Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ ስያሜ የመጣው ‹‹ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ›› ከታክስ በፊት 370 ሚሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ስያሜውን ‹‹ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ›› በሚል መቀየሩን ያስታወቀው ደቡብ ግሎባል ባንክ፣ በተጠናቀቀው የ2014 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙ ከታክስ በፊት 370 ሚሊዮን ብር ያተረፈ።

ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የነበረው የሥራ አፈጻጸም ስኬታማ እንደነበር የገለጸ ሲሆን፣ በዓመቱ መጨረሻ ያገኘው 370 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ41 በመቶ ዕድገት፣ ወይም የ108.4 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው አመላክቷል።

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ ባለፈው ቅዳሜ ለባንኩ ባለአክሲዮኖች ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ ባንኩ በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ አልፎ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡  

አመርቂ ውጤት ተገኝቶበታል የተባለውን የባንኩን የ2014 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም በዝርዝር ባቀረቡበት ሪፖርታቸው፣ በቀዳሚነት የጠቀሱት በተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ረገድ ባንኩ አገኘ ያሉትን ውጤት ነው፡፡ በዚህም መሠረት በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ26 በመቶ በማሳደግ፣ 10.99 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል ብለዋል፡፡ 

የብድር ሥርጭት አንፃርም  ከቀዳሚው ዓመት 9.3 በመቶ ዕድገት ያለው ብድር በማቅረብ የብድር ክምችቱን 9.48 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን፣ እንዲሁም የባንኩ ጠቅላላ ገቢ 2.12 ቢሊዮን ብር መድረሱን አብራርተዋል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ገቢ ጋር ሲነፃፀርም የ23 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ወጪውም በ20 በመቶ ጨምሮ 1.75 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ እንዲህ ባለው አፈጻጸሙ ባንኩ ከታክስ በፊት 370 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን፣ ይህ የትርፍ ምጣኔ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ41 በመቶ ዕድገት፣ ወይም የ108.4 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡ ባንኩ ያስመዘገበው ትርፍ የአንድ አክሲዮን የትርፍ ድርሻ 182 ብር ያስገኘ መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ በቀዳሚው ዓመት አንድ አክሲዮን የነበረው ትርፍ 166 ብር እንደነበር ከባንኩ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡  

የዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎት አንፃርም በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ግጭት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና ተያያዥ የሆኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች በባንኩ ዓለም አቀፍ ንግድና የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ላይ ጫና የፈጠረ ቢሆንም፣ እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች ተቋቁሞ 32.34 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡  

ደቡብ ግሎባል ባንክ ጠቅላላ የሀብት መጠኑን በ21 በመቶ አሳድጎ 14.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ 

የባንኩ የተከፈለ ካፒታልም የ17 በመቶ ዕድገት በማሳየት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ 1.63 ቢሊዮን ብር መድረሱንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ባንኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ እስከ 2018 ድረስ የተከፈለ ካፒታሉን አምስት ቢሊዮን ብር ማድረስ ስለሚገባው፣ ይህንን ለማሟላት ባለአክሲኖች ዕገዛ እንዲያደርጉ በዕለቱ ከቦርዱ ጥሪ ተላልፏል፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኩ ከዚህ በፊት ይጠቀምበት የነበረውን ስያሜና ዓርማ ጥናት ላይ በመመርኮዝ ራሱን ይበልጥ ሊያጎላና ሊገልጽ በሚችል መልኩ የሪብራንዲንግ ሥራ ተጠናቆ በዕለቱ ለባለአክሲዮኖች ቀርቦ እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡ ‹‹ይህ የስያሜና የዓርማ ለውጥ ዝም ብሎ ለውጥ ሳይሆን ባንካችን ተሃድሶ፣ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲወጣና በአገልግሎት ተጠቃሚው ዘንድ አዎንታዊ ገጽታ እንዲኖረው የሚያስችለው ነው፤›› ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ‹‹እንዲህ ያለው ለውጥ ገበያ ውስጥ ያለውን ውድድር በቀላሉ እንዲያሸንፍ ከማገዙም በላይ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ብራንድ እንዲኖረው ያስችላል፤›› ብለዋል፡፡ ባንኩ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለወደፊት የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ የሚሆን 5,550.9 ካሬ ሜትር ቦታ ሜክሲኮ በተለምዶ ኬኬር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደተረከበ፣ እንዲሁም ለዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ የሚሆን ሌላ ቦታም ለመግዛት የመጨረሻ ጫፍ ላይ ስለመድረሱ የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡ 

የባንኩን ቀጣይ ሥራዎች በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡት የባንኩ ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ቦሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ባንኩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የተጀመሩ ሥራዎች ውጤት እንደሚያመጡና ተወዳዳሪነታቸውን እንዲጨምሩ ለባለአክሲዮኖች ተናግረዋል፡፡   

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘውን ውጤት ዕድገት ጠብቆ እንዲሄድ፣ እንዲሁም በኢንዱሰትሪው ውስጥ ጠንካራና ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል ለማስቻል፣ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ሁኔታዎችን መሠረት ያደረገ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቅሰዋል፡፡ 

ከዚህ በኋላ ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ በሚል መጠሪያ መጠራት የሚጀምረው ይህ ባንክ፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 2,332 የሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ቅርንጫፎቹን ቁጥርም በ22 ጨምሮ 133 አድርሷል፡፡

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች