Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርላይጠቀሙበት የሚያጠራቅሙት የጡረታ መዋጮ

ላይጠቀሙበት የሚያጠራቅሙት የጡረታ መዋጮ

ቀን:

በአብርሃም ጴጥሮስ

መቼም ላይጠቀሙበት የሚያጠራቅሙት ምንድነው? ማለታችሁ አይቀርም ሰው ብዙ ስላለው ሳይሆን ካለችው ትንሽም ቢሆን ቆጥቦ የሚያስቀምጠው ለክፉ ቀን ይሆነኛል ብሎ ነው፡፡ ዛሬ በሌለን የምንቆጥበው ስለተረፈን ሳይሆን፣ የነገ መሠረቱ ዛሬ ነው በሚለው ብሂል ነው፡፡ የዛሬው ሐሳቤ ስለቁጠባ ታሪካዊ ዳራና ጠቀሜታ ለማውራት አይደለም፡፡

የሐሳቤ መነሻ ጠያቂም ባለቤትም ስለሌለው የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ መዋጮ ጉዳይ ነው፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ከተቀጠረበት ወር ጀምሮ ፈጣሪ አድሎት በሕይወት ከጡረታ እስኪገለል ወይም ባለመታደል፣ ዕድሜው ለጡረታ ሳይደርስ ከዚህ ዓለም በሞት እስኪለይ ድረስ በግዴታ ውዴታ መልኩ ሲያዋጣ ይኖራል፡፡ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ አንድ ዝቅተኛ ደመወዝና አንድ ከፍተኛ ደመወዝ የሚያገኝ ሠራተኛ በወርና በዓመት የሚቆጥበውን እንመልከት፡፡ ይህ መረጃ የዝቅተኛ ደመወዝ መነሻና የከፍተኛ ደመወዝ ጣሪያ የሚያሳይ ሳይሆን ለማነፃፀሪያ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው፡፡

 

ደመወዝ

የጡረታ መዋጮ የመንግሥት ድርሻ

(11%)

የጡረታ መዋጮ የራስ ድርሻ (7%)

 

ጠቅላላ ጡረታ

ዓመታዊ ጠቅላላ የጡረታ ተቀናሽ

15,000.00

1,650.00

     1,050.00           

     2,700.00

32,400.00

9,000.00

990.00

       630.00

     1,620.00

19,440.00

9,000.00

990.00

630.00

     1,620.00

19,440.00

8,500.00

935.00

595.00

     1,530.00

18,360.00

6,000.00

660.00

420.00

     1,080.00

12,960.00

5,000.00

550.00

350..00

900.00

10,800.00

 

በአንቀጽ ሁለት በጠቀስኩት መሠረት በሰንጠረዡ የተቀመጠው ያልተጣራ ደመወዝ ያገኝ የነበረ ሰው ያልታደለ ሆኖ ከዚህ ዓለም በሞት ቢገለል/ብትገለልና አምስት ልጆች ኖረውት ልጆቹ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ከሆነና ባለቤቱ ደግሞ ቀደም ብላ ይህን ዓለም የተሰናበተች ከሆነች፣ 30 ዓመትም 40 ዓመትም ያገልግል ገና ሀ ብሎ ሥራ ሲጀምር ጀምሮ ለዚያን ያህል ዓመታት ከራሱ ደመወዝ ተቆርጦና መንግሥት ለእሱ ብሎ የቆጠበውን ገንዘብ የበላው ጅብ አይጮህም፡፡ ልጆቹ አሥራ ስምንት ዓመት ይለፋቸው እንጂ የራሳቸው ገቢ ያላቸው ሳይሆኑ በእሱ/ሷ ትከሻ የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በእሱ/ሷ ሕልፈት ምክንያት ከትምህርታቸው ይስተጓጎላሉ፣ የቤት ኪራይ የሚከፍሉበት ያጣሉ፣ የሚበሉት አያገኙም፣ በአጠቃላይ ሕይወት ተመሰቃቅሎባቸው ለማኅበራዊ ኑሮ ቀውሶች ተጋላጭ የመሆናቸው ዕድል በጣም ሰፊ ነው፡፡ 

የመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አጀማመሩ ሠራተኞች ዕድሜያቸው ለጡረታ በሚደርስበት ወቅት በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት የራሳቸውም ይሁን የቤተሰባቸው ሕይወት እንዳይናጋ ለማድረግ መሆኑ አስረጂ አይሻም፡፡ ከላይ በጠቀስኩት ምሳሌ ሥሌት ስንሄድ ግን ተቸግሮ ያጠራቀመውና መንግሥት ያጠራቀመለትን ሀብት ጡረታ ወጥቶም ቢሆን ለራሱም ሳይጠቀምበት ጥሎት ያልፋል፡፡ ጡረታ ሳይወጣ ከሆነ ደግሞ ቤሳቤስቲን ቤተሰቡ ሳያገኝ ወደተፈጠረበት ይመለሳል፡፡ ይህን ያህል ጊዜ መንግሥት በአደራ ያስቀመጠለት ገንዘብ በመንግሥት ወይም በግል ባንክ አስቀምጦት ቢሆን ኖሮ፣ እኮ ቤተሰቡ ለእንግልትና ለጉስቁልና አይዳረግም ነበር፡፡

ስለዚህ ኮሚሽኑ ሰሚ ጆሮ ካለው ከሠራተኞች ለጡረታ ተብሎ የሚጠራቀመው ገንዘብ በምን ዓይነት ኢንቨስትመንት ውስጥ ቢገባ የተሻለ ገቢ ሊኖረው እንደሚችል፣ ለሠራተኛውና ለቤተሰቡ ሕይወት መቀጠል መደረግ ያለባቸው የድጋፍ ዓይነቶች ለይቶ የሚያቀርብለት የመንግሥት ሠራተኛ ተወካዮች በአማካይነት ሊኖረውና የሠራተኛው ድምፅ ሊሰማ ይገባል፡፡

እንደ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በግሌ ለኮሚሽኑ የምመክረው የተቋቋመበትን ዓላማ ዘንግቶ ዜጎች የሌላቸውን ገንዘብ ላይጠቀሙበት እንዲያጠራቅሙ ከማድረግ ይልቅ፣ ሠራተኛው ያጠራቀመው ገንዘብ ለራሱና ለቤተሰቡ የመኖር ህልውና እንዲያውለው ማቀድ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንፃር ከላይ ለማሳያነት ካነሳኋቸው የዝቅተኛና ከፍተኛ ጡረታ ከፋዮችን የዓመት ክፍያ ብቻ ብናይ፣ የዝቅተኛው በዓመት 10,800.00 (አሥር ሺሕ ስምንት መቶ) ብርና የከፍተኛው በዓመት 32,000.00 (ሰላሳ ሁለት ሺሕ) ብር ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ ማለት ሁለቱም 30 ዓመት አገልግለው ጡረታ ሳይወጡ ቢሞቱ በየወቅቱ ከሚታዩ የደመወዝ ጭማሪዎች አንፃር የሚጨምረው የመዋጮ መጠን ታሳቢ ሳናደርግ፣ በትንሹ ደመወዝተኛ በአገልግሎት ዘመኑ 324,000.00 (ሦስት መቶ ሃያ አራት ሺሕ) ሲያስቀምጥ ትልቁ ደግሞ 960,000.00 ብር (ዘጠኝ መቶ ስልሳ ሺሕ) ብር ያስቀምጣል ማለት ነው፡፡

ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች ይህ ብር ለቤተሰብ አገልግሎት አይውልም፡፡ የት እንደሚሄድ፣ ምን እንደሚደረግበት፣ ማን እንደሚወስንበት አይታወቅም፡፡ ኮሚሽኑ ለሠራተኛውና ለቤተሰቡ የቆምኩ ነኝ የሚል ከሆነ የኢንሹራንስ ኩባንያ በቀን አንድ ብር፣ በዓመት ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ብር ካስቀመጠ አንድ ቤተሰብ አባወራው/ዋ በሞት በሚለዩበት ወቅት ለቤተሰብ መቋቋሚያ 100,000.00 (አንድ መቶ ሺሕ) ብር ስለሚከፍል፣ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ የዚህ መድን ዋስትና አባል አድርጎ ተጠቃሚ ቢያደርገው ቤተሰብን ከማፍረስ፣ ወደ ጎዳና ከመውጣትና ለማኅበራዊ ኑሮ ቀውስ ተጋላጭ ከመሆን መታደግ ይችላል፡፡ ይህን ማድረግ የማይችል ከሆነ ግን ለሠራተኛ እኔ እሻልሃለው ያለው የመንግሥት አካል ላይጠቀምበት ከሚያጠራቅምለት ሠራተኛው በራሱ የባንክ ሒሳብ ቁጥር በመንግሥት ወይም በግል ባንኮች አሊያም በማይክሮ ፋይናንሶች፣ ለዚህን ያህል ዓመት ቢያስቀምጥ ከወለድ የሚገኝ ትርፍና የትርፍ ትርፍ በማግኘት የዕለት ኑሮውን ከመደጎም አልፎ ወደ ትልቅ ኢንቨስትመንት ሊያስገባው የሚያስችል ብድር በማግኘት የቤተሰብ ሕይወት መታደግ ስለሚቻል ቆጣቢውም አስቆጣቢውም ሊያስቡበት ይገባል እላለሁኝ፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...