Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ማኅበር 40 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳኑን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ብቸኛው የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ የሆነው የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር፣ በተጠናቀቀው የ2014 የሒሳብ ዓመት ከኢትዮጵያ ውጪ ካሉ ኩባንያዎች ከ25.3 ሚሊዮን ብር በላይ (ወደ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር) ዓረቦን ሲሰበስብ ወደ 40 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ማዳኑን አስታወቀ፡፡

ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ኩባንያው ከተቋቋመበት ዓላማዎቹ አንዱ ለጠለፋ መድን ሽፋን ወደ ውጭ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ መቀነስና ለውጭ ኩባንያዎች የጠለፋ መድን ሽፋን በመስጠት የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ነው፡፡ በመሆኑም በ2014 የሒሳብ ዓመት ብቻ ከኢትዮጵያ ውጪ ካሉ ኩባንያዎች የ25.3 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ገቢ በውጭ ምንዛሪ ማግኘት ችሏል፡፡

ከኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ የጠለፋ መድን ሽፋን ለማግኘት እየሠሩ ያሉ አሥር አገሮች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በሒሳብ ዓመቱ የጠለፋ መድን ሽፋን ለማግኘት የዓረቦን ገቢ ካስገኙ የአፍሪካ አገሮች የታንዛኒያ፣ የኬንያ፣ የሩዋንዳና የጋና ኩባንያዎች ይገኙበታል፡፡

በጠለፋ የመድን ሽፋን ወደ ውጭ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከማዳን አንፃርም፣ ኩባንያው ከተመሠረተበት ጊዜ ወዲህ ወደ 40 ሚሊዮን ዶላር (ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ) ማዳን ማስቻሉንና ከዚህም በኋላ ለውጭ ኩባንያዎች የሚወጣውን የመድን ሽፋን መጠን በመቀነስ ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል ተብሏል፡፡

የጠለፋ መድን ኩባንያው ከመቋቋሙ በፊት የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓመት ከሚሰበስቡት ዓረቦን፣ በአማካይ እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን በውጭ ምንዛሪ ከኢትዮጵያ ውጪ ላሉ የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያዎች ያውሉ እንደነበር፣ የኩባንየው  የስትራቴጂክና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አሁን ግን ኩባንያዎቹ ለውጭ ጠለፋ መድን ይሰጡ የበረውን የመድን ሽፋን ለኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ እየሰጡ በመሆኑ፣ ወደ ውጭ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እንዲቀንሱ እያደረገ ነው፡፡ አሁን ላይ አንዳንድ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለውጭ ጠለፋ መድን ሰጪዎች ይሰጡ ከነበሩት እስከ 40 በመቶ ድረስ የሚሆነውን፣ በኢትዮጵያ ለተቋቋመው የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ እየሰጡ ስለመሆኑ ከአቶ ፍቅሩ ገለጻ ለመዳት ተችሏል፡፡ ትናንት በተካሄደው የኩባንያው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደተገለጸው ደግሞ በ2014 ሒሳብ ዓመት ብቻ አገር ውስጥ ካሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ለውጭ አገር ኩባንያዎች ለሰጠው የጠለፋ መድን ሽፋን ያሰባሰበው ዓረቦን 1.36 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ19 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡ ከዚህ ዓረቦን ውስጥ በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያው ለካሳ ክፍያ ያዋለው የገንዘብ መጠን 392.9 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከቀዳሚው ዓመት በ91 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ክፍያ መፈጸሙንም የሒሳብ ዓመቱን አፈጻጸም በተመለከተ ያወጣው መግለጫ ያሳያል፡፡ የካሳ ክፍያለው በ34 በመቶ በልጦ ለመገኘቱ ዋና ምክንያት ናቸው ብሎ ከጠቀሳቸው ውስጥ፣ ለዋልያ ኢንዱስትሪ ለባህር ላይ ጉዞ የተከፈለውና በሶማሌ ክልል ለአየር ንረት ሽፋን የተከፈለ ከፍተኛ ካሳ ክፍያ በማጋጠሙ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ለተሽከርካሪና በቦንድ ዘርፍ የተከፈሉ ክፍያዎች መጨመር የካሳ ክፍያውን ከፍ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በኋላ 223.5 ሚሊዮን ብር ሲያተርፍ ይህ ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት በ14.6 ብልጫ አሳይቷል፡፡ የኩባንያው አጠቃላይ የሀብት መጠኑንም በ34.8 በመቶ በማሳደግ 3.1 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ የኩባንያው ካፒታልም 1.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ ባለአክሲዮኖች ከመንግሥትና ከግል ዘርፍ የተውጣጡ ሰባት ባንኮች፣ 17 የመድን ኩባንያዎች 93 ግለሰቦችና አንድ የሠራተኛ ማኅበር ናቸው፡፡ በትናንትናው ዕለትም አዳዲስ ባለአክሲዮኖችን በማካተት አጠቃላይ የባለአክሲዮኖችን ቁጥር 118 አድርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች