Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቱሪዝም አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የሚጣለው ተጨማሪ እሴት ታክስ ቀሪ እንዲደረግ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኮቪድ-19፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነትና በፀጥታ ችግር የተቀዛቀዘው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እስኪያንሰራራ ድረስ፣ ረቂቅ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጁ በቱሪዝም አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የሚጥለውን ምጣኔን እንዲያስቀር ተጠየቀ፡፡

ጥያቄው የቀረበው የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ትናንት ታኅሳስ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ‹‹በኢትዮጵያ ያለው የቱሪዝም አስጎብኚዎች  ዘርፍ ዕድልና ተግዳሮት›› በሚል ርዕስ ባሰናዳው የቢዝነስ ፎረም ላይ ነው።

በረቂቅ ደረጃ ላይ የሚገኘው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ዜሮ የታክስ ምጣኔ ተፈጻሚ ይደረግባቸዋል ተብለው ከተለዩት ውስጥ የቱሪዝም ውጤቶች ወይም አገልግሎቶች እንደማይገኝበት፣ ዘርፉ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ እንደሚሆን መደንገጉን በፎረሙ ላይ የመነሻ ጥናት ያቀረቡት፣ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የግልግል ተቋም ዳይሬክተር  አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ አገሮች የቱሪዝም ዘርፉን ለማትጋት ተብሎ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ ዜሮ እንደሚሆን፣ ያ ካልሆነም በጣም ዝቅተኛ የሚባል ምጣኔ እንደሚጣልበት ተገልጾ፣ በኢትዮጵያም በረቂቅ ላይ ባለው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ምጣኔ ላይ በሥራ ላይ ካለው አዋጅ የተሻሻለ ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ በድንጋጌው የዘርፉ ተዋንያኖች በሚያቀርቡት ጥቅል አገልግሎት ሒሳቦች ላይ የ15 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ በማከል እንዲያስከፍሉ ሕግ እንደሚያስገድዳቸው ጠቁመው፣ በሚያቀርቡት ግዥዎች ላይ ለግብዓትነት ያወጡትን የተጨማሪ እሴት ታክስ ማቀናነስ እንዲችሉ ሕጉ ቢፈቅድላቸውም፣ ነገር ግን ዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ለአገር እንደማስገኘቱ ለማበረታት በሚል የተለየ የታክስ ማበረታቻ እንዳልተቀመጠለት አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የመንግሥት የግብርና የታክስ ግዴታዎች ተፈጻሚ መሆን እንዳለባቸው በፅኑ ቢያምንም፣ የቱሪዝም ዘርፉ ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በማጤን፣ እስካሁን የነበረበት የተወሳሰበ ቸግር ከግምት ውስጥ በመክተት፣ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር መፍታት እንደሚገባ በፎረሙ ላይ የተሳተፉ ተወያዮችና ጥናት አቅራቢዎች አስረድተዋል፡፡

ዘርፉ በሚገባ ጠንክሮ ጥሩ ቁመና ላይ እስኪደርስ ድረስ ከተቻለ በዜሮ ምጣኔ ካልሆነም በዝቅተኛ ምጣኔ ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግለትና በረቂቅ ድንጋጌው ላይ ሊካተት እንደሚገባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

 አቶ ዮሐንስ  በኢትዮጵያ በተለይም በአስጎብኚ ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ የሚፈጸሙት ግዢዎች ከሞላ ጎደል በተጨማሪ እሴት ታክስ የሚሸፈኑ አለመሆናቸውን በመነሻ ጥናት ገለጻቸው ላይ አስረድተዋል።

ከሆቴሎች ጋር ተያይዞ በሚሰጡት አገልግሎቶች በታክስ ማስረጃ የሚሸፈኑ ቢሆንም፣ ከዚያ ውጭ ያሉት የትራንስፖርት፣ የባህላዊና ቅርስ ቦታዎች ጋር የተገናኙት ወጪዎች የታክስ ሕጉ የማይሸፍናቸው በመሆናቸው ወጪዎችን በአግባቡ ለማቀናነስ የማይቻልበት ሁኔታ መኖሩ ተገልጿል።

አስጎብኚዎች ሥራቸውን በሚያከናውኑበት  ወቅት ለጨራቸው አስፈላጊ የሆኑ ማናቸውም ዕቃዎችና አገልግሎቶች ሲገዙ በተመሳሳይ ሁኔታ የተጨማሪ እሴት ታክስ መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ያስረዱት አቶ ዮሐንስ፣ እስካሁን በሥራ ላይ ባለው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ የተለያየና ጉራማይሌ የሆነ የታክስ አከፋፈል በግብር ሰብሳቢ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት እየተወሰደ የዘርፉ ተዋንያንን በተለያየ መልኩ እንዲከፍሉ ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።

የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ ባደረገው ጥናት ‹‹የጉራማይሌ አሠራሩ የዘርፉ ተዋንያንን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጋቸው መሆኑን ተገንዝበናል.›› ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ ዘርፉ ዕቃን ወደ ውጭ ልከው የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኙ ዘርፎች (የዕቃ አቅራቢዎች፣ ላኪዎች) አበርክቶ ቢኖረውም፣ ተገቢው ድጋፍ፣ ጥበቃና ማትጊያዎች የሚያደርገለት የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ከግንዛቤ ተወስዷል ብለዋል፡፡

የወጭ ምንዛሪ ለአገር የሚያስገኙ ዕቃዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ ሆነው ወይም ተመላሽ እየተደረገላቸው የሚሠሩበት ሁኔታ መኖሩ ተገልጾ፣ በተመሳሳይ አገልግሎት ሸጠው (ሰጥተው) የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ በአስጎብኚነት ለተሰማሩ አካላት መሰል ድጋፍ እንደማይሰጣቸው በፎረም ላይ በቀረበው ጽሑፍ ተዳሷል፡፡

አስጎብኚ ድርጅቶች ልክ እንደ ዕቃ ላኪዎች በግብዓትነት የሚከፍሉት የተጨማሪ እሴት ታክስ በሙሉ ተመላሽ እንደሚሆን በመጥቀስ፣ ተመሳሳይ መብት ለእነሱም ሊሰጥ እንደሚገባና የሚሰጡት አገልግሎት የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ ዜሮ ሊሆን እንደሚገባ በተደጋጋሚ ለመንግሥትና የተለያዩ አካላት ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ ውጤት አለመገኘቱን የኢትዮጵያ አስጎብኚዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አንድነት ፈለቀ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች