Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የብሔራዊ መታወቂያ ሙሉ በሙሉ ሲተገበር አገራዊ ጠቅላላ ምርትን 11 በመቶ ያሳድጋል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፕሮጀክት ሥራው ከተጀመረ አራት ዓመታት ያስቆጠረው የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ፣ ብሔራዊ ጠቅላላ ምርቱን (ጂዲፒ) በ11 በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው ተገለጸ፡፡

በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ መላው ኢትዮጵያን ያካተተ ምዝገባ እንደሚያደርግ የተነገረለት ይህ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት፣ በተያዘው 2015 ዓ.ም. 12 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክት ኃላፊው እንደገለጹት፣ የዲጂታል መታወቂያ መዘጋጀት ኢትዮጵያውያን ብድር ጠይቀው በማግኘት፣ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች፣ ማዳበሪያና ሌሎች አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል፡፡

ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ኢኮኖሚውን ከማስፈንጠር ባለፈ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታየውን አለመረጋጋት ለማስተካከል፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ የማጭበርበር ድርጊቶችን ለመቀነስና ግልጽነትን ለማስፈን ቁልፍ ሚና መጫወት የሚችል በመሆኑ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስፈጸሚያ ረቂቅ አዋጁን በፍጥነት እንዲያፀድቀው ጠይቀዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ታኅሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት አድርጓል፡፡

ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ወዲህ 1.4 ሚሊዮን ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማካሄዳቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ዜጎች ይህን አገራዊ ዲጂታል መታወቂያ ባለማግኘታቸው የደኅንነት ሥጋት ውስጥ መግባታቸውን፣ እንዲሁም በአገራቸው ላይ የሚተማመኑ እንዳይሆኑ እንዳደረጋቸው የተናገሩት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሕግ ቡድን መሪ አቶ ድልነሳው እስራኤል ናቸው፡፡

አቶ ድልነሳው እንደገለጹት፣ በዚህ ወጥ በሆነ የአገራዊ መታወቂያ ዕጦት ዜጎች መሠረታዊ የመታወቅ መብታቸው ሳይከበር ቀርቷል፡፡

በሌላ በኩል የፕሮጀክቱ ኃላፊ አገራዊ የሆነና በአሻራ የተደገፈ መታወቂያ ባለመኖሩ የተነሳ፣ ባንኮች በድብቅ ማንነት በሚፈጸምባቸው ማጭበርበር ባለፈው ዓመት ቢያንስ 1.5 ቢሊዮን ብር ማጣታቸውን ፍትሕ ሚኒስቴርን ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡

ከፓስፖርትና ከቀበሌ መታወቂያ ጋር እኩል ተቀባይነት ይኖረዋል የተባለው የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦች መሠረታዊ የሆኑ የግል ዲሞግራፊክና ተፈጥሮዓዊ የሆነውን የዓይን፣ የጣትና የፊት የባዮሜትሪክ መረጃዎችን በማዕከላዊ ቋት መዝገቦ የሚይዝ ነው፡፡ ማንኛውም ነዋሪ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ካከናወነ በኋላ በልዩ ቁጥር የተደራጀና አስተማማኝ የዲጂታል መታወቂያ የሚሰጥበት ሥርዓት ነው።

የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ የሚፈጸመው በኢትየጵያ ውስጥ በሚገኝ በማንኛውም ሰው ላይ ሲሆን፣ በዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ሥርዓት የሚሰበሰቡት መረጃዎች በቀጥታ ከእያንዳንዱ ዜጋና ሕጋዊ ነዋሪ (የውጭ አገር ዜጎችንም ጨምሮ)  መሆኑ በአዋጁ ተብራርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች