Wednesday, February 28, 2024

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አሜሪካ ጉባዔ ምን አተረፈች?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፈው ሳምንት ለሦስት ቀናት የተካሄደው የአፍሪካ አሜሪካ መሪዎች ስብሰባ ብዙ ጉዳዮች የተደመጡበት ነበር፡፡ ወደ 49 የአፍሪካ መሪዎችና የአፍሪካ ኅብረት የተካፈሉበት የዋሽንግተን ጉባዔ፣ አፍሪካን እንደ አንድ አጋር አሜሪካ ማየት የጀመረችበት አጋጣሚ ነው እየተባለ ነው፡፡ በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እ.ኤ.አ. በ2014 የተጀመረው የአፍሪካና የአሜሪካ መሪዎች ጉባዔ፣ ከስምንት ዓመታት በኋላ ነበር ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደው፡፡ አሜሪካ በእነዚህ ዓመታት ላልቶ የቆየውን ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለመጠገን ፍላጎት እንዳደረባት የጉባዔው መካሄድ ማሳያ ሆኖ እየቀረበ ነው፡፡

በጉባዔው ወቅት እንደ ተጠበቀውም የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለአፍሪካ መሪዎች የሚጥም ንግግር አድርገዋል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን፣ ‹‹አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር አጋርነት ትፈልጋለች እንጂ ፖለቲካዊ አስገዳጅነት መጣል አትፈልግም፡፡ ጥገኝነት ሳይሆን የጋራ ስኬት መፍጠር ትፈልጋለች፡፡ አፍሪካ ሲሳካላት አሜሪካ ይሳካላታል፣ ዓለምም እንደዚያው ነው፤›› ብለው መናገራቸው፣ ከአፍሪካ መሪዎች የሞቀ ጭብጨባ አስገኝቶላቸዋል፡፡

የባይደን ምክትል ካማላ ሃሪስ በበኩላቸው፣ ‹‹አስተዳደራችን ለአፍሪካ የሚያደርገውን ሳይሆን ከአፍሪካ ጋር በጋራ የሚሠራው ላይ የሚያተኩር ነው፤›› ብለው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን፣ ‹‹አፍሪካውያን ከማን ጋር እንደሚወዳጁ አሜሪካ አጋር አትመርጥላቸውም፣ የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው ፍላጎት የመወሰን ሙሉ መብት አላቸው፤›› ብለው ከዚህ ቀደም የተናገሩትን እንደገና አስተጋብተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ግን ይህን ጉባዔ በሚመለከት በተቃርኖ የተሞላ ምልከታ ነው ሲያስተጋቡ የተሰሙት፡፡ አሜሪካ አሁን ከሌሎች ኃያል አገሮች ጋር የገባችበት የኢኮኖሚና የጂኦ ፖለቲካ ፉክክር ዳግም ወደ አፍሪካ ፊቷን ለማዞር እንዳስገደዳት የገለጹ በርካታ ናቸው፡፡ በአልጄዚራ ላይ የአሜሪካ አፍሪካን ቅርምት (The US Scramble for Africa) የሚል ተቺ ጽሑፍ ያስነበበው ማርዋን ቢሻራ፣ አሜሪካ በትራምፕ ዘመን የተናደውን ከአፍሪካ ጋር የነበራትን መተማመንና መልካም ወዳጅነት መልሳ ለመጠገን መፈለጓን ይጠቅሳል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን እንደ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ቱርክና መሰል አገሮች ከአፍሪካ ጋር የፈጠሩት ሥር እየሰደደ የመጣ ወዳጅነት ከጨዋታ ውጪ እንዳያደርጋት በመሥጋት፣ የራሴን ድርሻ ልቀራመት በሚል ወደዚህ አኅጉራዊ መድረክ ዝግጅት መመለሷን ጸሐፊው ይተርካል፡፡

በዚህ ጉዳይ ተከታታይ ጽሑፎችን ሲያስነብብ የቆየው ሀዋርድ ፍሬንች በበኩሉ፣ አፍሪካን ለማማለልና የራሱን ጥቅም ለማፈስ ዕቅድ ይዞ የሚመጣው የዓለም አገር መብዛቱን በትዝብት ይገልጻል፡፡ በፎሬይን ፖሊሲ ላይ አፍሪካ እንዴት ከኃያላኑ ቅርምት ትዳን በሚል (How Africa Can Avoid Getting Scrambled) ርዕስ ባቀረበው ትንተና የኃያላኑ በአፍሪካ ሸሪክ ለማፍራት የሚደረግ ግብግብና ፉክክር መጠኑን አይለፍ እንጂ፣ ለአፍሪካዊያን ጠቃሚ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በዚህ የአፍሪካ አገሮችን የመወዳጀት ፉክክር ውስጥ ያልገባ አገር እንደሌለ ትዝብቱን አሥፍሯል፡፡ የቻይና አፍሪካ፣ የፈረንሣይ አፍሪካ፣ የብራዚል አፍሪካ፣ የጃፓን አፍሪካ፣ የሳዑዲ አፍሪካ፣ የቱርክ አፍሪካ፣ የሩሲያ አፍሪካ፣ የባህረ ሰላጤው አገሮችና የአፍሪካ እየተባለ ሁሉም የራሱን ማኅበር ይዞ መምጣቱን የጂኦ ፖለቲካ ቁንጅና ውድድር ሲል ይገልጸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ማሌዥያ፣ ደቡብ ኮሪያና ቬትናምን የመሳሰሉ አገሮች ጭምር የራሳቸውን አፍሪካን የማማለያ ዕቅድ ይዘው መምጣታቸውን ያወሳል፡፡

አፍሪካዊያን ከዚህ ሁሉ ወዳጅ እንሁን ጥያቄ ማትረፍና የራሳቸውን ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚችሉ የሞገተው ጸሐፊው፣ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም አርቆ አሳቢ የሆነ አካሄድን ሊከተሉ ይገባል ይላል፡፡ ከሁሉም ጋር ሚዛኑን የጠበቀ ወዳጅነት መፍጠርን መከተል ለአፍሪካ እንደሚበጅ ነው ጸሐፊው የሚመክረው፡፡

በዚህ ረገድ ስትቸገር አትታይም ስትባል የቆየችው ኢትዮጵያ፣ በቅርብ ዓመታት ግን ከምዕራባዊያን ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ስትፈተን ቆይታለች፡፡ አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች በተለይ የትግራይ ክልል ጦርነት መፈንዳትን ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ ያሳደሩት ዓለም አቀፍ ጫና ቀላል አልነበረም፡፡ ይህ ጫና ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ወደ ማዕቀብ ያደገ ሲሆን፣ በቅርቡ የሰላም ስምምነት እስከተፈረመ ጊዜ ድረስ ጫናው ሲጨምር እንጂ ሲረግብ አልታየም፡፡ ከሰሞኑ በአፍሪካ አሜሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሚመራ የልዑካን ቡድን የተወከለችው ኢትዮጵያ፣ አጋጣሚው ከምዕራባዊያኑ ጋር የነበራትን የሻከረ ግንኙነት ለማለዘብ በእጅጉ ተጠቅማበታለች እየተባለ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ለሪፖርተር አስተያየቱን የሰጠው ጋዜጠኛና የውጭ ግንኙነት ባለሙያ ፍትህአወቅ የወንድወሰን፣ አጋጣሚው ለኢትዮጵያ ዳግም ከምዕራቡ ዓለም ጋር ግንኙነቷን ያደሰችበት መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ‹‹ከጥቂት ወራት በፊት እኮ ኢትዮጵያን ማናገርም ሆነ ማድመጥ አይፈልጉም ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ እየተለወጠ መሆኑን በዚህ መድረክ ታዝበናል፡፡ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ብቻ የተደረገ ግንኙነት ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ለማግባባትም ምቹ ዕድል አግኝተናል፡፡ በግሌ በኢትዮጵያ ላይ ብዙ መለሳለስ ምዕራቡ ዓለም እያሳየ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማቱም ቢሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር ዳግም ለመቀራረብ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል፡፡ ብድርና ዕርዳታ ከመልቀቅ በተጨማሪ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የዕዳ ስረዛና ማራዘም ዕርምጃዎችን ወደ መውሰድ እንደሚሄዱ እገምታለሁ፤›› በማለት ነው ስለዚህ ጉባዔ ያለውን ምልከታ ያጋራው፡፡  

የዓለም ባንክ ተጨማሪ የ700 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጥ ማስታወቁ ከዚህ ጉባዔ ጎን የተሰማ ትልቅ ዜና ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ (ዶ/ር) የመሩትና በአፍሪካ አሜሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ የተሳተፈው ልዑክ ስኬታማ ቆይታ አድርጎ ስለመመለሱ በመንግሥት በኩል ሲገለጽ ሰንብቷል፡፡ ከአሜሪካ ጋር ሻክሮ የቆውን ግንኙነት ለማሻሻል የልዑካን ቡድኑ ጉዞ አስፈላጊ ነበር ተብሏል፡፡ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ተፈጥሮ የነበረውን ግንኙነት መላላት ለማስቀረት የልዑኩ ጉዞ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኑ ተነግሯል፡፡ በጦርነት የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ሒደት የዓለም አቀፍ አጋሮችን ድጋፍ ለማግኘት፣ የልዑካን ቡድኑ ጥረት ስለማድረጉ ሳይቀር በመንግሥት በኩል ይፋ ተደርጓል፡፡

ይህ ሁሉ የተገኘው ደግሞ በኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት ለማስቆም የቻለ የሰላም ስምምነት መደረግ በመቻሉ ነው ተብሏል፡፡ በሌላም በኩል አገሪቱ እያካሄደች ያለችው የኢኮኖሚ ሪፎርም በትክክለኛ መንገድ እየተጓዘ መሆኑ ሌላው የቡድኑን ጉዞ ውጤታማ እንዲሆን ማገዙ ተወስቷል፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) የመሩት የልዑካን ቡድን በአሜሪካ አፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ከመካፈል ባለፈ፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ለመነጋገርና አጋርነትን ለማደስ አጋጣሚን የፈጠረ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡ ከልዑካን ቡድኑ ጋር ተጉዘው የነበሩ ሦስት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው እንደተናገሩት፣ በጉባዔው መካፈል ኢትዮጵያን በብዙ መንገዶች የጠቀመ ጉዳይ ነበር፡፡ ከ22 በላይ የውይይት መድረኮች ጉባዔው እንደነበሩትና ኢትዮጵያን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ልዑካን ቡድኑ ሲሳተፍ መቆየቱን የልዑካን ቡድኑ አባላት አስረድተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ በዲፕሎማሲውና በፖለቲካው የተገኘውን ጥቅም ዘርዝረዋል፡፡ በርቀትና በስሚ ሰሚ ስለኢትዮጵያ የሚያውቁትን የተሳሳተ መረጃ በአካል ተገኝቶ እውነታውን ለማስረዳት፣ ዳግም መተማመንና ቅርርብ ለመፍጠር ጉባዔው የሚያስችል ነበርም ብለዋል፡፡

በምዕራቡ ዘንድ በኢትዮጵያ ላይ ሲራመድ የቆየውን የተሳሳተ ፖሊሲ ለማስተካከል፣ ከአሜሪካ ፖለቲከኞችም ሆነ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች ጋር ብዙ ውይይቶች መደረጋቸውን አክለዋል፡፡ ‹‹ሰላም በሌለበት ወቅትም ቢሆን በእግር ለመቆም ያደረግነው ጥረት፣ ለሰላም መምጣት ያለን ፍላጎትና ያሳየነው ተነሳሽነት ከሁሉ በላይ ዕውቅና አግኝቷል፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ ይህ ደግሞ የተዛቡ አመለካከቶችን ለመቀየር የረዳ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ 

ስለአጎዋ ዕድል መመለስም ሆነ ስለ ፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ያወሱት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ‹‹አጎዋ ትንሽ ዕድል ነው፡፡ እኛም እኮ ከቦይንግ ስንገዛ ለአሜሪካ ዕድል እየፈጠርን ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ጥቅም እስከሆነ ከማንም ጋር እንወዳጃለን፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች አፍሪካ ለሁሉም አጋርነት ፈላጊ በቂ ዕድል አላቸው፤›› በማለት ነበር ያስረዱት፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ ‹‹አፍሪካ የዓለም ልማት ምንጭ ልትሆን እንደምትችል አሳይታለች፡፡ የአፍሪካ ስኬትና ዕድገት ለዓለም መሻሻል መፍትሔ ነው የሚል መልዕክት አፍሪካ አስተላልፋለች፤›› ሲሉ የጉባዔውን ጠቀሜታ ገልጸዋል፡፡

‹‹ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር የተደረጉ ውይይቶችና የተደረሱ ስምምነቶች ናቸው የዚህ ጉባዔ ትልቅ ስኬትም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አገራዊ የዕዳ ጫናችን ቀላል አይደለም፡፡ ኮሮናና የዩክሬን ጦርነት ችግሩን አባብሶታል፡፡ ብድሮችን ለማቃለል አሳማኝ ምክንያትም እያለ ለጫና ስለሚጠቀሙበት ብቻ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁነት ብዙም አይታይም ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ መቀየሩን አይተናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በዚህ ጉዞ ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ መገኘቱን ትልቅ ስኬት ያሉት አቶ መላኩ፣ ከአሜሪካና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል ለኢትዮጵያ የውጭ ባለሀብቶችን መተማመን በመጨመር፣ ወደ አገሪቱ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ይስባል ነው ያሉት፡፡ ይህ ደግሞ የተጀመረው የኢኮኖሚ ሪፎርም ሥራ እየተሳካ እንዲሄድ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ እንደሚያደርግ ነው ያስረዱት፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ፣ ጉባዔው የቢዝነስ ዕድሎችንና የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ስኬት ለማስተዋወቅ ብዙ እንደጠቀመ አውስተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉበትና የአሜሪካ ንግድ ሚኒስትር ኃላፊ ካትሪን ታይ በተካፈሉበት፣ ከ300 በላይ ኢንቨስተሮችና ነጋዴዎች የተካፈሉበት ቢዝነስ ስብሰባ መደረጉን አንዱ ትልቅ አጋጣሚ ብለውታል፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ የቢዝነስ ስብሰባዎች ጎን ለጎን መደረጋቸውን በማውሳትም፣ አሜሪካውያን በሚዲያ ትርክት ብቻ ከአፍሪካ ጋር ግንኙነት ማጠናከር እንደማይቻል እየተረዱ መምጣታቸውን በጉባዔው መታዘባቸውን አብራርተዋል፡፡

ሦስቱ የልዑካን ቡድን አባላት የመንግሥት ባለሥልጣናት ምንም ቢሉም ግን፣ የአፍሪካና የአሜሪካ ወዳጅነትና አጋርነት በሚባለው ልክ መጠናከር አለመቻሉን ብዙዎች በመረጃ ይሞግታሉ፡፡ 

አሜሪካ በቡድን 20 አባል አገሮች ማኅበር ውስጥ አፍሪካ ቋሚ አባልነት እንዲኖራት እንደምትደግፍ ማስታወቋን፣ ይሁን እንጂ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አፍሪካ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያለው ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት መፈለጓን ስትገልጽ አልታየችም ነው የሚሉት፡፡

አሜሪካ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት በአፍሪካ በተለያዩ መስኮች ፈሰስ የሚደረግ የ50 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ዕቅድን ይፋ አድርጋለች፡፡ አሜሪካ ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟንም ይፋ አድርጋለች፡፡ ይሁን እንጂ አሜሪካ በተናጠል ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ምጣኔ ለማሳደግ ስላላት ዕቅድ ይፋ ያደረገችው ነገር የለም ሲሉ ያክላሉ፡፡

ደቡብ አፍሪካ ባለፈው ዓመት ከአሜሪካ ጋር 21 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ልውውጥ ነበራት፡፡ ይህ በአሜሪካና በአንድ የአፍሪካ አገር መካከል የተመዘገበ ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ ምጣኔ ነው፡፡ አሜሪካ በክሊንተን ዘመን የሰጠችው ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገሮች ከቀረጥና ታሪፍ ነፃ ወደ አሜሪካ ገበያ ምርት እንዲልኩ የሚያስችለው የአጎዋ ንግድ ዕድል ላለፉት 25 ዓመታት የዘለቀ ቢሆንም፣ አኅጉሪቱ በዚህ መንገድ ብዙ አለመጠቀሟ ይነገራል፡፡ ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር ሸቀጥ በዚህ ንግድ ዕድል ተጠቅማ ስትልክ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዕድሉ ተጠቃሚነት እንድትወጣ ተደርጋለች፡፡ ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ተመሳሳይ ዕጣ የገጠማቸው ሲሆን፣ የንግድ ዕድሉን ለመጠቀም በሚጠይቀው ውጣ ውረድና በራሳቸው በአፍሪካ መንግሥታት ደካማ እንቅስቃሴ የተነሳ ዕድሉ ለአፍሪካ ያመጣው ትሩፋት ውስን ነው ሲባል ቆይቷል፡፡

ቻይና ከአፍሪካ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት በመተሳሰር ቀዳሚዋ አገር ናት፡፡ እ.ኤ.አ. 2021 ከአፍሪካ ጋር 254 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ልውውጥ ያደረገችው ቻይና፣ ከአሜሪካ የ65 ቢሊዮን ዶላር ልውውጥ በአራት እጥፍ ይበልጣል፡፡ ቻይና ይህም ብቻ አይደለም በአፍሪካ ቀዳሚዋ የውጭ ኢንቨስትመንት ምንጭ ናት፡፡ በሁለተኝነት የምትገኘው አሜሪካ፣ ፈረንሣይና ቱርክ በዚህ ረገድ ቀጣዮቹን ቦታዎች ይይዛሉ፡፡ አሜሪካ አሁን የአፍሪካ ሁነኛ አጋር ለመሆን ተነስቻለሁ ብትልም፣ በተናጠልም ሆነ በማኅበር ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማሳደግ እጅግ ብዙ መንገድ ገና እንደሚቀራት ነው በርካታ መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

አፍሮ ባሮ ሜትር ሕዝብ አስተያየት መገምገሚያ ጥናት እንዳረጋገጠው ከሆነ ደግሞ፣ የተለያዩ አፍሪካ አገሮች ዜጎች በአሜሪካ ላይ ያላቸው መተማመን እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አሜሪካ በአገራቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ በጎ አስተዋጽኦ አላት ብለው የሚያምኑት ወደ 60 በመቶ አፍሪካዊያን ብቻ ናቸው፡፡ ቻይና በአገራችን በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ በጎ ተፅዕኖ አላት የሚሉ 63 በመቶ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ሩሲያ 35 በመቶ ተፅዕኖዋ በጎ ነው ይላሉ፡፡ አውሮፓ ደግሞ 46 በመቶ በጎ ተፅዕኖ አላት የሚሉ አፍሪካዊያን አሉ፡፡ ይህ የጥናት ውጤት አሁን የአፍሪካ ዜጎች ለምዕራባዊያን የተጋነነ ግምት መስጠትን እየተው መምጣታቸውን ያረጋገጠ ነው ተብሎለታል፡፡ በአፍሪካ አገሮች ዜጎች መካከል ከአንዱ የዓለም ኃያል (ከምዕራባዊያን) ጋር ብቻ ከመጣበቅ ይልቅ፣ አገሮቻቸው ከተለያዩ የዓለም አገሮች ጋር ሚዛኑን የጠበቀ ግንኙነት እንዲመሠርቱ የመፈለግ ስሜት እየተፈጠረ መሆኑን አመላካች ተብሏል፡፡

የአፍሪካ አሜሪካ ጉባዔ ሲጀመር በስትራቴጂክና ዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል (Centre for Strategic and International Studies) ውይይት መድረክ ላይ የቀረቡት ካሜሮን ሀድሰን የተባሉ አንድ የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ፣ የአሜሪካና የሌሎች አገሮችን አፍሪካ ወዳጅነት ለማፎካከር ሞክረዋል፡፡

‹‹የቻይና አፍሪካ ስትራቴጂን ብንመለከት ከቃላቱ ጀምሮ አጻጻፉ የአሜሪካን ግልባጭ ነው፡፡ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች የቻይና አፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ከፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር የ15 ደቂቃ ውይይት ለማድረግ ተፈቅዶላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በስትራቴጂ ካየን አሜሪካ ቻይና ይዛ ከቀረበችው የተለየ ነገር የላትም፤›› ብለዋል፡፡

አፍሪካዊያን አሁን የስትራቴጂም ሆነ የዕቅድ ጋጋታ ሳይሆን፣ ተጨባጭና ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ የተግባር ዕርምጃ ነው የሚያስፈልጋቸው ሲሉም ባለሙያው አክለዋል፡፡

አሜሪካ ለአፍሪካ ችግሮች በተግባር መፍትሔ ለማፈላለግም ስትሠራ የታየችበት አጋጣሚ ብዙ መሆኑን ያወሱት አጥኚው፣ ‹‹በኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልል ሰላም እንዲሰፍን ያደረግነው እኛ ነን እኮ፡፡ ቻይናውያን በአፍሪካ ንግድ እንጂ ፖለቲካ በተደረገበት ድርሽ አይሉም፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ካሜሮን ሀድሰን ትንተናቸውን ሲቀጥሉም አፍሪካ ተጨባጭ ችግር የሚፈታ ዕቅድ ትፈልጋለች ብለዋል፡፡ ‹‹አሜሪካም ብትሆን እስካሁን ካደረገችው በበለጠ በአፍሪካ ጉዳይ ውስጥ በመግባት የዴሞክራቲክ ኮንጎውን መሪ ሺሴኬዲን ከሩዋንዳው መሪ ካጋሜ ጋር የማቀራረብ ዓይነት ጥረት ልታደርግ ይገባል፡፡ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ አልሲሲንና ዓብይን (ዶ/ር) በማቀራረብ ተጨባጭ የሆኑ የአፍሪካ ችግሮች እንዲፈቱ አሜሪካም ብትሆን መሥራት ይጠበቅባታል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -