Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አንበሳ ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ቢቀንስም 310 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የተበላሸ የብድር ምጣኔው 16.23 በመቶ ደርሷል

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ምክንያት ግማሽ የሚሆኑ ቅርንጫፎቹ ተዘግተውበት የቆየው አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔው ቢቀንስም 310.6 ሚሊዮን ብር አተረፈ፡፡

የባንኩ የ2014 የሒሳብ ዓመት ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ከታክስ በኋላ ያስመዘገበው ትርፍ ደግሞ 268.81 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ባንኩ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት 104 ሚሊዮን ብር መቀነሱ ታውቋል፡፡

ለባንኩ ትርፍ መቀነስ ዋነኛ ምክንያት በሰሜኑ ጦርነት አብዛኛዎቹ ቅርጫፎች በመዘጋታቸውና በእነዚህ ቅርጫፎች የሰጠውን ብድር ማስመለስ ካለመቻሉ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ባንኩ የሰሜኑ ጦርነት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የትርፍ ምጣኔውን  እየቀነሰ እንዲመጣ ያደረገው ሲሆን፣ ከጦርነቱ በፊት በ2011 ዓ.ም. ከታክስ በፊት 680 ሚሊዮን ብር አትርፎ የነበረ ሲሆን፣ ይህንን የትርፍ ምጣኔውን በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ወደ 780.6 ሚሊዮን ብር ማሳደግ ችሎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ባንኩ በዚህ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ 310.6 ሚሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉ እንደ ትልቅ ስኬት የሚታይ ስለመሆኑ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት ሳይጠቁም አላለፈም፡፡

ባንኩ የ2013 የሒሳብ ዓመት ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት፣ የባንኩ ዓመታዊ ትርፍ ከ2012 የሒሳብ ዓመት ትርፍ አንፃር ሲታይ፣ በ366 ሚሊዮን ብር መቀነሱንና በርካታ ብድሮች ጤናማ ያልሆነ ምድብ ውስጥ እንደገቡበት ገልጾ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ሰሞኑን ይፋ በተደረገው የባንኩ ዳይሬክተሮች ሪፖርት ጦርነቱ የደረሰበት ጫና ወደ 4.1 ቢሊዮን ብር የሚሆን ብድር ውስጥ እንዲገባበት አድርጓል፡፡ ይህም በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የተበላሸ የብድር ምጣኔው 16.23 በመቶ ሊደርስ መቻሉን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡  

ጦርነቱ በርከት ባሉ ቅርንጫፎቹ ላይ የተፈጸመው ዘረፋና የንብረት ውድመት በተጨማሪ፣ በአካባቢው የነበሩ ሁሉም ቅርንጫፎች ከሥራ ውጪ መሆናቸውን፣ አጠቃላይ እንቅስቃሴውን ያዳከመው ሲሆን፣ በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረገው ስምምነት እነዚህን የተዘጉ ቅርንጫፎችን ሥራ ለማስጀመር ተስፋ የፈነጠቀ በመሆኑ፣ ባንኩ በጦርነቱ የደረሰበትን ጉዳት ሊያካክስ የሚችልበት ዕድል እንደሚኖር ተጠቁሟል፡፡ የተዘጉ ቅርጫፎቹን ለመክፈት ተጠሪነቱ ለባንኩ ፕሬዚዳንት የሆነና ሁሉንም ምክትል ፕሬዚዳንቶች ያካተተ ዓብይ ኮሚቴ በማቋቋም ቅድመ ዝግጅቶች እያደረገ ነው፡፡ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የሽሬ ቅርንጫፉ ሥራ ጀምሯል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የተዘጉ ቅርንጫፎች ከመክፈቱ በፊትም በጦርነቱ ወቅት የገጠማቸውን ጉዳት የደንበኞችን ሒሳብ የማመሳከርና አጠቃላይ የኦዲት ሥራዎችን እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡

በሌሎች የባንኩ የሥራ አፈጻጸሞች ዙሪያ በዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርቱ ላይ እንዳሰፈረው፣ የባንኩ ተቀማጭ የገንዘብ መጠን 25.93 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ግን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ቅናሽ ያለው ሆኗል፡፡ አንበሳ ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የነበረው ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 25.99 ቢሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የብድር ምጣኔው ግን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ መጨመሩን የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ በ2013 መጨረሻ ላይ 21.82 ቢሊዮን ብር ነበረው አጠቃላይ የብድር ክምችት በ2014 መጨረሻ ላይ 23.79 ቢሊዮን ብር መድረስ ችሏል፡፡ በባንኩ በዓመቱ አራት ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ መሆኑን ገልጿል፡፡ የባንኩ ሀብት መጠንም 33 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት በሁለት በመቶ ማደጉን ያመለክታል፡፡  

አንበሳ ባንክ በ3,793 ባለአክሲዮኖች በ432.5 ሚሊዮን ብር የተፈረመና በ108.2 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የባለአክሲዮኖቹን ቁጥር ከ12 ሺሕ በላይ አድርሷል፡፡ ባንኩ የቅርንጫፎቹ ቁጥር 278 ሲሆን 4,189 ሠራተኞች አሉት፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉበዔ፣ የባንኩን ካፒታል ወደ አሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የቀረበውን ሐሳብ ባለአክሲዮኖች አፅድቀውታል፡፡ በዚህ ውሳኔ መሠረት ተጨማሪውን ካፒታል በሰባት ዓመት ውስጥ አጠናቆ ለመክፈል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ባንኩ አሁን ያለው የተከፈለ ካፒታል 2.6 ቢሊዮን ብር ነው፡፡      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች