Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊድርቅና ረሃብ የተንሰራፋባቸው የጎፋ ዞን ወረዳዎች

ድርቅና ረሃብ የተንሰራፋባቸው የጎፋ ዞን ወረዳዎች

ቀን:

አካባቢው በበቆሎ አምራችነቱ ይታወቃል፡፡ በተለይ በክረምት ወቅት የበቆሎ እሸት ምርት እስከ ለማዕከላዊ ገበያ ድረስ በማቅረብ ይታወቃል፡፡ የቁም እንስሳት ከብቶችን በማደለብ ለገበያ በማቅረብም ስማቸው ከሚነሱት መካከል ደቡብ ክልል ጎፋ ዞን ዛላ፣ ኡባ ደብረ ፀሐይ፣ ደንባ ጎፋ ወረዳዎች ለረዥም ዓመታት የበቆሎ ምርትና የቁም እንስሳት ከብቶችን በማደለብና ለገበያ በማቅረም ይታወቃሉ፡፡

ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት በእነዚህ ወረዳዎች ማምረት ቀርቶ ለዕለት ጉርሳቸው ያጡ ዜጎች ቁጥር በርከት ማለቱ ከወረዳዎቹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ዛላ ወረዳ ከሚገኙ 15 ቀበሌ ነዋሪዎች ከግማሽ የሚበልጡት የሚላስ የሚቀመስ አጥተዋል፡፡ ችግሩ የሚከፋው ደግሞ አጎራባች ወረዳዎችም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ በመሆናቸው ነው፡፡ የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምርያ ኃላፊ አቶ አብርሃም ዞራ፣ በወረዳዎቹ ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መቆራረጥ እንደነበር፣ ፈጽሞ ሰብል የጠፋባቸው ቀበሌዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

ድርቅና ረሃብ የተንሰራፋባቸው የጎፋ ዞን ወረዳዎች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በወረዳዎቹ ባሉ ቆላማ ቀበሌዎች ባለፈው የበልግ ወቅት 233 ሺሕ ቤተሰብ የአስቸኳይ ዕርዳታ ያስፈልጋቸው እንደነበር ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ከየካቲት እስከ ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ከዞኑ ለከፋ ጉዳት የተጋለጡትን በመለየት 169 ሺሕ ቤተሰብ ዕርዳታ እንዲያገኙ መደረጉን አቶ አብርሃም ጠቁመዋል፡፡ በመኸር ወቅት በተመሳሳይ መቸገራቸውን ኃላፊው ጠቁመው፣ ከሰኔ 2014 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም. ድረስ በወረዳዎቹ ከፍተኛ የሆነ የዝናብ እጥረት ማጋጠሙንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በተለይ በዛላ ወረዳ የሚገኙ 15 ቀበሌዎች፣ በኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ አምስት ቀበሌዎች ላይ ሰብሉ ሙሉ ለሙሉ መጥፋቱን አመልክተዋል፡፡

እንደ አቶ አብርሃም መግለጫ፣ በደንባ ጎፋ ወረዳ የሚገኙ ቆላማ ቀበሌዎች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የምርት መቀነስ ማጋጠሙን፣ ችግሩ የጎላው ግን በዛላ ወረዳ ነው፡፡ በተጠቀሱት ወረዳዎች በዛላ ወረዳ ሙሉ በሙሉ፣ ኡባ ደብረ ፀሐይ በከፊል፣ ደንባ ጎፋ 60 በመቶ ሰብል መጥፋቱንም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሌሎችም ወረዳዎችና በሳውላ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ በከፊል ሰብሉ መጥፋቱን፣ በመኸር ወቅት በአብዛኛዎቹ ማሳዎች ቢዘራባቸውም ዝናብ ባለማግኘቱ ለተከታታይ ዓመታት ችግሩ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡

በመኸር ወቅት በዞኑ 74,000 ሔክታር በሰብል እንደተሸፈነ 30,000 ሔክታሩ የበቆሎ እንደሆነ 54 በመቶ የሚሆነው ምርት እንደመከነ አስረድተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት አጠቃላይ በዞኑ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ቤተሰቦች በርካታ መሆናቸውን፣ ይህም 155,247 ሰዎች የዕለት ጉርስ ፈላጊ ናቸው ብለዋል፡፡ በዛላ ወረዳ ብቻ 67,907 ቤተሰብ የዕለት ጉርስ ለማግኘት ዕርዳታ የሚጠብቁ መሆናቸውን፣ ለአምስትና ከዚያ በላይ ወራት የሚዘልቅ ድጋፍ የሚሹ ናቸው ብለዋል፡፡

በአቶ አብርሃም አገላለጽ፣ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን 3,515 ኩንታል እህል ዕርዳታ እንደሰጠ፣ ድጋፉም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኘው ዛላ ወረዳ ብቻ እንደዋለ ጠቁመዋል፡፡

የሚመጡ ዕርዳታዎችም በቂ ባለመሆናቸው የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ሀብት የማሰባሰብ ሥራ መሥራት መጀመራቸውን ለዚህም የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት መልሶ ማቋቋሚያ ፈንድ የሚል ቡድን መዋቀሩን አስረድተዋል፡፡

ከፌዴራልና ከክልል በቂ ዕርዳታ እስኪመደብ በዞንና በወረዳ ደረጃ ሀብት የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ መሆኑን፣ እስካሁን ከክልሉ መንግሥት የመጣ ዕርዳታ እንደሌለ የተናገሩት ኃላፊው፣ ከፌዴራል የመጣው ዕርዳታም ቢሆን ከችግሩ ስፋት አኳያ በቂ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት፣ የመንግሥት አመራሮችና ሠራተኞችን በማስተባበር ከደመወዛቸው ከአሥር እስከ ሃያ በመቶ ተቆራጫ እንዲያደርጉ ከስምምነት መደረሱን፣ ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ1,900 ኩንታል በላይ በማሰባሰብ በይበልጥ ተጎጂ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ወረዳዎቹ በከርሰ ምድር ውኃ የበለጸጉ በመሆናቸው፣ ቆፍሮ በማውጣት አርሶ አደሩ በመስኖ የሚያለማበትን ሁኔታ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት፣ እንዲሁም ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ማመቻቸት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ነገር ግን ችግር ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦች በዚሁ ከቀጠሉ ለከፋ ረሃብ የሚጋለጡበት አጋጣሚ ከፍተኛ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በድርቅ የተጎዱ እናቶችና ሕፃናት

የጎፋ ዞን ጤና መምርያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማኖቴ እንደተናገሩት፣ በድርቅ ምክንያት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ሕፃናትና እናቶች ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡ በዛላ ወረዳ 4,288 ሕፃናት በተመላላሽ የምግብ እጥረት ሕክምና እየተሰጣቸው ይገኛሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በዚሁ ወረዳ ከሦስት ሺሕ በላይ የሚያጠቡ እናቶችና ነፍሰ ጡሮች በሕክምና ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

በጎፋ ዞን በድርቅ የተጠቁ ወረዳዎች 129 ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ለተከታታይ ዓመታት በወረዳዎቹ የዝናብ ዕጥረት በመከሰቱ በርካታ ቀበሌዎች በችግር ተጋልጠዋል፡፡ የጎፋ ዞን ትምህርት መምርያ ኃላፊ አቶ አሸብር ብርሃኑ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ለተከታታይ አራት ዓመታት የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥና መቅረት ቁጥር ከፍ ብሏል፡፡

በዛላ ወረዳ 47፣ ኡባ ደብረ ፀሐይ 19፣ በቶ ከተማ 6፣ ደንባ ጎፋ 57 ትምህርት ቤቶች ላይ መጠነ ማቋረጥና መቅረት ቁጥሩ ከፍተኛ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም. ትምህርት ዘመን ብቻ በሁሉም ወረዳዎች 66,359 ተማሪዎች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ በድርቅ ሳቢያ 2,231 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው አቋርጠዋል፡፡

የጎፋ ዞን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ውባለም ዝናቸው በበኩላቸው፣ እስካሁን ክልሉ ምንም ዕርዳታ አላቀረበም፡፡ በፌዴራል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተወሰነ ዕርዳታ ቢቀርብም፣ ከችግሩ ስፋት አኳያ በቂ አይደለም፡፡ ለወረዳዎቹ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አመራሮች ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው፣ ለተከታታይ ሰባትና ስምንት ወራት ዕርዳታ የማይሰጥ ከሆነ ነዋሪዎች ለከፋ ጉዳት አለፍ ሲልም ሞት ሊያጋጥም ይችላል ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ጋሞአ እንደተናገሩት፣ በክልሉ ጎፋ ዞንን ጨምሮ ጋሞ ዞን ቆላማ ወረዳዎች፣ ደቡብ ኦሞ ዞን፣ ኮንሶና አራት ልዩ ወረዳዎች ላይ ድርቅ ተከስቷል፡፡

በተለይም ጎፋ ዞን ሁለት ወረዳዎች ከፍተኛ ችግር የገጠማቸው መሆኑን፣ ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ለተከታታይ ዓመታት ዝናብ ያላገኙ በመሆናቸው በሰብል ላይ ጉዳት መድረሱና ዜጎችም ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ችግር ምላሽ ለመስጠት ሀብት የማሰባሰብ ሥራዎች ለመሥራት የ2013/14 የመኸር ግምገማ መደረጉን አመልክተዋል፡፡

ከግምገማው በኋላ ከጥር 1 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ ዜጎች የምግብ ዕርዳታ ሲሰጥ መቆየቱን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

የድርቁ ችግር የጎላው በመኸር ወቅት የተዘራው ዝናብ ባለማግኘቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም እህል እየገዛ እያቀረበ እንደሚገኝ፣ ረጂ አካላትንም እያስተባበረ ድጋፍ እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በክልሉ 48 ወረዳዎች ድርቅ በመኖሩ እናቶችና ሕፃናት እንዳይጎዱ በቀጥታ አልሚ ምግብ እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

የዕርዳታ መቆራረጥና ውስንነት መኖሩን ጠቁመው፣ ነገር ግን ችግሮቹን ለመፍታት ከፌደራል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በጋራ እየሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ 2015 ዓ.ም. ለችግር የተጋለጡ ዜጎች በመለየት ከጥር ወር ጀምሮ የምግብ እጥረት ለገጠማቸው ዜጎች ዕርዳታ ለማድረስ በሒደት ላይ ነው ብለዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...