Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኒያላ ኢንሹራንስ ያልተጣራ 263 ሚሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኒያላ ኢንሹራንስ በ2014 ሒሳብ ዓመት ያልተጣራ 263 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፣ ጠቅላላ ጉባዔው ደግሞ የኩባንያውን ካፒታል ወደ 2.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ተቀብሎ አጽድቋል።

የኩባንያው ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ቢርቦ ባለፈው ሐሙስ ታኅሳስ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው የኢንሹራንሱ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደተናገሩት በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በአገሪቱ ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውሶች የተከሰቱ ቢሆንም ኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ችግሮችን ተቋቁሞ 263 ሚሊዮን ያልተጣራ ትርፍ ማስመዝገብ ችሏል፡፡ የተገኘው የትርፍ መጠንም ከቀዳሚው ዓመት ከ36 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ 

የቦርዱ ሊቀ መንበር አያይዘውም በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው የትርፍ መጠን በኩባንያው ታሪክ ውስጥ እስካሁን ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡንና ይህም ሊሆን የቻለው ኩባንያው አዳዲስ ስትራቴጂዎችንና ሥልቶችን በመከተሉ እንዲሁም የደንበኞችን ፍላጎት በማጥናት አዳዲስ የኢንሹራንስ አገልግሎቶችን ለገበያ ማቅረብ በመቻሉ ነው ብለዋል፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ 909.4 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ34.1 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ ከዓረቦን ገቢው ውስጥ 723.2 ሚለዮን ብር ወይም 97.5 በመቶ የሚሆነው የተገኘው ከጠቅላላ መድን ሽፋን መሆኑንም ገልፈዋል።

ከአጠቃላይ መድን ሽፋኑ 196.2 ሚሊዮን ብር የውል ሥራ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን ይህም መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ35.6 ሚሊዮን ብልጫ ማሳየቱን የቦርድ ሊቀመንበሩ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡ 

በተመሳሳይ ሁኔታ በሕይወትና በጤና የኢንሹራንስ ዘርፍ 186.2 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ገቢ ያገኘ ሲሆን ፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 64 በመቶ ከፍ ብሎ መታየቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም የሕይወት መድን ተካባች (Life Fund) 174.7 ሚሊዮን ብር ሊደርስ መቻሉንም በሪፖርታቸው ያመለክታል፡፡

የኩባንያው ጠቅላላ የሀብት መጠን በ2013 መጨረሻ ላይ ከነበረበት 2.4 ቢሊዮን ብር በ21 በመቶ በማደግ ሦስት ቢሊዮን ብር መድረሱንም አመልክተዋል።

‹‹ኒያላ ኢንሹራንስ አመርቂ የሚባል ውጤት አስመዝግቧል›› ያሉት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ ሞላ በበኩላቸው በሒሳብ ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ሊገኝ የቻለው ኩባንያው በተከተለው ጥንቃቄ የተሞላበት የሥጋት አመራር፣ የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ አዳዲስ አገልግሎቶችን በገበያ ላይ በማዋል አዳዲስ ደንበኞችን ማፍራት በመቻሉ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ እንዲሁም ደንበኞችን ማዕከል ያደረጉ ሌሎች ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት በመቻሉ በመድን ሥራ ሽፋኑም ሆነ በትርፍ ምጣኔው ላይ ዕድገት ሊታይ ችሏል ብለዋል፡፡ 

ኩባንያው አገልግሎቱን ለማስፋትና ሊሠራቸው ያቀዳቸውን ሥራዎች አስመልክቶም በቀጣይ ዲጂታላዜሽንና የኢንሹራንስ ቴክኖሎጂዎችን መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ደንበኞቹን ለማገልገል መዘጋጀቱን አመልክቷል፡፡ ኩባንያው የዲጂታል ኢንሹራንስ አገልግሎትን በማቅረብ እስካሁን የኢንሹራንስ ገበያው ላላቀፋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚሆንበትን መንገድ በመቀየስ አገልግሎቱን ለማቅረብ እየሠራ መሆኑንም አቶ ያሬድ ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ከዚህ ቀደም በነበሩት ተከታታይ ዓመታት እንዳደረገው ሁሉ ከ2014 ዓመት የተጣራ ትርፍ ላይ 126 ሚሊዮን ብሩን የኩባንያውን ካፒታል ለማሳደግ እንዲውል በጠቅላላ ጉባዔው አስወስኗል፡፡ ይህም የኩባንያውን ጠቅላላ የተከፈለ ካፒታል መጠን ወደ 830 ሚሊዮን ከፍ ያደርገዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኩባንያው በኢንሹራንስ ገበያው ውስጥ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል እንዲችል አጠቃላይ ካፒታሉን ወደ ብር 2.5 ቢሊዮን እንዲያደርስ በዕለቱ ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አስወስኗል፡፡ በውሳኔው መሠረትም ተጨማሪ ካፒታሉን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ እንዲጠናቀቅ በጠቅላላ ጉባዔው ስምምነት ተደርሷል፡፡ 

ኒያላ ኢንሹራንስ ካፒታሉን ወደ 2.5 ቢሊዮን ብር ውሳኔ ማሳለፉ በኢንዱስትሪው ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሁለተኛው ከፍተኛ ካፒታል የሚኖረው የኢንሹራንስ ኩባንያ ያደርገዋል፡፡ 

አሁን ካሉት የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛ የሚባለውን የካፒታል ማሳደግ ውሳኔ ያሳለፈው አዋሽ ኢንሹራንስ ሲሆን፣ የኩባንያው ጠቅላላ ጉባዔ አሁን ያለውን የኢንሹራንስ ኩባንያውን ካፒታል ወደ አራት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ በቅርቡ መወሰኑ አይዘነጋም፡፡ 

ኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በ1987 ዓ.ም. በብር ሰባት ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ የዳያስፖራ ልዩ ኢንሹራንስ መጠኑ እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ዓለም አቀፍ የሕክምና አገልግሎት እንዲሁም የሞባይል ኢንሹራንስ አገልግሎቶችን ለገበያ በማቅረብ ይታወቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች