ሕፃናትን ለከፋ ስቃይና ለሞት ከሚዳርጉት ልዩ ልዩ ዓይነት በሽታዎች መካከል አንዱና ግንባር ቀደሙ የኩፍኝ በሽታ ነው፡፡ መንስዔው ከባክቴሪያ ሲሆን፣ በአብዛኛው መከላከያው ደግሞ መደበኛ ክትባት ነው፡፡ በዘመቻ የሚከናወነው ክትባት መደበኛውን ክትባት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ዘመቻው የመደበኛው ክትባት እንዲያጠናክር የማድረጉ ሥራ የሚከናወነውም በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ሳቢያ መደበኛው ክትባት ያለፈባቸውና ያቋረጡ ሕፃናትን የመድረስ አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ክትባቱ ሳይሰጥ ለሁለትና ለሦስት ዓመታት ያህል ከተራዘመ ወይም ከቆየ እንደገና ሊከሰት ይችላል፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መሠረት፣ በኢትዮጵያ ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት በዘመቻ ስታካሂድ ብትቆይም ምንም ዓይነት ክትባት ያልወሰዱ አንድ ሚሊዮን፣ ክትባቱን ያቋረጡ ደግሞ 1.7 ሚሊዮን ሕፃናት ይገኛሉ፡፡ ይህም ሁኔታ ክትባቱን ያቋረጡ ሕፃናት በብዛት ከሚገኝባቸው አገሮች ተርታ አሰልፏታል፡፡
የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀውም በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ በስድስት ክልሎች የታየ ሲሆን፣ በወረርሽኙም ከተያዙ ውስጥ 47 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል 46 በመቶ የሚሆኑት ምንም ዓይነት የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ያልወሰዱ ናቸው፡፡
ሕፃናትን ከዚህ ወረርሽኝ ለመታደግ እንዲቻልም 15.5 ሚሊዮን ሕፃናትን ተጠቃሚ የሚያደርግ አገር አቀፍ የተቀናጀ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ከታኅሣሥ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለአሥር ቀናት ያህል መካሄድ ጀምሯል፡፡
እየተካሄደ ያለው የተቀናጀ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻው ከኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት በተጨማሪ የአጣዳፊ የምግብ እጥረት ልየታ፣ የቫይታሚን ኤ ጠብታ እደላ፣ የሆድ ጥገኛ ትላትል መድኃኒት እደላ፣ የሕፃናት የዞረ እግር ልየታ እንዲሁም በወሊድ ምክንያት የሚከሰት ፊስቱላ ልየታ በቅንጅት የሚሠራበት ነው።
በጤና ሚኒስቴር የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተመስገን ለማ እንደገለጹት፣ በዚህም ዘመቻ ተጠቃሚ ከሆኑት ሕፃናት መካከል ዕድሜያቸው ከዘጠኝ ወር እስከ አምስት ዓመት እንዲሁም ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች ሆኖ በተለያዩ ምክንያቶች ምንም ክትባት ያልወሰዱና ያቋረጡ (ዜሮ ዶዝ) ሕፃናት ይገኙበታል፡፡
ክትባቱ የሕፃናቱን በሽታ የመከላከል አቅም እንደሚያሳድግ፣ አቅማቸውንም እንደሚያጎለብት፣ የደም ማነስን እንደሚከላከል ትክክለኛ ዕድገት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግና ከተጠቃሚዎቹም መካከል 95 ከመቶ ያህሉ ከተከተቡ ሳይከተቡ የሚቀሩት ከበሽታው መጠቃት ሊድኑ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ኅበረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ወረርሽኙ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል ሶማሌ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦት ክልሎች በሚገኙና ሁከትና ብጥብጥ፣ ያለመረጋጋትና የፀጥታ መደፍረስ በሚታይባቸው፣ እንዲሁም ከፊል አርብቶ አደሮች ባሉባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡
በአዲስ አበባም ፈረንሣይ ሌጋሲዮን አካባቢና አቃቂ ዙሪያ ክትባቱን ያልወሰዱና ያቋረጡ ሕፃናት መኖራቸውንም ተገልጿል፡፡
በመካሄድ ላይ ያለው የክትባት ዘመቻ ውጤታማነት ኅብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ፣ የክትባቱም ሥራ የሚከናወንው በጤና ተቋማትና በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች ውስጥ መሆኑን የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡
ከአስተባባሪው ለመረዳት እንደተቻለው የክትባት ሥራው የሚካሄደው ከሌሎች የሕክምና አገልግሎቶች ጋር በማቀናጀት ነው፡፡ ከሚከናወኑት አገልግሎት መካከል ዕድሜያቸው ከስድስት ወር እስከ አምስት ዓመት የሆኑና የአጣዳፊ የምግብና የቫይታሚን ኤ እጥረት እንዲሁም ከሁለት እስከ አምስት ዓመት የሆኑና የአንጀት ጥገኛ ትላትል ያለባቸው ሕፃናትን የመለየትና ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት መስጠት ነው፡፡
ከዚህም ሌላ ከ12 ዓመት በላይ ለሆኑት የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት የሚሰጥ ሲሆን፣ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የፌስቱላ ችግር ያለባቸውን እናቶችና የዞረ/ ቆልማማ እግር የሚታይባቸውን ሕፃናት መለየትም በተጓዳኝ የሚሰጡ ናቸው፡፡
በሕፃናት ላይ የሚታየው ቆልማማ እግር በወሊድ ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች አብሮ የሚከሰት እንጂ የእግዚአብሔር ቁጣ አይደለም ያሉት አስተባባሪው በእርጥቡ ወይም በለጋው ቶሎ ከተደረሰበት በሕክምና ሊቃና ይችላል ብለዋል፡፡ ስለዚህ ወላጆች ችግሩ ያለባቸውን ልጆቻቸውን ከደበቁበት አውጥተው ወደ ሕክምና እንዲወስዱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፌስቱላ የእናቶችን የመራቢያ አካል ከሽንት ከረጢትና ትልቅ አንጀት ጋር በማገናኘት የሽንትና የሰገራ መቆጣጠር ችግር ያስከትላል ያሉት ደግሞ የጤና ሚኒስቴር የእናቶች ጤና ፕሮግራም ባለሙያ ወ/ሮ ልኬለሽ ሞላ ናቸው፡፡ እንደ ባለሙያዋ አነጋገር በወሊድ ጊዜ የልጅ ጭቅላትና የእናት ዳሌ አጥንት አለመመጣጠን የማሕፀንና የሽንት ፊኛን ይጎዳል፡፡
ይህ ዓይነቱ ችግር በእናቶች ላይ ከሚያስከትለው የፌስቱላ ስቃይ ባሻገር ሽታና መጥፎ ጠረን ሊያስከትል ይችላል፡፡
ይህን መሰል ጉዳት የሚታይባቸው እናቶች ቶሎ ብለው ወደ ጤና ተቋማት ሊሄዱ እንደሚገባ፣ ለዚህም ተብሎ በተለያዩ አካባቢዎች ስምንት የጤና ማዕከላት እንደተቋቋሙ፣ ማዕከላቱም በዓመት ከ3,000 በላይ ታካሚዎችን የመርዳት አቅም እንዳላቸው አሁን ግን እየሠሩ ያሉት ከአቅማቸው በታች እንደሆነ ነው ባለሙያዋ ያመላከቱት፡፡