Monday, February 26, 2024

ፖለቲካ የተጫነው ትምህርት የፈጠረው ቀውስ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ትምህርት ከባድ ሸክም የተጫነው መሆኑ ይነገራል፡፡ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ አለመውጣቱ እንደ አንድ መሠረታዊ ችግር ይነሳል፡፡ ሌላው ከባድ ፈተና ደግሞ የትምህርት ጥራት መጓደል ተብሎ ይጠቀሳል፡፡ የትምህርት ተደራሽነት ጥያቄ ቢሰፋም ሙሉ ለሙሉ ገና አልተመለሰም፡፡ የትምህርት ተሳትፎ ቁጥር ቢጨምርም በሁሉም ዕርከን የትምህርት ቤት ደጃፎችን ያልረገጠው ሕዝብ ቁጥር እጅግ ብዙ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህን ሁሉ መሠረታዊ የትምህርት ዘርፍ ችግር ከቀደመው አስተዳደር የተሸከመው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር፣ ዘርፉን ለማሻሻልና ለመቀየር ልዩ ትኩረት መስጠቱን ሲያስታውቅ ቆይቷል፡፡ ከሁሉ በላይ ለትምህርት ጥራት መጓደል ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የገለጸው የዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር፣ ‹‹የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፍኖተ ካርታ›› የሚል ዕቅድ አውጥቶ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የጀመረው ወዲያው ወደ ሥልጣን እንደመጣ ነበር፡፡

ባለፉት 30 ዓመታት በትምህርት ዘርፍ የታዩ ድቀቶችን ለማረም እጀግ ብዙ ተስፋ የተጣለበት የዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር፣ የትምህርት ጥራት ማሻሸያ ፍኖተ ካርታ ዘርፉን በብዙ መንገድ እንደሚለውጠው ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በዘርፉ ብዙ ለውጥ ይመጣል ተብሎ ከተጠበቀው ተስፋ ይልቅ፣ ባለፉት 30 ዓመታት የተፈጠሩ ችግሮችና እንቅፋቶች መልሰው መላልሰው መታየታቸው ትልቀ ስብራት መሆኑን ብዙዎች በፀፀት ይገልጹታል፡፡

እ.ኤ.አ. በመስከረም 2018 በብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) ‹‹Education Policy and the Politics of Change in Ethiopian›› በሚል ርዕስ የቀረበው ጽሑፍ፣ የለውጡ መንግሥት የትምህርት ዘርፉን ለመለወጥ የሚገደድባቸውን መሠረታዊ ችግሮች ያነሳ ነበር ሊባል ይችላል፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ለክልል መንግሥታት መተውና በአፍ መፍቻ ቋንቋ መሰጠቱ፣ የዘርፉን ተሳትፎ የጨመረ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ጸሐፊው ያነሳሉ፡፡

ለውጡን ተከትሎ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፍኖተ ካርታ መቀረፁ ጥሩ ጅማሮ መሆኑን ጽሐፊው በበጎ ጎኑ ያወሱታል፡፡ በተውሶና በቅጂ የመጣ የትምህርት ፖሊሲ እንደማያስፈልግ፣ የሚያስፈልገው እየገጠሙ ላሉ አዳዲስ ችግሮች ምላሸ መስጫ የሚሆን የትምህርት ሥርዓት ነው በማለትም ጸሐፊው ያብራራሉ፡፡

ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) ይህን ከጻፉም ሆነ አዲሱ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ ከተባለ አራት ዓመታት ተቆጠረ፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ እየሆነ ካለው በመነሳት የትምህርት ሥርዓቱ የአገሪቱን ቀውስ መፍቻ መፍትሔ ከማፍለቅ ይልቅ፣ ራሱም የቀውስ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

የትምህርት ጥራት መጓደል ችግር ዛሬም በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑም ብዙዎችን ያስምማል፡፡ ብሔራዊ ፈተናዎች መስጫና ውጤት ይፋ ማድረጊያ ወቅቶች በመጡ ቁጥር፣ ማጭበርበርና ፈተና ስርቆት ብቻ ሳይሆን የሚነሳው የፖለቲካ ውዝግብ እየተባባሰ ነው፡፡ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዘር ፖለቲካ ውዝግብና ብጥብጥ ስማቸው መጠራቱ ቀጥሏል፡፡

በእነዚህ ሁሉ ችግሮች እየታመሰ የሚገኘው የትምህርት ዘርፍ አሁን ደግሞ አዳዲስ የቀውስ እርሾዎችን እያገኘ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ከሰሞኑ የሰንደቅ ዓላማና የመዝሙር ጥያቄን ተንተርሶ በአዲስ አበባ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች የተፈጠረው ውዝግብ፣ የትምህርቱ ዘርፍ እየገጠሙት ያለውን አዳዲስ ተግዳሮቶች የሚያመለክት መሆኑ በጉልህ እየተነሳ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች አሁን የትምህርት ጥራት ወይም የፈተና አሰጣጥና ዕርማት ጉዳይ ሳይሆን፣ የሰንደቅ ዓላማ መሰቀልና የመዝሙር ሥነ ሥርዓት ዋነኞቹ የውዝግብ ምንጮች እየሆኑ ነው፡፡

ስለማተሪዎች ምገባና ስለዩኒፎርም አሰፋፍ ባለፉት አራት ዓመታት ላይ ታች ሲል የታየው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ዛሬ በተማሪ ቤቶች ስለሚዘመረው መዝሙርና ስለሚሰቀለው ሰንደቅ ዓላማ ላይ ታች ሲል እየታየ ነው፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ባሉ ትምህርት ቤቶች የተነሳውን ከኦሮሚያ ሰንደቅ ዓላማና ክልላዊ መዝሙር ጋር የተገናኘውን ውዝግብ አስመልክቶ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)፣ ችግሩ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ የተፈጠረ መሆኑን ገልጿል፡፡

ባለፈው ዓመት በለሚ ኩራ፣ በየካ፣ በቂርቆስና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍላተ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ ከመስቀልና ክልላዊ መዝሙር ከመዘመር ጋር በተገናኘ ሁከት ተፈጥሮ ነበር ይላል የኢሰመጉ መግለጫ፡፡ የሚመለከታቸው የክፍለ ከተማ ትምህርት ተወካዮችና ወላጆች ባደረጉት ውይይት ችግሩ በጊዜያዊነት ሰክኖ መቆየቱንም ያስታውሳል፡፡

ሆኖም ችግሩ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሔ ባለመፈለጉ የተነሳ ዘንድሮም ማገርሸቱን የሚጠቅሰው ኢሰመጉ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከኦሮሚያ ክልል መዝሙርና ሰንደቅ ዓላማ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ሁከቶች ከቁጥጥር ውጭ ሳይሆኑ በፊት መንግሥት ትኩረት ይስጥ ይላል፡፡

ኢሰመጉ በዚህ መግለጫው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የአብዮት ቅርስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የጠብመንጃ ያዥ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር ጋር በተገናኘ ከባድ ሁከት ከሰሞኑ እንደተከሰተባቸው ይጠቅሳል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ በእንጦጦ አምባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለት ጊዜ ሁከት ተፈጥሯል ይላል፡፡ ድል በትግልና አዲስ ተስፋ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁከት ተከስቶ ነበር ብሏል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ደግሞ ከፍተኛ 12 ትምህርት ቤት በተፈጠረ ከባድ ሁከት የተኩስ ድምፅ መሰማቱን የጠቀሰው የኢሰመጉ መግለጫ፣ በቦታው በአካል ተገኝቶ ባደረገው ማጣራት አንድ ተማሪ በጥይት መመታቱንና መሞቱን ነዋሪዎች መናገራቸውን ይዘረዝራል፡፡ የተማሪውን መሞት ለማረጋገጥ መረጃ ጠይቆ በመጠባበቅ ላይ መሆኑንም መግለጫው አክሏል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ወንድይራድ ትምህርት ቤት ሌላ ግጭት መቀስቀሱም ተነግሯል፡፡ በሌላ በኩል በአዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ተመሳሳይ ግጭት መከሰቱን ኢሰመጉ አረጋግጧል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተፈጠረው ግጭት መንስዔው የኦሮሚያ ክልል መዝሙርን ዘምሩ፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ሰንደቅ ዓላማ ስቀሉ በመባሉ የተፈጠረ መሆኑን ነው ኢሰመጉ ማረጋገጡን የገለጸው፡፡ ተማሪዎች የማናውቀውን መዝሙር አንዘምርም፣ እንዲሁም የክልል ሰንደቅ ዓላማን አንሰቅልም በሚል አስገዳጅ ሆኖ የቀረበውን ዕርምጃ መቃወማቸውን ያወሳል፡፡

በዚህ ተቃውሞ መነሻነትም በርካታ ተማሪዎች በፖሊስ የመደብደብና የመታሰር ዕጣ እንደገጠማቸው ነው መግለጫው በሰፊው ያተተው፡፡ ይህ ከኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር ጋር ተያይዞ የተነሳው ችግር እንዳይባባስና ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ያሳሰበው ኢሰመጉ፣ በበርካታ ተማሪዎችና ወላጆች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰ መሆኑንም ያስረዳል፡፡

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የተፈጠረው ግጭትና ተቃውሞ ለትምህርት ዘርፉ ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው አገሪቱ ሁለንተናዊ ሰላም አሳሳቢ አደጋ ይዞ የመጣ ችግር ይመስላል፡፡

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ፣ እንዲሁም ጊዳ አያና ወረዳዎች ከሰሞኑ የደረሰው ብሔር ተኮር ጭፍጨፋ ከዚህ ቀደም ያልታየ ዓይነት ተቃውሞና ውዝግብ በትምህርት ተቋማት አካባቢ ማስነሳቱ ይታወሳል፡፡ በወለጋ የፋኖ ኃይል ገብቶ ጥቃት አደረሰ የሚል ውንጀላ ጎልቶ ከመስተጋባቱ ጋር በተያያዘ፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ተቃውሞ ሲስተጋባ ነበር፡፡

ኦነግ ሸኔ የሚያካሂደውን ጭፍጨፋ መንግሥት ማስቆም አልቻለም የሚል ተቃውሞ በየዩኒቨርሲቲዎቹ የሚያቀርቡ ተማሪዎች፣ በፋኖ ላይ ተቃውሞ ከሚያሰሙ ተማሪዎች ጋር ሌላ ዓይነት ውዝግብ እንዳይፈጠር ሲሠጋ ነው የከረመው፡፡

የደመወዝ ጥያቄን መሠረት ያደረገው የመምህራን የሥራ ማቆም አድማ ዕቅድም፣ በመላ አገሪቱ ባሉ በርካታ ዩኒርሲቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተጨማሪ ራስ ምታት የፈጠረ ጉዳይ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡

ይህ ሁሉ በየአቅጣጫው ዘርፉን የወጠረ ችግር ባለበት ወቅት ግን፣ የኦሮሚያ ሰንደቅ ዓላማና መዝሙርን መነሻ ያደረገ ቀውስ በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤቶች ተከስቷል፡፡

መንግሥት በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ ጉዳይ ተጠምዶ ነው የከረመው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከአምስት ቀናት በፊት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ውይይት መሠረታዊ የችግሩን ምንጭ ትቶ በአዲስ አበባ በኦሮሚኛ ቋንቋ ትምህርት ከመስጠት ጉዳይ ጋር ወደ ማያያዝ ማምራቱን ብዙዎች ተችተዋል፡፡

ከንቲባዋ አዳነች ፅንፈኛው የፋኖ ኃይልና አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ችግሩን እንደፈጠሩት አድርገው መግለጻቸው ደግሞ፣ ሌላ ትችትና ወቀሳ እያስከተለ ነው የሚገኘው፡፡

ከንቲባዋ ከጠሩት ስብሰባ በኋላ በኦፌሴላዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባወጡት መግለጫም፣ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች በኦሮሚኛ ቋንቋ ትምህርት መስጠት ከተጀመረ አምስት ዓመት እንደተቆጠረ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአንዳንድ አካላት በኦሮሚኛ ትምህርት መስጠት ዛሬ እንደተጀመረ ተደርጎ ይቀርባል፡፡ እነዚህ አካላትም የአንድ ክልል ባንዲራና መዝሙር ለመጫን የተደረገ አስመስለው ያቀርቡታል፤›› ያሉት ከንቲባዋ፣ የችግሩ ምንጮች የውጭ አካላት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከንቲባዋ ተጠንቶና በውይይት ዳብሮ፣ በምክር ቤትም ፀድቆ የቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ ሥርዓተ ትምህርት ወደ ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የቋንቋ ሥርዓተ ትምህርት ደግሞ ከኦሮሚኛ በተጨማሪ ሶማሊኛና ጋሞኛ የማስተማር ዕቅድ የያዘ ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ወ/ሮ አዳነች አቤቤም ሆኑ ሌሎች አመራሮች በአዲስ አበባ በኦሮሚኛና በተለያዩ ቋንቋዎች ትምህርት እንዳይሰጥ ማን ተቃወመ? ለሚለው ሙግት ተጨባጭ መልስ ሲሰጡ አልታዩም የሚል ወቀሳ እየቀረበባቸው ነው፡፡

ከንቲባዋ መግለጫ ባወጡበት የፌስቡክ ግርጌ ሙግት ያቀረቡት የፓርላማ አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ከንቲባዋና አንዳንድ አመራሮች ጉዳዩን በኦሮሚኛ ከማስተማር ጋር ማገናኘታቸው ስህተት ነው ብለውታል፡፡ ‹‹እንኳን በአገራችን ቋንቋ ኦሮሚኛ መማር ቀርቶ ከውጭ ተውሰን ልጆቻችንን በሌሎች አገሮች ቋንቋ እናስተምራለን፤›› ሲሉ ሙግት ያቀረቡት አቶ ክርስቲያን፣ በኦሮሚኛ የማስተማር ጉዳይ የሰሞኑ ሁከት መነሻ አለመሆኑን ሞግተዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ እንዲሰቀል፣ የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እንዲዘመር ይደረግ መባሉና ይህ ዕርምጃም ያለ ወላጆችና ተማሪዎች ይሁንታ እንዲተገበር ዕቅድ መቅረቡ፣ የችግሩ ዋነኛ ምንጭ መሆኑን አቶ ክርስቲያን ገልጸዋል፡፡

እሳቸው የወከሉት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ ደግሞ፣ አገር አፍራሽ ያላቸው ኃይሎች በአዲስ አበባ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ሰንደቅ ዓላማና የኦሮሚያ መዝሙርን አስታውሰው አገር የማተራመስ እንቅስቃሴ መፍጠራቸውን ገልጿል፡፡ እነዚህ ኃይሎች በሕፃናትና በመምህራን ላይ ነውረኛ ጫና በመፍጠር፣ አዲስ አበባን የቀውስ ማዕከል ለማድረግ እየተጉ መሆኑን አብን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ በበኩሉ፣ ከኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር ጋር በተያያዘ የተነሳውን ግጭት አውግዟል፡፡ በየትኛውም መመዘኛ ሕጋዊ መሠረት የሌለው መሆኑንም ገልጿል፡፡ መንግሥት ከአስገዳጅ እንቅስቃሴው ካልተቆጠበ ጉዳዩን ወደ ፍትሕ አካላት እንደሚወስደው ነው ኢዜማ ያስታወቀው፡፡

የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ከሪፖርተር ጋር በትምህርት ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ሰፊ ቆይታ፣ የሚመሩትን የትምህርት ዘርፍ ከፖለቲካ የማላቀቅ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረው ነበር፡፡ በዘርፉ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ጥናት መካሄዱን በዚህ ቆይታቸው ያወሱት የትምህርት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ትምህርትና ፖለቲካ በተክሊል ነው የተጋቡት›› የሚል የአንድ መምህር ንግግርን አጣቅሰው፣ ፖለቲካ በዘርፉ ጣልቃ መግባቱ የፈጠረውን ሰፊ ቀውስ አብራርተው ነበር፡፡

ትምህርትና ፖለቲካ ዛሬም ፍቺ አለመፈጸማቸው ከሰሞኑ ከተከሰቱ ቀውሶች መረዳት እንደሚቻል ብዙዎች እየገለጹ ነው፡፡ ዛሬ ፖለቲካው ያመጣው ቀውስ ብቻ ሳይሆን፣ የትምህርት ዘርፉ የፖለቲካ ቀውስ ምህዋር እየሆነ መምጣቱ በብዙዎች ዘንድ ይነገራል፡፡

ስለትምህርት ጥራት ማሻሻል ለውጥ የጻፉት ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር)፣ ‹‹ትምህርታችን ልጆቻችንን ስለመጽሐፍ የሚያውቁበት፣ ስለሞራልና ግብረገብ የሚማሩበት መድረክ ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚኖሩበት ሊሆን ይገባል፤›› የሚል ነጥብ ጠቅሰው ነበር፡፡

የትምህርት ዘርፍ በኢትዮጵያ ዛሬ ከሚታየው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ተላቆና የፖለቲካ ቀውስ አዙሪት ማዕከል ከመሆን ወጥቶ ሳይንስ፣ ዕውቀትና ግብረገብ የሚገበይበት መድረክ እንዲሆን አገሪቱ ብዙ ርቀት መጓዝ እንዳለባት ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የተፈጠሩ ችግሮች ማሳያ መሆናቸውን ብዙዎች እያሳሰቡ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -