Sunday, February 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለኢትዮጵያ የሚበጃት በሥርዓት መመራት እንጂ ሥርዓተ አልበኝነት አይደለም!

ከአስደናቂው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ በኋላ ወደ ወትሮው ሕይወት ስንመለስ ኢትዮጵያ ከሌሎች የውድድሩ ተሳታፊ የአፍሪካ አገሮች ባልተናነሰ ከእግር ኳስ በተጨማሪ፣ በሌሎች ዘርፎች ለምን ተፎካካሪ መሆን ያቅታታል የሚለው መነጋገሪያ ሊሆን ይገባል፡፡ ‹‹አይቻልም›› የሚለውን ሞራል ገዳይ ስሜት ‹‹ይቻላል›› በሚለው ቁርጠኝነት ለመቀየር ከወዲሁ ማብላላት ያስፈልጋል፡፡ ኳታር በውስን የነዳጅ ዘይት ሀብቷ ጠንካራ ሥርዓት የገነባች ትንሽ አገር መሆኗ ቢታወቅም፣ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ይህንን የመሰለ አስገራሚ ዝግጅት አድርጋ የዓለምን ቀልብ ትቆጣጠራለች ተብሎ አልተገመተም ነበር፡፡ የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ በፊት ኳታር ለምዕራቡ ዓለም የማይስማሙ ዕርምጃዎች መውሰድ ስትጀምር የገጠማት ተቃውሞ ሊመክን የቻለው፣ የአገርን ክብር የሚጠብቁና ስፖርታዊ መንፈስን ብቻ የተከተሉ ሥራዎችን በሥርዓት በማከናወኗ ነው፡፡ የዓለምን ትኩረት በሳቡ አስደናቂ ስታዲዮሞቿና ሌሎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ አስደናቂ በሆኑ ክስተቶች ታጅባ እንግዶቿን ተቀብላ ማስተናገድ መቻሏ ትልቅ ክብር አጎናፅፏታል፡፡ የዓለም ዋንጫው ከዚህ ቀደም ከታዩት ሁሉ በበለጠ ድንቅ ሆኖ መጠናቀቁ እንዳለ ሆኖ፣ ይህንን መሳይ ዝግጅት አሳምሮ ጀምሮ መጨረስ በሥርዓት የመመራት ውጤትን ያሳያል፡፡

ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ከዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ውድድሮች በርካታ ነገሮች መማር አለባቸው፡፡ አፍሪካን ወክለው ከተሳተፉት አገሮች ሞሮኮ አራተኛ ሆና ማጠናቀቋ ለሞሮኮያውያን ብቻ ሳይሆን፣ ለሁሉም አፍሪካውያን ወጣቶች የኩራትና ለወደፊት ውድድሮች ራስን ማዘጋጃ መንደርደሪያ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሞሮኮ እንደ ስፔን፣ ቤልጂየምና ፖርቹጋል የመሳሰሉ የአውሮፓ ኃያላንን አሸንፋ ለዚህ ክብር የበቃችው ‹‹ይቻላል›› በሚለው አይበገሬ መንፈስ ነው፡፡ እነዚያ የአትላስ አንበሶች ለአፍሪካውያን ይህንን ትንግርት ከማሳየታቸው በፊት ሩብ ፍፃሜ ከመድረስ የዘለለ ታሪክ ላልነበራት አፍሪካ፣ የዓለም ዋንጫ ኮታዋን ለማስጨመር ከባድ ግፊት እንደሚፈጥር የታወቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ሆነ ከዚያ በታች ባሉ ውድድሮች የሚሳተፉ ወጣት ተጫዋቾች፣ ከአሁን በኋላ ሕልማቸው ለአፍሪካ ዋንጫ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በላይ መሆን እንዳለበት መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ከወዲህ ራሳቸውን ጠብቀው በአውሮፓም ሆነ በሌሎች ትልልቅ ሊጎች ተፈላጊ እንዲሆኑ መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሌሎችን በቴሌቪዥን እየተመለከቱ ከማድነቅ ‹‹ይቻላል›› ብሎ መነሳት ያዋጣል፡፡

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ የአርጀንቲናና የፈረንሣይ ኮከብ ሆነው ያመሹት ሊዮኔል አንድሪያስ ሜሲና ክላይን ምባፔ በዕድሜ ቢለያዩም፣ ሁለቱም ለአገራቸው ያደረጉት ተጋድሎ ፉክክሩን እንዴት ደማቅ እንዳደረገው መቼም ቢሆን አይዘነጋም፡፡ ሁለቱ ከዋክብት አንዱ ለወጣቶች ሌላው ሌላው ለጎልማሶች የፅናት ተምሳሌት በመሆናቸው፣ በእግር ኳስም ሆነ በሌሎች የሥራ መስኮች አርዓያነታቸው ሊታሰብ ይገባል፡፡ ሁለቱን ለምሳሌ ያህል አነሳን እንጂ በዚህ የዓለም ዋንጫ አንፀባራቂ የነበሩ በርካታ ወጣትና አንጋፋ ተጫዋቾች ተስተውለዋል፡፡ ከወጣት አሠልጣኞች ደግሞ የአርጀንቲናው ሊዮኔል ካስታሎኒና የሞሮኮው ዋሊድ ሪግራጉዊ አይዘነጉም፡፡ ሁለቱም በዕድሜና በልምድ የሚበልጡዋቸውን አሠልጣኞች አልፈው ለዚህ ክብር የመብቃታቸው ዋነኛ ሚስጥር፣ ኃላፊነታቸውን በሥርዓት የመወጣት ችሎታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መሥራች ከሆኑት ከግብፅና ከሱዳን ጋር አብራ የነበረች ናት፡፡ ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በማሸነፍ ስሟ በታሪክ ይነሳል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከዘመኑ ጋር እኩል እየተራመዱ ሥርዓት መገንባትን ካላወቁበት ልፋታቸው መና ነው የሚሆነው፡፡

ለዓመታት የምንኮራበት አትሌቲክሳችን በተለያዩ ትውልዶች ኢትዮጵያን እያኮራ እዚህ ደርሷል፡፡ ከጀግናው ሻምበል አበበ ቢቂላ እስከ ለተሰንበት ግደይ ድረስ ኢትዮጵያን ወርቅ በወርቅ፣ ብር በብር፣ ነሐስ በነሐስ እያደረጉ ስሟን በኦሊምፒክና በዓለም ሻምፒዮና ያስጠሩ ድንቅ አትሌቶቻችን መቼም አይዘነጉም፡፡ በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ዘርፎች እነዚያን ድንቅ አትሌቶቻችንን አርዓያ ማድረግ ቢቻል ኖሮ፣ ኢትዮጵያ የበርካታ ድሎች ባለቤት ትሆን እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አሁንም አዲሱ ትውልድ በሁሉም የስፖርት ዘርፎች በመሰማራት በሥርዓት መመራት የሚለውን የጀግኖች አትሌቶቻችንን መርህ መከተል አለበት፡፡ በጥብቅ ዲሲፕሊንና ሥርዓት ባለው መንገድ ሕይወትን በመምራት ካሰቡበት ለመድረስና በዓለም የኢትዮጵያን ስም ለማስጠራት፣ ለነገ ይዋል ይደር የሚባል ቀጠሮ መያዝ የለበትም፡፡ ከዛሬ ጀምሮ በተሰማሩበት የስፖርት ዘርፍ ዘመኑ የደረሰበትን ሥልጠና በማግኘት፣ ከአፍሪካ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ ለመሆን እንቅስቃሴ ይጀመር፡፡ ዓለም በአስደማሚ ሁኔታ እየተጓዘ ቆሞ ማንቀላፈት ለማንም አይበጅም፡፡ ለሌሎች ድልና ዝና ቆሞ ከማጨብጨብ ባለፈ ‹‹እኔም እችላለሁ›› ብሎ በሥርዓት መመራት ነው የሚያዋጣው፡፡

ከስፖርቱ ዓለም ወጣ ስንል ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለንበትን ምስቅልቅል መመልከት የግድ ይሆናል፡፡ ብዙዎቹ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከትናንት ስህተቶቻቸው ተምረው ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ቁመና ላይ ሲገኙ፣ እኛ ግን ለአፍሪካውያን የነፃነት ተጋድሎ አርዓያዎችና ደጋፊዎች እንዳልነበርን የብሔርተኝነት ማጥ ውስጥ ተዘፍቀናል፡፡ ብሔሮቻችን፣ ቋንቋዎቻችን፣ ባህሎቻችን፣ እምነቶቻችን፣ እሴቶቻችንና የመሳሰሉት ጌጦቻችን ሆነው ሀብታም ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን መገንባት ሲገባን፣ ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ ማኅበራዊ እሴቶቻችንን አሽቀንጥረን ጥለን ለመፋጀት እያደባን ነው፡፡ ያለፉት ትውልዶች በደምና በአጥንት መስዋዕትነት ያቆዩልንን አገራችንን፣ ውኃ በማይቋጥሩና አርቆ ማሰብ በተሳናቸው ሰበቦች ለማፍረስ እንቅልፍ አጥተናል፡፡ ይህ አስፈሪና አሳፋሪ ድርጊታችን በዓለም ፊት መሳቂያ እያደረገን መሆኑን ዘንግተን፣ ለከንቱ የበላይነትና ዝና ስንል ብቻ ጦርነት እየቀሰቀስን ንፁኃንን አስፈጅተናል፡፡ አሁንም ያንን ወንጀል ለመድገምና ሌላ ዙር ጦርነት ለማስነሳት፣ በቋንቋና መሰል ልዩነቶች ተፋጠን ዕልቂት እየደገስን ነው፡፡ አገርን ተባብሮ በማሳደግ በእኩልነት የሚያኖር ሥርዓት መገንባት ይቻላል ማለት ሲገባ፣ በሰይጣናዊ መንፈስ አገር ለማፍረስ መቅበዝበዝ ያሳፍራል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን የሚያስፈልጋት ቅንነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ስክነትና ብልኃት የተጎናፀፈ የፖለቲካ አመራር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አመራር ሕዝብ የሚያከብርና ታሪክን የሚያስጠብቅ ሲሆን፣ ችግሮች ሲያጋጥሙም ከዘፈቀደ ዕርምጃ በፊት ምክክርን ያስቀድማል፡፡ ከዚህ በፊት የተሰሩ ስህተቶች ቢኖሩ እንኳ እነሱን ላለመድገም እየተጠነቀቀ፣ ለመፍትሔ የሚበጁ ሐሳቦች ላይ በማተኮር የጋራ አማካይ ይፈጥራል፡፡ በግራና በቀኝ የተሠለፉ የዘመኑ ፖለቲከኞች ግን ማስተዋል የጎደላቸው፣ ከበፊት ስህተቶች የማይማሩ፣ ለሕዝብ ክብር የማይሰጡ፣ ራሳቸውንና የተደራጁበትን ቡድን ከአገር የሚያስበልጡ፣ ዘመኑ ከደረሰበት የአስተሳሰብ የዕድገት ደረጃ ጋር የማይመጣጠኑ፣ ከቂምና ከበቀል ያልፀዱና ሴረኝነት የተጠናወታቸው ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ይህንን የመሰለ አስተዋይና አርቆ አሳቢ ሕዝብ መምራት እየተሳናቸው፣ አንዱ ችግር በስንት መከራ አበቃ ሲባል ሌላ ችግር ፈልፍለው እያወጡ አገሪቱን ያምሳሉ፡፡ ለሰላምና ለአብሮ መኖር መከፈል ያለበትን ሁሉ ከፍለው ኢትዮጵያውያንን በአሳታፊና በጠንካራ ሥርዓት ማስተባበር ሲገባቸው፣ ልዩነትና ጥላቻ እየዘሩ አገሪቱን የደም መሬት ለማድረግ ይዋደቃሉ፡፡  ይህ ክፋት መቆም አለበት፡፡ ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት በሥርዓት መመራት እንጂ ሥርዓተ አልበኝነት አይደለም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል በተባሉና በኦሮሚያ መንግሥት ላይ ክስ ለመመሥረት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...