Wednesday, April 17, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የነገውን ሰው ለመቅረፅ…

በመምህር ሳህሉ ባዬ ዓለሙ

በአንድ ወቅት የቅርብ ቤተሰብ አባላትን ብቻ ያካትት የነበረ ጠባብና ውስን ቤት አሁን ትምህርት ቤት ወደተባለ ሰፊ አካባቢ ተሸጋግሯል፡፡ የአካባቢው መለወጥ በርካታ ሌሎች ሰዎች በአካባቢው መኖራቸውን ሕፃኑ እንዲያውቅና እንዲረዳ ማረጋገጫ ሆኖታል፡፡ ለምሳሌ መምህራን፣ ነርሶች፣ ጥበቃ ሠራተኞች፣ ፅዳት ሠራተኞችና አትክልተኞች ወዘተ መኖራቸውን እየተረዳ ነው፡፡ 

ሕፃኑ አሁን ለተጨማሪ አዳዲስ ሁኔታዎች ተጋላጭ ሆኗል፡፡ ከወላጆቹ ሌላ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ትልቅና ጎልማሳ የሆኑ መምህራንና እጅግ በርካታ አዳዲስ ፊቶች ያሏቸውን ሕፃናት ማየት ጀምሯል፡፡ የሕፃኑ ዓለም እየተቀያየረ መጓዝን ቀጥሏል፡፡ ባህሪውም እንዲሁ እየተቀየረ ነው፡፡ እሱም ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ራሱን በማላመድና በማስማማት ላይ ነው፡፡ በአዲስ ሁኔታዎች በመዋጥ ለመጀመርያ ጊዜ ከሚያስተውላቸው ነገሮችና ክስተቶች ጋር ራሱን እያላመደ በዕድገት ላይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚከናወነው በተከታታይ በሚተገበር ሙከራና ልምምድ ነው፡፡ ካለተሞክሮ፣ ልምድና ዕውቀት እንዴት ሊገኝ ይችላል? 

ሕፃኑ ይጥራል፣ በአካባቢው የሚያገኛቸውን ነገሮች ይሞክራል፣ ይፈትሻል፣ ለመመርመር ይጣደፋል፣ ዕውቀትና ስኬቶች ወደ ስብስቡ ለማካተት ይጓጓል፣ ያገኛቸውን ነገሮች ይነካካል፣ ይዳስሳል፣ ያስተውላል፡፡ የሕፃኑ ሙከራና የመማሩ ሚስጥር ይኸው ነው፡፡ ሙከራውና ልምዱ በሕፃኑ ዕድሜ፣ የዕድገት ደረጃ፣ ጤና፣ ባህልና ሰብዕና ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ መምህራንና ወላጆች የሕፃኑን አዳዲስ ነገሮች የመሞከር ጥረትና የመለማመድ ፍላጎት በጥንቃቄ ተከታትሎ ማገዝ የዕለት ተዕለት ተግባራችን ይሁን፡፡ የሰብዕና ቀረፃ ምስጢር ይኸው ነው፡፡

በእንክብካቤ የሚያድጉ ሕፃናት

ከፍተኛ ትምህርት የማጠናቀቅ ዕድላቸው የላቀ ነው፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ጉልህ ነው፣ በወንጀል ተግባር የመሳተፍ ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው፣ የማሰብና የመጠበብ ችሎታቸው (አይኪው) ከፍተኛ ነው፣ የሥራ ዓለም ገቢያቸው በ50 በመቶ ብልጫ አለው፣ በኢኮኖሚ ተሳትፎ ለአገራቸው የትርፍ ጥቅም ያስገኛሉ፡፡ በሥጋት፣ በሥነ ልቦና ጫናና በመርዛማ ጭንቀት የመጠቃት ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው፡፡

አገራዊ ዕድገት ዕውን የሚሆነው አዳዲስ ሐሳቦችን ማፍለቅ፣ መሠረተ ልማት ግንባታ ማከናወን፣ ቴክኖሎጂ አቅም ማጎልበት፣ ተፈጥሯዊ ሀብትን መንከባከብ፣ ምርታማ መሆን፣ ሕዝባዊ ተሳትፎን ማሳደግ፣ ንቁና ብቁ የሠራተኛ ኃይል ማደራጀት ሲቻል ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ተግባራት ዕውን የሚሆኑት ደግሞ ሕፃናት የዘላቂ ልማት ዕቅድና ግብ ማዕከል መሆን ሲችሉ ነው፡፡

የሕፃናት ‹‹ጥቁር ሳጥን››

ለስሜት ጎጂ ስድብ፣ ድህነት፣ እርዛት፣ አለመረጋጋት፣ ግጭት፣ ጦርነት፣ በደል፣ እንግልትና ሰቆቃ የተጋለጡ ልጆች ዘላቂ የሕይወት ስኬት ሲመዘን በጣም ዝቅተኛ ነው። የችግሮቹ ጫና መርዛማ ጭንቀት ይፈጥራል፡፡ የትምህርት አቀባበል፣ የባህሪ ቀረፃ፣ ሥራ ፈጠራና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ደካማ ይሆናል፡፡ በዘርፉ የተከናወኑ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ጨቅላ ሕፃናት ለስድስት ወይም ሰባት ማኅበራዊ ችግሮች ሲጋለጡ ከ90 እስከ 100 በመቶ ያህሉ በስሜት፣ በማኅበረ ሥነ ልቦና፣ በግንዛቤ፣ በዕውቀትና ቋንቋ ዕድገታቸው የተጓዱ ናቸው። 

በዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ ያለ ጭንቀት የአዕምሮ ሕመም ባይሆንም ከጭንቀትና ድብርት ጋር ሊገናኝ ይችላል። ጭንቀት ከቁጣ፣ ከፍርኃት፣ ከጥርጣሬ፣ ከድንጋጤና ተስፋ መቁረጥ ስሜቶች ጋር የተቆራኘ ነው። እናም እነዚህን ስሜቶች በወቅቱ መቆጣጠር ካልተቻለ ወደ መርዛማ ጭንቀት በማደግ የሕይወትን አቅጣጫ ያስታሉ ወይም ያሰናክላሉ። አፈጣጠራቸው በውጫዊና ውስጣዊ ጎሽማጭ ምክንያቶች ነው። መፍትሔው ችግሮቹንና የሚስከትሉትን ጉዳት ትስስር በማጥናት ለመከላከልና ለመፈወስ ጥረት ማድረግ ነው፡፡ 

በልጅነት ዕድሜ የሚያጋጥሙ አስቸጋሪ የሕይወት ገጠመኞች

መጥፎ የልጅነት ጊዜ ገጠመኞች ከዜሮ እስከ 17 ዓመት የዕድሜ ክልል የሚከሰቱ የሕይወት ፈተናዎች ናቸው። ጥቂቶቹ፦ አካላዊ ጥቃት፣ የቃላት ጥቃት፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ ሥነ ልቦናዊ/ስሜታዊ ጥቃት፣ ትኩረት መነፈግ/ቸል መባል፣ የቤት ውስጥ ሁከት፣ ብጥብጥ/እክል፣ እስር ላይ ያለ የቤተሰብ አባል፣ በአልኮል/አደንዛዥ ዕፅ ሱስ የተጠቃ የቤተሰብ አባል፣ በመርዛማ ጭንቀት/ የአዕምሮ ሕመም የተጠቃ የቤተሰብ አባል፣ ወዘተ ይጠቀሳሉ።

እነዚህ ችግሮች ጉዳታቸው ለረዥም ጊዜ መቆየት ይችላል። የአዋቂ ዕድሜ ድረስ ይዘልቃል። ጠባሳቸው ያለጊዜ ሞት፣ የአዕምሮ ሕመም፣ የጤና እክልና በጣም ከፍተኛ ጭንቀት ያስከትላል። ልብ ይሏል መርዛማ ጭንቀት ከአንጎል ውቅርና ተግባር ጋር የተያያዘ ነው። 

ለልብ ሕመም የሚያጋልጡ የልጅነት ዘመን አስከፊ ሁኔታዎችም እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በለጋ ዕድሜ ያሉ ልጆችን ለደካማ አዕምሯዊ ዕድገትና በአዋቂ ዕድሜ ለልብ ሕመም ከሚያጋለጡ ችግሮች መካከል ዝቅተኛና ጥራት አልባ የማኅበረ ሥነ ልቦና ማነቃቂያ ከባቢ (ለምሳሌ ንግግርና ጨዋታ) እጦት፣ ደካማ የጡት ማጥባት ሒደት፣ ማክሮና ማይክሮ ንጥረ ነገር አልባ ምግቦች፣ አካባቢያዊ ኢንፌክሽኖች (ምሳሌ  ትራኮማና ተቅማጥ)፣ በእርግዝናና በቅድመ እርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ዋና ምክንያቶች ናቸው።

ለሚከተሉት ምክሮች ትኩረት ይስጡ

ወላጅና አሳዳጊ ሆይ የልጅዎን ጤና ለመንከባከብ ትልቅ ሚና ይጫወታሉና ለሚከተሉት ምክሮች ትኩረት ይስጡ፡፡

ስለ ልጅዎ ሕመም ለማወቅ ይጣሩ፣ የቤተሰብ ምክር ግምት ውስጥ ያስገቡ፣ ልጅዎን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይውደዱ፣ ልጅዎ ስሜቱን እንዲያጋራ በማበረታታት ስሜቱን ይገምግሙ፣ መጀመርያ ያዳምጡ፣ ቀጥሎ ይናገሩ፣ ስለ ውሎው ይጠይቁ።  ለጨዋታና አዝናኝ ቀልዶች በቂ ጊዜ ይመድቡ፣  ልጅዎ ጥሩ የእንቅልፍ ልምዶች እንዲያዳብር ያስተምሩ፣ ለልጅዎ ከዕድሜው ጋር ተስማሚ የሆነ መረጃ ሲያጋሩ ሐቀኛ ​​ይሁኑ፡፡

እርስዎ አዎንታዊ ራስን መንከባከቢያ ሞዴል ይከተሉ፣ ልጅዎ ጤናማ ምግቦች እንዲያገኝ አቅም በፈቀደ ለማሟላት ይጣሩ፣ የልጅዎን ጥንካሬና ችሎታ ያመስግኑ፣ ያድንቁ፣ ያወድሱ ወይም ያሞግሱ፡፡ ልጅዎ በራስ መተማመን እንዲያዳብር ያበረታቱ፣ ችግር ፈቺ እንዲሆን ይርዱ፡፡ የልጅዎን ሰብዕና ሲቀርፁ በአክብሮትና በማስተማር እንጂ በማስፈራራት አይሁን። በተረጋጋ ሁኔታ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የጭንቀት አስተዳደር ዘዴዎች ያስሱ፡፡ ከልጅዎ ጋር ተረቶችና ቀልዶች  እየተጫወቱ የሚደሰቱበትና የሚዝናኑባቸው ሁኔታዎችን ያመቻቹ፡፡ በሕፃናት አስተዳደግ ለወላጆች በሚዘጋጁ የሥልጠና ፕሮግራሞች በተለይ የአዕምሮ ጤና ሥልጠናዎች ይውሰዱ።  የልጅዎን አስቸጋሪ ባህሪያት መለየትና ምላሽ መስጠት የሚያስችሉዎ ዕውቀት ለመቅሰም ባለሙያ ያማክሩ።  መልካም፣ መልካሙን ለሕፃናት!         

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው፣ የሕፃናት አስተዳደግ ስፔሻሊስትና ፕሮጀክት ማናጀር ሲሆኑ፣ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ ‹‹MA in Chid Development, BA in Psychology, MBA & IDPM in Project Management›› አግኝተዋል፡፡  ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles