Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየላሊበላ ታሪካዊ ሙዚየም ግንባታ በሲሚንቶ እጥረት መቋረጡ ተነገረ

የላሊበላ ታሪካዊ ሙዚየም ግንባታ በሲሚንቶ እጥረት መቋረጡ ተነገረ

ቀን:

በኢዮብ ትኩዬ

የላሊበላ ታሪካዊ ሙዚየም ግንባታ በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት ለወራት መቋረጡን፣ በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን የላሊበላ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የታሪካዊ ሙዚየሙ ግንባታ በሲሚንቶ እጥረት ሳቢያ ከወራት በላይ መቋረጡን የላሊበላ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊና ምክትል ከንቲባ ዲያቆን አድሴ ደምሴ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሕወሓት ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰሜኑ በኩል ለሦስተኛ ጊዜ ቀስቅሶት በነበረው ጦርነት ግንባታው ቆሞ የነበረ መሆኑንና ጦርነቱ ሲቆም ደግሞ የሲሚንቶ እጥረት ስላጋጠመው ግንባታው እንዳይቀጥል መሰናክል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የሲሚንቶ እጥረቱን በማስመልከት የከተማ አስተዳደሩ ከክልሉ እስከ ፌዴራል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ድጋፍ ባለመገኘቱ እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ) ግንባታውን ማስቀጠል አለመቻሉን ነው ምክትል ከንቲባው የገለጹት፡፡

የሙዚየሙን ግንባታ ለማጠናቀቅ 250 ሚሊዮን ብር ገደማ ድረስ ወጪ እንደሚጠይቅ፣ ከክልሉና ከፌዴራል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በተገኘ 30 ሚሊዮን ብር መነሻ በጀት በ2014 ዓ.ም. ግንባታው እንደተጀመረ የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በወቅቱ ገልጾ ነበር፡፡

ሆኖም የግንባታ ሥራው በተጀመረበት ወቅት የነበረው የሲሚንቶ ዋጋ አሁን ከሚሸጥበት ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት ስላለው፣ ፕሮጀክቱ ይጠናቀቃል በተባለለት በጀት ማስፈጸም መሠረታዊ ችግር ሳይሆን እንደማይቀር ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል፡፡ ግንባታው በተጀመረበት ወቅት እስከ 300 ብር ሲገዛ የነበረው አንድ ከረጢት ሲሚንቶ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 2,200 ብር ከፍ በማለቱንና ከአራት እጥፍ በላይ የዋጋ ልዩነት ስላሳየ ተጨማሪ በጀት እንደሚጠይቅ አክለዋል፡፡

የተጀመረውን ፕሮጀክት ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ የፌዴራል ቅርስና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች ዕርዳታ ማድረግ እንዳለባቸው ግንባታው ሲጀመር ጥሪ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ድጋፍ አለመገኘቱ ሌላው ለግንባታው መቋረጥ ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠገን በፈረንሣይ መንግሥት የተደረገው ጥናት ቢጠናቀቅም፣ ኢትዮጵያ የነበረችበት ወቅታዊ ሁኔታ ሥራ ለመጀመር ምቹ ባለመሆኑ ሲጓተት ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ጥገናው በከፊል መጀመሩን ከቢሮው በተገኘ ምላሽ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የፈረንሣይ መንግሥት ለላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት ጥገና የገባውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ፣ አስፈላጊ ግብዓቶችን ወደ አገር ውስጥ እያስገባ መሆኑ በመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. መግለጹ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም በኅዳር 2015 ዓ.ም. ለጥገናው የሚሆን አምስት ሚሊዮን ዮሮ ለላሊበላ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ቢሮ ማስረከቡንና አንዳንድ ጥገናዎችን መጀመሩን ምክትል ከንቲባው አያይዘው ገልጸዋል፡፡

በፈረንሣይና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በነበረው ውይይት ዕድሳቱን ለመጀመር የአብያተ ክርስቲያኑ መጠለያ እንዲነሳ ጥያቄ ቢቀርብም፣ ዕድሳቱ የሚጀመረው ግን ዩኔስኮ በዓመት አንድ ጊዜ በሚያደርገው ስብሰባ በመጪው ሰኔ ወር ለውይይት ቀርቦ ካፀደቀው በኋላ መሆኑ ታውቋል፡፡ አስቸኳይ ጥገና ይሻሉ ተብለው በጥናት የተለዩ ፕሮጀክቶች ግን ግንባታቸው መጀመሩ ተገልጿል፡፡

ሕወሓት ከፍቶት በነበረው ጦርነት ከአሥራ አንዱ ውቅር አብያተ ክርስትያናት መካከል፣ በተለይም ለከባድ መሣሪያ ማስቀመጫነት የተጠቅመባቸው የነበሩ ቤተ መድኃኔዓለምና ቤተ ማርያም የመሰነጣጠቅ አደጋ ስለተጋረጠባቸው ጥገና እንደሚሹ፣ እንዲሁም በተጓዳኝ የላሊበላ ታሪካዊ ሙዚየምን ለመገንባት ማቀዱን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...