Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገቡ የአገር ውስጥ ድርጅቶች ቁጥር  ጨመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ካስመዘገቡ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ተፈራረመ

በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በአመዛኙ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ተቀዛቅዞ የቆየው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስትመንት ፍሰት፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በመሻሻሉ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገቡ የአገር ውስጥ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተነገረ፡፡

ለአብነትም ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ቁጥራቸው 20 የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሠማራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር መፈራረማቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ባለሀብቶቹ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች የለማ መሬትና ሼድ ተከራይተው ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመራቸው ታውቋል፡፡ ይህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከነበረው ፍሰት የተሻለ መነቃቃት የታየበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ፣ በቀጣይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ለማልማት በሒደት ላይ ያሉ በርካታ ባለሀብቶች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከአጎዋ መታገድ ጋር ተያይዞ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች በተመቻቸው ዕድል የአገር ውስጥ ድርጅቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው ለማልማት ስምምነት እያደረጉ መሆኑን  የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለዋል፡፡

‹‹ባለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ሁኔታ ብዙ ትምህርት ወስደናል፡፡ አንዱ ከወሰድነው ትምህርት መካከል የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት፣ የአገር ውስጥ አምራቾችና ባለሀብቶች ማበረታታት እንደሚገባን ተገንዝበናል፤›› ያሉት አቶ አክሊሉ፣ ‹‹ችግር በገጠመን ወቅት ኮሽ ባለ ቁጥር ጥሎ የሚፈረጥጥ በጣም በርካታ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተያያዘም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ካስመዘገቡ ሦስት አምራች ኩባንያዎች ጋር የውል ስምምነት በተጠናቀቀው ሳምንት ተፈራርሟል።

በጅማና በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም በአዲስ ኢንዱስትሪ መንደር ገብተው ለማልማት የውል ስምምነት የተፈራረሙት ኩባንያዎች፣ በጠቅላላው ከ600 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሏል፡፡

ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል ካሠሩ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ጉምሳ ትሬዲንግ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ አሥር ሺሕ ካሬ ሜትር የለማ መሬት በመከራየት፣ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት በማድረግ የመድኃኒት ማሸጊያ ቁሳቁሶችን የሚያመርት፣ ለ140 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ፋብሪካ እንደሚገነባ ተገልጿል።

ሱጂ ሊያና የተሰኘው በሁለት ህንዳውያንና ኢትዮጵያዊ ባለሀብት የተመሠረተው ኩባንያ በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 800 ካሬ ሜትር የለማ መሬት በመረከብ፣ ከ206 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት በማድረግ የኦክስጅንና የናይትሮጅን ማምረቻ እንደሚገነባና ለ300 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር በስምምነት መርሐ ግብሩ ላይ ተነግሯል፡፡

እንዲሁም ኢምፓክት ፕሪንቲንግና ግራፊክስ የተሰኘው ድርጅት በኅትመትና አልባሳት ምርት የተሠማራ ኩባንያ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በአዲስ ኢንዱስትሪ መንደር 1,150 ካሬ ሜትር የማምረቻ ሼድ በመከራየት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት በማድረግ በአልባሳት ኅትመትና ዣንጥላ ማምረት ሥራ ላይ እንደሚሠማራና በዚህም ለ200 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ሲል ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡

የሱጂ ሊያና ትሬዲንግ ፒኤልሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ግርማ አባቢ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በሕክምናው ዘርፍ የቆየው ተቋማቸው ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስትመንት ገብተዋል፡፡ የሕክምናው ዘርፍ ግብዓት ማግኘት ከባድ ከመሆኑ አንፃር ግብዓቱን ለማምረት የተሰናዳው ሱጂ ሊያና፣ ኦክስጂንና ናይትሮጅንን በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እንደሚያመርት ተገልጿል፡፡

ድርጅቱ ለኢንዱስትሪና ለሕክምና አገልግሎት የሚያገለግለውን የኦክስጅንና የናይትሮጅን ፍላጎት ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያመርት እንደቆየ፣ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን ያለውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ምርቱን ለማቅረብና የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገብቶ መሥራቱ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ግርማ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

አገሪቱ የነበረችበት የሰላም ሁኔታ የድርጅቱን የውጭ አጋሮች በኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ሥራው ላይ ወደኋላ እንዲሉ አድርጎ መቆየቱን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሰላም ሁኔታ ጥሩ መልክ መያዝ ባለሀብቶቹ በድፍረት እንዲመጡ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች