Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለመገናኛ ብዙኃን የቀረጥ ማበረታቻ ማስፈጸሚያ የሕግ ማዕቀፎች  እንዲወጡ ተጠየቀ

ለመገናኛ ብዙኃን የቀረጥ ማበረታቻ ማስፈጸሚያ የሕግ ማዕቀፎች  እንዲወጡ ተጠየቀ

ቀን:

መገናኛ ብዙኃን በጉጉት የሚጠብቁትንና በፖሊሲ ውስጥ የተዘረዘሩ የቀረጥና ሌሎች ማበረታቻዎችን ለማስፈጸም የሚረዱ የሕግ ማዕቀፎችን የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በማዘጋጀት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡

በመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ የተዘረዘሩ የቀረጥ፣ የመሥሪያ ቦታ አቅርቦት፣ ቅድሚያ የውጭ ምንዛሪ ዕድልና የመሳሰሉትን ማበረታቻዎችን ለማስፈጸም የሚረዱ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት፣ ለተግባራዊነታቸው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲወጡ የጠየቁት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የፈቃድና ምዝገባ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋንታሁን አስረስ ናቸው፡፡

የፈቃድና ምዝገባ ዋና ዳይሬክተሩ ይህን የተናገሩት፣ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት ይፋዊ ሥርጭቱን ሐሙስ ታኅሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በጀመረው ትርታ ኤፍኤም 97.6 ሬዲዮ ጣቢያ መደበኛ ሥርጭት ማብሰሪያ መርሐ ግብር ላይ ነው፡፡

መገናኛ ብዙኃንን በተመለከተ የተሻሻሉና የተዘጋጁ የሕግ ማሻሻያዎችን ያስታወሱት አቶ ፋንታሁን፣ ይህንን መሠረት አድርጎ ባለሥልጣኑ ቅርንጫፎችን ሳይጨምር 23 የሕዝብ፣ 54 የንግድና 68 የማኅበረሰብ በድምሩ 145 የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፈቃድ የሰጠ መሆኑን፣ ከእነዚህ ውስጥ ትርታን ጨምሮ ሥርጭት ላይ ላሉ 14 የሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ መስጠቱን አክለዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ፣ የፕሬስ ነፃነትን ማክበር ለድርድር የማይቀርብ ሆኖ ከፕሬስ ነፃነት ጎን ለጎን የሚዲያ ሥነ ምግባርን ማስፈጸም ግዴታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከሐሰተኛ መረጃ፣ ከጥላቻ ዘገባ፣ ካልተረጋጋጠ መረጃ፣ እንዲሁም ከሙስና ነፃ ሆኖ ሥራ መሥራት የሚያስችል የሚዲያ ተግባርና የሰው ኃይል የተሰባሰበበት ትርታ የሬዲዮ ጣቢያ፣ ኃላፊነቱን በተግባር መወጣት ብቻም ሳይሆን በተግባር እንደሚያሳይ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

የሙያ ግዴታቸውን በሚገባ የሚወጡ ሚዲያዎች ቢኖሩም ከተገቢው የሚዲያ ሚና ውጪ መስመር የሳቱ መበራከታቸውን ያስታወሱት አቶ አማረ፣ ከጥላቻ ንግግር መበራከት ባሻገር ሙስናና ሐሰተኛ መረጃዎችም የአገር ሰላምና አንድነት እየረበሹ ስለሆኑ፣ ትርታን ጨምሮ ሌሎች ሚዲያዎች ልዩና የላቀ ሚና የሚጫወቱ አገራዊና ሕዝባዊ ግዴታዎችን የሚወጡ ተቋማት ሊሆኑ እንደሚገባ አበክረው አሳስበዋል፡፡

ትርታ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ግንቦት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ተቋቁሞ ሐምሌ 2 ቀን 2012 ዓ.ም የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ያወጣውን ጨረታ በማሸነፍ በ97.6 ኤፍኤም የሬዲዮ ሥርጭት ለማድረግ ፈቃድ አግኝቶ፣ ሃምሳ ሚሊዮን ብር መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ በማድረግ በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. የመጀመሪያ የሙከራ ሥርጭት ማድረጉን የሬዲዮ ጣቢያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘካርያስ ስንታየሁ አስታውቀዋል፡፡

የሃይብሪድ ዲዛይንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሳምራዊት ፍቅሩን ጨምሮ በኅትመትና በሬዲዮ ዘርፍ ለረዥም ዓመታት ባገለገሉ ባለሙያዎች የተቋቋመው ትርታ ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ፣ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች የጋዜጠኝነትን የሙያ ሥነ ምግባርና መርሆች በመጠበቅ ለአገርም ሆነ ለሕዝቡ ጥቅም በርትቶ የሚሠራ መሆኑ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...