- ፓርቲያችን ባቀረበው ሰነድ ላይ እየተወያየን ነበር።
- የምን ሰነድ?
- አቅምን በውጤት ፈተናን በስኬት የሚል ሰነድ ነው።
- ታዲያ እንዴት ነበር ውይይቱ?
- በስኬት ተጠናቋል፡፡
- መቼም የዚህ አገር ችግርና ችግሩን ለመፍታት የሚደረግ ስብሰባ ማለቂያ የለውም።
- እንዴት?
- አንድ ችግር ሲመጣ እናንተ ችግሩን ለመፍታት ስትሰበሰቡ፣ ሌላ ችግር ሲመጣ እናንተ ስትሰበሰቡ …
- እሺ …
- የሰሜኑ ችግር ተቀረፈ ሲባል ይኸው በመሀል አገር ደግሞ የባንዲራና የመዝሙር ተቃውሞ ሲቀሰቀስ እናንተም ስትሰበሰቡ ….
- እሺ…?
- ይኸው …መከራና ስብሰባ እየተፈራረቁብን ጊዜያችንን ፈጀነው ማለቴ ነው።
- አትሳሳቺ!
- ምን ተሳሳትኩ?
- እኛ ችግርና ፈተናን አንቺ እንደምታስቢው አንመለከታቸውም፣ ሥጋትም አይፈጥሩብንም።
- ምንድነው ታዲያ የሚፈጥሩባችሁ?
- ብርታት!
- ምን አለ ደንዳና ልብ ሰጥቶን እንደናንተ በሆን!
- አትሳሳቺ!
- እንዴት?
- ይህ አመለካከታችን ከድንዳኔ አይደለም የሚመነጨው።
- እ…
- ከትንታኔ ነው፡፡
- ታዲያ ትንታኔያችሁ ለምን ሊፈታው አልቻለም?
- ምኑን?
- ችግርና ፈተናውን?
- እንደነገርኩሽ ነው።
- ምን?
- የእኛ ትንታኔ ችግርና ፈተናዎችን ስለመፍታት አያተኩርም።
- ታዲያ ምን ላይ ነው የሚያተኩረው?
- ትንታኔያችን?
- እህ…?
- ፈተናዎችን ወደ ዕድል መቀየር፡፡
- ከዚያስ?
- ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ማሸጋገር!
- ብቻ እንዳይሰሟችሁ?
- እነ ማን?
- ማትሪክ ተፈታኞች፡፡
- ትቀለጃለሽ አይደል?
- ቀልዴን አይደለም። እንዲያውም ሕዝቡ ራሱ እዚህ ላይ ቢያተኩር ጥሩ ነበር።
- ምን ላይ ቢያተኩር?
- ፈታናውን ወደ ዕድል ስለመቀየር፡፡
- ምንድነው የሕዝቡ ፈተና?
- እናንተው!
[ክቡር ሚኒስትሩ በሰሞኑ የፓርቲ ስብሰባ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚያሻግሩ ውሳኔዎች መወሰናቸውን ለሕዝብ እንዲያሳውቁ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት የሚያደርጉትን የንግግር ይዘት ከአማካሪያቸው ጋር ሆነው እያረቀቁ ነው]
- ፈተናን ወደ ዕድል በመቀየር ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ማሻገር የሚለው እንዳይቀር!
- ክቡር ሚኒስትር እሱማ አይቀርም፣ ይካተታል ግን…?
- ግን ምን?
- ያው ሕዝቡ ካለበት ችግር አኳያ መጠየቁ አይቀርም።
- ምን?
- ፈታናዎቹ እንዴት ነው ወደ ዕድል የሚቀየሩት ማለቱ አይቀርም።
- ንግግር እንጂ ውይይት እኮ አይኖርም።
- ቢሆንም እንዴት የሚለውን መስማት ይፈልጋል።
- ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?
- ያልተለመዱ ሐሳቦችን ማንሳት ጥሩ ይመስለኛል።
- ያልተለመዱ ማለት?
- አሃ …የሚያስብል ካልሆነም ኮንፊውዝ ማድርግ የሚችል ሐሳብ ቢነሳ ተስፋ ወይም…
- ወይም ጊዜ ይሰጣል።
- እና ምን ቢነሳ ይሻላል?
- ለምሳሌ የFive D ሞዴልን በመጠቀም ችግሮችን ወደ ዕድል ለመቀየር ይሠራል ማለት እንችላለን።
- እሱ ባለፈው ተብሏል።
- ተብሏል?
- የሰማሁ መሰለኝ።
- ከሆነ የ5ቱ መ ሕጎች ተግባራዊ እንዲደረጉ ተወስኗል ማለት እንችላለን፣ ምን ያስባሉ?
- ሳይሻል አይቀርም፣ ግን ምንድናቸው የሚል ጥያቄ አይፈጥርም?
- እንዘረዝራቸዋለን።
- ጥሩ። ቀጥል…
- የመጀመሪያው ‹‹መ›› መሥራት ነው።
- እሺ …
- ሁለተኛው ‹‹መ›› መለወጥ ነው።
- ጥሩ ነው።
- ሦስተኛው ‹‹መ›› … ሙስናን መታገል ነው።
- ‹‹ሙ›› ገባሃ?
- ምን አሉኝ?
- ዘለልክ ወደ ‹‹መ›› ተመለስ?!
- ኦ… ይቅርታ ምን ብንለው ይሻላል?
- ‹‹መ›› መስረቅን መታገል፣ አይሆንም?
- በጣም ጥሩ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- በል እየተጠነቀቅክ?
- ለምን?
- ከ 5 እንዳናልፍ!