Monday, February 26, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት የቋንቋዎች ዕድገት አሳስቦታል? ወይስ ፖለቲካው ተጭኖታል?

በያሬድ ነጋሽ

አንድ አዛውንት በበቅሎ ሆነው ሲጓዙ በደረቱ የተኛ እረኛ ዘንድ ይደርሳሉ። እረኛው ከተኛበት ሆኖ አንጋጦ ይመለከታቸው ጀመር። ‹የማን ልጅ ነህ?› አዛውንቱ ጠየቁ። መለሰ እረኛው። ‹የወዳጄ ልጅ ነሃ! ለአባትህ እንደምትለው ስልቻውን አልፋው ብሎሃል ጓደኛህ በልልኝ› አሉ አዛውንቱ። ነገር ግን ስለአባቱ ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበራቸውም።

እረኛው እቤት እንደደረሰ በተባለው መሠረት ለአባቱ መልዕክቱን አደረሰ። ‹እሳቸው ሲመጡ አንተ የት ነበርክ› ብለው አባት ጠየቁ። ‹ተኝቼ ነበር› መለሰ እረኛው፡፡ አዛውንቱ ኖር ብሎ ተነስቶ ሰላም አላለኝም፣ ልጅህን ቅጣ፣ እየተጣመመ ነው የሚል መልዕክት እንደደረሳቸው የገባቸው አባት ጉማሬውን በጀርባው ያጮሁ ጀመር።

ቋንቋ ሲጠፋ እንደቀላል የሚመለከቱ በርካቶችን ታዝበናል። የማይተዋወቁ ሰዎች፣ ለምሳሌ አዛውንቱ ለእረኛው የራሱን የግረፈው ትዕዛዝ መልዕክት በስውር አሲዘው እንደላኩትና አባትም ትርጉም ሰጥተው ትዕዛዙን እንደተገበሩት ሁሉ፣ የትላንት ሰው ጥበቡን በቋንቋው ሰውሮ ለቀጣይ ትውልድ ያሸጋግርበታልና ቋንቋ ሲጠፋ የማኅበረሰቡ ጥበብ ለትውልድ ሳይተርፍ አብሮ እንደሚጠፋ ልንገነዘብ ይገባል።

መንግሥትም በአንድ አገር ውስጥ ያለ የማኅበረሰብ ቋንቋ ዕድገትና ሥርጭት ሲያሳስበው መመልከታችን የነገሩን ፋይዳ በጉልህ እንደተረዳ ያስገነዝበናል። በዚህ መሠረት በአገራችን በተለይ ኦሮምኛ ቋንቋን በአዲስ አበባ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ለማካተት እየተሞከረ ያለበትን ሒደት በበጎ ጎኑ የምንመለከተው ነው። ኦሮምኛ ቋንቋን በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ማካተትም ይሁን በተለያየ መልኩ በመላው አገሪቱ እንዲስፋፋ ማድረጉ ሁለት ጉልህ ጠቀሜታዎችን ያበረክትልናል። አንደኛው፣ ኦሮምኛ ቋንቋ በመላው አገሪቱ ተዘውታሪ ቢሆን በአገራችን የፖለቲካ ውጥረት ሰፍኖ በምናይባቸው በተለይም በአማራና በኦሮሞ ማኅበረሰብ መካከል የተገነባውን የሐሰት የጥል ግድግዳ ያፈርሳል፣ የወለደውን ሲስሙለት የዘሩት ሲቀምሱለት እንዲል ተረቱ፣ ሒደቱ ወገንተኝነት ያፀናል፣ አጎራባቾቹ ሲሻቸው በአማርኛ፣ ሲሻቸው በኦሮምኛ የልባቸውን ይለዋወጣሉ፣ ይቀራረባሉ፣ በአንድ ገበያ ነግደው ያተርፋሉ፣ በሁለቱም ቋንቋ የተዘጋጁ አብሮነታቸውን የሚዘክር የታሪክ ሰነድ ያዛምዳሉ፣ ስህተቱን ያርማሉ፣ ከዚህ ቀደም አንደኛቸው የሌላኛቸውን ቋንቋ አለመናገራቸው፣ መጻሕፍትን ያለማዘጋጀታቸው ከክፋት የመነጨ እንዳልሆነ መግባባት ላይ ይደርሳሉ፣ የልባቸውን ሳይለዋወጡ በስማ በለው ስለተከሰተው አለመግባባት፣ ግጭትና ደም መፋሰስ ይቆጫሉ፣ ሌላም ሌላም።

በሁለተኝነት፣ ኦሮምኛ ቋንቋ በመላው አገሪቱ ተዘውታሪ ቢሆን አገር በቀል የሆነው የኩሽ ሥልጣኔ በተለይም ሥር ሰዶ በሚታይበት በገዳ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ዕውቀቶች ፋይዳ በሚኖራቸው መልኩ በመላው ኢትዮጵያውያን ማለትም ቋንቋው በሚስፋፋባቸው አካባቢዎች ምሁራን ዘንድ እንዲጠኑ፣ በአፍ ይነገር፣ በአገር ሽማግሌዎች ዘንድ ህሊና ብቻ ይዘከር የነበረው ዕውቀት ሰነድ እንዲዘጋጅለት፣ ተግባራዊ እንዲሆኑና ከተወሰኑበት አካባቢ ተሻግረው የመላው ኢትዮጵያዊ ሀብት የሚሆኑበት መንገድ ይጠርጋል፣ ከሰሜናዊው ክርስቲያናዊ አስተሳሰብ ጋር ተዛምደውና በአንድ ተገምደው እንድናያቸውና አገራዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ የራሱ የሆነው ጠፍቶ፣ የሌላ አስተሳሰብ እንደተጫነበት የሚሰማው ማኅበረሰብ አስተሳሰብን ቃኝቶ ወገንተኝነትን በማፅናት አገራዊ ድል ያመጣል። ሆኖም ግን ኦሮምኛን በትምህርት ሥርዓት ለማካተት፣ በተቀረው ማኅበረሰብ ዘንድ እንዲዘወተር የማድረጉና የሥራ ቋንቋ የሚሆንበትን መንገድ ጠረጋ ላይ በርካታ ጥያቄዎችን እንድናነሳ የሚያስገድዱ ክፍተቶችን ለመመልከት ችለናል።

ጥያቄዎቻችንን አገሪቷን በፌዴራል መሥሪያ ቤት ደረጃ በሚመሩትና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ላይ በሚል በሁለት ከፍለን ለማንሳት እንሞክራለን። በፌዴራል ደረጃ አገሪቷን ከሚመሩ አመራሮች ዘንድ የኦሮምኛ ቋንቋን በአዲስ አበባ ትምህርት ሥርዓት ውስጥ ለማካተትም ይሁን ክልላዊ መዝሙሩን ለመዘመር በተሞከረበት ሒደት ውስጥ የገጠመውን ተግዳሮት ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጨምሮ ‹‹ኦሮሞ ጠልነት›› በሚል መነሳቱን ተመልክተናል።

ሆኖም በተለያየ መልኩ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ላይ በቀደመ ሥርዓት ወቅት እንደጨቋኝ ጣት የሚቀሰርበት የአማራ ማኅበረሰብ ብንወስድ እንኳ፣ ኢሕአዴግ በሥልጣን በነበረበት ወቅት በበድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) የሚመራ ግብረ ኃይል በአማራ ክልል ላይ ሁለተኛ ቋንቋ ሆኖ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት የምትፈልጉት ቋንቋ በሚል ባሰባሰበው መጠይቅና ባደረገው ጥናት አብላጫው ድምፅ ኦሮምኛ ቋንቋን መማር እንደሚፈልግ መግለጹን፣ ከሚዲያ አዳምጠናል (የአማራ ሕዝብ ኦሮምኛን ማወቁ በሁለቱ ማኅበረሰብ ዘንድ የተገነባውን የፀብ ግድግዳ እንደሚያፈርስና የአገሪቷን ዳግም መነሳት ብሥራት ነጋሪ ሆኖ የታያቸው ወይም ይህ እንዳይሆን የማይፈልጉ ወገኖች ተግባራዊነቱን እንዳመከኑት አዳምጠናል)። ከዚህ አኳያ ኦሮምኛ ቋንቋ በአዲስ አበባ የገጠመውን ተግዳሮት ኦሮሞ ጠልነት ነው ለማለት ያስደፍራል? በዚህ መልኩ መገለጽ አለበት? በጥላቻ ትርክት በከንቱ የፈሰሰው ደም እየተመለከትን ባለንበት ወቅት በአገር መሪ ደረጃ በዚህ መልኩ መገለጽ ይገባው ነበር? የሥጋ ዝምድና ባይኖረውም፣ በክርስትና እና በዓይን አባት፣ በዕቁብና በዕድር ሰበብ ዝምድናን ለሚያጠነክር ማኅበረሰብ ቃላቱ ይገባዋል? የሚሉ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያስገድደናል።

ሌላው በፌዴራል ደረጃ ያሉ አገር መሪዎች ላይ የምናነሳው ጥያቄ፣ ምንም እንኳን የኦሮምኛ ቋንቋ ዕድገትና መስፋፋት እንደአገር መሪነታቸው አሳስቧቸው መመልከታችን ተገቢ ቢሆንም፣ አጣዳፊነቱ ከዚህ ይልቅ በሕዝብ ብዛት፣ በቋንቋው ሥርጭት ሰፊ ቁጥርና ፅኑ መሠረት ባላቸው ቋንቋዎች ላይ ከሚሆን ይልቅ ለመጥፋት አንድ ሐሙስ ቀራቸው የሚባሉ ቋንቋዎች ጉዳይ ራስ ምታት ሲሆንባቸው መመልከት አይገባም ነበር? እንድንል የሚያስደፍር በአገራችን የአንዳንድ ቋንቋዎች አሁናዊ መረጃ ያስገድደናል። ከ500,000 በላይ የጥናታዊ ጽሑፎችን በመደርደሪያው አሰናድቶ እንካቹ ያለን የበይነ መረብ ቤተ መጻሕፍት (Internet Public Library)፣ ከጥናቶቹ መካከል ‹በመጥፋት ላይ ያሉ ቋንቋዎች በኢትዮጵያ› የሚል ይገኝበታል።

በዚህ ጥናት በሚቀጥሉት 100 ዓመታት ውስጥ ግማሽ ያህሉ የዓለም ቋንቋዎች ለአደጋ ይጋለጣሉ ወይም ይጠፋሉ የሚለውን ያስቀድምና በኢትዮጵያ እንደ አማርኛና ኦሮምኛ ያሉ በሰፊው የሚዘወተሩ ቋንቋዎች እንዳሉ ሁሉ፣ በመዘውተር ደረጃና በማኅበረሰቡ የሕዝብ ቁጥር አኳያ፣ እንደ ወላይታ (በሁለት በመቶው ሕዝብ ይነገራል)፣ ጉራጌ (በሁለት በመቶ የሚነገር)፣ አፋር (1.7 በመቶ)፣ ሃዲያ (1.7 በመቶ ) እንዲሁም ጋሞ (1.5 በመቶ) ዓይነት ቋንቋዎች በቀጣይ የመጥፋት ሥጋት ከተጋረጠባቸው ቋንቋዎች ተርታ መድቧቸዋል። ታዲያ ይህንን ስንመለከት፣ ለመታደግ የሚጣደፉለት፣ መፍትሔ ሳያገኙለት እንቅልፍ የማያሸልቡበት ወይም አጀንዳ ሊሆን የሚገባው የቱ ነበር? በእውኑ መንግሥት የቋንቋዎች ዕድገት አሳስቦታል? ወይስ ፖለቲካው ተጭኖታል? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል። በሁለተኝነት ምዕራፍ ጥያቄ የምናነሳበት፣ ኦሮምኛ ቋንቋ የመላው ኢትዮጵያን ሀብት ቢሆንም ከቋንቋ መስፋፋትና ዕድገት ጋር ሥራ በመሥራቱ ሒደት በይበልጥ ተያይዞ ሲነሳ በተገነዘብንባቸው በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥትና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ ይሆናል።

ጥያቄዎቻችን የኦሮምኛ ቋንቋ በአገሪቱ ተዘውታሪ የማድረጉ ሒደት በአንድ ጀንበር የሚጠናቀቅ ሥራ ነው? ለማኅበረሰቡ በምን ዓይነት መንገድ ቀረበ? የቋንቋና የባህል ማዕከላትስ ተሰናድተውለታል? የሚለውን እናነሳለን። ስተዲ ፍሬንች ስፓኒሽ የሚል ድረ ገጽ፣ (Methods and Strategies to Help You Learn a Language) ቋንቋ እንዴት እንደሚለመድና እንደሚስፋፋ ከሚመክርበት መንገድ አንዱ ‹‹በዕቅድና በጊዜ ገደብ ውስጥ የሚተገበር፤›› ይለዋል። ይህንን ስንመለከት የኦሮምኛ ቋንቋ የአገሪቱ ክፍል ተዘውታሪ እንዲሆን የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ምን ያህል ነው? ዘወትር ተነፃፃሪ ሆኖ የሚነሳው የአማርኛ ቋንቋ፣ የቤተሰብ ቋንቋችንን አስረስቶ ሥፍራውን ሲቆናጠጥ በቀደመ ጊዜ በመንግሥት ደረጃ ወይም በሃይማኖት ተቋማት ይደገፍም ወይም ሌላ ምክንያት ይኑረው፣ ቢያንስ የ300 ዓመት ሒደትን እንደተጓዘ በድፍረት መናገር እንችላለን።

መቶ ዓመታቱ ይቅርና የኦሮምኛን ቋንቋ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ዕቅድ ምን ያህል ፈቅና ተዘውታሪ ለማድረግ ታቅዷል? በአንዴ ለመጫን በሚደረግ ትግል አለመግባባቱን አያንረውም? አለመግባባቱ ሲያይል ጉዳዩን በዕቅድና በዘመን ከፋፍሎ ለማሳካት የሚደረገው ጥረት ደካማ መሆኑ እንደአንድ ምክንያት መነሳት ሲገባውም፣ ‹ኦሮሞ ጠልነት› በሚል መፈረጁ ምን ያህል ያስኬዳል? የሚሉ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያደርገናል። ይህ ስተዲ ፍሬንች ስፖኒሽ የተሰኘ ድረ ገጽ ቋንቋ ለሌሎች ማስረፅ የሚቻልበትን ሌላኛውን መንገድ ሲጠቁም፣ ቋንቋ ባህል ነው። ባህል በኪነ ጥበብ ላይ በተሻለ ሕይወት ዘርቶ ለሌሎች በጉልህ የሚታይ ይሆናል። ቋንቋ በፊልም፣ በሙዚቃ፣ በመድረክ ድርሰት መልኩ ቢቀርብ አስተማሪውንም ተማሪውንም አያለፋም ይለናል።

ከዚህ ተነስተን የኦሮምኛ ቋንቋ ተዘውታሪ ለማድረግ የዓመታት ዕቅድ ይዘን ብንነሳም እንኳን የሥርጭት መንገዱ በደረቁ ሊሆን ይገባል? ተዘውታሪው የአማርኛ ቋንቋ ለተዘውታሪነቱ ምቹ ሁኔታ ነበረው ብንል እንኳን፣ ብራና ፍቀው ድርሰት ለማሳካት ለዘመናት አልተለፋበትም? ፊልም ቲያትሩ አልተሰናዳበትም? እንደህ ኦሮምኛ ቋንቋ ተዘውታሪ ለማድረግ ድካም አይጠይቅም? በደፈናው መዘውተር አለበት የሚል አምባገነናዊ ገጽታ ከማላበስ ይልቅ፣ ማሳለጫ መንገዶችን ሊከተል አይገባውም? መጻሕፍት፣ የመድረክና የስክሪን ተውኔት ሊሰናዳበትና የሌላውን ማኅበረሰብ ቀልብ በሚገዙ መንገዶች ተደራሽ ሊሆን አይገባውም? የሚሉ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያስገድደናል።

የመጨረሻ የምናደርገው አንድን ቋንቋ ለማስፋፋት በዕቅድና በጊዜ ገደብ ተቀምጦ፣ በኪነጥበብ ዓይነት የማዘውተሪያ ሥልት ተቃኝቶ ለሕዝብ ማድረሻ የባህል ማዕከላት ያስፈልጉታል። የውጭ አገሮች ተሞክሮ ስንወስድ፣ የጀርመን፣ የፈረንሣይ፣ የእንግሊዝ፣ የሩሲያ ቋንቋና ባህል ለማስፋፋት ዕቅድና የጊዜ ገደብ በያዙበት አካባቢ ላይ ባህል ማዕከሎቻቸውን በማዋቀር ቋንቋው በነፃ የሚማሩበት፣ ፊልሞቻቸው የሚታይበትን፣ ድርሰቶቻቸው የሚነበብበትን አቋራጭ ሥልት ይቀርፃሉ። የኦሮምኛ ቋንቋን ተዘውታሪ፣ ባህሉን ተስፋፊ ለማድረግ ብዙ አገራዊ ኃላፊነት በተሸከሙ አመራሮች ደረጃ፣ ሌላ ትርጉም በሚያሰጥ መልኩ አጀንዳ ከሚሆን ይልቅ፣ ዓላማውን በኃላፊነት ተረክበው፣ ተግባራዊነቱን በጊዜ ገደብና በዕቅድ አዘጋጅተው ለሕዝብ ለማድረስ ያሰናዳናቸው ማዕከላት ምን ያህል ናቸው? (አዲስ አበባ አለ) በየክልሉ ለመገንባት ዕቅድ አለን? ያሉትስ ቢሆን ቋንቋውን በነፃ ለማስተማር፣ ባህሉን በኪነጥበብ ቃኝቶ ለማስፋፋት ሞክረናል? ወይም ማዕከላቱ የተቋቋሙበትን ዓላማ ግብ መተዋል? በአጠቃላይ ከእኛ የሚጠበቀውን ቅድመ ሁኔታ አሳክተን ጨርሰናል? የሚሉ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያስገድዳል።

በዚህ አንቀጽ ዝግጅት ላይ ማንሳት የፈለግናቸው ሁለት ሐሳቦች እናጠቃል። የአንድ ማኅበረሰብ አባል መሆን ማለት አባላቱ የሚጋሩትን የግንዛቤ ሕይወት፣ የእሴቶች፣ የተግባራት አወቃቀሮችንና ዕድገትን የሚመራበት መንገዶችን ተጋሪ መሆን ማለት ነውና አንደኛችን የሌላችንን ባህልና ቋንቋ ማወቃችን የማኅበረሰቡ አንድ አካል እንድንሆን የሚያደርገንን ምቹ ሁኔታ እንደሚቸረን እንገነዘባለን። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ በርካቶቻችን በዚህ መሰል ግንዛቤ ውስጥ ባለንበት ወቅት፣ ቋንቋችንና ባህላችንን ለማስፋፋት ስንነሳ በቅድመ ዝግጅት መሥራት ያለብንን የቤት ሥራ ሳንከውን ቀርተን፣ ነገር ግን የአንድ ጀንበር ስኬት ለማድረግ ስንሞክር ለሚገጥመንን ተግዳሮት መነሻው ጥላቻ ነው ከሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ምን ያህል ያስኬዳል? ከዚህ ቀደም በጥላቻ ፖለቲካ መነሻነት የተነሳው እሳት ላይ ነዳጅ እንደማርከፍከፍ አይቆጠርም? የሚለውን በዚህ የአንቀጽ ዝግጅት ለመመልከት ሞክረናል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles