Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ብቻ አንድ ቢሊዮን ብር በማትረፍ የመጀመሪያው ባንክ ሆነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ ብቻ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማትረፍ የመጀመርያው ባንክ ሆነ። 

ባለፈው ቅዳሜ የባንኩ የ2014 የሒሳብ ዓመት ሪፖርት ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፣ የባንኩ አጠቃላይ ትርፍ ከታክስ በፊት 2.8 ቢሊዮን ብር ሆኖ ተመዝግቧል።

የባንኩ አጠቃላይ ዓመታዊ ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት በ1.7 ቢሊዮን ብር ወይም የ67.63 በመቶ ጭማሪ ያለው መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋው ገልጸዋል፡፡ በዚህም የባንኩ ባለአክሲዮኖች በአንድ አክሲዮን የሚያገኙት የትርፍ ድርሻ በ34 በመቶ እንዲያድግ ማስቻሉን ተናግረዋል።

ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዘርፍም በ2014 የሒሳብ ዓመት በኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ የሚባለውን ትርፍ ያገኘበት መሆኑንም አመልክተዋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋው እንደገለጹት ፣ ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት የወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎቱ ብቻ ከታክስ በፊት 1.06 ቢሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡ በዚህም ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማትረፍ የመጀመርያው የአገር ውስጥ ባንክ ለመሆን እንደቻለ ገልጸዋል።

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያሰባሰበው ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ መጠንም 17.12 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ49 በመቶ ብልጫ እንዳለው ታውቋል፡፡ 

በ2014 የሒሳብ ዓመት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሰጠው ብድር (ፋይናንስ ያደረገው) 13.51 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም በኢንዱስትሪው በዚህ ዘርፍ በአንድ ባንክ የተሰጠ ከፍተኛ ብድር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ 

ባንኩ የ2014 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን በማስመልከት ይፋ ባደረገው ሪፖርት ጎን ለጎን በሰጠው ተጨማሪ መረጃ፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት 84 ቢሊዮን ብር የነበረውን የባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችት በአዲሱ የሒሳብ ዓመት አጋማሽ ላይ ከ101 ቢሊዮን ብር ሆኗል። ይህም እስካሁን የብድር ክምችታቸውን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ከቻሉ ሦስት የግል ባንኮች ውስጥ አንዱ ለመሆን አስችሎታል።

ባንኩ በአንድ ዓመት ብቻ ተጨማሪ 37.6 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር የሰጠ ሲሆን፣ በ2015 ሒሳብ ዓመት ያለፉት አምስት ወር ውስጥ ደግሞ የለቀቀው አዲስ የብድር መጠን ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ከባንኩ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡ 

በሒሳብ ዓመቱ (2014) ብቻ የተሰጠው ብድር በቀዳሚው ዓመት ከተሰጠው በ54.6 በመቶ በመጨመር አጠቃላይ የባንኩ የብድር ክምችት 84.26 ቢሊዮን አድርሷል፡፡ ከተሰጠው ብድር ውስጥ የወጪ ንግድ ከፍተኛ ድርሻ ሲኖረው ከጠቅላላው ብድር 32.4 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ የአገር ውስጥ ንግድና ፋብሪካዎች ደግሞ ቀጣዩን ሥራ ይዘዋል፡፡ 25.87 በመቶና 19.58 ድርሻ አላቸው፡፡

ባንኩ ከብድር አመላለስ ረገድ በሒሳብ ዓመቱ 19.16 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን ይህ አፈጻጸሙ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የ29 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የተበላሸ የብድር ምጣኔውም ዓምና ከነበረበት 2.22 በመቶ ወደ 2.03 በመቶ ዝቅ ያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድም በሒሳብ ዓመቱ 25.65 ቢሊዮን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻለው ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 96.77 ቢሊዮን ብር ማድረስ አስችሎታል፡፡ ይህ አፈጻጸሙ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ36 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሆኗል፡፡ 

በአዲሱ 2015 የሒሳብ ዓመት አጋማሽ ላይ ደግሞ ይህ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 108 ቢሊዮን ብር መድረሱን ባንኩ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ባንኩ 438.28 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ገልጾ ይህም ባለፈው ዓመት ከተሰበሰበው ጋር ሲነፃፀር የ27.4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ 

ባንኩ በኢንዱስትሪው ውስጥ ለዓመታት በቀዳሚነት ሲጠቀስበት የነበረው አፈጻጸሙ የአስቀማጭ ደንበኞችን ቁጥር በየዓመቱ ማሳደጉ ሲሆን በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ብቻ 1.35 ሚሊዮን ተጨማሪ አዲስ ደንበኞችን በማፍራት አጠቃላይ የአስቀማጮቹን ቁጥር ዘጠኝ ሚሊዮን አድርሷል፡፡ 

በአዲሱ የሒሳብ ዓመት አጋማሽ ላይ ደግሞ ይህንን ቁጥር ከአሥር ሚሊዮን በላይ በማሻገር ከግል ባንኮች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ደንበኞች በመያዝ አሁንም በቀዳሚነት መዝለቁን ባንኩ ጠቅሷል፡፡

ባንኩ በ2014 ሒሳብ ዓመት ከፍተኛ አፈጻጸም አስመዝግቤበታለሁ ብሎ የጠቀሰው ዓመታዊ ገቢውን 12.05 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን ነው፡፡ ይህ ገቢ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ የ50.25 በመቶ ወይም የ4.03 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል፡፡ ባንኩ ዓመታዊ ወጪው ደግሞ በ45 በመቶ ጨምሮ 9.21 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ 

ባንኩ አጠቃላይ ካፒታሉን ወደ 11.31 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን ያመለከቱት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ፍቅሩ ዴክሲሳ (ዶ/ር) አጠቃላይ የባንኩ የሀብት መጠንም 114.6 ቢሊዮን መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡ 

የተከፈለ ካፒታል መጠኑን ደግሞ 7.73 ቢሊዮን ማድረሱን የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ 

በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ባንኩ 124 አዳዲስ ቅርንጫፎች የከፈተው የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ይህም አጠቃላይ የቅርንጫፎችን ቁጥር 593 አድርሶለታል፡፡ ከእነዚህ ቅርንጫፎች ውስጥ 77 በመቶው ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ መሆኑም ታውቋል፡፡ ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ 6,547 ሠራተኞች አሉት፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች