Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናምርጫ ቦርድ ውድቅ አድርጎት የነበረውን የአብን ጠቅላላ ጉባዔ ውጤት እንደገና ተቀበለው

ምርጫ ቦርድ ውድቅ አድርጎት የነበረውን የአብን ጠቅላላ ጉባዔ ውጤት እንደገና ተቀበለው

ቀን:

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በደብረ ብርሃን ከተማ ከየካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ያካሄደውን ሁለተኛ መበደኛ ጠቅላላ ጉባዔ ውጤትን ውድቅ አድርጎት የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደገና መቀበሉን አስታወቀ፡፡

ቦርዱ ማክሰኞ ታኅሳስ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ለአብን በጻፈው ደብዳቤ እንዳስታወቀው፣ አብን ታኅሳስ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ፣ የካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በደብረ ብርሃን ያካሄደውን ጉባዔ ቦርዱ የማይቀበለው ከሆነ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም.  የፀደቀውን የፓርቲውን ሕገ ደንብ፣ የብሔራዊ ምክር ቤትና የሌሎች የፓርቲው አካላትን ብቻ እንደሆነ ማሳወቁ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጾ፣ ቦርዱ ጉዳዩን መርምሮ የዕርምት ውሳኔ እንዲሰጠው ተጠይቆ ነበር፡፡

ይህንንም ተከትሎ ቦርዱም ፓርቲው ያቀረበውን አቤቱታ ከሕጉና ከፓርቲው ሰነዶች አኳያ በመመርመር አብን የካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በደብረ ብርሃን ከተማ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎችም ሆኑ፣ በጉባዔው የተመረጡት የፓርቲው አመራር አካላት በሕጉ የተቀመጠውን መሥፈርት አለማሟላታቸውን ገልጾ ምላሽ ሰጥቶት እንደነበርም አስታውቋል፡፡

በዚህም የጉባዔውን ውጤት እንዳልተቀበለው በመግለጽ፣ የተጓደሉ የተባሉ ነጥቦችን አሟልቶ ጉባዔ እንዲያደርግ በመስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. እና በሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ቦርዱ ማሳወቁን አስታውሷል፡፡

ይሁን እንጂ ቦርዱ ሰኔ 2013 ዓ.ም. እና መስከረም 2014 ዓ.ም. በተደረገው አገራዊ ምርጫ የተለያዩ ክንዋኔዎችን ሲመራና ውሳኔ ሲያስተላልፍ በመቆየቱ ከፍተኛ የሥራ ጫና የነበረበት ከመሆኑ አንፃር፣ ለፓርቲው የሰጠውን መመርያ ተከታትሎ ሳያስፈጽም መቅረቱን ገልጿል፡፡

ቦርዱ በሥራ ጫና ውሳኔውን ባለመከታተሉና ባለማስፈጸሙ ምክንያት አብን በደብረ ብርሃን ባካሄደው ጉባዔ ውሳኔ መሠረት ሥራ አመራሩ ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ዕጩ ማቅረብና በምርጫ መወዳደር፣ ከቦርዱ ለፓርቲዎች የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ መቀበል፣ የኦዲት ሪፖርት ማቅረብና ፓርቲውን ወክሎ ከቦርዱ ጋር ግንኙነቶችን ማድረጉን አብራርቷል፡፡

በመሆኑም አሁን በሥራ ላይ ያሉትን በደብረ ብርሃኑ ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡ የፓርቲው አመራር አካላትን ዕውቅና አለመስጠት፣ ፓርቲው ለሦስት ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራት ዋጋ አልባ የሚያደርግ መሆኑን ቦርዱ በመገንዘቡ፣ እንዲሁም የፓርቲውን ህልውና ለማስቀጠል ሲባል በደብረ ብርሃን የተካሄደውን የጉባዔ ውሳኔ መቀበሉን አስታውቋል፡፡

በመሆኑም ለፓርቲው በጻፈው ደብዳቤ ላይ ማስተካከያ በማድረግ አብን በደብረ ብርሃን ጉባዔ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎችም ሆኑ፣ የውሳኔዎቹ ውጤቶች ተቀባይነት ሊኖራቸው ይገባል ሲል የማስተካከያ ውሳኔ መስጠቱን ቦርዱ በመግለጫው አትቷል፡፡

ፓርቲው በቀጣይ በሚያከናውነው ጉባዔ ላይ ሊሳተፉ የሚገባቸው የጉባዔ አባላት በባህር ዳር ጉባዔ የተሳተፉ የጉባዔ አባላት መሆን እንዳለባቸው፣ እንዲሁም በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በወቅቱ ያልተካተቱ ወይም በባህር ዳሩ ጉባዔ ተገኝተው አሁን መገኘት በማይችሉት ምትክ ሌሎችን በመተካት ተሰባሳቢዎችን መጥራት እንዳለበት ቦርዱ አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል በፓርቲው ጉባዔ ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን በተመለከተ ቦርዱ ከዚህ ቀደም ለፓርቲው በደብዳቤ በገለጸው መሠረት አንዱ አጀንዳ የሆነው፣ ‹‹የሪፎርም ሰነድ›› ለጉባዔ የሚቀርብበትን አግባብ በዝርዝር እንዲያዘጋጅ፣ በተጨማሪም የሚሻሻለው ደንብና ሌሎች ተጨማሪ የሚቀርቡ አጀንዳዎች (ካሉ) ዝርዝሩን በቅድሚያ በማዕከላዊ ኮሚቴ አስወስኖ ለቦርዱ ሊያቀርብ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ቦርዱ አክሎም የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ከላይ በተገለጹት ነጥቦች ላይ ስብሰባ በሚያደርግበት ጊዜ ሁሉ፣ ፓርቲው ለቦርዱ በቅድሚያ እንዲያሳውቅና የቦርዱ ተወካይ በስብሰባው ላይ እንዲገኝ ማድረግ የሚገባ መሆኑን መወሰኑን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...