልተኛ ሆነው ይታነፁ  ማለት ጥቃት ደረሰበት፣ ጦርነት ተከፈተበት፡፡

በዚህ ምክንያት ከፈላጭ ቆራጭነት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል፣ ወይም በሌላ አባባል ሕግ፣ መንግሥትንና የሥልጣን አካላቱን ጭምር ወደሚገዛበት ሥርዓት የመሸጋገር ደፋ ቀናችን ከብዙ ድርብርብ ግዳጆች ጋር በርካታ አደጋ ካለበት አገርን የማዳን የህልውና ተልዕኮ ጋር ተጣብቆና ያንኑ ያህልም ገዝፎ መጣ፡፡ ከዚህም የተነሳ ላለፉት ሁለት ዓመታት ዕልቂት ያመረተ፣ በአገር ህልውና፣ በሕዝብ ነፃነት ላይ አደጋ ያስከተለ ጦርነት ውስጥ ነበርን፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትና በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል ግጭትን በቋሚነት በመግታት አማካይነት ለዘላቂ ሰላም የተደረገ ስምምነት (ይህ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የተደረገው ስምምነት የይፋ ስምና መጠሪያ ነው) መፈረሙና ወዲያውኑም ከዚያው ቀን መንፈቀ ሌሊት ጀምሮ ሥራ ላይ መዋሉ፣ ተኩስ፣ ግጭትና ነውጥ መቆሙ፣ ትጥቅ የመፍታት/የማስፈታት ከባድና ሊታመን ይችል ያልነበረ ሁኔታና ውለታ ያለበት ስምምነት አፈጻጸም አሁንም ድረስ (ከስድስት ሳምንት በላይ/ሰባት ሳምንት ያህል) ያላንዳች ኮሽታ መቀጠሉ ለኢትዮጵያ ታላቅ ዕድልና ድል ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህንን የሰላም ስምምነት ስናከብር ክብር ሰጥተን፣ የከበረ ፍቅራችንን እየገለጽን እንደ ዓይን ብሌናችን ከጥንቃቄ ጋር ስንንከባከብ ተኩስና ነውጡ ማቆሙ፣ የአገር መናጥ መገታቱ በገዛ ራሱ ምክንያት የሰላምን ትርፍ ያሳያል፡፡ ዕርዳታ በተሻለ መጠን መድረስ ጀመረ፣ ሰው እርስ በራሱ መገናኘት ቻለ፣ የእርስ በርስ ወሬ መስማት ቻለ ማለት የስምምነቱ አዝመራ ነው፡፡ በአገር ህልውና ላይ የተንጠለጠለው የ‹‹ጠላትነት›› ጎራዴም ማስፈራሪያነቱ ትርጉም እያጣ መጥቷል፡፡ እጅግ በጣም ብዙ ቅጥር አዝማሪ፣ ጋዜጠኛ፣ ምሁር፣ ሚዲያ፣ ቲንክ ታንክ፣ እንደራሴ (ይህ ሁሉ ቅጥር ነው) የሚያጅበው/ያጀበው የነበረውን በማዕቀብና በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያን እነቁልኝ ይል የነበረውን ኡኡታና ክስ አጠወለገ፣ የምዕራባውያን አድራጊ ፈጣሪዎችንም (እንደ ፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር) ያሉትን ‹‹ምስክርነት›› ጨምሮ እነዚህ ሁሉ ከእነ ተቋሞቻቸው ኢትዮጵያን ለመሰቀዝ ሰበብ እንዲያጡ አደረገ፡፡

ስምምነቱ የኢትዮጵያ ጠላቶችና ቅጥር የ‹‹ሰላም ተቋም››ዎቻቸው፣ እንዲሁም የኪራይ ሚዲያዎቻቸው፣ ወኪል ነገረ ፈጆቻቸው ‹‹የእርስ በርስ ጦርነት›› እያሉ ከሚጠሩት ከውስጥ ጦርነት ከመገላገሉም በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያን መንግሥት ብቻ ሳይሆን አገረ ኢትዮጵያን ራሷን በማዕቀብ ለማንበርከክም፣ በወታደራዊ ጣልቃ ገብነትም ለመበርገድና ለመበርቀቅ ይፈልግ የነበረውን ሰበብ አስባብና ቀዳዳ ውድቅ ቢያደርግም፣ እንደ ዶክተር ዮናስ ብሩ ያሉ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ‹‹የቆረቡ›› የኢትዮጵያ ተቆርቋሪ ነን ባዮች ሳይቀሩ፣ የ‹‹ኖ ሞር›› ትግል ጅልነትና እንከፍነት እንዴት አድርጎ ያለ ዓለም አቀፋዊ ጣልቃ ገብነት እንዳስቀረን ሲከራከሩ ሁሉ ሰምተናል፡፡ በዚህ ስምምነት መፈረም ማግሥት መልዕክቱ ተደጋግሞ እንደተገለጸውና ግልጽ እየሆነ እንደመጣው፣ በሰው ልጆች መብትም ሆነ በሰብዓዊ ርኅራኄ ስም ለጦረኞቹ ባለ ብዙ መልክ ዕገዛ ሲሰጡ የነበሩ አገሮችና ተቋማት በድጋፋቸው የትግራይን ሕዝብ ስቆቃና የደም ግብር ምን ያህል እንዳቃለሉና እንዳባባሱ በሒደት ቁልጭ እያለ መጥቷል፡፡ የሰው ልጆችን መብትና ክብር ከመንከባከብ አንፃርም ሆነ ድኅረ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተመድ ቻርተር፣ በ‹‹ዩኒቨርሳል ሒዩማን ራይትስ ዴክላሬሽን›› አማካይነት የተዘረጋውን ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ረግጠው፣ በራሳቸው ጠባብ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የተኩትም በአርዓያነት የምንጠቀስና የምንታወቅ እያሉ ኢትዮጵያን እንደ ደመኛቸው ቆጥረው የቆዩ አገሮችና ተቋማትም፣ በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ እንኳን የፍትሕነታቸውን ልክ እያወቁት መጥተዋል፡፡

በእኔ በኩል እውነቱን ለመናገር የዚህ የሰላም ስምምነት ይዘት ‹‹የሰማይ መላዕክት የምድር ሠራዊት ሊያስቡትና ሊውቁት…›› ከሚችበት በላይ አስደናቂ ነው፡፡ መጀመርያ የስምምነቱ ማዕቀፍ የአገር ሕገ መንግሥት ነው፡፡ የዚህ ምክንያት ድርድሩንና ስምምነቱን የመራው የአፍሪካ ኅብረት መተዳደሪያና ዋና የበላይ ሕግ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል መለወጥን ስለሚያወግዝና ስለሚከለክል ብቻ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥትንና በእሱ መሠረት የተቋቋመውን ሥርዓት የማስጠበቅም ሆነ የመለወጥ ሥራ በሕግ መሠረትና በሕዝብ ፈቃድ መሠረት መሆን አለበት ማለት፣ ዛሬ የሠለጠነው ዓለም የጥበብ መጀመርያ መሆኑ ጭምር ነው፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በስምምነቱ ድንጋጌዎች ላይ ኢትዮጵያ አንድና አንድ ብቻ የመከላከያ/የታጠቀ ኃይል አላት ማለት የውለታቸው ዋልታና ማገር ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ለፈረሙት ለፕሪቶሪያው ስምምነት ምሥጋና ይግባውና ያን ያህል ውድ ዋጋ ባስከፈለ ስምምነት ‹‹የኢፌዴሪ የመከላከያ ኃይል አንድ ብቻ ነው›› ተብሎ ሲወሰን፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ የማሻሻያ ለውጥ መደረጉ ወይም የሕገ መንግሥት ትርጉም መስጠቱ አይደለም፡፡ መጀመርያ ነገር ይህንን ሕገ መንግሥት መኗኗሪያ አለማድረጋችሁ ነው ችግሩን ያመጣው ማለት ነው፡፡ የብዙ ፓርቲ ውድድርን ማበብና መንተርከክ፣ በሕዝብ ፍላጎትና ባልተጭበረበረ ምርጫ የሕዝብ እንደራሴያዊ ምክር ቤቶችን ማደራጀት የሚያስችል ሕይወት ያለው ሕገ መንግሥት ሲጀመር ብዙ ተባዙ፣ አማራጭም ይዛችሁ ኢትዮጵያንም ሙሏት ተብለው ነፃ የተለቀቀ የምናማርጣቸው ፓርቲዎች ከሁሉ አስቀድሞ መሠረታዊውንና መንዕሱን የዴሞክራሲን አደረጃጀትና አኗኗር ራሳቸው በውስጣቸው የሚኖሩ መሆን አለባቸው፡፡ በገዛ ራሱ በቡድኑ ወይም በፓርቲ ውስጥ የተሻለ ሐሳብንና የተሻለ ችሎታን በክርክር የማንጠር፣ በድምፅ የመለየት እስትንፋስና ፍጥርጥር የሌለው ፓርቲ ፓርቲ ሆኖ አይኖርም፣ አይመዘገብም ብቻ ሳይሆን ፓርቲ ተብሎ አይጠራም፡፡ እንኳን ሊታጠቅ፡፡ በዚህ ምክንያት ስምምነቱ የሚቃኘውና የሚገራው ትጥቅ እንዲፈታ የተወሰነበትን አንድ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፣ ሁላችንምና ‹‹ሁልሽንም›› ነው፡፡ ለሥልጣን የሚወዳደርንም፣ ከሥልጣን የተጠጋን ፓርቲ ሁሉ ነው፡፡

ስምምነቱ ገና በሚቀጥሉት የተፈጻሚነትና ተፈጻሚነቱን በዕውንና ከምር በሚፈታተኑት የትግበራ ዘመኑ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ በገዛ ራሷ መንግሥትና በጎረቤት አገር ላይ የሚተኩስ የታጠቀ ቡድን ብቅ የማይልባት የማይበቅልባት አገር ሆኖ እንድትገነባ ምን ማድረግ አለባት? ባለፉት 27 እና 30 የሕገ መንግሥታዊነት ዓመታት ውስጥ ይህ ሳይሆን የቀረው በምን ምክንያት ነው? የሚሉ ፈተናዎች አሉባት፡፡ ውሉ በአንቀጽ 1.10 የሥር የመሠረት ልዩነቶችን ስለመፍታትና ለዚህም ስለሚያስፈልገው ቁርጠኝነት፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ችግሮች የሚፈቱት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ደጋግሞ የሚናገረው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ላይ የሚተኩስ፣ ‹‹የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል አንድ ብቻ ነው›› በተባለው ብቸኛ የታጠቀ ሠራዊት ላይ የሚተኩስ፣ እሱኑ ‹‹ማስከዳት››፣ ጎርዶና ሰንጥቆ የእኔ ነው ማለት ጭምር የሚችል ቡድን ‹‹ማፍራት››ና ያን ያህል ገንግኖ ‹‹ወራሪ›› እስኪሆን የውስጥ ወረራ እስኪፈጸም ድረስ ዋጋ ቢስ የሆነችው በየትኞቹ ብልሽቶቻችን ምክንያት ነው? የአገር ታላቅ የቤት ሥራና አፍሪካንም፣ የተቀረውንም ዓለም ማስተማርና ማገልገል የሚገባው ትምህርት ነው፡፡ የሥልጣን አያያዛችን ነው? የመንግሥታዊ ዓምዶች አወቃቀራችን ነው? ፓርቲያዊ አደረጃጀታችን ነው? ስምምነቱ አፈጻጸም ውስጥ መማርና መቀመር ያለብን ተግባር ነው፡፡

የስምምነቱ አፈጻጸም እስካሁን እንደምንሰማው ከተዋዋይ ወገኖችም ሆነ፣ ያኔም በጦርነቱ ወቅት ‹‹ያገባናል›› ከሚሉት ሁሉ ይህንን ያህል ለዜና የሚበቃ ችግር አጋጠመው ሲባል አልሰማንም፡፡ ስምምነቱን አደጋ ላይ ድንገት እንዳይጥል የሚፈራው አዳናቂዎችም ይሁኑ፣ ሲጀመርም ስምምነቱ ከመሬት ሳይነሳ እንዲከሽፍ የሚፈልጉ የሚያነሱት የ‹‹ባዕድ ሠራዊት››ና ወይም ‹‹የአገር መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ ኃይሎች›› የሚባሉትን ጉዳዮች እያነሱና እያቁለጨለጩ ነው፡፡ አንዳንዴ ደህና ሆኑ ስንላቸው ድንገት ‹‹አውሬ›› የሚሆኑና በባህርያቸው ግልብጥብጥ የሚሉ ወገኖች፣ የስምምነቱን የትግበራ ሒደት ራሱን አድንቀው/ባያደንቁም በደህና እየሄደ ነው የሚለትም በዚያው መግለጫቸው፣ ሆኖም ግን የተጠያነት ጉዳይ ‹‹ለዓለም አቀፋዊ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን›› ክፍት የመሆኑ ጉዳይ ‹‹ያሳስበናል›› እያሉ ስንፈልግና በፈለግነው መጠን ሁሉ ገና ‹‹አልተፋታናችሁም›› ብለው ያስፈራሩናል፡፡

በዚህ ሁሉ መካከል የመንግሥትም ለሕዝብ መግለጫ የመስጠት፣ ኢንፎርሜሽን የመመገብ ሥራ በዚህ አስደናቂ የዝግጅትና አመርቂ ውጤት በተገኘበት ድርድር አፈጻጸም ውስጥ አጣማጅ አቻ ትጋት ሲደረግበት አናይም፡፡ ይህ ሁሉ የመንግሥት ጎዶሎና ድክመት ግን ስምምነቱን ራሱን ጠልፎ ከመጣል በርትቶ ከሚታገለው አፍራሽ ተግባሩ ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡

ከዚህ ቀደም በዚሁ የሁለት ዓመት ጦርነት ውስጥ ተደጋግሞ እንደተገለጸው፣ በኢትዮጵያ መንግሥት አንፃር ጠላት የሚያካሂው ጦርነት ባለሁለት ምድብ ነው፣ ወይም ነበር፡፡ የኦነግ ሸኔ ዓይነቶቹ የዋናው ተዋጊ/ባለጦር ሎሌዎች የሚና ምድባቸው እዚህም እዚያም ውር ውር እያሉ እየ‹‹ወረሩ›› ጭምር፣ እየገደሉም እየጨፈጨፉም በማውደም የዕገታ ገንዘብ በመዝረፍ የውንብድና ተግባራቸው፣ አገራዊ የህልውና ርብርቡ ላይ ቀልቡን ያሳረፈውን የሕዝቦችና ይህንኑ የአገራዊ ርብርብ ዋና መገናኛውን ደግሞ መንግሥት ላይ ያደረገውን ኃይል ደኅንነት እንዳይሰማውና እንዲማረር አድርጎ ቀልቡን ማሳት፣ የስሜት ግለቱን መስለብ፣ እንዲያም ሲል ርብርቡን መበታተን ነው፣ ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን ሁኔታ የሚጠቀመው ዋናውን የጦርነት ሥራ የማቀናበሩ ሥራ ደግሞ የማን እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ የሥራ ባለድርሻ ዓላማና ግብ ደግሞ ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ሥልቶችን/ማደናገሪያዎችን ተጠቅሞ የውጭ ወታደራዊ ኃይል መትከል ቀዳሚ ፍላጎቱ ነበር፡፡ አሁን ሰላም ሲወርድ፣ ተኩስና ነውጥ በማቆም የስምምነቱ ተፈጻሚነት ምክንያት ዋናው የጦር ግንባር ላይ አካትቶ የጠመንጃ/የብረት ትግል ላንቃ ሲዘጋ ኦሮሚያ ምድር ‹‹ምድር ቁና›› እንድትሆን የሚፈለግበት ምክንያት ዋናው ሕመማችን በተሰጠው ሕክምና ላይ አፍራሽና ተቃራኒ ውጤት ለማስከተል መሆኑን መረዳት አዳጋች ነገር አይደለም፡፡

ይህንን መርጠርጠና በተገቢውም የማጣሪያ ዘዴ ምርምሮና አጣርቶ ምላሹ ላይ ለመድረስና ይህ ቢሆን ያ ብሎ ማስተንተን፣ ስምምነቱ የሚደነግገውንና ከተዋዋይ ወገኖች የሚፈለገውን የቅን ልቦና ወይም የበጎ መንፈስ ስያሜ አሽቀንጥሮ መጣል አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ተዋዋይ ወገኖች እስካሁን በየጊዜው ከሚያቀርቡት ቁጥብና ውስን ‹‹ፕሮግሬስ ሪፖርት›› አንፃር እርስ በርስ ሲካሰሱና ክፉ ሲነጋገሩ አልሰማንም፡፡ በግራ ቀኙም በኩል ‹‹አፈንጋጮች›› ወይም አፈንጋጭ የሚባሉ መኖራቸውን ተዋዋይ ወገኖች ራሳቸውም አይክዱም፡፡ ይህም እውነት መሆኑንና አለመሆኑኑ ከመፈተሽ ነፃ የሆነ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለማንኛውም ግን ስምምነቱ ውስጥ የተጠመደ ባለ ከፍተኛ ዋስትና ነው የተባለው ናይሮቢ ዴክላሬሽን ውስጥ እመጫት የተጨመረው ወይም የተፍታታው የውጭ ኃይሎችና የአገር የአገር መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ ኃይሎች የሚለው አዲስ ነገር የተለፈገውን ያህል ሳይፈነዳ/ፈንድቶ ሳያተራምስ በመቅረቱ ኅዳር ወር መጀመርያ ላይ፣ ኅዳር ወርን አንድ ብሎ ጀምሮ ኦሮሚያን ማተራመስ፣ ኦሮሚያን ዋናው አጀንዳው ያደረገ አዲስ የቤት ሥራና የርብርብ ግንባር ተፈጠሩ፡፡ ይህንን ፓተርን ወይም ደብዛ ከ2014 ዓመታዊ ሪፖርት ቀጣይ ወይም ተከታይ ከሆነው ወይም ‹‹ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት ይፋ ከተደረገበት ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም.›› የሚጀምረው የኦሮሚያ ክልል የኢሰመኮ የኅዳር 2015 ዓ.ም. ሪፖርት ማየት አይቻልም ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን የኅዳርን ወር አንድ ክፍለ አገር/የአገር ክፍልና በእሱም አማካይነት መላውን ኢትዮጵያን ያመሰና ያተራመሰ ጉዳይ ጥርጣሬ ዝም ብሎ ውድቅ የሚያደርግ አይደለም፡፡

ተራ ጥርጣሬም ሆነ መላምት፣ ይህ ግን የእኔ ብቻ አይደለም፡፡ ባለፈው ሳምንት ማለትም የ2015 ዓ.ም. ኅዳር ወር መጨረሻ ላይ እየበረታ የመጣው፣ በተደረገው የሰላም ስምምነት ውጤት ላይ ጥላውን በማጥላት ላይ ብቻ ሳይወሰን፣ ጥቅምት 23 ቀን በተፈረመው የዘላቂ ሰላም ስምምነት አማካይነት መተማመኛ ያገኘውን የአገሪቱን የፖለቲካ ሰላም የናጠው የኦሮሚያ/ወለጋ ነገር የአገር አደጋና አጀንዳ በመሆኑ ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች/ጠባቂ ድርጅቶች አቋማቸውንና ሐሳባቸውን ሰጥተው ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ኢዜማ ነበር፡፡ የዚህ ፓርቲ መግለጫና አቋም ይፋ በተደረገበት የጋዜጣ ስብሰባ መድረክ የተገኙት ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በዚህ ጉዳይ የፓርቲያቸው አቋም ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ወለጋ ውስጥ ለሚፈጸመውና እያዳገመ ላስቸገረው ዕልቂት ‹‹ኮንቴክስት›› (ዓውድ) ይፈልጋል ብለው ሲናገሩ፣ ለምንድነው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በዚያ ጊዜ ሁሉ ጦርነቱ ሲያበቃ፣ አንዱ ወገን ሲሸነፍ፣ አሁን ደግሞ የፕሪቶሪያው ስምምነት በተፈረመ በሳምንቱ እንዲህ ያለ ነገር ወለጋ ውስጥ ወይም ሌላ ቦታ የሚመጣው? ብለው ጠይቀው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እዚህ ላይ መንቃትና ይህን ነገር ማወቅ አለበት ብለዋል፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘውም የመንግሥትን ተግባርና ግዴታ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ ነገር አገረ መንግሥቱን የሚያናጋ እንደሆነ፣ ተቀባይነትም እንደሌለው እየተናገረ፣ እንቅስቃሴዎችም እያደረገ፣ ሥራ ላይ እንደሆነ እየተናገረና እንደሚሠራም ጭምር እናውቃለን ብለው፣ ይህንን ግን ለተራው ሕዝብ በሚገባው መልክ ማቅረብና መንግሥት እንዳለ ይህንንም እንደሚያስቆም ማሳየት፣ የሚወሰዱትንም ዕርምጃዎች መናገር እንዳለበት፣ በሥራ እናሳያለን ብሎ ነገር የማኅበረሰቡን እምነት/መታመን እንደሚሸረሽር ገልጸው ተናግረዋል፡፡

የአገር ሆድ ቁርጠት ሆኖ የቆየው መጀመርያ ስምምነት ላይ ይደረሳል ወይ? ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላስ ለስምምነቱና ለአፈጻጸሙ መታመንና መገዛት ቀላል ይሆናል ወይ ነበር፡፡ የሚገርምና ያልተጠበቀ ውጤትና ስምምነት ላይ ከተደረሰና ውል ሆኖ ከተፈረመ በኋላ ግን ተከታዩ ሥጋት አንድ ወይም ሌላው ድርድሩ ላይ ያጣውን፣ ስምምነቱ አፈጻጸም ላይ ይጫወትብን ይሆን ወይ ነበር ተከታዩ አሳሳቢ ጉዳይ፡፡ ከሁለቱም ተዋዋይና ፈራሚ ወገኖች ዋና መምርያ የሚመጣውና የሚወጣው የአፈጻጸምና የትግበራ መረጃ፣ እንዲሁም አግባብ ካላቸው ባለጉዳዮች የሚሰማው ወሬ፣ ምንም እንኳን ቁጥብና በጣም ‹‹ቆንቋና›› ቢሆንም ቢንያስ ቢንያስ ስምምነቱ አደጋ እንዳላጋጠመው፣ ፈረሰ፣ ተበላሸ፣ አለቀ፣ ደቀቀ የመባል ዕጣ ፈንታ ላይ እንዳልወደቀ፣ ይልቁንም በተቃራኒ እደግ ተመንደግ እየተባለ እንደሆነ የአሜሪካና የአፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ሳይቀር የሚነገር ሀቅ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርድሩ በመዘጋጀት ብቁ ሆኖ በመገኘት፣ እንዲሁም ድርድሩንና ስምምነቱን በድል ለመቀዳጀት ያደረገው ጥረትና ትጋት የአገር መኩሪያ ቢሆንም፣ የስምምነቱን አፈጻጸምና አተገባበር የሚመለከተው የ‹‹ሙያ በልብ›› ‹‹አቅጣጫው›› ወይም ‹‹መመርያው›› ግን እዚህ ላይ በጭራሽ አልሠራም፡፡ እዚያ ላይ የሠራውም ይህ ‹‹ዝምታ››ው ስለመሆኑ መወራረድ አይቻልም፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የመንግሥት ክፍተት/ጎዶሎ መሆኑ ዛሬም ቀጥሏል፡፡

መንግሥትን የመታፈሪያነትና የመኩሪያነት ማማ ላይ ከፍ ያደረገው፣ በድርድሩ ዝግጅትና ሒደት ላይ የተደረገው (አስቀድሞ ከምጣዱ የሚታወቅ ባይሆንም) ልበ ሙሉነትንና ብልህነትን ያጣመረ የአያያዝ ጥበብ ነው፡፡ የአፍሪካውያንን ጉዳይ በአፍሪካውያን እፈታለሁ መርህ እታመናለሁ መባሉ፣ በዘህ መርህ መሠረት በኦባሳንጆ የተጀመረውን ጥረት አክብሮ እንዲቀጥል ማድረጉ፣ ያለ ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር እገባለሁ ማለት በቅድሚያ ተኩስ ማቆም የሚል ጥያቄን በቅድመ ሁኔታነት ውድቅ ያደረገ መሆኑ፣ ይህ ሁሉ ደግሞ ከሌሎች ጋር ሆነው የኢትዮጵያን አንድነትና ሕገ መንግሥቱን መነሻውና መሠረቱ ማድረጉ፣ በአጠቃላይ የድርድሩ የማዕቀፍ ግቢ ከመነሻው የሕወሓትን አገር የመሆን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የታጠቀ ኃይል መሆን፣ ባለመከላከያ ኃይልነት ጭምር ኢሕገ መንግሥታዊ አድርጎ መጀመሩ ነው፡፡ እዚህ ላይ የተመሰከረውና ፈርዶብን ደጋግመን የገለጽነው የአገር መኩሪያና መታፈሪያ የሆነው ብልህነትና መንግሥታዊ አያያዝ ግን የተደረሰበት ስምምነት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ አደጋ የተጠመደበት መሆኑን ማወቅና መረዳት፣ ይህንንም ለሕዝብ ማሳወቅና ማስረዳት አለመቻል ድረስ መንግሥት ‹‹ዝርክርኩ›› ወጣ፡፡ አሜሪካ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለውን የአሜሪካና የአፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ አጋጣሚ በማድረግ በታኅሳስ ወር ሁለተኛ ሳምንት (በዚህ ሳምንት) የተደረጉት የትግራይ፣ የኦሮሞና የአማራ ብሔርተኞች የተናጠል የተቃውሞ ሠልፎች ለየብቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን የየብሔረሰቦቻቸው ጠላት አድርገው ኮንነዋቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው በ‹‹ኖ ሞር›› ንቅናቄ የተሳተፈው ዳያስፖራም አዘጋጅቶት የነበረውን የድጋፍ ሠልፍ መሰረዙን ወይም በእሱ ላይ ማስተካከያ ማድጉን ሰምተናል፡፡

ይህ አላንስ ብሎ ደግሞ፣ ማለትም የሰላም ስምምነቱን ከየት የሚመጣ አደጋና ጠላት እንዴት አድርጎ ‹‹አሳቻ›› ቦታና አካባቢ ጆሮ ግንዱን ብሎና ማጅራቱን መትቶ ሊያጨናግፈው እንደሚችል፣ አርቆ ማሰብና መጠርጠር አቅቶን መከላከል ያቃተን መሆኑ ሳያንስ፣ በዚህ ረገድ መንግሥት ለሕዝብ ያለበትን ሪፖርት የማድረግ፣ የማስረዳትና ሲጠየቅም የቁም መልስ የመስጠት ኃላፊነትንና የጠያቂነትን ግዴታ የመወጣት ጀብድ ሳይሆን ተራ ግዳጅ መወጣት አለመቻላችን ሳያንስ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ውስጣቸው ፈንጂ የታጨቀባቸው የ‹‹ቋንቋ››፣ የ‹‹ባንዲራ››፣ የ‹‹መዝሙር›› አሻንጉሊቶች እየዘራን ነው፡፡

ኢትዮጵያ የብዙ ቋንቋዎች አገር መሆኗ የታወቀ ነው፡፡ ባለብዙ ቋንቋዎች ባለሀብትነቷም የኢትዮጵያ ብቸኛና አምሳያ የሌለው ፀጋ አይደለም፡፡ ይህንን ሀብት፣ ፀጋና ዥንጉርጉርነት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተቻለ መጠንና የሚቻለውን ያህል እያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ የሚታይ ሀብት ማድረግ አለብን፣ ይቻላልም፡፡ የኢትዮጵያ የባህል፣ የታሪክና የቋንቋ ሀብታችን ማጥናት፣ ማደረጃት ለዛሬና ለነገ ሕይወት ባላቸው የቅርስነትና የመኗኗሪያነት ፋይዳ የሚሸጋገሩ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ አዲሶቹ ወጣቶች የአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊነትን ያሰበ ብዙ ቋንቋዎች የሚያውቁ አድርጎ ማሳደግና ማስተማር የግለሰቦችን ሰብዕና ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊ ህልውናችንንም መሠረት ነው፡፡ በዚህ አቅጣጫ መሥራት አንድ ነገር ነው፡፡ ከዚህም ተነስቶ ለምሳሌ በመላ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ኦሮሚኛ ቋንቋ መጠቀምን ተጨባጭ እንዲሆን መሥራት፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ እዚያው የሚወስድ መንገድ ነው፡፡ ይህን በማድረግ ፈንታ አዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሚያ ክልልን መዝሙር ዘምሩ፣ የኦሮሚያን ባንዲራን ስቀሉ ብሎ ውዝግብ የሚያስነሳ ቀሽምና አገር የሚያተራምስ ድግስ አሰናድቶ ለሕዝብ እንካችሁ ከ‹‹ጠብ ያለው በዳቦ›› በላይ ‹‹ጦር አምጣ›› ማለትና ለዚያም ግብ መሥራት ነው፡፡       

በተለይም ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግርና የለውጥ ሥራ ገና በጮርቃነቱ ጠንቀኛ ተቃውሞ አጋጥሞት ጦርነት ተከፍቶበት፣ በዚህም ምክንያት የአገር ህልውናን የማዳን ሥራ ሁሉንም ነገር አጠቃልሎና ቅድሚያውን ይዞ ከብዙ መስዋዕነትነት በኋላ የሰላም ስምምነቱን የመሰለ ድል ከተጎናፀፈ በኋላ ሕግ የማስበርን፣ እንዲሁም ሕግ ማክበርንና ለሕግ ተገዥ መሆንን መንግሥትን ራሱን የሚመለከትና ይህንንም በተግባር ማረጋገጥ ቀዳሚው ተግባሩ መሆን ባለበት ጊዜ፣ እነዚሁ የመንግሥት ባለሥልጣናት ራሳቸው ቅደም ተከተል እየታማታባቸው፣ የዴሞክራሲን የራሱን መደላደል ቅድሚያ የሚፈልጉ/የሚጠይቁ ጉዳዮችን አሁን ዛሬ ካልተፈጸሙ ሞቼ እገኛለሁ ማለታቸው፣ የሚሞትለትን ዴሞክራሲን የማደላደልና ገለልተኛ ተቋማትን የመገንባት ተግባር ከመግደል የተለየ አይደለም፡፡

አዲስ አበባ ራሱ ውስጥ ብዙ አከርካሪና በሕገ መንግሥቱ በራሱ ማዕቀፍ ውስጥ የሚፈቱም፣ አለዚያም ሕገ መንግሥቱን በማሻሸልም አስቀድሞ ነባራዊና ባለቤታዊ ለውጥና ዝግጅት የሚሹ በርካታ አወዛጋቢም አከራካሪም የሆኑ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የከተማው ስም አንዱ ነው፡፡ ወሰን ሌላው ነው፡፡ ‹‹ዕድሜ›› ሕገ መንግሥቱን አምጦ ለወለደው መርዘኛ ፖሊሲና የፌዴራል አባላት/አካላት አከፋፈልን የየብቻ መሬትና የርስት የባለቤትነት ማረጋገጫ ማድረግ ድረስ በመማገጣችን፣ ዛሬ የትም ሌላ አገር በጭራሽ ስለማይገባ ልዩ ጥቅም ማውራትና መከራከር ድረስ ዘቅጠናል፡፡ እነዚህን (እነዚህ ብቻ ግን አይደሉም) የዴሞክራሲን የራሱን በሚገባ መደላደል የሚጠይቁ ጉዳዮች በቀጠሮ ማሳደር አቅቶን፣ ሌላው ቀርቶ ‹‹ካሪኩለም›› የመዋስ፣ የመቅዳት ተራ ወግ ገድዶን (ወይም እንዲህ ያለ ሰበብና ማመካኛ እየሰጠን) አገር የሚያተራምስ የእርስ በርስ መጨራረሳችንን የሚደግስ አደጋና ቀውስ ውስጥ ገባን፡፡

በቋንቋ መማር መብት ነው፡፡ እንዲያውም የምንፈራው መንግሥት አቅሜ ይህን አይፈቅድም ብሎ ወገቤን እንደይል ነው፡፡ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርን ግን ባንዲራ ከማውለብለብ ወይም ከማክበር፣ መዝሙር ከመዘመር ጋር ማምታታትን ይህንንም ባላዋቂነትና በድንቁርና ላይ ማመካኘት የመልካም አስተዳደር ወግ አይደለም፡፡ በየደረጃው የሚገኘው አስተዳደር (የፌዴራልም የከተማውም) ሰበብ ሳያበዛ ክንብንብና ሽፍንፍን ሳይሻ፣ የቋንቋ (የንግግር ማለቴ ነው) ሆነ የሎጂክ ማምታታት ውስጥ ሳይገባ ጥፋቱን ማመን፣ ይቅርታ መጠየቅ ወደ ነበረበት ቦታ መመለስና እነዚህን ጥያቄዎች የዴሞክራሲያችንን መደላደልና የገለልተኛ ተቋማትን የመትከል ሥራችን የተዋጣ እስኪሆን ድረስ በቀጠሮ ማቆየት ይኖርበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...