Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሕወሓት ታጣቂዎች ከባድ የጦር መሣሪያዎችን እስከ ሐሙስ እንዲያስረክቡ ‹‹መግባባት›› ላይ መደረሱ ተገለጸ

የሕወሓት ታጣቂዎች ከባድ የጦር መሣሪያዎችን እስከ ሐሙስ እንዲያስረክቡ ‹‹መግባባት›› ላይ መደረሱ ተገለጸ

ቀን:

  • ወደ መቀሌ የተጓዘው ልዑክ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥቷል
  • የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ወደ መቀሌ መብረር ይጀምራል

የሕወሓት ታጣቂዎች ከባድ የጦር መሣሪያዎችን ለአገር መከላከያ ሠራዊት እስከ ሐሙስ ታኅሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ለማስረከብ ‹‹መግባባት›› ላይ መደረሱ ተገለጸ፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊትም ‹‹ሕገ መንግሥታዊ›› ኃላፊነቱን መቀሌ ከተማ በመግባት ይጀምራል ተብሏል፡፡

ይህንን የገለጹት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ መሪነት ሰኞ ታኅሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ወደ መቀሌ ከተጓዙት የልዑካን ቡድን አባላት መካከል፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ናቸው፡፡ ልዑኩ የፌዴራል መንግሥት ተወካዮችንና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አመራሮችን ይዞ የነበረ ሲሆን፣ በመቀሌ ከተማም ከሕወሓት ከፍተኛ አመራሮችና ከማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይቷል፡፡

የልዑክ ቡድኑ ከመቀሌ ጉዞው በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ገለጻ ማድረጉን፣ ማክሰኞ ታኅሳስ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ሬድዋን (አምባሳደር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ጠቅሰዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተደረገው ሁለተኛው የናይሮቢ ስምምነት መሠረት፣ ከልዑካን ቡድኑ ጉብኝት በኋላ ሕወሓት ከባድ የጦር መሣሪያን የማስረከቡ ሥራ እስከ ሐሙስ ታኅሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ለማከናወን ‹‹መግባባት›› ላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የፌዴራል መንግሥት ለሰላም ስምምነቱ ላሳየው ቁርጠኝነትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ምሥጋና ያቀረቡት የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ በእነሱ በኩል ተኩስ ማቆማቸውንና ከባድ መሣሪያዎችን ማሰባሰባቸውን ከልዑካን ቡድኑ ጋር ባደረጉት ውይይት ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለመቀሌው ጉዞ ከተደረገላቸው ገለጻ በኋላም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ አገልግሎቶችን በድጋሚ የማስጀመር ሥራዎችን በአፋጣኝ እንዲያከናውኑ ትዕዛዝ መስጠታቸው ተገልጿል፡፡

ከዚህ በማስቀጠልም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ክልል መዲና መቀሌ ከተማ በዛሬው ዕለት በቀን አንድ በረራ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ማክሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ይህ በየቀኑ አንድ ሆኖ የተጀመረው በረራ እንደ ፍላጎት መጠኑ እየታየ ብዛቱን እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡

አቶ መስፍን ወደ መቀሌ ከተጓዘው ቡድን ውስጥ አንደኛው ሲሆኑ፣ ከእሳቸው ጋርም ሌሎች የአየር መንገዱ ባለሙያዎች አብረው ተጉዘው የመቀሌ አሉላ አባነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን በረራ የማስተናገድ ይዘት ገምግመው ነበር፡፡ አየር መንገዱ በላከው መግለጫው ደንበኞች ወደ መቀሌ ለመጓዝ ማንኛውንም የአየር መንገዱን ትኬት ቢሮዎች በመጎብኘት፣ እንዲሁም የደንበኞች አገልግሎት ስልክ ቁጥር በመደወል ትኬት መቁረጥ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡

አየር መንገዱ በቀን በአንድ በረራ እንደሚጀምር የገለጸው ማክሰኞ ታኅሳስ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠዋት ሲሆን፣ ሪፖርተር ከአየር መንገዱ ትኬት ቢሮ በትናንትናው ዕለት ረፋድ ላይ ለማጣራት እንደሞከረው በረራዎች ለሁለት ሳምንታት (እስከ ጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም.) ሙሉ ለሙሉ ሞልተው ነበር፡፡ ወደ መቀሌ መብረር የፈለገም ሆነ ከመቀሌ መምጣት የፈለገ ባዶ ቦታ ያለው ለጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ብቻ ነበር፡፡

ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በተወሰኑ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ውስን አገልግሎት የጀመሩ ሲሆን፣ መቀሌን ጨምሮ በአብዛኞቹ አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡ የኢትዮቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖም፣ ሰኞ ታኅሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ወደ መቀሌ ከተጓዙት መካከል ይገኙበታል፡፡

ለሁለት ዓመታት በጦርነት የቆዩት የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት፣ በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በአፍሪካ ኅብረት አስተባባሪነት በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ የመጀመርያውን ስምምነት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት በሬድዋን (አምባሳደር)፣ እንዲሁም ሕወሓት በቃል አቀባዩ በአቶ ጌታቸው ረዳ አማካይነት  የመጀመርያውን የሰላም ስምምነት በፕሪቶሪያ ከፈረሙ ከአንድ ሳምንት በኋላም፣ በናይሮቢ የሁለቱ አካላት ጦር አመራሮች በድጋሚ ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደ መቀሌ የተጓዙት የእነዚህ ስምምነቶች ቀጣይ ክፍልና ‹‹ፕሪቶሪያ 2›› በማለት እየተጠራ ያለው ያለፈው ሳምንት የናይሮቢ ስምምነት ከተከናወነ በኋላ ነው፡፡ ይህ ተግባርም የሕወሓት ባለሥልጣናትን ከማስገረም አልፎ፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት ጀምሮ ተጠቅሰው የነበሩ እንደ ትጥቅ ማስፈታት ዓይነት ክንውኖችን ተፈጻሚነት እንደሚያፀና ይጠበቃል እየተባለ ነው፡፡

‹‹በነገራችን ላይ እዚህ የመጡት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አንድም የግል ጠባቂ አልያዙም፡፡ ይህም በትግራይ ሕዝብ በኩል ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት መገንዘባቸውን የሚያሳይ ነው፤›› ሲሉ የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...