Wednesday, February 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በሥርዓት መምራትና መመራት አለመቻል መዘዙ የከፋ ነው!

ኢትዮጵያዊው የ20ኛው ክፍለ ዘመን የኢኮኖሚና የሕዝብ አስተዳደር ሊቅ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ ‹‹በሥርዓት ከማይተዳደር አገር ይልቅ በሥርዓት የምትመራ አንዲት ትንሽ ከተማ ሙያ አላት›› በሚለው ንግግራቸው ይታወቃሉ፡፡ ነጋድራስ ከዚህ ዓለም ከተለዩ ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ የተፈራረቁ መንግሥታት፣ ከዚህ ዘመን ተሻጋሪ ቁምነገር አዘል መልዕክት ለመገንዘብ ባለመፈለጋቸው በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል፣ ዛሬም እየደረሱ ነው፡፡ አገርን የመምራት ኃላፊነት የተቆናጠጡም ሆኑ በተለያዩ መስኮች የሠለጠኑ ምሁራንና የፖለቲካ ልሂቃን፣ ለነጋድራስ ዘመን አይሽሬ ማሳሰቢያ ባዕድ በመሆናቸው ምክንያት አንዳቸው ከሌላቸው ጥፋት ለመታረም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ኢትዮጵያ የመከራ ቋት ሆናለች፡፡ አገር በሥርዓት ስትመራ ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም በላይ ብሔራዊ ጥቅም ስለሚቀድም፣ የመገፋትና የመከፋት አባዜ ተወግዶ በሰላም መኖርና ማደግ የኢትዮጵያውያን መታወቂያ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን በሥርዓት አብሮ ከመኖር ይልቅ፣ ሥርዓተ አልበኝነትን የሚያስፋፉ ድርጊቶች እየበዙ ኢትዮጵያ የደም ምድር ለመሆን ተገዳለች፡፡

መሰንበቻውን የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ እንደገና አገርሽቶበት በትምህርት ቤቶች አካባቢ የተስተዋለው ችግር፣ አገርንና ሕዝብን ማዕከል ማድረግ ተስኖት ሁሉም በፈለገው መንገድ ያሻውን ሲል ሰንብቶበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ልማድ መሠረት አንዳች ችግር ሲያጋጥም መፍትሔውን ከመፈለግ ይልቅ፣ ከብሔራዊ ጥቅም በተፃራሪ የፖለቲካ ሒሳብ ማወራረጃ ማድረግ እንደ ጀብዱ ይታያል፡፡ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን፣ የአፍሪካውያን መናኸሪያ መሆኗ ጭምር እየተዘነጋ የፖለቲካ ቁማሩ ይደራል፡፡ አዲስ አበባ ከኒዮርክና ከብራሰልስ ቀጥላ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗ ጭምር እንደ ዋዛ እየታለፈ፣ የፖለቲካው ግርግር አየሩን እየተቆጣጠረው የግለሰቦችና የቡድኖች ሽኩቻ ይጧጧፋል፡፡ ይህ ከሴረኝነት ጋር የተሸራረበ አርቆ ማሰብ የተሳነው ነውጠኝነት፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ሆነ በዙሪያዋ ላሉ አካባቢዎች የሚያተርፈው መከራና ሥቃይ እንደሆነ አሁንም መማር አልተቻለም፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የሃይማኖት ፀብ በመቀስቀስ አብሮ በሰላምና በፍቅር ሲኖር የነበረውን ሕዝብ ለማፋጀት የተነሱ አሉ፡፡ የትርምስ አጀንዳ እየቀያየሩ አገርን ማመስ ትልቅ ሙያ እየሆነ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማም ሆነ የሌሎች ችግሮቻችን መፍቻ መሆን ያለበት ሥርዓት ባለው ምክክር መሠረት የሚገኝ መፍትሔ መሆን ሲገባው፣ አሁን በስፋት እንደሚታየው የተማረውን ካልተማረው መለየት እስኪያስቸግር ድረስ ማዶ ለማዶ ሆኖ መሰዳደብና መወጋገዝ ነው፡፡ አብዛኞቹ የፖለቲካ ልሂቃን ሙሉ ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ለአገር የሚበጁ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን፣ ተቃራኒያቸውን እንዴት በሾኬ ጥለው ሥልጣን ላይ መንጠላል እንደሚቻል ሲያውጠነጥኑ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ካሉትም አብዛኞቹ የሥልጣናቸውን ወንበር እንዴት ቢያጠባብቁት ላዩ ላይ ተጣብቀው እንደሚሰነብቱ እንጂ፣ በሕግና በሥርዓት እየተመሩ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ እንዳልሆነ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ሥልጣን ለማግኘት ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የሚካሄድበት ሥርዓት ስለመገንባት ሳይሆን፣ ሥልጣን በግርግር ለመያዝ የሚያስችሉ ደባዎችንና ተንኮሎችን ማቀናበር የዘመኑ ልማድ ከሆነ ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ላይ ያተኮሩ ውይይቶችና ምክክሮች አይፈለጉም፡፡ በየዕለቱ የችግር አጀንዳ እየመዘዙ አንዴ በብሔር፣ ሌላ ጊዜ በሃይማኖት ውዝግብ ሕዝብ ማደንዘዝ ነው የበረታው፡፡ በዚህም ምክንያት በሥርዓት መኖር ብርቅ እየሆነ፣ ግጭትና ውድመት የየዕለት መታወቂያ ሆነዋል፡፡

ሌላው በሲሚንቶ ገበያ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ሥርዓተ አልበኝነት ነው፡፡ የሲሚንቶ ግብይት ውስጥ መንግሥት ሰተት ብሎ ገብቶ ትርምስ ከፈጠረና ዋጋውን እንደ ሮኬት ካስተኮሰ፣ ጥቂቶች በአቋራጭ የሚከብሩበት ዕድል አመቻችቶ ብዙ ነገሮች ከተበላሹና በሲሚንቶ ንግድ ውስጥ የተሰማሩ በርካቶች ሥራ አጥ እንዲሆኑ ከተደረገ በኋላ ሰሞኑን ጣልቃ መግባቱን እንዳቆመ አስታውቋል፡፡ የነፃ ገበያ ሥርዓት እከተላለሁ የሚል መንግሥት ገበያውን አተራምሶ ምስቅልቅሎችን ካደረሰ በኋላ፣ ድንገት ጣልቃ መግባቱን እንዳቆመ ሲያስታውቅ ማነው የሚጠየቀው? በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት የመንግሥት አሠራር ተጠያቂነት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ መንግሥት ሥራውን በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ ማከናወን እንዳለበትም እንዲሁ፡፡ መንግሥት የሲሚንቶ ግብይት ውስጥ ጣልቃ ሲገባ ብዙዎች በሕግ አምላክ ቢሉ የሚያዳምጥ አልነበረም፡፡ የሲሚንቶ አምራቾችም አቤት ሲሉ አዳማጭ አልነበራቸውም፡፡ በዚህ መሀል ግን ጊዜ የሰጣቸውና ተባባሪ ደላሎች ገበያውን ተቆጣጥረው ኩንታሉ በ500 ብር መሸጥ የነበረበት ሲሚንቶ፣ ከሁለት ሺሕ ብር በላይ በኮንትሮባንድ ተቸበቸበ፡፡ ሥርዓት ሲጠፋ አገር እንደሚጠፋ የሲሚንቶ ገበያ አንዱ ማሳያ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለች አገር ሆና ከ120 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝቧ ለምን ምግብ ይቸግረዋል? ለምን ንፁህና ፅዱ መኖሪያ አይኖረውም? ለምን በቂ መታከሚያ አያገኝም? ለምን ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት አያገኝም? ለምን በቂ ኤሌክትሪክና ንፁህ ውኃ አይቀርብለትም? ለምን ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች አንሶ በድህነት እየማቀቀ ምፅዋት ይለመንለታል? የሚሉና የመሳሰሉ በርካታ የብሶት ጥያቄዎች ሲነሱ፣ ብዙዎቹ የመንግሥትም ሆኑ የፖለቲካ ልሂቃን መልስ የላቸውም፡፡ ከአጠቃላይ ሕዝባችን ከ70 በመቶ በላይ እንደሆነ ከሚነገርለት ወጣት ኃይል ውስጥ፣ እጅግ በጣም ብዙው ሥራ አጥ ሆኖ የቤተሰብ ተጧሪ ሊሆን ለምን ተገደደ ሲባል ምንም ምላሽ የለም፡፡ ይህንን ግራ የተጋባ ወጣት ግን በብሔር እያደራጁ ለማፋጀት ግን ማንም አይሰንፍም፡፡ ለአገር ዕድገትና አንድነት የሚበጁ ሥራዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ አገር አፍራሽ መፈክሮች አሸክሞ ንፁኃንን ማስፈጀትና መንደሮችን ማስጋየት የሚያኮራ ተግባራቸው ነው፡፡ ብሔራዊ ጥቅምን ወደ ጎን በማለት ሥርዓተ አልበኝነት ማስፈን ነው የተለመደው፡፡

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጓት ብሔራዊ ደኅንነቷንና ጥቅሞቿን የሚያስከብሩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ናቸው፡፡ በዕውቀትና በጥናት ላይ በመመሥረት የሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የሚጠቅሙት፣ ከሥርዓተ አልበኝነት በመላቀቅ በሕግና በሥርዓት ለመመራት ነው፡፡ የዘፈቀደ ውሳኔና ዕርምጃ መውሰድ ልማድ በሆነባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በትምህርትና በልምድ የካበተ ዕውቀት ካላቸው ሰዎች ይልቅ ጥራዝ ነጠቆች የበላይነቱን ስለሚይዙ በሥርዓት መነጋገርም ሆነ መከራከር አልተቻለም፡፡ አንድ ችግር ሲያጋጥም በሕጋዊ መንገድ መላ ከማፈላለግ ይልቅ ጉልበት የሚመረጠው፣ ሃይ ባይና ገሳጭ አዋቂዎች ወደ ጎን በመገፋታቸው ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ሥርዓት ባለው መንገድ ተነጋግሮ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ አማካይ መፍጠር ሲገባ፣ ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ እርስ በርሱ ለማዋጋት እሳት የሚያቀጣጥሉ ትርክቶች ነው የሚሰሙት፡፡ ይህ ትርምስ ውሉ ሳይታወቅ ካልታሰበ አቅጣጫ የሃይማኖት ጦርነት የሚያስነሳ ሌላ አጀንዳ ይፈበረካል፡፡ አገርን ጤና መንሳት ሌላ መዘዝ እንዳለው የማይገነዘቡ ወይም ሆን ብለው ትርምስ የሚፈለጉ እየበዙ ነው፡፡ መታወቅ ያለበት ግን በሥርዓት መምራትና መመራት አለመቻል መዘዙ የከፋ እንደሆነ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...

የጋራ ድላችን!

ከፒያሳ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ለበርካታ ደቂቃዎች ሠልፍ ይዘን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...