Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊራስን ማጥፋት ለምን?

ራስን ማጥፋት ለምን?

ቀን:

የአሥራ አራት ዓመት ታዳጊ ሳለች በአጎቷ ወሲባዊ ጥቃት ይፈጸምባታል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ደግሞ ከወትሮው የተለዩ ስሜቶችን ማስተናገድ ትጀምራለች፡፡ ባልጠነከረው ሰውነቷ ማርገዟን የሚያሳብቅ ምልክቶች አየች፡፡ ሰማይ እንደተደፋባትና አማራጭ እንደሌላት አዕምሮዋ ይሞግታት ጀመር፡፡ በወቅቱ በሕይወት ለመቆየት ምንም ጭላንጭል አልታያትም፡፡ ከብዙ የአዕምሮ ሙግት በኋላ መፍትሔ ያለችውን ዕርምጃ ወሰደች፡፡ በአቅራቢያዋ ያገኘችውን የንፅህና መጠበቂያ ኬሚካል ተጎነጨች፡፡

ከዚህ ዓለም ዕፎይ ያስብለኛል ያለችው ሙከራዋ በሆዷ የያዘችውን ፅንስ ቢያቋርጥም ለእሷ የፈለገችውን ሞት አልሰጣትም፡፡ ይህን ጊዜ ነበር ለመኖር ሁለተኛ ዕድል እንደተሰጣት የተገነዘበችው፡፡ ይህ ታሪክ የታዋቂዋ ጥቁር አሜሪካዊ የሪያሊቲ ሾው አቅራቢና የሥራ ፈጣሪዋ ኦፕራ ዌንፍሪ ነው፡፡

ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር እ.ኤ.አ. በ2017 ዕትሙም፣ ‹‹እኔ ከውድቀት መጨረሻ የተነሳሁ፣ በፈተናዎች አልፌ ለስኬት ማማ የደረስኩ ሴት ነኝ፤›› ስትል ያለፈችውን የሕይወት ውጣ ውረዶች በፊት ገጹ አስነብቧል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከ1986 ጀምሮ ለሩብ ምዕት ዓመት አየር ላይ የዋለው ‹‹ኦፕራ ዌንፍሪ ሾው›› አጠቃላይ ሀብቷን ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር እንዲልቅ ማድረጉን ፎርብስ መጽሔት በ2022 ዘግቧል፡፡

በአነቃቂ ንግግሮቿ የምትታወቀው ኦፕራ ኤ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ‹‹ኦፕራ ዌንፍሪ ኔትዎርክ›› የተሰኘ የኬብል ቴሌቪዥን ባለቤትም ሆናለች፡፡

የኬብል ቴሌቪዥን ባለቤት ከሆነች ከጥቂት ዓመታት በኋላ የመጀመርያዋ ጥቁር ሴት ቢሊየነር ሆና መመዝገቧንም አስነብቧል፡፡ በወቅቱ አጠቃላይ የሀብት መጠኗ አንድ ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡

ዓለም በበርካታ ውጣ ውረድና ውጥንቅጥ የተሞላች ብትሆንም፣ ችግሮች የስኬት መነሻ እንደሆኑ የኦፕራ ታሪክ ማሳያ ነው፡፡

ራስን ማጥፋት ከማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊና ከፖለቲካዊ ችግሮች የሚመነጭ ቢሆንም፣ ማኅበራዊ እሴቶችን በማጠንከር መከላከል እንደሚቻል የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ሰዎች ለምን ራሳቸውን ያጠፋሉ?

በራስ ላይ ጉዳት ማድረስ ተብለው ከተመደቡ ድርጊቶች አንዱ ራስን ማጥፋት ነው፡፡ 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ሕክምና ክፍል ሐኪምና መምህር ዮናስ ባህረ ጥበብ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ በዓለም ራስን የማጥፋት ችግር ሥር እየሰደደ ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በራሳቸው ላይ ጉዳት ለማድረስ በብዙ አጋላጭ ሁኔታዎች ተከበዋል፡፡

በክርስትናና በእስልምና ሃይማኖት ራስን ማጥፋት ክልክል ቢሆንም፣ ሰዎች ተደብቀው ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ሰዎችን በራሳቸው ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ በርካታ ገፊ ምክንያቶች እንደሚገጥማቸው ከዚያ ውስጥ የማኅበራዊ እሴቶች መላላት እንደሚገኝበት ይገልጻሉ፡፡

ክብሬ ተነካ፣ ተናቅኩና ተሰደብኩ በማለት ለሆነ ቡድን ራሳቸውን በመስጠትና በሥነ ልቦና ችግሮች ምክንያት ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች አሉ፡፡

በሥነ ልቦና ችግሮች በሚመደቡት ጭንቀት፣ ድብርት (ድባቴ)፣ አንዳንድ የአዕምሮ ሕመሞች እንዲሁም በከፍተኛ ሕመም ውስጥ የሚገኙ፣ የተለያዩ ሱስ አምጪ መድኃኒቶችና አልኮል የሚጠቀሙ ዜጎች ራሳቸውን ለማጥፋት ተጋላጭ መሆናቸውንም ዮናስ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

በልጅነት ወላጆችን በሞት ማጣት፣ ሥራ አለማግኘት በሕይወት ላይ ያልተጠበቁ ክስተቶች ሲገጥሙም ለችግሩ ይጋለጣሉ፡፡

‹‹የማኅበራዊ እሴቶች መላላት ወይም ግለኝነት ሲደጋገም ራስ ላይ ጉዳት የማድረስ ድርጊቶች እንዲያሻቅብ ምክንያት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡  

ብቸኝነትን የሚያመጡ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አጠቃቀም ከአዎንታዊ ነገሮች ይልቅ አሉታዊው እያመዘነ መምጣቱና ለችግሩ መፍትሔ አለመሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሲዲቲ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ኃላፊና የሳይካትሪስት ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር አበባው ፈቃዱ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ራስን ማጥፋት ወይም መጉዳት የተለመደ ባህርይ አይደለም፡፡ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችም በብዛት ድባቴ ሕመም ያለባቸው ናቸው፡፡

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ 90 በመቶ ሰዎች ራሳቸውን ካጠፉ በኋላ ሲመረመሩ ‹‹የድባቴ›› ሕመም እንዳባቸው ያሳያል ብለዋል፡፡

የአዕምሮ ሕመም ዓይነቶች ራስን የማጥፋት መንስዔ ሊሆኑ እንደሚችሉ የገለጹት አበባው (ዶ/ር)፣ የአልኮል መጠጥ ማዘውተር (ሱስ)፣ ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ ማኅበራዊ መፋለስ ሲያጋጥም ማለትም ኑሮ ውድነት፣ መበሳጨት ‹‹የድባቴ›› ሕመም ሲያጋጥም ራሳቸውን በሞት የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችልም ይጠቁማሉ፡፡

እንደ አበባው (ዶ/ር) ራስን ለማጥፋት የአዕምሮ ሕመም የሚገፋ ቢሆንም፣ በአመዛኙ ታስቦበትና ታቅዶ የሚደረግ ክንውን ነው፡፡ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችም ድርጊቱን ለመፈጸም ከመወሰናቸው በፊት ለሚቀርቡት ጓደኛ ያማክራሉ፡፡ የዓለም አቀፍ መረጃን ዋቢ አድርገው እንደገለጹትም፣ ከ60 በመቶ እስከ 70 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ከማጥፋታቸው በፊት ስለጉዳዩ ለሰዎች ያወራሉ፡፡ ይህ ድርጊቱን ሳይፈጽሙት ዕርዳታ እንደሚፈልጉ የሚያሳይ ነው፡፡

የትኛው ዕድሜ ክልል ላይ ችግሩ ይጎላል?

ራስን ማጥፋት በዕድሜ ገደብ ሲታይ ከአገር አገር የሚለያይ ቢሆንም፣ በወጣትነትና ወደ መጨረሻ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ላይ ችግሩ ጎልቶ ይታያል፡፡ የመጨረሻዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ለዚህ ችግር ተጋላጭ የሚሆኑበት ምክንያት ከጤና እክል፣ ከልጆቻቸው መለየትና ከሌሎችም ሊሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ፡፡

ታዳጊና ወጣቶች ላይ ደግሞ ስሜትን አለመቆጣጠርና ሱስ አምጪ መድኃኒቶችን መጠቀም፣ ከብስጭት፣ ከንዴትና ችግሮችን ባለመቋቋም ምክንያት ራሳቸውን ለማጥፋት ሊገፋፉ እንደሚችሉ አበባው (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስትና ‹‹የአማኑኤል ሆስፒታል ታሪኮች›› የሚለው መጽሐፍ ጸሐፊ ዮናስ ላቀው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በየዓመቱ ከ800,000 በላይ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ በዓመት 8,000 ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ ይላሉ፡፡

በዓለም 95 በመቶ የሚሆነው ራስን የማጥፋት ድርጊት ከጭንቀት፣ ከድባቴ፣ ከተስፋ መቁረጥ የሚመነጭ መሆኑን ያክላሉ፡፡

እንደ ዮናስ (ዶ/ር) ማኅበረሰብ ጥናት ላይ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችን በሦስት ይከፍሏቸዋል፡፡

የመጀመርያው ለሌሎች ሰዎች መስዋዕት መሆን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከጭንቀትና ከድብርት የሚመነጭ ነው፡፡ በሦስተኛነት የማኅበረሰብ ውጥንቅጥ ማለትም ጦርነት፣ መፈናቀል፣ የኑሮ ውድነት ሲበዛ ሰዎች ራሳቸውን ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡

ዮናስ (ዶ/ር) እንዳስረዱት፣ አንዳንድ ጊዜ ድብርትና ጭንቀት ለሌሎች ሰዎች የማይታይ በመሆኑ ‹‹ፈገግተኛ ድባቴ›› የሚል መጠሪያም ተሰጥቶታል፡፡ ስለሆነም ሰዎች ስለሳቁ፣ ስላወሩና ስለተጫወቱ ጭንቀትና ድብርት የለባቸውም ማለት አይደለም፡፡  

መፍትሔው

እንደ አበባው (ዶ/ር) ራስን ለማጥፋት የሚገፋፉ ችግሮችን ለይቶ በማወቅ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የአዕምሮ ሕመምና ሱስ ያለበት በቂ ሕክምና እንዲያገኝ በማድረግ ድርጊቱን ከመፈጸሙ በፊት ሊደረስበት ይችላል፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር ጥልቅ ቁርኝት ወይም ማኅበራዊ ሕይወት ላይ በደንብ በመሳተፍም ከችግሩ መራቅ ይቻላል፡፡

ራሳቸውን የሚያጠፉ ዜጎችን ለመታደግና ለመከላከል የመጀመርያው መፍትሔ ስለአዕምሮ ጤና ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ ሲሆን፣ ይህም ችግሩ ያለባቸው ሰዎች ችግራቸውን እንዲለዩት፣ ቤተሰብ ወይም ጓደኞቻቸው ምልክቶች ሲታዩባቸው ለማወቅ እንዲችሉ ያስችላል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አዕምሮ ጤና ላይ ያለው መገለልና አድልኦ እንዲቀንስ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግና ይህ ካልሆነ ድብርትና ተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ እንደሆነ ያወቀ ሰው ወደ ሕክምና ለመሄድ እንደሚያመነታ ይጠቁማሉ፡፡

አብዛኛው ችግሩ ያለበት ሰው ወደ ሕክምና መሄድ የሚያመነታውም የአዕምሮ ሕመም ላይ ከባድ የሆነ ማግለል በማኅበረሰቡ ውስጥ ስላለ ነው ብለዋል፡፡  

‹‹ወንድ ልጅ እንዴት ያለቅሳል›› የሚባል አባባልን ያስታወሱት ዮናስ (ዶ/ር)፣ ታፍነው፣ ጭንቀት ውስጥ ሆነው አሳዛኝ ዕርምጃ በራሳቸው ላይ ሲወስዱ የሚስተዋሉበት ምክንያት ይህ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

አዕምሮ ሕክምና ሲባል ቀድሞ ወደ ሰዎች አዕምሮ የሚመጣው የአማኑኤል ሆስፒታል መሆኑን፣ ስለተቋሙ የሚነገሩ የተሳሳቱ ነገሮች በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ይህም ትክክለኛውን አዕምሮ ሕክምናን የሚገልጽ አለመሆኑንና ሰዎች በጭንቀታቸው ጊዜ እንኳን አገልግሎቱን ለማግኘት እንደማይደፍሩ አክለዋል፡፡

የአዕምሮ ሕክምና ተደራሽ አለመሆኑ ሌላው ችግር መሆኑን የገለጹት ዮናስ (ዶ/ር)፣ በአራቱም ማዕዘን ወደ አማኑኤል ለመምጣት የሚቸገሩ ሕሙማን ብዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ‹‹እከሌ ሞተ›› ሲባል ብዙዎች እንደሚደነግጡ፣ ነገር ግን በየገጠሩ በጭንቀትና በተስፋ መቁረጥ ምክንያት የሚሞተው ቁጥሩ ከፍ ሊል እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

በጭንቀት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን እንደምንወዳቸው፣ እንደምናስብላቸው በመንገር ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ማስቀረት እንደሚቻልም አስረድቷል፡፡

ራስ ማጥፋትና የሃይማኖቶች አስተምህሮ

የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የአካዴሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ቀሲስ መዝገቡ ካሳ (ዶ/ር)፣ ራስን የማጥፋት ተግባር በሁሉም ማኅበረሰብ ውስጥ አለ ብለዋል፡፡

በአመዛኙ በምዕራቡ ዓለም ማኅበረሰብ ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ችግር ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ይልቅ የምዕራቡ ዓለም ችግር የሆነበት ምክንያትም ሕይወታቸው ከቁስ ስኬት ጋር መያያዙ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

‹‹የሕይወት ትርጉም ለእነሱ ቁስ ሲኖር ይኖራል፣ ሲጠፋባቸው ወይም ሲወድምባቸው አብረው ይፈርሳሉ፤›› ይላሉ፡፡

እነሱ ከተፈጠረባቸው የሥነ ልቦና ቀውስ ለማምለጥ በአማራጭነት የሚጠቀሙት ራስን ማጥፋት ሲሆን፣ በኢትዮጵያውያን ደግሞ የምዕራቡን ዓለም አኗኗርና ሌሎች ነገሮች ተግባራዊ እያደረጉ መምጣታቸውን የራሱ ተፅዕኖ ሊያሳድር ችሏል ብለዋል፡፡

እንደ ቀሲስ መዝገቡ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያም ቁሳዊነት ላይ የተመረኮዘ ሕይወት መምራት ሲበራከትና በተፈለገው ልክ ሳያሳካ ሲቀር እንደ መፍትሔ ራሳቸውን የሚያጠፉ አሉ፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ሚና መጫወት ትችላለች፡፡ ቁሳዊ ነገሮች ቢጎሉም እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ ነገን ዕውን ማድረግ እንደሚቻል ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ራስን የማጥፋት ችግር ያልጎላው፣ ማኅበረሰቡ እግዚአብሔር ላይ ያለው እምነት ከፍተኛ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በጭንቀት፣ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚገኙ አማኞች በንስሐ አባት አማካይነት ችግርን እንዲናዘዙና እንዲያወጡ የሚደረግበት አሠራር እንዳለም ያስረዳሉ፡፡

ግለሰቡ የገጠመውን ችግር ለካህኑ የሚናዘዝበት (የሚናገርበት) ዕድል መኖሩ፣ የግለሰቡን ችግር ከሃይማኖታዊ አስተምህሮት አኳያ ስለሚመረምረው፣ ሊጥለው የሚገባውን አስጥሎ፣ ሊወስድ የሚገባው ሰጥቶ ወደ ትክክለኛ መንገድ እንዲገባ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሰፊው እየሠራችበትም ነው፡፡

በጭንቀትና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ከንስሐ አባት ጋር በመነጋገር ፀበል መጠመቅ፣ አዘውትሮ መጸለይ፣ ጾም ጸሎት በማድረግ ካሉባቸው ችግሮች መውጣት እንዲችሉ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች ብለዋል፡፡

በእስልምና አስተምህሮት ምሕረት ከማይሰጣቸውና በፍጡራን ቁጣ ከሚያመጡ ወንጀሎች ውስጥ አንዱ ‹‹ነፍስን ማጥፋት›› ነው፡፡

ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እንደተናገሩት፣ በእስልምና አስተምህሮ ራስን ማጥፋትና ሌላ ንፁህ ነፍስን ማጥፋትም የሰው ዘርን እንዳጠፋ ይቆጠራል፡፡ የሰው ልጅ ሲፈጠር በነፍሱ ላይ ሥልጣን እንደሌለው የሚገልጹት ኡስታዝ፣ በሰው ተፈጥሮ ማንነት ላይ የሚወሰነውና ዋስትና የሚሰጠው ፈጣሪ ብቻ እንደሆነ አስተምህሮቱ እንደሚያዝ ገልጸዋል፡፡

ስለዚህ በፈጣሪ ሥራ ገብቶ፣ ትዕዛዝና መመርያ ጥሶ በራስ ላይ ውሳኔ መስጠት መጨረሻው ምሕረት የለውም፡፡

በጭንቀትና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ለሚገኙ አማኞች የመንፈሳዊ ሕክምና ትልቁ መፍትሔ ሲሆን፣ ቅዱስ ቁርዓን በመጥቀስም፣ ‹‹ሰዎች ፈጣሪን (አላህን) በማስታወስና በመፈለግ ይረጋጋሉ፤›› ሲሉ ኡስታዝ ይናገራሉ፡፡

በሕይወት ውስጥ የሚገጥሙ ፈተናዎች የሕይወት መጨረሻ እንዳልሆኑ፣  በምድር ባይመቻቸው በሰማይ የተሻለ ነገር እንደሚጠብቃቸው ማስተዋል እንደሚገባ፣ ትልቁንና ዘለዓለማዊውን ነገር ለመውረስ ከፈጣሪ ጋር ያላቸውን ትስስር ማጥበቅ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

በእስልምና እምነት ውስጥ አንድ ሰው ሲጨነቅ፣ ሲረበሽ ቁርዓን ይቀራለታል፣ ሶላት እንዲሰግድ ይደረጋል፡፡ እነዚህ የመንፈሳዊ ሕክምናዎች ሰዎች ውስጣቸው እንዳይረበሽና እንዳይጨነቁ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

ዘመናዊ ሕክምና ለአዕምሮ ጭንቀት ሌላው መፍትሔ መሆኑን፣ ዶክተር አክሞ ፈጣሪ ስለሚያድን ይህንን እንዲያደርጉና የሕክምና ክህሎት በተሰጣቸው ሰዎች አማካይነት ዕገዛ እንዲያገኙ ማድረግ ተጨማሪ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡

እነኢዮብ፣ ዮሴፍና ሌሎችም በቅዱሳት መጻሕፍት ታሪካቸው የተሰነደላቸው ለፈጣሪ ቅርብ የሚባሉ ቢሆንም የሕይወት ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡

እነዚህ ታሪኮችም ጨለማ እንደጨለመ እንደማይቀር፣ ከፈተና በኋላ የተሻለ ብርሃን እንዳለ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ስለዚህ በጭንቀት፣ በድብርትና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያሉ ወገኖች የተሻለ ‹‹ነገ›› እንደሚኖር በማሰብ ፅናትና ትዕግሥት ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የ2021 ሪፖርት እንደሚያሳየው በዓለም በዓመት 700,000 ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡

ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ላይ ባሉ ወጣቶች አራተኛው የሞት ምክንያትም ራስ ማጥፋት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 77 በመቶ በደሃና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የሚፈጸም ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከሴራ ፖለቲካ በስተጀርባ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁ ኃይሎች

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ የአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት የወደቀው ከመቅደላ በፊት...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...

አማርኛ ተናጋሪዋ ሮቦት

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም፣ ሚያዝያ 2 ቀን...

ወዘተ

ገና! ከእናቴ ሆድ ሳለሁ፤ ጠላት ሲዝትብኝ ሰምቻለሁ። በዳዴ ዘመኔም፣ በ'ወፌ ቆመችም!'፤ አውዴ ክፉ ነበር...