በኢዮብ ትኩዬ
የደረቅና የፈሳሽ ሳሙና አምራች ግለሰቦች፣ በአነስተኛ ጥቃቅን የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች በኬሚካል እጥረት ምክንያት ሥራ ለማቆም መገደዳቸውን ተናገሩ፡፡
አምራቾቹ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ፈሳሽና ደረቅ ሳሙና ለማምረት የሚያገለግሉ የተለያዩ ኬሚካሎች ዋጋቸው በየጊዜው ከእጥፍ በላይ ከፍ እያለ ከመሆኑ ባሻገር፣ ሰሞኑን ደግሞ በየማከፋፈያው ማግኝት አልተቻለም፡፡
ኤስኤልኢኤል (SLEL) የተሰኘ የሳሙና ማምረቻ ኬሚካልን ጨምሮ ሌሎችን በየማከፋፈያው ማግኘት እንዳልቻሉና ፈሳሽ ሳሙና የማምረት ሥራ እንዳቆሙ፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹ አስታውቀዋል፡፡
ሥራ ካቆሙት የግል ፈሳሽ ሳሙና አምራቾች መካከል የሆኑት ትዝታ አየለ፣ በዘርፉ ከተሰማሩ ዓመታት አስቆጥረው እንደነበርና የኬሚካል ዕጥረት ስለገጠማቸው ሥራ ለማቆም መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡
‹‹የዋጋ ንረቱን ተቋቁመን ፈሳሽ ሳሙና እያመረትን ነበር፤›› ያሉት ትዝታ፣ በተለይ በ2015 ዓ.ም. ከዋጋ ንረቱ ባሻገር የኬሚካል አቅርቦትም ስለሌለ መሥራት አልቻልንም ነው ያሉት፡፡
በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ፈሳሽ ሳሙና የሚያመርቱት አቶ ዓለሙ ይርዳው በበኩላቸው፣ ሳሙና ማምረት አቁመው ወደ ሌላ የሥራ ዘርፍ ለመሰማራት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
አምራቾቹ እንደሚሉት ከሆነ ኤስኤልኢኤል (SLEL)፣ ሱትሪክ አሲድ፣ ኮስቲክ ሶዳና ሌሎች ኬሚካሎች ካለፈው ዓመት ወዲህ ዋጋቸው በእጥፍ እየጨመረ መሆኑን፣ ሰሞኑን ደግሞ ወደ ማስፋፊያ አቅንተው ማግኘት እንዳልቻሉ ነው ያስረዱት፡፡
በተለይም ኤስኤልኢኤል እና ላብሳ (Labsa) የተሰኙት ከውጭ የሚገቡ ኬሚካሎችን ማግኘት አልተቻለም ተብሏል፡፡
የሲትሪክ አሲድ ዋጋ በ2014 ዓ.ም. የካቲት ወር ሲሸጥበት ከነበረው 2,000 ብር ወደ 7,000 ብር ከፍ ማለቱን ያስታወሱት አምራቾች፣ በ2015 ዓ.ም. ደግሞ ዋጋው ከአሥር ሺሕ ብር በላይ ንሯል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከዋጋ ንረቱ ባሻገር ኬሚካሉን በማከፋፈያዎች ማግኘት አለመቻሉ፣ በዘርፉ ለተሰማሩ አምራቾች ሥራ መቋረጥ ዋነኛ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ እንዲሁም ፈሳሽ ሳሙና ለማምረት አገልግሎት የሚውለው ሲትሪክ አሲድ ባለፈው ዓመት በኪሎ 300 ብር ሲሸጥ እንደነበር፣ በ2015 ዓ.ም. ግን ዋጋው ከእጥፍ በላይ ከመጨመሩም ባሻገር ማግኘት አልተቻለም ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡
ሶዲየም ሲልኬት የተሰኘ ኬሚካል ሌላኛው የአቅርቦት ችግር የተስተዋለበት የዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን አምራቾቹ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ አምራቾቹ በገለጹት መሠረት በተለይም ፈሳሽ ሳሙና ለማምረት እንዳይቻል ያደረገው የኮስቲክ ሶዳና ላብሳ ኬሚካል የዋጋ ንረትና የአቅርቦት ችግር ነው፡፡
ላብሳ ኬሚካል ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር በፊት ሲሸጥበት ከነበረው 75 ብር በወር ውስጥ 180 ብር ከፍ ብሎ እንደነበር፣ ዘንድሮ ግን በማከፋፈያዎች የለም ተብሏል፡፡
የኬሚካል አከፋፋዮች በበኩላቸው አብዛኞቹ የፈሳሽ ሳሙና ማምረቻ ኬሚካሎች ከውጭ እንደሚገቡ ገልጸው፣ እጥረቱ መከሰቱን አምነዋል፡፡ የፈሳሽና የደረቅ ሳሙና ጥሬ ዕቃዎች መወደድና አቅርቦት አለመኖር መንስዔው፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የጥሬ ዕቃዎች መወደድና የአቅርቦት አለመኖሩን ተከትሎ እጥረቱ ከመከሰቱ በፊት፣ በርከት ያሉ ኬሚካሎችን ገዝተው የነበሩ አምራቾች የፈሳሽ ደረቅ ሳሙና መሸጫ ዋጋውን ከእጥፍ በላይ ከፍ እንዳደረጉትም ተጠቃሚዎች በማማረር ገልጸዋል፡፡
የፈሳሽ ሳሙና ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው ባለፈው ዓመት 15 ብር ሲገዙት የነበረው አንድ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ሰሞኑን ወደ 45 ብር ከፍ ማለቱን፣ ወ/ሮ ዮርዳኖስ አስፋው በምሬት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት እስከ 30 ብር ሲሸጥ የነበረው ስካይ የተሰኘ ደረቅ ሳሙና፣ በመደብሮች ሰሞኑን ከ60 እስከ 70 ብር እየተሸጠ መሆኑን ተጠቃሚዋ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት እስከ 40 ብር ሲሸጥ የነበረው ትንሹ ዱሩ ደረቅ ሳሙና ወደ 90 ብር ከፍ ማለቱ ተመላክቷል፡፡ የዋጋ ጭማሪ ያሳዩት ከላይ የተጠቀሱት የደረቅ ፈሳሽ ሳሙና ዓይነቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌሎች ማለትም የመፀዳጃ ቤት ንፅህና መጠበቂያዎች ሻምፖና ኮንዲሽነር ጭምር መሆናቸውን ተጠቃሚዎች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡