Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊስደት መጋዝ የሆነባቸው

ስደት መጋዝ የሆነባቸው

ቀን:

ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸው እንዲያልፍላቸው ከዛሬ አሥር ዓመታት በፊት ነበር ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የተጓዙት፡፡ ወደ ሳዑዲ ከአንዴም ሁለቴ ባቀኑበት ወቅት ያላቸውን ጥሪት አሟጠውና  ቤተሰቦቻቸውን አስቸግረው ነበር፡፡ ሆኖም ከአገር ወጥቶ መሰደድ አንድም ለጤና መቃወስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ላልተፈለገ እንግልት መጋለጥ እንደሆነ የስደት ሕይወት አስተምሯቸዋል፡፡

‹‹ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ስጓዝ በሕገወጥ መንገድና በሕጋዊ መልኩ ነበር፡፡ ደላላ አመቻችቶልኝ በሕገወጥ መንገድ በሄድኩ ጊዜ በርካታ ሰዎች ባህር ላይ ሕይወታቸው ሲያልፍ አይቻለሁ፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያም ተቀጥረው ሲሠሩ በቤቱ ባለቤት ወይም በአሠሪያቸው በኩል ፆታዊ ጥቃት የሚደርስባቸው፣ በየወሩ የሚከፈላቸውን አበል በአግባቡ የሚያገኙም ነበሩ፤›› ይላሉ፡፡

ወ/ሮ ስንታየሁ ደረሰ፣ በተለይ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እስር ቤት ውስጥ እንደሚማቅቁ፣፣ ከዚህ ችግር ውስጥ ለመላቀቅ በርካታ ዜጎች ፈተና ውስጥ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡

- Advertisement -

በመጀመርያው የሳዑዲ ዓረቢያ ጉዞዋቸው በሕገወጥ መንገገድ መሄዳቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ስንታየሁ፣ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጉዞ ተሳክቶላቸው ሳዑዲ በመግባት አምስት ዓመታት ያህል ሠርተው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም በእነዚህ ዓመታት የልፋታቸውን ያህል ጥሪት አልያዙም፡፡ የላኳቸውን ቤተሰቦቻቸውንም የሚደግፍ ገንዘብ አላገኙም፡፡ ይህ በራሳቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ቤተሰቦቻቸውን መርዳት አለመቻላቸው የቆጫቸው ወ/ሮ ስንታየሁ፣ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ዳግም ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ አቅንተዋል፡፡   

የመጀመርያውን ሕገወጥ ስደት ከማድረጋቸው በፊት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እንደነበሩ፣ ትምህርታቸውንም አቋርጠው ወደ ስደት ሕይወት መግባታቸውን፣ በወቅቱም ትምህርታቸውን ከስምንተኛ ክፍል ያቋረጡበት ዋነኛ ምክንያት ገና በ16 ዓመታቸው ልጅ በመውለዳቸውና የልጃቸው አባትም ትቷቸው በመሄዱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከዚሀ ሁሉ ትንቅንቅ በኋላ ስደትን አማራጭ ማድረጋቸውንና የወለዷትንም ልጅ ቤተሰባቸው ላይ ጥለው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በሕገወጥ መንገድ መጓዛቸውን ሆኖም  በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ምንም ዓይነት ጥሪት አለመያዛቸውን፣ በቅርቡም ከሳዑዲ ዓረቢያ ተመልሰው ቤተሰቦቻቸው ላይ ጥገኛ ሆነው ልጃቸውን እያሳደጉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

እንደ ወ/ሮ ስንታየሁ፣ አሥር ዓመታት በሳዑዲ ዓረቢያ በሠራተኝነት ተቀጥረው ሲሠሩ ዕድሜና ጉልበታቸው አልቋል፡፡ ምንም ዓይነት ጥቅም ሳያገኙም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡

‹‹ስደት መጋዝ ነው፤›› የሚሉት ወ/ሮ ስንታየሁ፣ ይህን ሁሉ ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሠርተው ቢሆን ኖሮ አንድም ቤተሰባቸውን በሌላ በኩል ደግሞ ለራሳቸውና ለልጃቸው ይተርፉ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

ከብዙ ዓመታት በኋላ ከስደት ኑሮ መላቀቃቸው እንዳስደሰታቸው፣ መንግሥት ከጃንቦ የፅዳት አገልግሎት ድርጅት ጋር በመተባበር በርካታ ስደተኞች በአገራቸው ሠርተው እንዲለወጡ ማድረጉ የሚበረታታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የጃንቦ ፅዳት አገልግሎት ድርጅትም ለስድስት ቀናት ያህል ሥልጠና እንደሰጣቸውና በቅርቡም ወደ ሥራ ሊያስገባቸው በመሆኑ ደስተኛ እንደሆኑ አክለዋል፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ ከተማ ከአሥር ዓመታት በላይ የቆየው ወጣት እስክንድር ዋቅበሎ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሕገወጥም ሆነ በሕጋዊ  መንገድ ስደትን አማራጭ አድርጓዋል፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ የስደት ኑሮው ችግሮች እንደገጠሙት፣ ከብዙ እንግልትና ስቃይ በኋላ መንግሥት ስደተኞችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ለአገሩ መብቃቱን አስረድቷል፡፡

መጀመሪያ ሳዑዲ ሲሄድ ጥሩ የሚባል አቀባበል ተደርጎለት በሹፍርና ይሠራ እንደነበር በኋላ ግን ለአንድ ዓመት ያህል መታሰሩን፣ ነገሮች ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኖበት እንደነበር፣ አብራርቷል፡፡

መንግሥት በ2014 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ማድረጉ ትልቅ ዕፎይታ እንደሰጠው፣ ስደት ላይ በቂ የሕክምናና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ሳያገኝ መቅረቱን አስረስድቷል፡፡

የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያለ በጓደኞች ግፊት ስደትን መምረጡን የሚያስታውሰው ወጣት፣ ከዚህ ሁሉ ችግር በኋላ ለአገሩ በቅቶ ዳግም በጃንቦ ፅዳትና አገልግሎት በኩል ሥልጠና ወስዶ ሥራ ለመያዝ እየተሯሯጠ መሆኑን አብራርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ጥሪታቸውን አሟጠው አሊያም ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን አስቸግረው ወደ ተለያዩ አገሮች የሚሰደዱ ዜጎች ስፍር ቁጥር እንደሌላቸው ይታመናል፡፡ እነዚህም ዜጎች የተሻለ ሥራ ፍለጋ በሕገወጥም ሆነ በሕጋዊ መንገድ ከአገር ቢወጡም ያላሰቡት ዱብ ዕዳና እንግልት ሲገጥማቸው ይታያል፡፡

በተለይም በሕገወጥ መንገድ ስደትን አማራጭ አድርገው የሄዱ ሰዎች ለተለያዩ ችግሮች ገፈት ቀማሽ ከመሆናቸውም ባለፈ፣ ሕይወታቸው በአጭሩ ሲቀጠፍ ማየት ተለመደ ሆኗል፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲገቡ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡

በዚህም መሠረት ከዓምና ጀምሮ እስካሁን ከ75 ሺሕ በላይ ዜጎች ወደ አገራቸው ገብተዋል፡፡ ወደ አገራቸውም ገብተው የተለያዩ ሥራዎች እንዲሠሩና ራሳቸውን እንዲያደራጁ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል፡፡

በቅርቡም ከ5,000 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከጃንቦ ፅዳት አገልግሎት ድርጅት ጋር ስምምነት አድርጎ ያሠለጠናቸውን ከአንድ ሺሕ በላይ ዜጎች ወደ ሥራ እንዲገቡ እያመቻቸ ነው፡፡ ሥልጠናውን ካገኙት መካከልም ወ/ሮ ስንታየሁና ሌሎችም ይገበኙበታል፡፡

የጃንቦ የፅዳት አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ ገብርዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከተለያዩ አገሮች ተሰደው ለአገራቸው የበቁ 5,000 ዜጎችን በተለያዩ ምዕራፎች ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ሥራ ያስገባል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ከስደት የተመለሱ ዜጎች ላይ እየሠራ ነው፡፡

 ሥልጠናውን ወስደው ወደ ሥራ የሚገቡ ስደተኞች የመረጃ ቋት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል እንደሚገኝ ገልጸው፣ ይህንንም መረጃ ተገን በማድረግ ተቋሙ ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ሥራ እያስገባ ይገኛል ብለዋል፡፡

የስደት ተመላሾችም ሥልጠናውን የሚወስዱበት አንዳንድ ወጪዎችን የሚችለው ‹‹ፈርስት ኮንሰፕት ብሪትሽ ፕሮግራም›› የሚባል ድርጅት መሆኑን አክለዋል፡፡

ሥልጠናውን የወሰዱት በተለያዩ የፅዳት ዘርፎች መሆኑን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ አብዛኛው ስደተኞች ሙያው በእጃቸው ስላለ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልገጠማቸው አብራርተዋል፡፡  

ጃንቦ የፅዳት አገልግሎት ድርጅት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ቤት ለቤት ሄዶ ምንጣፎችን በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ግንባታዎችን፣ ሶፋዎችና ሌሎችንም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራና ሥምሪት ገበያ ዘርፍ የሥራ ሥምሪት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ አበራ በበኩላቸው፣ ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ ብለው ከአገር የወጡ ስደተኞችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት መልሰው እንዲቋቋሙና ራሳቸውን እንዲችሉ እየሠራ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

ከስደት የተመለሱ ዜጎችም የሥነ ልቦናና የሕይወት ክህሎት ሥልጠና የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ሥልጠናውን ከወሰዱ በኋላ የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል ብለዋል፡፡

ከተለያዩ አገሮች የሚመለሱ ስደተኞች በመደበኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ ውስጥ መካተታቸውንና በአገር አቀፍ ደረጃ ስደተኞችን ወደ ሥራ ለማስገባት ሚኒስቴሩ ጥረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ከስደት ተመላሾች ቴክኒክና ሙያ ሥልጠናዎች እንዲወስዱ እየተደረገ ነው፤›› የሚሉት አቶ ብርሃኑ፣ በተለይም ካፒታል የሌላቸውን ስደተኞች መነሻ ገንዘብ በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከስደት ተመላሾችን ለመቀበል ከፍተኛ የሆነ ወጪ እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ እነዚህን ሁሉ ሥራዎች ለመሥራትና ቅንጅታዊ አሠራርን ለመተግበር ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም ብለዋል፡፡

ከዓምና ጀምሮ እስካሁን ከ75 ሺሕ በላይ ዜጎች ወደ አገራቸው መግባታቸውን፣ ይሁን እንጂ 35 ሺሕ ብቻ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና መውሰዳቸውን አክለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ  የሕይወት ክህሎት ሥልጠናና መነሻ ካፒታል ሰጥቶ ወደ ሥራ ለማስገባት እንደ ትልቅ ተግዳሮት የሆነበት በርካታ ስደተኞች ውስጥ ሲመዘገቡ የሚሰጡት አድራሻና ለሥራ ሲፈለጉ በአድራሻው አለመገኘታቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከተለያዩ አገሮች ከሚመጡ ስደተኞች የአዕምሮምና ሌላ የጤና እክል ያለባቸው በመኖራቸው፣ በተቋም ደረጃ የሥነ ልቦና ምክር እንዲያገኙና የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጣቸው እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

አማራ ክልል 25 ሺሕ ስደተኞችን መዝግቦ 17 ሺዎቹን የሕይወት ክህሎት ሥልጠና መስጠቱን፣ ይህንንም ተግባር በተለያዩ ክልሎች ላይ ተፈጻሚ እየተደረገ መሆኑን አክለዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ክልሉ 2 ሺሕ የሚሆኑ ስደተኞችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ሥራ ማስገባቱን ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፣ ሚኒስቴሩም ከጃንቦ ፅዳት አገልግሎት ድርጅት ጋር ስምምነት በመፈጸም 5,000 ዜጎችን ወደ ሥራ ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...