Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲስ የማዕድን ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀርብ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የማዕድን ኩባንያዎች ሁለት በመቶ ትርፍ ማዕድን ያመረቱበት ክልል ነፃ ድርሻ ይሆናል
  • ማዕድን ሳያለሙ ፈቃድ ይዘው በሚቀመጡ ኩባንያዎች ላይ ግዴታዎችን ይጥላል

በሥራ ላይ የሚገኘውን የማዕድን ሥራዎች አዋጅ የሚተካ ረቂቅ የሕግ ሰነድ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ።

ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው የሕግ ሰነድ፣ ‹‹የማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ አዋጅ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን፣ የማዕድን ዘርፉ ላለፉት 12 ዓመታት ሲመራበት የቆየውን የማዕድን ሥራ አዋጅ ቁጥር 678/2002 በአዲስ የሚተካና በተለያዩ ሕጎች ተበታትነው የሚገኙ ዘርፉን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን በአንድ አሰባስቦ የያዘ መሆኑም ታውቋል።

የማዕድን ፈቃድ ወስደው ሳያለሙ ለረዥም ዓመታት የማዕድን ሀብቱን ይዘው ለሚቀመጡ ኩባንያዎች መፍትሔ ያመጣል ተብሏል።

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የማዕድን ፍለጋ፣ ምርት፣ እንዲሁም ፕሮሰሲንግ ፈቃድ ወስደው ለረዥም ዓመታት በአንድ ባለፈቃድ ሳይለሙ ተይዘው ቢቆዩ አስገዳጅ ሁኔታዎችን የማያስከትል በመሆኑ፣ ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደው ሳያለሙ ለረዥም ዓመታት መቆየትን በሕግ እንደተፈቀደ በመቁጠር የአገር ሀብት ሳይለማ እንዲቀመጥ ምክንያት መሆኑን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለማዕድን ልማት ዘርፍ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ሰፊ ውጥኖችን እንደያዘ የሚገልጹት ምንጮች፣ መንግሥትና ሕዝብ ከአገሪቱ የማዕድን ሀብት የሚጠብቀውን ጥቅም እንዲያገኙና ሀብቱን በተደራጀና አገራዊ ተልዕኮን ሊያሳካ በሚያስችል መንገድ ለማልማት እንዲቻል የማዕድን ልማት ፈቃድ የሚወስዱ ሁሉም ተዋንያን፣ በተሰጣቸው ጊዜና ኃላፊነት ብቻ እንዲተገብሩ የሚያስችሉ አስገዳጅ ድንጋጌዎች በረቂቁ እንዲካተቱ መደረጉን ገልጸዋል።

በመሆኑም ፈቃዱ ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜና የፈቃድ ዕድሳት፣ የባለፈቃድ መብትና ግዴታዎች፣ ፈቃድ የሚሻሻልባቸው ሁኔታዎችና የማዕድን መብቶችን ማገድና መሰረዝን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በረቂቁ መካተታቸውን ገልጸዋል።

ከማዕድን ሥራዎች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አስመልክቶ በዘርፉ ለሚሰማሩ፣ ወይም ለተሰማሩ ባለሀብቶች የምክር አገልግሎት ለሚሰጡ እንደ ላቦራቶሪና ድሪሊንግ በመሳሰሉ የቴክኒክ ሥራዎች በመሰማራት የማዕድን ሥራዎችን ማገዝ ለሚፈልጉ አካላት የሚሰጡ ፈቃዶችን የሚመለከቱ ጉዳዮችም በረቂቁ ተካተዋል።

አንድ የማዕድን ሥራ ባለፈቃድን መንግሥት ፈቃዱን ያገኘበትን መሬት ለሌላ የሕዝብ ጥቅም ለማዋል ቢፈልግ እንዴት ማስለቀቅ እንዳለበት የሚደነግግ ሕግ ባለመኖሩና ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ የተመለከቱ ድንጋጌዎችም በረቂቁ መካተታቸውን ምንጮች ገልጸዋል።

የማዕድን ኩባንያዎች ለመንግሥት መክፈል ከሚጠበቅባቸው የሮያሊቲ ክፍያ በተጨማሪ፣ ከዓመታዊ ትርፋቸው ሁለት በመቶው ፈቃድ የወሰዱበትና ማዕድን የሚያመርቱበት ክልል ነፃ ድርሻ መሆኑን የሚያመላክት ድንጋጌ በረቂቁ መካተቱንም ለማወቅ ተችሏል።

በአጠቃላይ ረቂቅ አዋጁ የማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚ ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር ያለውን አስተዋፅኦ ከግምት በማስገባት አገራዊ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የገቢ ማዕድናት ምርት በአገር ደረጃ እንዲመረት፣ የወጪ ንግድ ማዕድናትን ደግሞ በጥራት፣ በብዛትና በዓይነት እንዲመረቱ፣ እንዲሁም ለዜጎች አማራጭ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ማድረግንና በጥቅሉ የአገሪቱ ዓብይ ኢኮኖሚ ማረጋጊያ እንዲሆን የሚያስችሉ ማሻሻያዎችና አዳዲስ ድንጋጌዎች ተካተውበት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ምንጮች አስረድተዋል። 

የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ በቅርቡ እንደሚወያይና ሕግ ሆኖ እንዲወጣም፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚመራው ይጠበቃል።

በሌላ በኩል አዲስ እየተዘጋጀ ባለው ሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም መሠረት የማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚውን የተመለከተ ጥቅል ፖሊስ (Guiding principle and blue print) የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ይህንን መሠረት በማድረግም የክፍለ ኢኮኖሚው ንዑስ ዘርፎችን የሚመለከቱ የፖሊሲ ማዕቀፍ የማዘጋጀት ሥራ በሒደት ላይ መሆኑንም ምንጮቹ አመልክተዋል። የዝግጅት ሥራው ሲጠናቀቅም የመሠረታዊ ብረታ ብረት ንዑስ ፖሊሲ፣ የመሠረታዊ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ማዕድናት ንዑስ ፖሊሲ፣ የመሠረታዊ ኬሚካሎች ማዕድናት ንዑስ ፖሊሲ፣ የሲሚንቶ ንዑስ ፖሊሲ፣ የድንጋይ ከሰል ንዑስ ፖሊሲ፣ መሠረታዊ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ንዑስ ፖሊሲ፣ የዕምነበረድ፣ ግራናይትና ሴራሚክስ ንዑስ ፖሊሲ፣ የጂኦተርማል ንዑስ ፖሊሲና የተፈጥሮ ጋዝ ንዑስ ፖሊሲ እንደሚወጣ ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች