Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሥነ ጥበባዊ አሻራ በዓለም ዋንጫው መድረክ

ሥነ ጥበባዊ አሻራ በዓለም ዋንጫው መድረክ

ቀን:

  • ይድነቃቸው ተሰማና ሞሮኮ ምንና ምን ናቸው?

የዓለምን ዓይንና ጆሮ ለአንድ የጨረቃ ወር ገዝቶ የነበረው የኳታሩ 22ኛው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ዛሬ በዕለተ ሰንበቱ ይቋጫል፡፡

በምድረ ዓረብ ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀው ሉላዊው ውድድር በሥነ ጥበባት በመታጀብ ነው ለፍጻሜው የደረሰው፡፡

ግጥሚያዎች በሚከናወኑባቸው ስታዲየሞች ዙሪያ በተለይ በተዘጋጁት ሥፍራዎች ሠዓሊያን በየዕለቱ እየሣሉ ለታዳሚያን ሲያቀርቡ እንደነበር ብዙኃን መገናኛዎች ሲዘግቡት ሰነባብተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከነዚህም ሠዓሊያን መካከል ኢትዮጵያዊው ተሰማ አሥራት ይገኝበታል፡፡ ተሰማ መኖሪያውን በኳታር ካደረገ አሥራ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በመደበኛ ሥራው በአቬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ በቴክኒሻንነት እያገለገለ መሆኑ ከትሪቡን ኒውስ ኔትወርክ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሯል፡፡

በትርፍ ጊዜው ሥዕልን በመሣል ከኅብረ ቀለማት ጋር እያወጋ ጥበባዊ ትሩፋቱን እያቀረበ ይገኛል፡፡ ‹‹ቀለሞች ለኔ ሕይወትና ውበት ናቸው፤ ቀልቤን የሚገዛው የምወደው ሰማያዊ ቀለምን ነው፡፡ ምክንያቱም ርጋታና ሰላምን አመልካች ነውና፤›› የሚለው ተሰማ፣ በዶሃ በተዘጋጁ በርካታ ዓውደ ርዕዮች ሥዕሎቹን አቅርቧል፡፡

ሥነ ጥበባዊ አሻራ በዓለም ዋንጫው መድረክ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በተለያዩ መድረኮች ከሚያቀርባቸውና ውስን ሰዎች ከሚያዩት ዓውደ ርዕይ በተለየ በሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች ሊያዩለት የሚችልበት መድረክ ያገኘው የኳታሩ 2022 የዓለም ዋንጫ ላይ ነው፡፡

አፍሪካዊቷ ሞሮኮ በምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች አንድም ጨዋታ ሳትሸነፍ በልዕልና የፍጻሜ ግማሽ ላይ መድረሷ ሠዓሊ ተሰማን አነቃቅቶት በስታዲየሙ ዙሪያ ሆኖ አስደማሚ ሥዕልን እንዲሠራ አድርጎታል፡፡

ሠዓሊው በስታዲየሞች አካባቢ በሚገኙትና ለደጋፊዎች/ለተመልካቾች በተከለሉ ቦታዎች ሥዕሎቹን በተለያዩ ጭብጦች ሲሠራ ሰንብቷል፡፡ አፍሪካውያኑ ‹‹የአትላስ አንበሶች›› በሚባል በሚታወቁት ሞሮኮዎች፣ እንዴት እንደሚያኮሩ ለማሳየት ነው ሥዕሉን የሠራው፡፡ ፖርቱጋልን 1ለ0 በማሸነፋቸው የፈነደቀው ተሰማ፣ ኢትዮጵያና ሞሮኮን በአፍሪካ ካርታ ጥላ ሥር አስተሳስሮ አቅርቦታል፡፡ ኮከቡን ተጫዋች ሐኪም ዚዬችና ‹‹የአፍሪካ እግር ኳስ አባት›› ተብለው በመጠራት ሕያው ስም ያኖሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማን አያይዞ አሳይቷል፡፡

እንደ ትሪቡን የዜና አውታር ዘገባ ‹‹በሸራው ላይ የሚታየው ሥዕል የአፍሪካን ካርታ፣ የሞሮኮ ሰንደቅ ዓላማ፣ የብሔራዊ ቡድኗ ተጫዋች ሐኪም ዚዬችና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን (ካፍ) ከመሠረቱት አንዱ የሆኑት አቶ ይድነቃቸው ተሰማን ያሳያል፡፡ አፍሪካ በብዙ ሀብቶች እንዴት እንደተባረከች ለማሳየት በሥዕሉ ላይ የብርቱካናማ ጥላዎች ጎልተው ይታያሉ፡፡››

በአል ቱማማ ስታዲየም በመገኘት ጨዋታውን ከተመለከቱ ሞሮካውያን መካከል ሥዕሉን በአድናቆት የተመለከቱት አያሌ ናቸው፡፡

‹‹ከኢትዮጵያዊነቴ በተጨማሪ በሞሮኮ በጣም የምኮራ አፍሪካዊ ነኝ፤›› በማለት ለኳታር ትሪቡን የተናገረው ተሰማ፣ ሞሮኮ ከዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ግማሽ በመድረስ የመጀመርያው የአፍሪካ ቡድን መሆኑ ትልቅ ክብር ነው ብሏል፡፡ አክሎም እንዲህ አለ፡፡ ‹‹ድጋፌን ለማሳየት የሞሮኮ ቡድን በፖርቱጋል ላይ የመጀመርያ ግቡን ሲያስቆጥር በሥዕሉ ላይ ሠርቻለሁ፡፡ በዓለም ዋንጫ ወቅት ችሎታዬን በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ማሳየቴ ትልቅ ልምድ ነው፡፡››

ሠዓሊ ተሰማ የአቶ ይድነቃቸውን ምስል በሥዕሉ ያካተተበት ምክንያት ሲገልጽ ለአፍሪካ እግር ኳስ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ነው ብሏል፡፡ በሞሮኮ በስማቸው የተሰየመ ስታዲየም መኖሩንም በመጥቀስ፡፡

ታላቁ ይድነቃቸው ተሰማ ማን ናቸው?

ከአንድ መቶ አንድ ዓመት በፊት (መስከረም 1 ቀን 1914 ዓ.ም.)፣ በዕለተ ዕንቁጣጣሽ በጅማ ከተማ የተወለዱት የኦሊምፒክና የስፖርቱ ፊታውራሪ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፣ በጥንካሬያቸውና በረቀቀ ክሂላቸው በተሰሚነታቸው የአውሮፓን የሞኖፖል አጥር የሰበሩ ቀዳሚው አፍሪካዊም ነበሩ፡፡ ይህም በፊፋ መድረክ በዓለም ዋንጫ ታሪክ የታየ ነበር፡፡ በዓለም ዋንጫ፣ የፍጻሜ ግጥሚያዎች የአፍሪካና የእስያ አሸናፊ አንድ ቡድን ብቻ እንዲያቀርብ የተደነገገውን ደንብ አሽረው፣ ሦስት እንዲሆን ከማስደረጋቸውም በላይ ለአሁኑ አምስት ኮታ መሠረት ጥለዋል፡፡

በኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥ ዓይነተኛ ሥፍራ ያገኙትና አኩሪ ምዕራፍ ሊይዙ የበቁት ይድነቃቸው፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ ስፖርት አብነት ሆነውታል፡፡

ያኔ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት የነበሩት ስፓኛዊው ዡዋን አንቶኒዮ ሳማራንሽ በይድነቃቸው ዜና ዕረፍት (ነሐሴ 13 ቀን 1979 ዓ.ም. በዕለተ ቡሔ) ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹ካለጥርጥር በዓለም ኦሊምፒክና ስፖርት ቤተሰብ ዘንድ እንደ እውነተኛው የአፍሪካ ስፖርት አባትና ብልህ መሪው ሲታወሱ ይኖራሉ›› በማለት የገለጹት፡፡ በእርግጥም ከ36 ዓመታት በኋላም በኳታር ይኸው በሥነ ጥበብ ተንፀባርቋል፡፡

አፍሪካ ፖለቲካዊ አንድነቷን ማሳያ የሆነው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (አ.አ.ድ) የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረትን ከመመሥረቷ በፊት፣ በእግር ኳስ አንድነቷን በ1949 ዓ.ም. የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በመመሥረት እንድትጀምር ከማድረግ ባሻገር፣ ለሦስት አሠርት በካፍ ፕሬዚዳንትነታቸው፣ ውድድሮች አንዴም ሳይቋረጡ ለማካሄድ የቻሉት፣ በብልሃዊና ቆራጣዊ አመራራቸው በመሆኑ በዓቢይነት ሊወሱ፣ በቀዳሚነት ሊታወሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

ይድነቃቸው ሰፊና ሁለገብ ችሎታቸውን በማሳየት የኢትዮጵያና የአፍሪካ ስፖርትና ኦሊምፒክ ሰንደቅ ቀዳሚው ተሸካሚ ሆነው መኖራቸው ይታመናል፡፡

የታላቁ ይድነቃቸው ተሰማ ማለፊያ ተግባራት ዘመን አልፎ ዘመን ሲቆጠር፣ ትተውት ያለፉት ቁምነገር ህልውናቸው እየተስተዋለ፣ እየለመለመ እንዲጓዝ እንጂ በሙታን ማኅደር ውስጥ ተሸፍነው እንዲቀሩ አላደረጋቸውም፡፡ ዘንድሮ ኳታር ላይ በሥነ ጥበብ የታየው ይኸው ነው፡፡

ስለዚህም ነው፣ ከሞቱ ከመንፈቅ በኋላ፣ በ1980 ዓ.ም. በሞሮኮ ከተሞች በተካሄደው 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ‹‹ይድነቃቸው የአፍሪካ ስፖርት ህልውናን አብሣሪና ፈጣሪ›› በማለት በሞሮኮው ንጉሥ ሀሰን ውሳኔ በካዛብላንካ ከተማ የሚገኘውን ታላቅ የስፖርት ኮምፕሌክስ፣ ‹‹ይድነቃቸው ተሰማ ስታዲየም›› ተብሎ እንዲጠራ ሲወስኑ ‹‹እውነተኛው አፍሪካዊ›› ብለው በመጥራትም ጭምር ነበር፡፡

ንጉሥ ሀሰን አቶ ይድነቃቸውን ‹‹እውነተኛ አፍሪካዊ›› እንዲሉ ካሰኟቸው ቁም ነገሮች አንዱ የ16ኛው አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነቷን በማፅናታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጨረሻ በምዕራብ ሰሃራ ምክንያት እሰጥ አገባ የገባችው ሞሮኮ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለሰሃራ ዕውቅና በመስጠቱና በአባልነት በመያዙ አባልነቷን ታቋርጣለች፡፡

በዚህ ጊዜ ነበር በጥር – የካቲት 1980 ዓ.ም. በሞሮኮ ሊካሄድ የታሰበው የአፍሪካ ዋንጫ በዚያ መካሄድ የለበትም፣ በሌላ አገር ይካሄድ ብለው አገሮች አቋም ይይዛሉ፡፡ ሞሮኮዎችም ሥጋት ይገባቸዋል፡፡ ለካፍም አቤት ይላሉ፡፡ ውድድሩ የአ.አ.ድ ሳይሆን የካፍ ነው፣ የሞሮኮን አዘጋጅነት የሚነጥቅ አንዳች ነገር አይኖርም ብለው አቶ ይድነቃቸው በሰጡት ውሳኔ ውድድሩ በሞሮኮ ለመካሄድ ችሏል፡፡

አቶ ይድነቃቸው በማረፋቸው ምክንያት በውድድሩ ሥፍራ ባይገኙም ልጃቸው አቶ ታደለ ይድነቃቸው የክብር እንግዳ ሆነው፣ በስማቸው የተሰየመውን ስታዲየም ከሞሮኮ መሪዎች ጋር በመሆን መመረቃቸው በወቅቱ የተዘገበ ነው፡፡

ካፍ በሕይወት እያሉ በ1971 ዓ.ም. በየሁለት ዓመቱ የሚያካሂደውን የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫን ‹‹የይድነቃቸው ተሰማ ዋንጫ›› ብሎ መሰየሙ ይታወቃል፡፡

‹‹ነውን ለማወቅ ነበርን ጠይቅ›› ስለተባለ፣ ነበርን ይድነቃቸው አንስተናል፡፡ ነውን በነበረ ላይ እየገነባን፣ በዓለም አቀፍና በአኅጉር የስፖርት ተቋማት ብዙ ይድነቃቸውን የምናይበትን መንገድ መንግሥታዊ ተቋማትና ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ሊያስቡበት፣ ላፍታም ቸል ሊሉት አይገባም፡፡

አቶ ይድነቃቸው፣ በፀረ አፓርታይድ ትግል የያኔዋን ዘረኛ ደቡብ አፍሪካ ከኦሊምፒክና ከእግር ኳሱ ዓለም ለማስሰረዝ ያደጉትና የተቀዳጁትን የክብር አክሊል፣ ለመንጠቅ የሚሞክሩ፣ ባልዋሉበት ጀግና ለመሆንና የኢትዮጵያንና የይድነቃቸው ተግባር በአዳዲስ የፈጠራ ታሪክ ለመለወጥ የሚሞክሩ፣ የባህር ማዶ ሰዎችን መከታተል፣ ሲያዛቡም ማስተካከያ እንዲያደርጉ ጠንክሮ ማሳሰብ የሁሉም ጥረት፣ በተለይም የኦሊምፒክ፣ የስፖርትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡

ነገር በነገር ቢወሳ አይደንቅምና አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ዓምና በመስከረም ከተወለዱ 100 ዓመት እንደሞላቸው እየታወቀ፣ ብሔራዊ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና መንግሥታዊው የስፖርት ተቋም ይልቁንም የፈጠሩት ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንዴት ዕለቱን መዘከር አቃታቸው?!

ለማንኛውም አባታቸው ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፣

‹‹ለመታሰቢያ ነው እግዜር የሠራቸው፣

በሰማይ ኤልያስ በምድር ይድነቃቸው›› ብለው ሦስቱን ልጆቻቸውን አስተሳስረው የተቀኙት ቅኔም ዕውንነት እንደቀጠለ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...