Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሕፃናትን አፍነው መውሰዳቸውን የጋምቤላ ክልል አስታወቀ ባለፉት ሰባት ዓመታት...

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሕፃናትን አፍነው መውሰዳቸውን የጋምቤላ ክልል አስታወቀ ባለፉት ሰባት ዓመታት 426 ሕፃናትና 4,761 ከብቶች ተወስደዋል

ቀን:

በኢዮብ ትኩዬ

ከደቡብ ሱዳን በመነሳት ድንበር ጥሰው ወደ ጋምቤላ ክልል ገቡ የተባሉ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሦስት ሕፃናት አፍነው መውሰዳቸውን የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ፡፡

ታጣቂዎቹ ባለፈው ሳምንት የጋምቤላና የደቡብ ሱዳን ድንበር ጥሰው በመግባት ሦስት ሕፃናት አፍነው መውሰዳቸውን፣ የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

‹‹ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊትም በሕገወጥ መንገድ ድንበር ጥሰው በመግባት የሰው ሕይወት አጥፍተዋል፣ ሕፃናትን አፍነው ወስደዋል፣ ከብቶችን ዘርፈዋል፤›› ያሉት አቶ ኡገቱ፣ አሁንም ቢሆን ድርጊቱ እንዳልቆመ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በክልሉ በሚገኙ አኮቦ፣ ዋንቲዋና መኮይ በተሰኙ ሦስት ወረዳዎች ሕፃናቱን አፍኖ ለመውሰድ፣ ንብረት ለመዝረፍና በሰዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የሙርሌ ታጣቂዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደተስፋፋ ተጠቁሟል፡፡ ታጣቂዎቹ ባለፈው ሳምንት ሦስት ሕፃናትን አፍነው የወሰዱትም ከላይ በተጠቀሱት፣ በተለይም በሦስቱ ወረዳዎች በነበራቸው መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ መሆኑን አቶ ኡገቱ ገልጸዋል፡፡

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎቹ ከላይ ከተጠቀሱት ወረዳዎች በተጨማሪ፣ በጋምቤላ ክልል አኙዋ ዞን ዲማ ወረዳ ሕፃናትን አፍኖ ለመውሰድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዳልቆመ ነው ማወቅ የተቻለው፡፡

‹‹በተለይም በክልሉ በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች ድርጊቱ ተባብሷል፤›› ያሉት አቶ ኡገቱ፣ ‹‹በታጣቂዎቹ የተወሰዱት ሕፃናት ይመለሳሉ የሚል ተስፋ የለንም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ ካልሞተ ይገኛል ብሎ ማሰብ ቢቻልም፣ እስካሁን በተደረገው ሕፃናትን የማስመለስ ሙከራ አንፃር፣ አሁንም ቢሆን ሰሞኑን የተወሰዱት ሕፃናት ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በሚደረግ ውይይት ይመለሳሉ የሚል ተስፋ የለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ታፍነው የተወሰዱት ሕፃናትና የተዘረፉ ንብረቶች ይመለሳል የሚል ተስፋቸው የተሟጠጠው፣ ከዚህ ቀደም የጋምቤላ ክልል መንግሥት ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት ቢያደርግም፣ ውይይቱ ውጤታማ ባለመሆኑ በተጨባጭ የተመለሰ ሕፃንም ሆነ ንብረት ስለሌለ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

እስካሁን የተወሰዱት ሕፃናትና ተዘርፈው የተወሰዱ ከብቶች ይመለሳሉ ከሚል ተስፋ ባሻገር፣ የክልሉ መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ያስችላሉ ብሎ ያመነባቸው ሁለት ዓበይት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እየሠራ እንደሚገኝና በአንዱ ተግባር ውጤታማ እየሆነ መሆኑ ተገልጿል፡፡

እንደ አቶ ኡገቱ ገለጻ ከሆነ፣ ከሁለቱ ጉዳዮች መካከል አንደኛውና የመጀመሪያው የክልሉን ፖሊሶችና ሚሊሻዎች ብቁ አድርጎ በማሠልጠን፣ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጥቃት በሚያደርሱበትና ድንበር ጥሰው በሚገቡበት አካባቢ አሰማርቶ፣ ከዚህ በኋላ ጥቃቱ እንዳይደገም የመከላከል ተግባር ላይ ማተኮር ነው፡፡

ክልሉ አሠልጥኖ ባሰማራቸው ፖሊሶችና ሚሊሻዎች አማካይነት ድንበር ጥሰው የሚገቡ ታጣቂዎችን በተደጋጋሚ ሙከራቸውን ለማክሸፍ እንደተቻለ፣ ለአብነትም ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊት በዲማ ወረዳ ከሦስት ጊዜ በላይ በተከታታይ ባደረጉት ሰው የመግደል፣ ሕፃናትን አፍኖ የመውሰድ፣ እንዲሁም ንብረት የመዝረፍ ሙከራ ከሽፎ ሙሉ ለሙሉ እንደተደመሰሱ ነው አቶ ኡገቱ ያስታወሱት፡፡

ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላል ሲል የጋምቤላ ክልል መንግሥት እየተገበረው ያለው ሁለተኛ ተግባር ነው ተብሏል፡፡

እንደ ገለጻው ከሆነ፣ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ከዚህ በፊት ታፍነው የተወሰዱ ሕፃናት እንዲመለሱ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ ‹‹ይሁንና በመጨረሻ የተገኘ ውጤት የለም፡፡ ይባስ ብሎም ችግሮችና ጥያቄዎች እየጨመሩ ስለመጡ ሕፃናቱ ይመለሳሉ የሚል ተስፋ መሰነቅ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

ትልቁ ተስፋ የክልሉን ፖሊስና ሚሊሻ እያሠለጠኑ ታጣቂዎቹን መከላከል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሕፃናቱን የሚወስዱት በደቡብ ሱዳን ለሚገኙ ባለሀብቶች ለሽያጭ ለማቅረብ ስለመሆኑ የጋምቤላ ክልል ከዚህ በፊት ሲገልጽ ነበር፡፡

በክልሉ አኙዋና ኑዌር ብሔረሰቦች አስተዳደር ዞኖች በሚገኙ ወረዳዎች ከ2008 እስከ 2014 ዓ.ም. የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳዎች 767 ሰዎችን እንደገደሉ፣ 289 ሰዎችን እንዳቆሰሉ፣ 423 ሕፃናትን እንደወሰዱ ከጋምቤላ ክልል የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ ሰሞኑን የተወሰዱት ሦስት ሕፃናትን ጨምሮ በአጠቃላይ 426 ሕፃናት ተወስደዋል፡፡ እንዲሁም ታጣቂዎቹ ከ2008 ዓ.ም. እስከ 2014 ዓ.ም. ባደረሱት ጥቃት ከ22 ሺሕ በላይ ዜጎች ከመኖሪያቸው እንደተፈናቀሉ፣ 4,761 ከብቶች እንደተወሰዱና ከ100 በላይ ቤቶች እንደተቃጠሉ መረጃው ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...